በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በነፍሳት የሚተላለፉ በሽታዎች እየከፋ የመጣ ችግር

በነፍሳት የሚተላለፉ በሽታዎች እየከፋ የመጣ ችግር

በነፍሳት የሚተላለፉ በሽታዎች እየከፋ የመጣ ችግር

በላቲን አሜሪካ በሚገኝ አንድ መኖሪያ ቤት የመኝታ ሰዓት ደርሷል። አንዲት እናት ሕፃን ልጅዋን አስተካክላ ካስተኛች በኋላ ደህና እደር ብላ ትሰናበተዋለች። መብራት ከጠፋ በኋላ ግን የሚያብረቀርቅ ጥቁር ቀለምና ከሦስት ሴንቲ ሜትር የማይበልጥ ቁመት ያላት የሜክሲኮ ትኋን በጣራው ላይ ካለ ስንጥቅ ትወጣና አልጋው ላይ ዱብ ትላለች። ማንም ሳያያት እንቅልፍ በወሰደው ሕፃን ፊት ላይ ታርፍና ለስላሳ ቆዳውን በአፏ ትበሳለች። ትኋኗ የሕፃኑን ደም ከመጠጠች በኋላ በተውሳክ የተሞላ ኩሷን ትጥልበታለች። ልጁ በእንቅልፍ ልቡ ፊቱን ያክክና ተውሳክ የሞላበትን የትኋን ኩስ ቁስሉ ላይ ይቀባል።

ሕፃኑ በዚህ ቅጽበታዊ የትኋን ንክሻ ምክንያት የቻጋስ በሽታ ይይዘዋል። በአንድ ወይም በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ኃይለኛ ትኩሳት ይይዘውና ሰውነቱ ያብጣል። ልጁ ከሞት ቢተርፍ እንኳ ጥገኛ ሕዋሳቱ ልቡን፣ ነርቮቹንና ውስጣዊ ሕዋሳቱን ይወርሩና ሰውነቱን መኖሪያቸው ያደርጋሉ። ምንም ዓይነት የሕመም ምልክት ሳይታይበት ከ10 እስከ 20 ዓመት የሚያክል ጊዜ ያልፋል። ከጊዜ በኋላ ግን ሆድ ዕቃው መቁሰል ይጀምራል፣ አንጎሉ ይመረዛል፣ በመጨረሻም ልቡ መምታቱን ያቆምና ይሞታል።

ይህ ታሪክ ልብ ወለድ ይሁን እንጂ የቻጋስ በሽታ የሚይዘው እንዴት እንደሆነ ያሳያል። በላቲን አሜሪካ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዚህች ቀሳፊ ትኋን የመነከስ አደጋ ያጋጥማቸዋል።

ባለ ብዙ እግሮቹ የሰው ልጅ ባልንጀሮች

ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ “ከዋና ዋናዎቹ የትኩሳት በሽታዎች መካከል አብዛኞቹ የሚተላለፉት በጥቃቅን ነፍሳት አማካኝነት ነው” ይላል። “ነፍሳት” የሚባሉት እንደ ዝንብ፣ ቁንጫ፣ ትንኝ፣ ቅማልና ጥንዚዛ ያሉ ባለ ስድስት እግር ፍጥረታት ሲሆኑ እንደ መዥገርና ማይት የመሰሉ ባለ ስምንት እግር ፍጥረታትንም ይጨምራል። የሳይንስ ሊቃውንት እነዚህን ነፍሳት በሙሉ አርትሮፖድ በሚባል በአንድ ትልቅ ምድብ ውስጥ ያካተቷቸው ሲሆን በዚህ ምድብ ውስጥ ቢያንስ አንድ ሚልዮን የሚደርሱ የታወቁ ዝርያዎች ይገኛሉ።

አብዛኞቹ ነፍሳት በሰው ልጅ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት የማያደርሱ ሲሆኑ እንዲያውም አንዳንዶቹ ጠቃሚ ናቸው። እነዚህ ነፍሳት ባይኖሩ ኖሮ በምግብነት የምንገለገልባቸው ዛፎችና እጽዋት ዘር ሊይዙ ወይም ፍሬ ሊያፈሩ አይችሉም ነበር። አንዳንድ ነፍሳት በቆሻሻነት የተጣሉ ነገሮች ተመልሰው አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ይረዳሉ። ብዙዎቹ ነፍሳት እጽዋትን ብቻ የሚመገቡ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ሌሎች ነፍሳትን ይመገባሉ።

