በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እንደገና ያገረሸው ለምንድን ነው?

እንደገና ያገረሸው ለምንድን ነው?

እንደገና ያገረሸው ለምንድን ነው?

ከአርባ ዓመት በፊት እንደ ወባ፣ ብጫ ወባና ደንግ ያሉ በትንኝ የሚተላለፉ በሽታዎች ከብዙ የምድር አካባቢዎች እንደተወገዱ ይታሰብ ነበር። ይሁን እንጂ ያልተጠበቀ ሁኔታ መታየት ጀመረና በነፍሳት የሚተላለፉ በሽታዎች እንደገና ማንሰራራት ጀመሩ።

ለምን? አንደኛው ምክንያት አንዳንዶቹ ነፍሳትና እነርሱ የሚሸከሟቸው ረቂቅ የበሽታ ተህዋሲያን እነርሱን ለማጥፋት የተሠሩትን መድኃኒቶች የመቋቋም ኃይል ማዳበራቸው ነው። ይህ ከአደገኛ ሁኔታ ጋር የመላመድ ተፈጥሯዊ ሂደት ፀረ ተባይ መድኃኒቶችን ከመጠን በላይ በመጠቀም ብቻ ሳይሆን መድኃኒቶችን አለአግባብ በመጠቀም ጭምር ተጠናከረ። ሞስኪቶ የተባለው መጽሐፍ “ብዙዎቹ ችግረኛ ቤተሰቦች የሚሰጣቸውን መድኃኒት ሕመሙ እስኪታገስላቸው ድረስ ብቻ ከወሰዱ በኋላ የቀረውን ለሌላ ጊዜ እንዲያገለግላቸው ያስቀምጣሉ” ይላል። እንደዚህ ካለው ያልተሟላ ሕክምና በኋላ በበሽተኛው ሰውነት ውስጥ የሚቀሩት የበረቱ ረቂቅ ተህዋሲያን መድኃኒት የማይደፍራቸው አዲስ ትውልዶችን ያፈራሉ።

የአየር ንብረት መለወጥ

ተፈጥሯዊና ማኅበረሰባዊ ለውጦች በነፍሳት በሚተላለፉ በሽታዎች ማገርሸት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በዚህ ረገድ የዓለም አየር ንብረት መለወጥ ተጠቃሽ ነው። የዓለም አካባቢዎች ሙቀት እየጨመረ መሄድ በሽታ አስተላላፊ ነፍሳት ቀዝቃዛ ወደነበሩ አካባቢዎች እንዲዛመቱ እንደሚያደርግ አንዳንድ ሳይንቲስቶች ይናገራሉ። አሁንም እንኳን እንዲህ ያለው አዝማሚያ መታየት እንደጀመረ የሚያሳዩ ማስረጃዎች አሉ። በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የጤናና የዓለም አካባቢዎች ማዕከል ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ፖል አር ኤፕስታይን “በዛሬው ጊዜ በአፍሪካ፣ በእስያና በላቲን አሜሪካ ተራራማ አካባቢዎች ነፍሳትና (እንደ ወባና ደንግ ያሉ) በነፍሳት የሚተላለፉ ሌሎች በሽታዎች መታየት ጀምረዋል” ብለዋል። እስካሁን ድረስ በፓስፊክ ውቅያኖስ ዳርቻዎች ብቻ ተወስኖ የቆየው ደንግ የተባለው በሽታ ወደ ኮስታ ሪካ ተራራማ አካባቢዎች ተዛምቶ አገሪቱን በሞላ አዳርሷል።

