በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማኅበራዊ እሴቶች—እንደተለወጡ ሆኖ ይሰማሃልን?

ማኅበራዊ እሴቶች—እንደተለወጡ ሆኖ ይሰማሃልን?

ማኅበራዊ እሴቶች—እንደተለወጡ ሆኖ ይሰማሃልን?

“በዚህች አገር ላይ ከተደቀኑት ችግሮች በሙሉ በጣም አሳሳቢ የሆነው ችግር የትኛው ነው?” በዩናይትድ ስቴትስ ይህ ጥያቄ ከቀረበላቸው ሰዎች መካከል አብዛኞቹ የቤተሰብ መፈራረስንና የሥነ ምግባር ውድቀትን በአንደኛ ደረጃ አስቀምጠዋቸዋል። የዚህ ችግር አሳሳቢነት የሚሰማቸው እነዚህ ሰዎች ብቻ አይደሉም።

ለምሳሌ ያህል ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪብዩን የተባለው የፓሪስ ዕለታዊ ጋዜጣ “በተለይ በወጣቶች ዘንድ ዓለምን በመዋጥ ላይ የሚገኘውን ስግብግብነትን፣ ራስ ወዳድነትንና በማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ የሚታየውን መከፋፈል የሚያለዝብና አንድነት የሚያስገኝ አንድ ዓይነት ራእይ፣ አንድ ዓይነት እውቅና ያገኙ መሠረታዊ ሥርዓቶች አስፈላጊነት በግልጽ ይታያል። . . . ዓለም አቀፋዊ እውቅና ያገኘ ሥነ ምግባር አስፈላጊ ስለመሆኑ የሚደረገው ክርክር እየተፋፋመ መምጣቱ አንድ የጎደለ ነገር መኖሩ ተቀባይነት እንዳገኘ ያሳያል” ብሏል።

የንግድ ድርጅቶችን ጨምሮ መንግሥታትና የዓለም መሪዎች ደስታ፣ ሰላምና ፀጥታ የሰፈነበት ዓለም ለማምጣት የሚያስፈልጉት እሴቶች እንዳሏቸው ሆኖ ይሰማሃል? በዙሪያችን በሚታየው የማኅበራዊ እሴቶች መለዋወጥ ምክንያት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ጉዳት እንደደረሰብህ ሆኖ ይሰማሃል?

በግልህ በጥብቅ ሊያሳስቡህ ከሚችሉት ነገሮች አንዱ የግል ደህንነትህ ሊሆን ይችላል። የምትኖረው ቤትህን ሳትቆልፍ ልትወጣ በምትችልበት አካባቢ ነው? ከመሸ በኋላ ሰፈርህ ውስጥ ሳትፈራ መዘዋወር ትችላለህ? የምትኖረው የተፋፋመ ጦርነት በማይካሄድበት፣ የተካረረ የጎሣ ግጭት ወይም በወንጀለኛ ቡድኖች መካከል የሚካሄድ አምባጓሮ በሌለበት አካባቢ ቢሆንም እንኳን ከማጅራት መቺዎች፣ ከዘራፊዎች ወይም ከሌቦች ስጋት ነጻ ላትሆን ትችላለህ። ይህ ሁሉ ጭንቀትና ሐሳብ መፍጠሩ የማይቀር ነው።

ከዚህም በተጨማሪ በመጠኑም ቢሆን ከዚህ በፊት ትመካባቸው በነበሩ ሰዎች ላይ ያለህን እምነት ሳታጣ አትቀርም። ምናልባት በሥራህ አካባቢ ወይም በግል ሕይወትህ ሰዎች የግል ፍላጎታቸውን የሚያራምድላቸው እስከሆነ ድረስ መጥፎ ነገር ቢያደርጉብህ ምንም ቅር እንደማይላቸው ሳትገነዘብ አትቀርም።