እርግጥ በኃይለኛ ንክሻቸው ወይም ብዙ ሆነው በመርመስመሳቸው ሰዎችንና እንስሳትን የሚያውኩና ሰብል የሚያወድሙ ነፍሳትም አሉ። ከእነዚህ ሁሉ የሚከፉት ግን በሽታና ሞት የሚያዛምቱት ናቸው። የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ ቁጥጥርና መከላከል መሥሪያ ቤት ባልደረባ የሆኑት ዱዋን ገብለር “ከ17ኛው እስከ 20ኛው መቶ ዘመን መግቢያ ባለው ጊዜ ውስጥ በነፍሳት በሚተላለፉ በሽታዎች ምክንያት የሞቱት ሰዎች ቁጥር በሌሎች ምክንያቶች ከሞቱት ሰዎች በሙሉ ይበልጣል” ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ ከስድስት ሰዎች መካከል አንዱ በነፍሳት በሚዛመት በሽታ ይያዛል። በነፍሳት የሚተላለፉ በሽታዎች በሰው ልጆች ላይ ከሚያደርሱት መከራና ሥቃይ በተጨማሪ በብዙ አገሮች፣ በተለይ ቀድሞውንም ብዙ ገንዘብ በሌላቸው ታዳጊ አገሮች ላይ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ኪሣራ ያስከትላሉ። የአንድ ወቅት ወረርሽኝ እንኳን ብዙ ኪሣራ ሊያስከትል ይችላል። በ1994 በምዕራባዊ ሕንድ የፈነዳ አንድ ወረርሽኝ ከአካባቢውና ከመላው ዓለም በቢልዮን የሚቆጠር ዶላር አስወጥቷል። የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እንደሚለው እነዚህ በሽታዎች በቁጥጥር ሥር እስካልዋሉ ድረስ እጅግ ድሃ የሆኑት የዓለም አገሮች ካሉበት ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ፈጽሞ ሊያንሰራሩ አይችሉም።

ነፍሳት በሽታ የሚያስተላልፉብን እንዴት ነው?

ነፍሳት በሽታ የሚያዛምቱባቸው ሁለት ዋና ዋና መንገዶች አሉ። አንደኛው መንገድ ተሸካሚ በመሆን ነው። ሰዎች በጫማቸው ቆሻሻ ይዘው ወደ ቤት እንደሚገቡ ሁሉ “ዝንቦችም በሽታ ሊያመጡ የሚችሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ጥቃቅን ተውሳኮችን በእግሮቻቸው ተሸክመው ሊመጡ ይችላሉ” ይላል ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ። ለምሳሌ ያህል ዝንቦች ከዓይነ ምድር ላይ ያነሱትን ቆሻሻ በምንበላው ምግብ ወይም በምንጠጣው መጠጥ ላይ ሊያራግፉ ይችላሉ። በዚህ ምክንያት እንደ ታይፎይድ፣ ተቅማጥና ኮሌራ የመሳሰሉ ቀሳፊ በሽታዎች ወደ ሰዎች ይተላለፋሉ። በተጨማሪም ዝንቦች በመላው ዓለም ዋነኛው የዓይነ ስውርነት መንስኤ የሆነውን የትራኮማ በሽታ ያዛምታሉ። ትራኮማ በውጨኛ የዓይን ክፍል ላይ የሚገኘውን ኮርኒያ የሚባለውን ክፍል በመጉዳት ዓይን እንዲታወር ያደርጋል። በመላው ዓለም 500, 000, 000 የሚያክሉ ሰዎች በዚህ በሽታ ይሠቃያሉ።

