በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መሳሳት እንደሌለብኝ የሚሰማኝ ለምንድን ነው?

መሳሳት እንደሌለብኝ የሚሰማኝ ለምንድን ነው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

መሳሳት እንደሌለብኝ የሚሰማኝ ለምንድን ነው?

“አባቴ አስተማሪ ስለነበር ሁሉም ሰው አንደኛ እንድወጣ ይጠብቅብኛል። አንዳንድ ጊዜ እንቅልፍ እስኪወስደኝ ድረስ አለቅሳለሁ።”​— ሊያ *

“የያዝኩትን ነገር ሁሉ የላቀ ጥራት ባለው መንገድ መሥራት እፈልጋለሁ። አንድን ነገር ከሁሉ በተሻለ መንገድ ወይም ከሌሎቹ ረቀቅ ባለ ሁኔታ መሥራት እፈልጋለሁ። ይህ ካልሆነ ግን ቢቀርብኝ እመርጣለሁ።”​— ካሌብ

ሥራህ ሁሉ እንከን የለሽ እንዲሆን ትፈልጋለህ? የቱንም ያህል በርትተህ ብትሠራ ገና ይቀረኛል በሚል ስሜት ትጨነቃለህ? ማንኛውንም ዓይነት ወቀሳ መቀበል ይከብድሃል? ስህተት በምትሠራበት ጊዜ ማሰብ እንደማትችል፣ ከሰው በታች ወይም የማትረባ እንደሆንክ በማሰብ ራስህን ትኮንናለህ? አንድ ነገር በትክክል እንዲሠራ ከፈለግህ አንተው ራስህ መሥራት እንዳለብህ ይሰማሃል? ባይሳካልኝስ ከሚል ፍርሃት የተነሳ መሠራት ያለባቸውን ነገሮች ለሌላ ጊዜ የማስተላለፍ ወይም ደግሞ ጭራሹኑ የመተው ዝንባሌ አለህ?

ከሌሎች ጋር ያለህ ግንኙነትስ ምን ይመስላል? አብረሃቸው ያሉ ሰዎች ወዳጆችህ ለመሆን እንደማይመጥኑ ስለሚሰማህ ጓደኛ ማግኘት ይቸግርሃል? ሌሎች የሚሠሩት ስህተት ወይም ድክመታቸው ከሚገባው በላይ ያበሳጭሃል? ከእነዚህ ጥያቄዎች ለአንዱም ቢሆን አዎን የሚል መልስ ከሰጠህ ከሌሎች ፍጽምና የመጠበቅ ባሕርይ ተጠናውቶሃል ማለት ነው። ጉዳዩ እንዲህ ከሆነ ደግሞ የችግሩ ሰለባ አንተ ብቻ አይደለህም። አብዛኞቹ ወጣቶች በተለይ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ወይም የላቀ ውጤት የሚያስመዘግቡ እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ይታይባቸዋል። *

አንድ ሰው ፍጽምና የመጠበቅ ባሕርይ እንዲኖረው የሚያደርገው ምንድን ነው? በዚህ ረገድ ተመራማሪዎች መላ ምት ከመሰንዘር ያለፈ መልስ የላቸውም። ፐርፌክሽኒዝም​—⁠ዋት ኢዝ ባድ አባውት ቢይንግ ቱ ጉድ? የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ፍጽምና የመጠበቅ ባሕርይ ከሌሎች የተጋባብህ ተላላፊ በሽታ አይደለም። ፍጽምና የመጠበቅ ባሕርይ በዘር የሚተላለፍ አብሮህ የተወለደ ነገር አይደለም። ታዲያ ይህን ባሕርይ ያዳበርከው እንዴት ነው? አንዳንድ ባለሞያዎች ፍጽምና የመጠበቅ ባሕርይ በልጅነት የሚዳብር እንደሆነ ያምናሉ። ቤተሰብ፣ ግለሰቡ ራሱ፣ ኅብረተሰቡና መገናኛ ብዙሃን የሚያሳድሩት ጫና እንዲሁም ምሳሌ ተደርገው የሚታዩ ሰዎችን ለመኰረጅ የሚደረግ ከአቅም በላይ የሆነ ጥረት አንድ ላይ ተዳምረው አንዳንድ ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ በጭንቀት እንዲዋጡ፣ የበደለኝነት ስሜት እንዲሰማቸውና ከልክ በላይ እንዲሠሩ የሚያደርግ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳድርባቸዋል።”

መንስኤው ምንም ይሁን ምን ፈጽሞ መሳሳት የለብኝም የሚል ስሜት ሕይወትህን ሊያበላሽብህ ይችላል። ፍጽምና መጠበቅ ምን እንደሆነና እንዴት ሊጎዳህ እንደሚችል እስቲ እንመልከት።

ፍጽምና መጠበቅ ምንድን ነው?