መንግሥታት ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑ ይገባ ነበር

በታሪክ ዘመናት በሙሉ አንድ ኅብረተሰብ በሚያምንበትና በሚከተለው እሴት እንዲሁም ያንን ኅብረተሰብ የሚያስተዳድረው መንግሥት በሚከተለው እሴት መካከል የቅርብ ትስስር ነበር። በኋላ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት የሆኑት ካልቪን ኩሊጅ “ሰዎች በተፈጥሮ ስለሚገኝ መብት ይናገራሉ። እኔ ግን በተፈጥሮ የተገኙ ወይም በሕግ ተደንግገው ከመታወቃቸው በፊት የተገኙ መብቶች የት አሉ ብዬ እጠይቃቸዋለሁ” ብለዋል።

እንደ ፕሬስ፣ የመሰብሰብ፣ የሃይማኖትና በሕዝብ ፊት የመናገር ነጻነት፣ ሕጋዊ ካልሆነ እስራት ወይም ማስፈራራት ነጻ እንደመሆንና ከአድልዎ ነጻ የሆነ ፍርድ እንደማግኘት ያሉትን ሰብዓዊ መብቶች ማስከበር ወይም መገደብ የሚችሉት (በምንም መንገድ ሥልጣን ላይ ይውጡ) ሥልጣን ላይ ያሉ መንግሥታት ናቸው ማለት ነው።

በኋላ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት የሆኑት አብረሃም ሊንከን በአንድ ወቅት “የአንድ መንግሥት ሕጋዊ ዓላማና ግብ አንድ የሰዎች ማኅበረሰብ ብቻውን በተናጠል ለራሱ ሊሠራ ያልቻለውን ወይም አሟልቶ ሊያከናውን ያልቻለውን ነገር ማድረግ ነው” ብለው ነበር። መንግሥታት እንደነዚህ ያሉትን ክቡር ዓላማዎች ለማሳካት ሲጣጣሩ ሕዝቦችም በባለ ሥልጣኖቻቸው ይታመናሉ።

ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ እንዲህ ያለው እምነት ለጥርጣሬና ላለመተማመን መንፈስ ቦታውን የለቀቀ ይመስላል። አንድ በቅርቡ በዩናይትድ ስቴትስ የተደረገ ጥናት ጥናቱ ከተካሄደባቸው ሰዎች መካከል 68 በመቶ የሚሆኑት የፌዴራል መንግሥት ባለ ሥልጣናት ሥነ ምግባር ያን ያህል ጥሩ የሚባል እንዳልሆነ እንዲያውም የተበላሸ እንደሆነ ተናግረዋል። በብዙ አገሮች ሕዝቦች ለመንግሥት ባለ ሥልጣናት ያላቸው አመለካከት በከፍተኛ ደረጃ በሚፈጸሙ የጉቦና የሙስና ቅሌቶች ተናውጧል። እንዲህ ያለው ሁኔታ በጣም ብዙ ሰዎች ግራ እንዲጋቡ አድርጓል።

የንጉሥ ሰሎሞን ጥሩ ምሳሌነት

በገዥነት ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች የሚከተሉት ማኅበራዊ እሴት በተገዥዎች ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንደሚኖረው የሚያሳይ አንድ የጥንት ምሳሌ እንመልከት። ንጉሥ ሰሎሞን በ12ቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ ከ1037 እስከ 998 ከዘአበ በነበረው ጊዜ ነግሦ ነበር። አባቱ ንጉሥ ዳዊት ከታላላቆቹ የእስራኤል ነገሥታት አንዱ ነበር። ዳዊት እውነትንና ጽድቅን የሚወድ ከሁሉ በላይ ደግሞ በይሖዋ አምላክ ሙሉ በሙሉ የሚታመንና የሚመካ ሰው እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ዳዊት ለልጁ ለሰሎሞን እነዚህኑ ማኅበራዊ እሴቶች አስተምሮታል።