የሙቀት መጨመር የሚያስከትለው ለውጥ በዚህ ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም። በአንዳንድ አካባቢዎች ወንዞች ወደ ረግረግነት እንዲለወጡ ሲያደርግ በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ዝናብና የጎርፍ መጥለቅለቅ ያስከትላል። ከዚያም ውኃው ተቋጥሮ ወደ ኩሬነት ይለወጣል። በሁለቱም ሁኔታዎች የተቋጠረው ውኃ ለትንኞቹ ምቹ የመራቢያ ቦታ ይሆናል። በተጨማሪም የሙቀት መጨመር የትንኞችን የመራቢያ ዑደት በማሳጠር በፍጥነት እንዲባዙ ያደርጋል እንዲሁም ትንኞች የሚባዙበትን ወቅት ያራዝማል። ትንኞች የአየር ሙቀት ሲጨምር ይበልጥ ንቁዎች ይሆናሉ። የአየር ሙቀት በትንኞቹ ሆድ ዕቃ ላይ ሳይቀር የሚያስከትለው ለውጥ አለ። በሽታ አማጭ ረቂቅ ሕዋሳት የሚራቡበት ፍጥነት እንዲጨምር ስለሚያደርግ በአንድ ንክሻ ብቻ በበሽታ የመለከፍን ዕድል ከፍ ያደርጋል። ሌሎች አሳሳቢ ሁኔታዎችም አሉ።

በሽታ እንዴት ሊዛመት እንደሚችል የሚያሳይ ምሳሌ

በሰዎች ማኅበራዊ ኑሮ ላይ የሚታይ ለውጥም በነፍሳት ለሚተላለፉ በሽታዎች መስፋፋት አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል። ይህ እንዴት ሊሆን እንደሚችል ለመረዳት የነፍሳትን ድርሻ ይበልጥ ጠለቅ ብለን መመልከት ይኖርብናል። ብዙ በሽታዎችን በማስተላለፍ ሂደት ውስጥ ነፍሳት የሚጫወቱት ሚና ከፊል ብቻ ሊሆን ይችላል። አንድ እንስሳ ወይም ወፍ በአካሉ ላይ ነፍሳትን በመሸከም ወይም በደሙ ውስጥ በሽታ አማጭ ሕዋሳትን በማኖር በሽታ ተሸካሚ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። ተሸካሚው እንስሳ በበሽታው ምክንያት ላይሞትና የበሽታው መጠራቀሚያ ሊሆን ይችላል።

በ1975 የተገኘውንና በሽታው ለመጀመሪያ ጊዜ በታየበት በዩናይትድ ስቴትስ፣ ከነቲከት ግዛት በሚገኘው በላይም የተሰየመውን የላይም በሽታ እንመልከት። የላይም በሽታ አማጭ የሆነው ባክቴሪያ ወደ ሰሜን አሜሪካ የገባው ከአውሮፓ በሚመጡ መርከቦች ላይ በተጫኑ አይጦች ወይም ከብቶች አማካኝነት ከመቶ ዓመታት በፊት እንደሆነ ይገመታል። ኢክሶደስ የተባለችው የአጋዘን መዥገር በበሽታው የተለከፈ እንስሳ ደም ከመጠጠች በኋላ ባክቴሪያው በመዥገሯ ሆድ ዕቃ ውስጥ እስክትሞት ድረስ ይኖራል። መዥገሯ ሌላ እንስሳ ወይም ሰው በምትነክስበት ጊዜ ባክቴሪያውን ወደተነከሰው ሰው ወይም እንስሳ ታስተላልፋለች።

የላይም በሽታ በሰሜናዊ ምሥራቅ ዩናይትድ ስቴትስ የተለመደ ሲሆን ለበርካታ ዓመታት በዚያ አካባቢ ተገድቦ ኖሯል። የላይም በሽታ አማጭ የሆነው ባክቴሪያ በዋነኝነት የሚኖረው በባለ ነጭ እግር አይጥ ውስጥ ነው። በተጨማሪም ይህ አይጥ የመዥገሮች በተለይም ገና በማደግ ላይ ያሉ መዥገሮች ማደሪያ ነው። እድገታቸውን የጨረሱ መዥገሮች መኖር የሚመርጡት በአጋዘኖች ላይ ሲሆን እነሱኑ እየተመገቡ ይራባሉ። ለአካለ መጠን የደረሰችው እንስት መዥገር በቂ ደም ከመጠጠች በኋላ መሬት ላይ ትወድቅና እንቁላሎቿን ትጥላለች። ከእንቁላሎቹ እጮች ይቀፈቀፉና አዲስ የመዥገሮች ሕይወት ኡደት ይጀምራል።