በቆሻሻ አካባቢ የሚርመሰመሱት በረሮዎችም በሽታ እንደሚሸከሙ ይገመታል። በተጨማሪም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አስም በተለይ በሕፃናት ላይ የበዛው በበረሮ አለርጂ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ሊቃውንት ይናገራሉ። ለምሳሌ በአስም ምክንያት ትንፋሽ እያጠራት ለበርካታ ምሽቶች እንቅልፍ አጥታ የቆየችውን አሽሊ የተባለች የ15 ዓመት ልጃገረድ እንመልከት። ሐኪሟ ሳንባዋን ሊያዳምጥ ሲጠጋ አንዲት በረሮ ከአሽሊ ሸሚዝ ውስጥ ወጥታ በመመርመሪያው አልጋ ላይ ዱብ አለች።

በነፍሳት ውስጥ የሚኖሩ በሽታዎች

ነፍሳት የቫይረስ፣ የባክቴሪያ ወይም የሌሎች ጥገኛ ሕዋሳት ማደሪያ ሲሆኑ በንክሻ ወይም በሌሎች መንገዶች በሽታ ያስተላልፋሉ። ይህም በሽታ የሚያስተላልፉበት ሁለተኛው መንገድ ነው። በዚህ መንገድ ወደ ሰው ልጆች በሽታ የሚያስተላልፉት ነፍሳት በጣም ጥቂቶች ናቸው። ለምሳሌ ያህል በሺህ የሚቆጠሩ የትንኝ ዝርያዎች ቢኖሩም ብዙ ሰዎችን በመግደል ከሳንባ ነቀርሳ ቀጥሎ ከዓለም ሁለተኛ ደረጃ የያዘውንና ተዛማጅ በሽታ የሆነውን ወባን የሚያስተላልፉት አኖፊሊስ የተባሉት ዝርያዎች ብቻ ናቸው።

ይሁን እንጂ በሌሎች ትንኞች የሚተላለፉ በርካታ በሽታዎች አሉ። የዓለም ጤና ድርጅት “በሽታ አስተላላፊ ከሆኑ ነፍሳት በሙሉ የትንኞችን ያህል አደገኞች የሉም። በየዓመቱ በመቶ ሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች መታመምና ለበርካታ ሚልዮኖች ሞት ምክንያት የሆኑት የወባ፣ የብጫ ወባና ደንግ የሚባል በሽታ የሚያስተላልፉት ትንኞች ናቸው” ሲል ዘግቧል። ቢያንስ ከምድር ነዋሪዎች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት ለወባ በሽታ፣ ሌሎች 40 በመቶ የሚሆኑ ደግሞ ደንግ ለሚባለው በሽታ የተጋለጡ ናቸው። በብዙ አካባቢዎች አንድ ሰው በሁለቱም በሽታዎች ሊያዝ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች አሉ።

እርግጥ በውስጣቸው በሽታ የሚሸከሙ ነፍሳት ትንኞች ብቻ አይደሉም። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያሠቃየውና በርካታ ማኅበረሰቦች ለም እርሻቸውን ትተው እንዲሰደዱ የሚያደርገው የእንቅልፍ በሽታም የሚዛመተው በጼጼ ዝንቦች ነው። ጥቁር ዝንቦች ዓይን የሚያሳውሩ ተውሳኮችን ወደ ሰው በማስተላለፍ 400, 000 የሚያክሉ አፍሪካውያንን ለዓይነ ስውርነት ዳርገዋል። የአሸዋ ዝንቦች ሊሽማንያሰስ በሚል አጠቃላይ ስያሜ የሚታወቁትን በዓለም ዙሪያ በርካታ ሰዎችን አመንምነው እስከ ሞት የሚያደርሱ በሽታዎች የሚያስከትሉትን ሕዋሳት ያስተላልፋሉ። የትም የማትታጣው ቁንጫ እንኳን የኮሶ ትል፣ በአንጎል ላይ ጉዳት የሚያስከትለው ኢንሰፍላይትስ የተባለው በሽታ እንዲሁም የቱላረሚያ እና በመካከለኛው መቶ ዘመን በስድስት ዓመት ጊዜ ውስጥ የአውሮፓን ሢሶ ያወደመው ቸነፈር ተሸካሚ ልትሆን ትችላለች።

