በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

አስደናቂ የሆነው የአእዋፍ ሚዛናቸውን የመጠበቅ ችሎታ

አእዋፍ በሚበሩበት ጊዜ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የሚያቀናጅላቸው ሚዛን መጠበቂያ አካል በውስጠኛው የጆሯቸው ክፍል ውስጥ አላቸው። ይሁን እንጂ “የወፍ አካል እንደ ሰው አካል ቀጥ ብሎ እንዲቆም የተፈጠረ ባለመሆኑና ጅራታቸውም ቢሆን ቀና አድርጎ ለማቆም የሚያስችል ክብደት ስለሌለው” ቀና ብሎ ለመቆምና ለመሄድ የሚችሉት በዚህ በጆሯቸው ውስጥ በሚገኘው ሚዛን ጠባቂ አካል ምክንያት ሊሆን አይችልም ይላል የጀርመኑ ላይፕሲገር ፎልክሳይቱንግ። “የእንስሳት አካል አጥኚ የሆኑት ራይንሆልት ነከር ከአራት ዓመት ምርምር በኋላ በርግቦች ላይ ሁለተኛ ሚዛን መጠበቂያ አካል አግኝተዋል” በማለት ጋዜጣው ያብራራል። በወፎች ሽንጥ አካባቢ ሚዛናቸውን እንዲጠብቁ የሚያስችላቸው የነርቭ ሴሎችና ጎድጓዳ ሥፍራ አግኝተዋል። ዘገባው “በጎድጓዳው ስፍራ የሚገኘው ፈሳሽ እንዲፈስ ከተደረገና ዓይናቸው ከተሸፈነ ርግቦቹ ቀጥ ብለው መቀመጥም ሆነ መራመድ አይችሉም። ከተቀመጡበት ቦታ በጎናቸው ይፈነገላሉ። መብረር ግን አያቅታቸውም።”

“ደንባራ” ትውልድ

የኒው ዮርኩ ዴይሊ ኒውስ “የወጣት አሜሪካውያን አላዋቂነት በጣም አሳዛኝ ደረጃ ላይ ደርሷል” ይላል። “11 በመቶ የሚሆኑት በዓለም ካርታ ላይ አሜሪካ የት እንደምትገኝ ማሳየት አይችሉም። የአገሮቹ ስም ያልተጻፈበት የዩ ኤስ ካርታ ሲቀርብላቸው ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ኒው ዮርክ የት እንደሚገኝ መጠቆም አይችሉም።” አዘውትረው በዜና ዘገባዎች የሚጠቀሱ ሌሎች አገሮችን በተመለከተም፣ ለምሣሌ ኢራቅን ወይም ኢራንን ማሳየት የቻሉት 13 በመቶ ብቻ ሲሆኑ አፍጋኒስታንን መጠቆም የቻሉት ደግሞ 17 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። እንዲያውም ከ18 እስከ 24 ዓመት ከሆናቸው አሜሪካውያን መካከል ከዓለም በትልቅነቱ አንደኛ የሆነውን ፓስፊክ ውቅያኖስን ማግኘት የቻሉት 71 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። ናሽናል ጂኦግራፊ ያዘጋጀው ባለ 56 ጥያቄ ፈተና በብሪታንያ፣ በካናዳ፣ በፈረንሳይ፣ በጀርመን፣ በኢጣሊያ፣ በጃፓን፣ በሜክሲኮ፣ በስዊድንና በዩናይትድ ስቴትስ ለሚገኙ 3, 250 ወጣቶች ተሰጥቶ ነበር። በአማካይ 42 ጥያቄዎችን ትክክል በመመለስ “ኤ” ያገኘ አንድም አገር አልነበረም። ቢሆንም 40 ጥያቄዎችን በመመለስ ስዊድን ወደ “ኤ” የተጠጋ ውጤት ስታገኝ ጀርመንና ኢጣሊያ 38 በማግኘት በሁለተኛነት ተከትለዋል። አሜሪካውያን 23 ትክክለኛ መልሶችን በመመለስ 21 በመመለስ የመጨረሻውን ደረጃ የያዘችውን ሜክሲኮን ብቻ በልጠዋል። የናሽናል ጂኦግራፊ ማህበር ፕሬዚዳንት የሆኑት ጆን ፋሂ “ወጣቶቻችን አንዳንድ ቦታዎችን ካርታ ላይ ማግኘት የማይችሉና ወቅታዊ ክንውኖችን መረዳት የማይችሉ ከሆኑ ዛሬ ከፊት ለፊታችን የተደቀኑትን የዓለማችንን ባሕላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የተፈጥሮ ሀብት ጥያቄዎች እንዴት ሊገነዘቡ ይችላሉ?” ሲሉ ጠይቀዋል።