ሁሉን የሚችለው አምላክ ለሰሎሞን በራእይ ተገልጦ “ምን እንድሰጥህ ለምነኝ” ሲል ነግሮት ነበር። (2 ዜና መዋዕል 1:​7) ሰሎሞንም ብዙ ሀብት፣ ታላቅ ክብር ወይም የፖለቲካ ድል እንዲሰጠው ከመጠየቅ ይልቅ የእስራኤልን ብሔር ጥሩ አድርጎ ለማስተዳደር እንዲችል ጠቢብ፣ አስተዋይና ታዛዥ ልብ እንዲሰጠው በመጠየቅ እንዲህ ላሉ ማኅበራዊ እሴቶች ትልቅ ቦታ እንደሚሰጥ አሳይቷል።

ታዲያ የሰሎሞን አገዛዝ ለሕዝቡ ምን ጥቅም አምጥቷል? የብሔሩን መንፈሣዊ እሴቶች አክብሮ እስከኖረበት ጊዜ ድረስ አምላክ ጥበብ፣ ክብርና ሃብት በመስጠት ባርኮታል። በሰሎሞን የንግሥና ዘመን ከፍ ያለ ቁሳዊ ብልጽግና እንደነበረ በመሬት ቁፋሮ ጥናት ተረጋግጧል። ዘ አርኪዎሎጂ ኦቭ ዘ ላንድ ኦቭ ኢዝራኤል የተባለው መጽሐፍ “ከሁሉም አቅጣጫዎች ወደ ንጉሣዊው አደባባይ ይጎርፍ የነበረው ሃብትና እየደራ የመጣው ንግድ . . . በሕዝቡ አኗኗርና ብልጽግና ላይ ፈጣን የሆነና በገሐድ የሚታይ ለውጥ አስከትሎ ነበር” ይላል።

አዎን፣ ጥሩ የነበረው የሰሎሞን መንግሥት ለተገዥዎቹ ሰላም፣ ደህንነትና ደስታ አስገኝቶ ነበር። “በሰሎሞንም ዘመን ሁሉ ይሁዳና እስራኤል ከዳን ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ተዘልሎ ይቀመጥ ነበር።”​—⁠1 ነገሥት 4:​20, 25

የንጉሥ ሰሎሞን መጥፎ ምሳሌነት

ይሁን እንጂ ሰሎሞን ይመራባቸው የነበሩት ማኅበራዊ እሴቶች እንደ ብዙዎቹ የዘመናችን መሪዎች ውሎ አድሮ ተለወጡ። የመጽሐፍ ቅዱሱ ትረካ እንዲህ ይላል:- “ለእርሱም ወይዛዝር የሆኑ ሰባት መቶ ሚስቶች ሦስት መቶም ቁባቶች ነበሩት፤ ሚስቶቹም ልቡን አዘነበሉት። ሰሎሞንም ሲሸመግል ሚስቶቹ ሌሎችን አማልክት ይከተል ዘንድ ልቡን አዘነበሉት፤ የአባቱ የዳዊት ልብ ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም እንደ ነበረ የሰሎሞን ልቡ እንዲሁ አልነበረም።”​—⁠1 ነገሥት 11:​3, 4

ታዲያ ሰሎሞን ትልቅ ቦታ ይሰጣቸው የነበሩት እሴቶች መለወጥ በሕዝቡ ላይ ምን ውጤት አስከተለ? ሰሎሞን ያን የመሰለ ታላቅ ችሎታና ጥበብ ቢኖረውም በኋለኞቹ የንግሥና ዓመታት ጨቋኝ ገዥ ሆነ። የመንግሥቱ ወጪ በጣም እየጨመረ መምጣቱ በብሔሩ ኢኮኖሚ ላይ ከባድ ድቀት አስከተለ። ሠራተኛው ሕዝብ መበሳጨት ጀመረ። የፖለቲካ ተቀናቃኞች ንጉሡን መቃወምና ሥልጣኑን መቀናቀን ጀመሩ። ብሔሩ የነበረውን የአንድነት ስሜት አጣ። ሰሎሞን ራሱ “ጻድቃን በበዙ ጊዜ ሕዝብ ደስ ይለዋል፤ ኀጥኣን በሠለጠኑ ጊዜ ግን ሕዝብ ያለቅሳል” ሲል የጻፈው በትክክል መፈጸሙ የሚያስገርም ነው።​—⁠ምሳሌ 29:​2