አንድን ነገር በጥሩ ሁኔታ ለመሥራት መፍጨርጨር ወይም በሚገባ በተከናወነ ሥራ እርካታ ማግኘት ፍጽምና እንደመጠበቅ ተደርጎ መታየት የለበትም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 22:​29 [የ1980 ትርጉም ] ላይ “ሥራውን በጥንቃቄ የሚሠራ” ሰውን በማድነቅ ይናገራል። ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ በተለያየ መስክ የላቀ ሙያ የነበራቸውን ሰዎች በመልካም ያነሳቸዋል። (1 ሳሙኤል 16:​18፤ 1 ነገሥት 7:​13, 14) በመሆኑም ጥራት ያለው ሥራ ለማከናወን መፍጨርጨርና ከፍ ያለ ሆኖም ሊደረስበት የሚችል ግብ ማውጣት የሚያስመሰግን ተግባር ነው። ይህም አንድ ሰው ‘በድካሙ ደስ እንዲለው’ ያደርገዋል።​—⁠መክብብ 2:​24

ፍጽምና የሚጠብቅ ሰው ግን እንዲህ ዓይነቱን እርካታ አያገኝም። ለስኬት ያለው አመለካከት የተዛባ ነው። አንዳንድ ባለሞያዎች እንደሚሉት ፍጽምና የመጠበቅ ባሕርይ “የማይደረስባቸው ግቦች ማውጣትን (ይህም ማለት እንከን የለሽ መሆንን) እና የቱንም ያህል ጥሩ ሥራ ቢሠራ እርካታ አለማግኘትን” ያጠቃልላል። ከዚህም የተነሳ ፍጽምና የመጠበቅ ባሕርይ “የጭንቀት ዋነኛ መንስኤ ከመሆኑም በላይ አብዛኛውን ጊዜ ግለሰቡ/ግለሰቧ የከንቱነት ስሜት እንዲያድርባቸው ያደርጋል።” በዚህም ምክንያት አንድ የመረጃ ምንጭ ፍጽምና የመጠበቅ ባሕርይ “አንተ እና/ወይም በአካባቢህ ያለው ሁኔታ ፍጹም መሆን አለበት የሚል ምክንያታዊ ያልሆነ አመለካከት” ነው ሲል ገልጾታል። “በሕይወትህ ውስጥ ለመሥራት የምትፈልገው ነገር ሁሉ ያለ ምንም መዛነፍ፣ ስህተት፣ ጉድለት ወይም ብልሽት እንከን የለሽ በሆነ መንገድ መሠራት አለበት የሚል ጠንካራ አቋም ነው።”

ኢየሱስ “እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ” ብሎ የለም እንዴ? (ማቴዎስ 5:48) አዎን፣ ብሏል። ሆኖም አንድ ሰው ሙሉ በሙሉ ፍጹም መሆን ይችላል ማለቱ አልነበረም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል” ይላል። (ሮሜ 3:23) ታዲያ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ፍጹም” የሚለው ቃል የተሟላ መሆን የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። (ማቴዎስ 19:​21) ኢየሱስ ፍጹማን ሁኑ ብሎ በተናገረበት ጊዜ ስለ ፍቅር እያስተማረ የነበረ ሲሆን ተከታዮቹ ፍቅርን ይበልጥ በተሟላ መልኩ እንዲያሳዩ እያበረታታቸው ነበር። ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? ፍቅራቸውን አስፍተው ጠላቶቻቸውን ጭምር በመውደድ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ሉቃስ ይህንኑ ሐሳብ “አባታችሁ ርኅሩኅ እንደ ሆነ ርኅሩኆች ሁኑ” በማለት አስፍሮታል።​—⁠ሉቃስ 6:36