የሁኔታዎች መለወጥ

በሽታ አማጭ ባክቴሪያዎች በሰው ልጅ ላይ ምንም ዓይነት የጤና ችግር ሳያደርሱ ለበርካታ ዓመታት ከእንስሳትና ከነፍሳት ጋር ኖረዋል። ይሁን እንጂ የሁኔታዎች መለዋወጥ በተወሰነ አካባቢ ብቻ ተወስኖ የኖረው በሽታ በርካታ ሰዎችን የሚያዳርስ ወረርሽኝ እንዲሆን ያደርጋል። በላይም በሽታ ረገድ የተለወጠው ሁኔታ ምንድን ነው?

በቀደሙት ዓመታት አጋዘኖችን የሚበሉ አዳኝ አራዊት መኖራቸው የአጋዘኖችን ብዛት ውስን ስላደረገው የአጋዘን መዥገሮች ሰው ላይ ሊያርፉ የሚችሉበትን አጋጣሚ ቀንሰውት ነበር። የመጀመሪያዎቹ አውሮፓውያን ሰፋሪዎች ጫካዎችን መንጥረው እርሻ ማስፋፋት ሲጀምሩ የአጋዘኖች ቁጥር ይበልጥ ከመቀነሱም በላይ እነርሱን የሚያድኑት አራዊትም ከአካባቢው ሸሹ። በ1800ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ላይ ግን እርሻዎች በስተ ምዕራብ ወዳሉ አካባቢዎች በመዛወራቸው ጫካዎች መስፋፋት ጀመሩ። አጋዘኖቹ ዳግመኛ መብዛት ሲጀምሩ ያድኗቸው የነበሩት አራዊት ግን እንደጠፉ ቀሩ። በዚህ ምክንያት አጋዘኖች ከመጠን በላይ ሲበዙ መዥገሮቹም አብረዋቸው ተራቡ።

ከጊዜ በኋላ የላይም በሽታ አማጭ የሆነው ባክቴሪያ ብቅ አለና ለበርካታ ዓመታት በሰዎች ላይ ምንም ዓይነት ሥጋት ሳያደርስ በእንስሳቱ ላይ መኖሩን ቀጠለ። ጫካዎቹን የሚዋሰኑ መንደሮች መመሥረት ሲጀምሩ ግን ወደ መዥገሮቹ ክልል ዘልቀው የሚገቡ ሕፃናትና ትላልቅ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ ጨመረ። ይህም መዥገሮቹ በሰዎች ላይ እንዲጣበቁና ሰዎች በላይም በሽታ እንዲያዙ አደረገ።

የዓለም ሁኔታ መለዋወጥ በሽታዎች እንዲስፋፉ አድርጓል

ከላይ የተመለከትነው ሁኔታ የሚያሳየው በሽታ ከሚዛመትባቸው መንገዶችና በሽታዎቹን በማዛመት ረገድ ሰዎች ከሚጫወቱት ሚና መካከል አንዱን ብቻ ነው። ዩጂን ሊንደን የተባሉት የአካባቢ ጥናት ሊቅ ዘ ፊውቸር ኢን ፕሌይን ሳይት በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “አዲስ ያገረሹት በሽታዎች በሙሉ ማለት ይቻላል፣ እንደገና ሊያገረሹ የቻሉት በሰዎች ጣልቃ ገብነት ነው” ብለዋል። ሌሎች ጥቂት ምሳሌዎች እንውሰድ:- የዘመናዊ መጓጓዣዎች ቅልጥፍናና ተወዳጅነት እየጨመረ መሄዱ የበሽታ ተውሳኮችና ተሸካሚዎቻቸው በመላው ዓለም በቀላሉ እንዲሠራጩ ያስችላል። በትላልቅም ሆነ በትናንሽ እንስሳት መኖሪያ አካባቢዎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት ሕይወት ባላቸው በተለያዩ ፍጥረታት ላይ ቀውስ ያስከትላል። “በውኃና በአየር ላይ የሚደርሰው ብክለት የእንስሳትንም ሆነ የሰው ልጆችን በሽታ የመከላከል አቅም ያዳክማል” ይላሉ ሊንደን። በማከልም ዶክተር ኤፕስታይን የደረሱበትን ድምዳሜ በመጥቀስ ‘የሰው ልጅ በተፈጥሮ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የዓለማችንን በሽታ የመከላከል ችሎታ በማዳከም ለረቂቅ ተህዋሲያን አመቺ ሁኔታ ፈጥሯል’ ብለዋል።