ጉልበተኛ ልጃገረዶች

“ጉልበተኛ የሆኑ ወንዶች ወደ መደባደብ የሚያዘነብሉ ሲሆን ልጃገረዶች ግን ከጉልበት ይልቅ ሥነ ልቦናዊ በሆኑና ስሜት በሚያቆስሉ ዘዴዎች ጥቃት እንደሚሰነዝሩ” ዘ ቶሮንቶ ስታር ዘግቧል። ልጃገረዶች ወደ ጉርምስና ዕድሜ ሲጠጉ በወንዶች እይታ ምን መስለው እንደሚታዩ መሥጋትን ጨምሮ ብዙ ዓይነት ፍርሃት ያድርባቸዋል። “ወንድ የሚያማልል ቁመና ይዘው ለመቅረብ የሚጥሩ የፊልም ተዋንያንን በመመልከት ልጃገረዶች ባላቸው ማራኪነት እርስ በርስ እንደሚቀናኑ” የሰዎች ባሕርይ አጥኚዎች ያምናሉ። ናሽናል አክሽን ኮሚቲ ኦን ዘ ስታተስ ኦፍ ዊመን የተባለው ድርጅት የቀድሞ ፕሬዚዳንት ደኒስ አንድርያ ካምፕቤል “ብዙ ልጃገረዶች በውስጣቸው የሚሰማቸውን የቁጣና የቅናት ስሜት እንዴት በቀጥታ እንደሚቋቋሙ አያውቁም” ብለዋል። በዚህም ምክንያት ይህ ስሜታቸው “በተዘዋዋሪና ጎጂ በሆነ መንገድ” ገንፍሎ ይወጣል። እንደ ማኩረፍ፣ መገላመጥና ሐሜት ማስፋፋት ባሉ ዘዴዎች ሌሎች ልጃገረዶችን ያሠቃያሉ።

የሥራ ውጥረት

“ከአምስት ካናዳውያን መካከል አንዱ ከሚሰማው ውጥረት ለመገላገል ሲል ራሱን ለመግደል አስቦ እንደሚያውቅ መናገሩን” ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል ዘግቧል። የዚህ ሁሉ ውጥረት ምንጭ ምንድን ነው? በ1, 002 ግለሰቦች ላይ የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው 43 በመቶ የሚሆኑት የውጥረት ምንጭ አድርገው የጠቀሱት ሥራቸውን ነው። “በዘመናዊው የሥራ ቦታ የሰዎችን አቅምና ሥነ ልቦና እስከመጨረሻ አሟጥጠን እየተጠቀምን ነው” ይላሉ የአሠሪ ድርጅቶች የሥነ ልቦና አማካሪ የሆኑት የሞንትሪያል ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ሺሞን ዶላን። “ሠራተኞች የሚፈለግባቸውን የሥራ ግዴታ መወጣት በራሱ ከባድ ሆኖ እያለ ከሥራ እባረር ይሆን የሚለው ሥጋት ተጨማሪ ውጥረት ይፈጥርባቸዋል።” ታዲያ ካናዳውያን ይህን ውጥረት የሚያረግቡት እንዴት ነው? በብዛት የተለመደው አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ሲሆን “መጽሐፍ በማንበብ፣ የሚያዝናኑ ሥራዎችን በመሥራት፣ በስፖርታዊ ጨዋታዎች በመካፈል፣ ከወዳጆቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው በመዝናናት” ውጥረታቸውን የሚያረግቡ እንዳሉ ዘ ግሎብ ዘግቧል።

ከወላጆች ጋር ማንበብ ልጆችን ጨዋ ያደርጋል

“የሚደባደቡ፣ የሚሠርቁና የሚዋሹ ረባሽ ልጆች ወላጆቻቸው ብዙ ጊዜ አብረዋቸው ሆነው መጽሐፍ ሲያነቡላቸው ጠባያቸው እንደሚሻሻል” የለንደኑ ዘ ታይምስ ዘግቧል። የሳይካትሪ ኢንስቲትዩት በአምስትና በስድስት ዓመት ዕድሜ በሚገኙ 100 የመሐል ለንደን ልጆች ላይ ባደረገው የአሥር ሣምንት ጥናት ወላጆች “ከልጆቻቸው ጋር ለማንበብ ቁጭ ከማለታቸው በፊት ሞባይል ስልካቸውን እንዲያጠፉ እንዲሁም የታሪኩን ዋና ዋና ሐሳቦች እንዲነግሯቸው፣ ከዚያም ሳይጣደፉ የመጽሐፉን ገጾች እያገላበጡ ሥዕሎቹን እንዲያሳይዋቸው ተነገራቸው።” የጥናቱ ውጤት “ከልጆች ጋር ቀላል በሆነና በታሰበበት እንቅስቃሴ መካፈል ከአነስተኛ ዕድሜ ጀምሮ የልጆችን ጠባይ እንደሚያሻሽል በግልጽ አረጋግጧል” ይላል ጋዜጣው። የጥናቱ መሪ የሆኑት ዶክተር ስቲፈን ስኮት “ልጆች በእርግጥ የሚፈልጉት የወላጆችን ትኩረት ነው። ይህን ደግሞ ከወላጆች ጋር መጽሐፍ በማንበብ ሊያገኙ ይችላሉ” ብለዋል።