ይሁን እንጂ ፍጽምና ለመጠበቅ የሚጣጣሩ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ፍጹም መሆን ይቻላል በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ በከንቱ ይደክማሉ። ከዚህም የተነሳ ከሌሎች ሰዎች ብዙ ይጠብቃሉ። ኔቨር ጉድ ኢነፍ ​—⁠ፍሪይንግ ዩርሰልፍ ፍሮም ዘ ቼይንስ ኦቭ ፐርፌክሽኒዝም የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው ፍጽምና የሚጠብቁ ሰዎች “ሌሎች ሥራቸውን የሚያከናውኑበት መንገድ ያበሳጫቸዋል። . . . በእነርሱ አስተሳሰብ አብረዋቸው ያሉ ሰዎች ወይ ጥሩ ሥራ ለመሥራት አይጣጣሩም አሊያም መሥራት የሚያስገኘውን እርካታ ለማግኘት አይሞክሩም።”

ለምሳሌ ያህል ካርሊ፣ የላቀ ችሎታ ያላቸው ተማሪዎች በሚማሩበት ክፍል ውስጥ የምትገኝ ሲሆን ጥሩ ውጤትም ታመጣ ነበር። ይሁን እንጂ ከሌሎች ጋር ባላት ግንኙነት ያን ያህል የተሳካላት አይደለችም። ሁሉም ነገር እንከን የለሽ እንዲሆን ትፈልግ ስለነበር አብዛኞቹ ጓደኞቿ ርቀዋታል። “ምንም ነገር በትክክል ማድረግ እንደማይችሉ ይሰማኛል” ስትል ተናግራለች።

አንዳንዶች ደግሞ ፍጽምና የሚጠብቁት ከሌሎች ሳይሆን ከራሳቸው ይሆናል። ኔቨር ጉድ ኢነፍ የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች “ብዙ እንደሚሳሳቱ ወይም የሚሠሩት ሥራ አጥጋቢ እንዳልሆነ [ይሰማቸዋል] . . . ሌሎች ስለ እነርሱ ያላቸው አመለካከት በጣም ያስጨንቃቸዋል።”

ፍጹም ለመሆን መጣር የሚያስከትለው ችግር

ፍጽምና ላይ ለመድረስ የሚደረግ ጥረት ጠቃሚ ከመሆን ይልቅ በአብዛኛው ጎጂ ነው። በተጨማሪም እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት የጥራት ደረጃን ከማሻሻል ይልቅ በአመዛኙ ለውድቀት ይዳርጋል። ዳንኤል የሚባል አንድ ክርስቲያን በይሖዋ ምሥክሮች የመሰብሰቢያ አዳራሽ በቃል እንዲያቀርብ የተመደበውን የተማሪ ንግግር ቀን ከሌት መለማመዱን ያስታውሳል። በስብሰባው ላይ የተገኙ ብዙ አድማጮች ግሩም ንግግር እንዳቀረበ በመግለጽ አመሰገኑት። ከዚያም ምክር ሰጪው ዘዴ በተሞላበት መንገድ አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦች ለገሰው። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ምክርን እንድንሰማና ተግሣጽን እንድንቀበል’ ያበረታታናል። (ምሳሌ 19:20) ሆኖም ዳንኤል የተሰጠውን ገንቢ ምክር በደስታ ከመቀበል ይልቅ የከንቱነት ስሜት አደረበት። “ራሴን ከሰው የማግለል ስሜት አደረብኝ” በማለት ያስታውሳል። ለበርካታ ሳምንታትም እንቅልፍ በዓይኑ አልዞረም።

በመሆኑም ፍጽምና የመጠበቅ ባሕርይ ትምህርት እንዳናገኝ እንቅፋት ይሆንብናል። ራሔል የተባለች ወጣት ለወጣቶች መረጃ በሚያቀርብ ድህረ ገጽ ላይ እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስገባ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ቆርጬ ነበር። ምንጊዜም የላቀ ውጤት አስመዘግብ የነበረ ሲሆን ከዚህም መውረድ የለብኝም የሚል አስተሳሰብ ነበረኝ።” ሆኖም ራሔል ብዙም ሳይቆይ ሒሳብ እንደሚከብዳት የተረዳች ከመሆኑም በላይ በዚህ ትምህርት ትንሽ ዝቅ ያለ ውጤት አመጣች። “ሌሎቹ ተማሪዎች ቢሆኑ በዚህ ውጤት ይደሰቱ ነበር፤ እኔ ግን እንደ ውርደት ቆጠርኩት” በማለት ታስታውሳለች። “ፍርሃትና ጭንቀት ይሰማኝ ጀመር . . . የቤት ሥራውን ለመሥራት እንደከበደኝ ብናገር ትምህርቱ እንዳልገባኝ አምኖ መቀበል ስለሚሆንብኝ አስተማሪዬን እንዲያስረዳኝ መጠየቅ አስፈራኝ። . . . አንዳንድ ጊዜ ከምወድቅ ብሞት ይሻለኛል ብዬ አስብ ነበር።”