የፖለቲካ አለመረጋጋት ጦርነት ያስከትላል። ጦርነት ደግሞ በሥነ ምሕዳር ላይ ጉዳት ከማድረሱም በላይ የጤና እንክብካቤና የምግብ ሥርጭት ይሰጡ የነበሩ ተቋማትን ያወድማል። ከዚህም በተጨማሪ “በቂ ምግብ በማጣት የተጎዱና የተዳከሙ ስደተኞች አብዛኛውን ጊዜ ሰዎችን ለተለያዩ በሽታዎች በሚያጋልጡ ንጽሕናቸው ያልተጠበቀና የተጣበቡ ካምፖች ውስጥ እንዲኖሩ ይደረጋል” በማለት ባዮቡለቲን የተባለው የአሜሪካ ሙዚየም የተፈጥሮ ታሪክ መጽሔት ይናገራል።

የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ሰዎች ከገጠር ወደ ከተማና ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር እንዲፈልሱ ያደርጋል። “የበሽታ ተውሳኮች ሕዝብ የሚበዛባቸውን አካባቢዎች ይወዳሉ” ይላል ባዮቡለቲን። የከተማ ነዋሪዎች እየበዙ ሲመጡ “ከሕዝቡ ብዛት ጋር የሚመጣጠን መሠረተ ትምህርት፣ የተመጣጠነ ምግብና የክትባት ፕሮግራም ማካሄድ ያቅታል።” በተጨማሪም የሕዝብ ብዛት በውኃ፣ በፍሳሽና በቆሻሻ ማስወገጃዎች አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር የግል ንጽሕናን መጠበቅ አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ ለነፍሳትና ለሌሎች በሽታ ተሸካሚ ፍጥረታት መራባት አመቺ ሁኔታ ይፈጠራል። ይሁን እንጂ የሚከተለው ርዕስ እንደሚያሳየው ሁኔታው ጨርሶ ተስፋ ቢስ አይደለም።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“አዲስ ያገረሹት በሽታዎች በሙሉ ማለት ይቻላል፣ እንደገና ሊያገረሹ የቻሉት በሰዎች ጣልቃ ገብነት ነው”

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የዌስት ናይል ቫይረስ ዩናይትድ ስቴትስን ወረረ

በዋነኝነት በትንኝ የሚተላለፈው ዌስት ናይል ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ ተለይቶ የታወቀው በ1937 በኡጋንዳ ነበር። በኋላም በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በእስያ፣ በኦሽንያ እና በአውሮፓ ታይቷል። ይህ ቫይረስ እስከ 1999 ድረስ በምዕራባዊው ንፍቀ ዓለም ታይቶ አያውቅም ነበር። ከዚያ ወዲህ ግን በዩናይትድ ስቴትስ ከ3, 000 የሚበልጡ ሰዎች በቫይረሱ እንደተለከፉ ሪፖርት ሲደረግ ከ200 የሚበልጡ ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።