ቅማል፣ መዥገርና ማይት ከሌሎች በሽታዎች በተጨማሪ የተለያዩ የተስቦ ዓይነቶችን ሊያስተላልፉ ይችላሉ። ከሐሩር መስመር ውጭ በሚገኙ አገሮች የሚኖሩ መዥገሮች በዩናይትድ ስቴትስና በአውሮፓ በጣም የተለመደ በነፍሳት የሚተላለፍ በሽታ የሆነውንና አካል የሚያጎሳቁለውን የላይም በሽታ ያስተላልፋሉ። አንድ የስዊድን ጥናት እንደሚያመለክተው ድንበር አቋራጭ ወፎች መዥገሮችን በሺህ የሚቆጠር ኪሎ ሜትር ርቀው ወደሚገኙ አገሮች በማጓጓዝ የተሸከሟቸውን በሽታዎች ወደ አዳዲስ አካባቢዎች ያደርሳሉ። ብሪታኒካ እንደሚለው “መዥገሮች ወደ ሰው በሚያስተላልፏቸው በሽታዎች ብዛት ረገድ ከትንኞች ቀጥለው አቻ የማይገኝላቸው ናቸው” ይላል። እንዲያውም አንዲት መዥገር እስከ ሦስት ሊደርሱ የሚችሉ በሽታ አምጪ ተውሳኮችን መሸከም ስትችል በአንድ ጊዜ ንክሻ ብቻ ሦስቱንም በሽታዎች ማስተላለፍ ትችላለች።

ከበሽታ “እረፍት” ማግኘት

ነፍሳት በሽታ እንደሚያስተላልፉ በሳይንስ ሊረጋገጥ የቻለው ገና በቅርቡ በ1877 ነው። ከዚያ ወዲህ በሽታ አዛማች ነፍሳትን ለመቆጣጠር ወይም ለማስወገድ ታላላቅ ዘመቻዎች ተካሂደዋል። በ1939 ዲዲቲ የተባለው ፀረ ተባይ መድኃኒት የተፈለሰፈ ሲሆን በ1960ዎቹ ዓመታት ከአፍሪካ ውጭ በነፍሳት የሚተላለፉ በሽታዎች ዋነኛ የጤና ችግር እንደሆኑ ተደርገው መታየታቸው ቀርቶ ነበር። በዚህ ምክንያት በሽታ አስተላላፊዎቹን ነፍሳት በመቆጣጠር ላይ ሳይሆን በሽተኞቹን በመድኃኒት በማከም ላይ ትኩረት ማድረግ ተጀመረ። በነፍሳትና በአኗኗራቸው ላይ ሲደረግ የነበረው ጥናትም ቀዘቀዘ። በተጨማሪም አዳዲስ መድኃኒቶች መገኘት ስለጀመሩ ሳይንስ ማንኛውንም በሽታ ሊመታ የሚችል “ተአምራዊ ጥይት” ማግኘት እንደማያቅተው ታስቦ ነበር። መላው ዓለም ከተዛማች በሽታዎች “እረፍት” ማግኘት ጀመረ። ይሁን እንጂ እረፍቱ ለብዙ ጊዜ አልዘለቀም። የሚቀጥለው ርዕስ እረፍቱ ያልዘለቀው ለምን እንደሆነ ያብራራል።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በአሁኑ ጊዜ ከስድስት ሰዎች አንዱ በነፍሳት በሚተላለፉ በሽታዎች ይሠቃያል

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሜክሲኮ ትኋን

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዝንቦች በሽታ አምጪ ተውሳኮችን በእግራቸው ይሸከማሉ

[በገጽ 5 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ብዙ ነፍሳት በውስጣቸው በሽታ ይሸከማሉ

ጥቁር ዝንቦች የሚያሳውር በሽታ ይሸከማሉ

ትንኞች ወባ፣ ብጫ ወባና ደንግ የሚባለውን በሽታ ያስተላልፋሉ

ቅማሎች ተስቦ ሊያስተላልፉ ይችላሉ

ቁንጫዎች የኢንሰፍላይትስና የሌሎች በሽታዎች ተሸካሚዎች ናቸው

ጼጼ ዝንቦች የእንቅልፍ በሽታን ያስተላልፋሉ

[ምንጭ]

WHO/TDR/LSTM

CDC/James D. Gathany

CDC/Dr. Dennis D. Juranek

CDC/Janice Carr

WHO/TDR/Fisher

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የሥዕሎቹ ምንጮች]

Clemson University - USDA Cooperative Extension Slide Series, www.insectimages.org