አንዳንድ ወጣቶች በትምህርቴ ብወድቅስ የሚል ፍርሃት ሕይወታቸውን ለማጥፋት እስከ ማሰብ ያደርሳቸዋል። ደግነቱ አብዛኞቹ ወጣቶች እንዲህ ዓይነት አስከፊ እርምጃ ለመውሰድ አያስቡም። ሆኖም የአእምሮ ጤና ባለሙያ የሆኑት ሲልቪያ ሪም እንደተናገሩት እነዚህ ወጣቶች እወድቅ ይሆናል ብለው ስለሚፈሩ መጀመሪያውኑም የቤት ሥራቸውን አለመሥራትን ይመርጣሉ። ሪም እንዳሉት ከሆነ አንዳንድ ፍጽምና የመጠበቅ ባሕርይ ያላቸው ተማሪዎች “የተሰጣቸውን የቤት ሥራ አያስረክቡም፣ በሥራቸው አይረኩም፣ የቤት ሥራቸውን ይረሳሉ፣ ሰበብ መደርደር ይቀናቸዋል።”

በአንጻሩ ደግሞ ሌሎች ወጣቶች ጥሩ ውጤት ለማምጣት ከሚገባው በላይ ጥረት ያደርጉ ይሆናል። “የቤት ሥራዎቼን ያለ ምንም ስህተት ለመሥራት ስል በጣም አመሻለሁ” በማለት ዳንኤል በግልጽ ተናግሯል። ችግሩ ብዙውን ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ ልፋት ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን መሆኑ ነው። በቂ እንቅልፍ የማያገኝ ተማሪ ዝቅተኛ ውጤት የማምጣቱ አጋጣሚ የሰፋ ነው።

በመሆኑም ፍጽምና የመጠበቅ ባሕርይ ቁጡ ከመሆን፣ ለራስ ጥሩ ግምት ከማጣት፣ ከበደለኝነት ስሜት፣ አሉታዊ አስተሳሰብ ከመያዝ፣ ከአመጋገብ ሥርዓት መቃወስና ከመንፈስ ጭንቀት ጋር የተያያዘ መሆኑ ምንም አያስገርምም። ከሁሉም የከፋው ደግሞ ፍጽምና የመጠበቅ ባሕርይ በአንድ ሰው መንፈሳዊነት ላይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል መሆኑ ነው። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች እምነታቸውን ለሌሎች መግለጽ እንዳለባቸው ያዛል። (ሮሜ 10:​10፤ ዕብራውያን 10:​24, 25) ይሁን እንጂ ቪቪያን የምትባል ወጣት ሐሳቤን በትክክል መግለጽ ቢያቅተኝስ በሚል ፍርሃት በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መልስ ከመስጠት ትቆጠብ ነበር። ሊያ የምትባል ወጣትም ተመሳሳይ ፍርሃት እንዳለባት ገልጻለች። “የተሳሳተ ነገር ከተናገርኩ ሌሎች ስለ እኔ የተዛባ ግንዛቤ ይይዛሉ። በመሆኑም ዝም ማለትን እመርጣለሁ” ስትል ተናግራለች።

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ፍጹም ለመሆን መፈለግ ጎጂ ነው። በዚህ ርዕስ ውስጥ ከተዘረዘሩት ባሕርያት አንዱን እንደምታንጸባርቅ በመገንዘብህ የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግ እንደሚኖርብህ ይሰማህ ይሆናል። ቀጥሎ የሚወጣው ርዕስ ለውጥ ማድረግ የምትችልበትን መንገድ ያብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.6 አንድ ጥናት እንዳሳየው በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ጥሩ ተሰጥኦ ካላቸው ተማሪዎች መካከል 87.5 በመቶ የሚሆኑት ፍጽምና የመጠበቅ ዝንባሌ አላቸው።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዳንድ ወጣቶች መጥፎ ውጤት እንዳላመጣ በሚል ፍርሃት የቤት ሥራቸውን መሥራት አይፈልጉም

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፍጽምና የመጠበቅ ባሕርይ የመንፈስ ጭንቀትና ለራስ አክብሮት የማጣት ስሜት ሊያስከትል ይችላል