አብዛኞቹ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ምንም ዓይነት የበሽታ ምልክት የማይታይባቸው ሲሆን አንዳንዶቹ የጉንፋን ዓይነት የሕመም ምልክት ይታይባቸዋል። ይሁን እንጂ ኢንሰፍላይትስ የሚባል የአንጎል ህመምና ኀብለሰረሰር ሜንንጃይትስን የመሰለ ከባድ በሽታ የሚመጣባቸው በጣም ጥቂቶቹ ናቸው። እስካሁን ድረስ ለዌስት ናይል ቫይረስ የመከላከያ ክትባትም ሆነ የተለየ ሕክምና አልተገኘም። የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታዎች ቁጥጥርና መከላከል መሥሪያ ቤት የዌስት ናይል ቫይረስ በቀዶ ሕክምና በሚቀየር የአካል ክፍል አማካኝነት ወይም ደም በመውሰድ ሊተላለፍ እንደሚችል ያስጠነቅቃል። የሮይተርስ ዜና አገልግሎት “በአሁኑ ጊዜ በደም ውስጥ ዌስት ናይል ቫይረስ መኖርና አለመኖሩን ለማረጋገጥ የሚያስችል ምርመራ የለም” በማለት በ2002 ዘግቧል።

[ምንጭ]

CDC/James D. Gathany

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ራስህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው? መደረግ ያለባቸውና የሌለባቸው አንዳንድ ነገሮች

ንቁ! ጤነኛ ሆኖ ለመኖር የሚያስችሉ ዘዴዎችን በተመለከተ በሽታ አስተላላፊ ነፍሳትና በሽታዎቹ በሚበዙባቸው አገሮች የሚኖሩ ሰዎችን ጠይቆ ነበር። እነዚህ ሰዎች የሰጧቸው ምክሮች በአንተም አካባቢ ጠቃሚ ሆነው ታገኛቸው ይሆናል።

ንጽሕና​—⁠ተቀዳሚ የመከላከያ እርምጃ

ቤትህ ሁልጊዜ ንጹሕ ይሁን

“የምግብ ማስቀመጫ ዕቃዎች ሁልጊዜ መከደን አለባቸው። የበሰሉ ምግቦች እስኪበሉ ድረስ ተከድነው መቆየት ይገባቸዋል። የተፈረፈረ፣ የተንጠባጠበ ወይም የተደፋ ምግብ ካለ ወዲያው ጠርገህ አጽዳ። የቆሸሹ ሣህኖች ሳይታጠቡ አታሳድር ወይም ጠዋት ለመድፋት አስበህ የተራረፉ ምግቦችን ውጭ አታሳድር። ከዚያ ይልቅ ትናንሽ ነፍሳት ወይም እንደ አይጥ ያሉ እንስሳት ምግብ ፍለጋ የሚመጡት ከመሸ በኋላ ስለሆነ ክደነው ወይም ቅበረው። በተጨማሪም ወለሉ አፈር ከሚሆን ይልቅ ስሚንቶ ቢሆን በንጽሕና ለመያዝና ትናንሽ ነፍሳትን ለማስወገድ አመቺ ይሆናል።”​—⁠አፍሪካ

“ፍራፍሬዎችን ወይም ማናቸውንም ትናንሽ ነፍሳትን ሊስቡ የሚችሉ ነገሮችን ቤት ውስጥ አታስቀምጥ። እንደ ፍየል፣ አሳማ፣ ዶሮ የመሰሉትን የቤት እንስሳት ከመኖሪያ ቤት አርቅ። ከቤት ውጭ ላሉ መጸዳጃ ቤቶች ክዳን አብጅላቸው። የከብቶች ፍግ የዝንቦች መራቢያ እንዳይሆን ወዲያው እንዲቀበር ወይም በኖራ እንዲሸፈን አድርግ። ጎረቤቶችህ እነዚህን ነገሮች የማያደርጉ ቢሆኑ እንኳ ትናንሽ ነፍሳት ከመጠን በላይ እንዳይበዙ ማድረግና ለአካባቢህም ጥሩ ምሳሌ መሆን ትችላለህ።”​—⁠ደቡብ አሜሪካ