ሰሎሞን ከሞተ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በተፈጠረ ሁከትና አለመተማመን ምክንያት አንድ የነበረው ሕዝብ ለሁለት ተከፍሎ የመከራ፣ የመነጣጠልና የውድቀት ዘመን ተከተለ። እስራኤላውያን በጣም ከባድ የሆነ ጉዳት ደረሰባቸው። መንግሥታቸው የሕዝቡን ጥቅምና ፍላጎት ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግ ይከተላቸው የነበሩትን እሴቶች ለወጠ። መሠረታዊው ጥፋት መሪዎቻቸው ይሖዋንና የይሖዋን ሕግጋት ችላ ማለታቸው ነበር። በዚህም ምክንያት መላው ሕዝብ ለመከራ ተዳረገ።

በዘመናችን ተስፋፍቶ የሚገኘው የአለመተማመን ስሜት

ዛሬ በመንግሥት፣ በንግድና በሃይማኖት አካባቢ ያሉ ብዙ ሰዎች ከፍተኛ የሆኑ ማኅበራዊ እሴቶችን ስለ ማክበር እምብዛም አይጨነቁም። ይህን በማድረጋቸውም በአጠቃላይ በሕዝባቸው አእምሮና ልብ ውስጥ ቅሬታ እንዲፈጠር አድርገዋል። የአገሮቻቸውን መሠረታዊ ችግሮች መፍታት የተሳናቸው መንግሥታትና መሪዎች ቁጥር ዕለት ተዕለት እየጨመረ መጥቷል።

ለምሳሌ ያህል ጦርነትን ለማጥፋት ወይም እየናረ የመጣውን የሕክምና ዋጋ ለመቀነስ ወይም ሕገወጥ አደገኛ ዕፆች የሚያስከትሉትን ጉዳት ለመገደብ አልቻሉም። የትምህርት ሥርዓቱም መፈራረስ ጀምሯል። ቁማር አደራጅተው እስከ ማጫወት የደረሱ መንግሥታትም አሉ። ብዙ የንግድና የሃይማኖት መሪዎች የፈጸሟቸው ነውሮችና የብልግና ድርጊቶች በእነርሱ ሥር የሚገኙትን ሕዝቦች አስደንግጠዋል። አመራር ይሰጣሉ ተብለው በሚታሰቡ ሰዎች አቋም ላይ ጥርጣሬና አለመተማመን እየተስፋፋ መሄዱ ሊያስደንቅ አይገባም።

ታዲያ መሠረታዊ የሆኑትን ሰብዓዊ መብቶችና ማኅበራዊ እሴቶች ለመጠበቅ ከዚያም አልፎ ለማስከበር የሚችል መንግሥት ሊኖር ይችላል? አዎን፣ ሊኖር ይችላል። የመደምደሚያ ርዕሳችን ይህን ያብራራል።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

‘ስግብግብነት፣ ራስ ወዳድነትና መከፋፈል መላውን ዓለም በማጥለቅለቅ ላይ ያለ ይመስላል።’​—⁠ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪብዩን

[በገጽ 26 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ንጉሥ ሰሎሞን የአምላክን ሕግጋት አክብሮ በኖረባቸው ጊዜያት በግዛቱ ውስጥ ከፍተኛ ማኅበራዊ እሴቶች እንዲሰፍኑ አድርጓል