[ሥዕል]

ምግብ ወይም ቆሻሻ ክፍት አድርጎ መተው ነፍሳት አብረውህ እንዲመገቡ የመጋበዝ ያህል ነው

የግል ንጽሕና

“ሣሙና እንደልብ የሚገኝ ነገር በመሆኑ እጅህንና ልብስህን ቶሎ ቶሎ በተለይ ደግሞ ከሰዎችና ከእንስሳት ጋር ከተነካካህ በኋላ ታጠብ። የሞቱ እንስሳት አትንካ። አፍህን፣ አፍንጫህንና ዓይንህን በእጅህ አትነካካ። ልብሶች የቆሸሹ መስለው ባይታዩ እንኳን ቶሎ ቶሎ መታጠብ አለባቸው። አንዳንድ ሽታዎች ነፍሳትን የመሳብ ጠባይ ስላላቸው ሽታ ባላቸው ሣሙናዎች አትጠቀም።”​—⁠አፍሪካ

የመከላከያ ዘዴዎች

የትንኝ መራቢያ ቦታዎች እንዳይኖሩ አድርግ

የውኃ ማጠራቀሚያ በርሜሎችንና የማጠቢያ ገንዳዎችን ክደን። ክፍት የሆኑ የውኃ ማጠራቀሚያ ቦታዎች እንዳይኖሩ አድርግ። አትክልት በተተከለባቸው ዕቃዎች ውስጥ ውኃ እንዳይቋጠር አድርግ። ትንኞች ከአራት ቀን በላይ በቆየ ማንኛውም እርጥብ ቦታ ሊራቡ ይችላሉ።​—⁠ደቡብ ምሥራቅ እስያ

በተቻለ መጠን ሰውነትህን ለትናንሽ ነፍሳት አታጋልጥ

ትናንሽ ነፍሳት ከሚመገቡባቸው ቦታዎችና ጊዜያት ራቅ። በምድር ወገብ አካባቢ በሚገኙ አገሮች ፀሐይ የምትጠልቀው ቀደም ብላ በመሆኑ ትናንሽ ነፍሳት በብዛት በሚንቀሳቀሱበት የምሽት ጊዜ የሚከናወኑ ብዙ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ይኖራሉ። ትናንሽ ነፍሳት በብዛት በሚኖሩበት ጊዜ ከቤት ውጭ መተኛትና መቀመጥ ለበሽታ ይበልጥ ያጋልጣል።​—⁠አፍሪካ

[ሥዕል]

ትንኝ ባለበት አገር ከቤት ውጭ መተኛት ትንኞች እንዲበሉህ የመጋበዝ ያህል ነው

በተለይ ጫካ ውስጥ በምትሆንበት ጊዜ በተቻለ መጠን ሙሉ ሰውነትህን የሚሸፍን ልብስ ልበስ። ነፍሳት የሚያባርሩ መድኃኒቶችን መመሪያዎቹን ተከትለህ ልብስህና ሰውነትህ ላይ አድርግ። ልጆችህ ከቤት ውጭ ቆይተው ሲገቡ መዥገር እንዳይኖርባቸው ፈትሽ። የቤት ውስጥ እንስሳት ጤናማና ከተባይ የጸዱ እንዲሆኑ አድርግ።​—⁠ሰሜን አሜሪካ

ትናንሽ ነፍሳት በሽታዎችን ከርቢ እንስሳት ወደ ሰው ሊያስተላልፉ ስለሚችሉ ከርቢ እንስሳት ጋር ያለህን ንክኪ በተቻለ መጠን ቀንስ።​—⁠ማዕከላዊ እስያ

ሁሉም የቤተሰብህ አባሎች ቢቻል ፀረ ተባይ መድኃኒት የተደረገበት የትንኝ መከላከያ አጎበር እንዲኖራቸው አድርግ። መስኮቶችህን ነፍሳት በማያስገባ ወንፊት ሸፍን። የተበሳ ቦታ እንዳይኖረው በየጊዜው ተቆጣጠር። ትናንሽ ነፍሳት ሾልከው እንዳይገቡ ከጣሪያ በታች የሚገኙ ክፍት ቦታዎችን ድፈን። እነዚህ የመከላከያ እርምጃዎች ወጪ የሚጠይቁ ቢሆኑም አንድ ልጅ ታሞ ሆስፒታል ሲወሰድ የሚያስወጣውን ወጪ ወይም የቤቱ አባወራ ታምሞ መሥራት ቢያቅተው የሚያጣውን ገቢ ያህል አይሆንም።​—⁠አፍሪካ

[ሥዕል]

ፀረ ተባይ መድኃኒት የተደረገበት የትንኝ መከላከያ አጎበር መግዛት ከመድኃኒት መግዣም ሆነ ከሆስፒታል መታከሚያ ይረክሳል

ነፍሳት ሊሸሸጉ የሚችሉባቸውን ቦታዎች በሙሉ ድፈን። ግድግዳዎችና ጣሪያዎች ላይ የሚገኙ ስንጥቆችንና ቀዳዳዎችን መርግ። የሣር ክዳን ያለው ቤት ከሆነ ጣሪያውን ነፍሳት ሊያሳልፍ በማይችል ጨርቅ አልብሰው። ነፍሳት ሊሸሸጉ የሚችሉባቸው የተዝረከረኩ ወረቀቶች፣ ጨርቆች ወይም ሌሎች ኮተቶች ወይም ግድግዳ ላይ የተንጠለጠሉ ሥዕሎችና ፎቶዎች ካሉ አስወግድ።​—⁠ደቡብ አሜሪካ

ትናንሽ ነፍሳትንና አይጦችን እንደ እንግዳ የሚቆጥሩ ሰዎች አሉ። እንግዶች አይደሉም! አጥፋቸው። መመሪያ እየተከተልክ ተባይ ማጥፊያና ማባረሪያ መድኃኒቶችን ተጠቀም። እንደ ጭራ ያሉ የዝንብ ማጥመጃና መግደያ መሣሪያዎች ተጠቀም። በፈጠራ ችሎታህ ተጠቀም። ለምሳሌ አንዲት ሴት ቀጠን ያለ የጨርቅ ከረጢት ሠርታ አሸዋ ሞላችውና ነፍሳት እንዳይገቡባት በበርዋ ሥር የሚገኘውን ክፍተት ደፈነችበት።​—⁠አፍሪካ

[ሥዕል]

ትናንሽ ነፍሳት የቤታችሁ እንግዶች መሆን የለባቸውም። አጥፏቸው!

የመከላከያ መድኃኒቶች

ተስማሚ ምግብ በመመገብ፣ በቂ እረፍት በመውሰድና ጥሩ አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ የበሽታ መከላከያ ኃይልህን አጠናክር። ውጥረት ቀንስ።​—⁠አፍሪካ

መንገደኞች:- በምትሄድበት አካባቢ ስለሚገኙ ነፍሳት ወቅታዊ የሆነ መረጃ አግኝ። ከጤና ጥበቃ መሥሪያ ቤቶችና ከመንግሥታዊ የኢንተርኔት ገጾች መረጃ ማግኘት ይቻላል። ጉዞ ከመጀመርህ በፊት ለምትሄድበት አካባቢ የሚያስፈልገውን የመከላከያ ሕክምና ውሰድ።

ሕመም ቢሰማህ

ቶሎ ብለህ የሕክምና እርዳታ ፈልግ

አብዛኞቹ በሽታዎች ቶሎ ከታወቁ በቀላሉ የሚድኑ ናቸው።

የምርመራው ውጤት የተሳሳተ እንዳይሆን ተጠንቀቅ

በነፍሳት ስለሚተላለፉና በሐሩር አካባቢዎች ስላሉ በሽታዎች በቂ እውቀት ያላቸው ሐኪሞች ፈልግ። የሚሰማህን የሕመም ስሜት በሙሉና ከብዙ ጊዜ በፊት ቢሆን እንኳ የት አካባቢ ሄደህ እንደነበረ ለሐኪምህ ንገረው። አንቲባዮቲክ መድኃኒቶችን አስፈላጊ ከሆነ ብቻ ውሰድ። የታዘዘልህን መድኃኒትም ሆነ የጀመርከውን ሕክምና አታቋርጥ።

[ሥዕል]

በነፍሳት የሚተላለፉ በሽታዎች ከሌሎች በሽታዎች ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። ለሐኪምህ ሙሉ ታሪክህን ንገረው

[ምንጭ]

Globe: Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

እንደ ትንኝ ያሉ ነፍሳት ኤች አይ ቪ ያስተላልፋሉን?

በነፍሳት ላይ ጥናት የሚያካሂዱ ሳይንቲስቶችና የሕክምና ባለሙያዎች በርካታ ዓመት የፈጀ ምርምርና ጥናት ካካሄዱ በኋላ ትንኞችና ሌሎች ነፍሳት ኤድስ አምጪውን ኤች አይ ቪ ቫይረስ እንደሚያስተላልፉ የሚያሳይ ማስረጃ ሊያገኙ አልቻሉም።

የትንኝ አፍ ደም በቀላሉ ሊያልፍበት የሚችል እንደ ሲሪንጅ ያለ ባለ አንድ ቧንቧ መስመር አይደለም። ከዚህ ይልቅ ትንኞች ደም በአንድ ቀዳዳ ሲመጡ በሌላኛው ቀዳዳ ምራቅ ይተፋሉ። በዚህ መንገድ የትንኟ ጨጓራና አንጀት ደሙን ያልምና ቫይረሱን ይገድለዋል በማለት የሞንጉ፣ ዛምቢያ ጤና አጠባበቅ ቡድን የኤች አይ ቪ ስፔሽያሊስት የሆኑት ቶማስ ዳማሶ ያስረዳሉ። ኤች አይ ቪ በነፍሳት ኩስ ውስጥ ተገኝቶ አያውቅም። በተጨማሪም ኤች አይ ቪ እንደ ወባ ተውሳክ ወደ ትንኝ የምራቅ እጢ ውስጥ አይገባም።

አንድ ሰው በኤች አይ ቪ የሚያዘው በጣም ብዙ ለሆኑ በካይ ቅንጣቶች ሲጋለጥ ነው። አንዲት ትንኝ ደም መጥጣ ሳትጨርስ ብትባረርና ሌላ ሰው ላይ ብታርፍ በአፏ ውስጥ የሚቀረው ደም በጣም ትንሽ ስለሚሆን ይህ ነው የሚባል ጉዳት አያስከትልም። ሊቃውንቱ እንደሚሉት ኤች አይ ቪ ያለበት ደም የጠገበች ትንኝ ቁስል ላይ ብትጨፈለቅ እንኳን ኤች አይ ቪ ሊተላለፍ አይችልም።

[ምንጭ]

CDC/James D. Gathany

[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የአጋዘን መዥገር (በስተቀኝ ጎልቶ የሚታየው) የላይም በሽታን ወደ ሰዎች ያስተላልፋል

ከግራ ወደ ቀኝ:- እድገታቸውን የጨረሱ እንስትና ተባዕት መዥገሮች እንዲሁም እጭ። ሁሉም የሚታዩት በትክክለኛ መጠናቸው ነው

[ምንጭ]

መዥገሮች:- CDC

[በገጽ 10 እና 11 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ጎርፍ፣ የንጽሕና መጓደልና የሰዎች ፍልሰት በነፍሳት ለሚተላለፉ በሽታዎች መስፋፋት እገዛ ያደርጋሉ

[ምንጭ]

FOTO UNACIONES (from U.S. Army)