ደስተኛ የሆኑ ነፃ ሠራተኞች

“ጊዜያቸውን ለነፃ አገልግሎት የሚሠዉ ሰዎች ከሌሎች ይበልጥ በሥራቸው፣ ሥራ ላይ በሚያሳልፉት ጊዜ፣ ከማህበረሰቡ ጋር ባላቸው ግንኙነትና በመንፈሣዊነታቸው እንደሚደሰቱ” ዘ ሲድኒ ሞርኒንግ ሄራልድ ዘግቧል። በአውስትራሊያ በሚገኝ አንድ የተመራማሪዎች ቡድን የተደረገ ጥናት ነፃ ሠራተኞች “ባላቸው ጤንነት፣ በሚያገኙት የዕረፍት ጊዜና የዕረፍት ጊዜያቸውን በሚያሳልፉበት ሁኔታ እርካታ እንደሚሰማቸው” ሪፖርቱ ይናገራል። የዲከን ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ቦብ ከሚንዝ በአውስትራሊያ በነፃ አገልግሎት የሚሰማራው የሰው ኃይል ብዛት በጣም ከፍተኛ እንደሆነና 32 በመቶ የሚሆኑት አውስትራሊያውያን የገንዘብ ክፍያ በማያስገኝ በአንድ ዓይነት ሥራ እንደሚካፈሉ ተናግረዋል። በተጨማሪም ሄራልድ በሣምንት 60 ሰዓት ያህል የነፃ አገልግሎት ሥራ የሚሠሩ ሰዎች “ያነሰ ሰዓት ከሚሠሩት ይበልጥ በጤንነታቸውና በሥራቸው እርካታ እንደሚሰማቸው” ዘግቧል።

ከጋብቻ ብዙ መጠበቅ

ዲ ቨልት የተባለው ጋዜጣ “በጀርመን አገር አብዛኞቹ ጋብቻዎች የሚፈርሱት ተጋቢዎች ከጋብቻቸው በጣም ብዙ ነገር ስለሚጠብቁ ነው” ሲል ዘግቧል። በቤተሰብ ኑሮ ላይ ምርምር የሚያደርጉት ፕሮፌሰር ቫሲልዮስ ፍተናኪስ “ሰዎች ከጋብቻቸው በጣም መቀራረብና ከፍተኛ ደስታ ለማግኘት ይፈልጋሉ” ብለዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ የስሜት ግለትና ፈንጠዝያ ለበርካታ ዓመታት ይቀጥላል ብሎ መጠበቅ የማይሆን ነገር ነው። ባሁኑ ጊዜ የሚታየው የራስን ደስታና እድገት የማሳደድ ዝንባሌ ባልና ሚስቶች ችግር ሲያጋጥማቸው ተቻችለው ለመኖር ፈቃደኛ እንዳይሆኑ እያደረጋቸው ነው። ሌላው የቤተሰብ ኑሮ ሊቅ ደግሞ “የወረቱ ጊዜ ካለፈ በኋላ ሰዎች ተወያይተው ትዳራቸውን ከመፍረስ ለማዳን እምብዛም ጥረት አያደርጉም” ብለዋል። ባሁኑ ጊዜ በጀርመን አገር ጋብቻዎች የሚቆዩት በአማካይ ለ12 ዓመት ያህል ነው።

ሕፃናት በቀላሉ የኒኮቲን ሱሰኞች ይሆናሉ

ዘ ጋርድያን በተባለው የለንደን ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ጥናት “ሕፃናት ማጨስ በጀመሩ ጥቂት ቀናት ውስጥ፣ እንዲያውም ካጨሷት የመጀመሪያ ሲጋራ ጀምሮ ሱሰኛ ይሆናሉ” ብሏል። “ለአንድ ጊዜ ብቻ ሲጋራ ከቀመሱ 332 ወጣቶች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት ሱሰኛ የመሆን ምልክቶች ታይተውባቸዋል። ጭሱን ከሳቡት 237 ወጣቶች መካከል 53 በመቶ የሚሆኑት የሱሰኝነት ምልክት ታይቶባቸዋል።” በዩናይትድ ስቴትስ የማሳቹሰትስ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ቤት ባልደረባ በሆኑት በጆሴፍ ዲፍራንሳ የተመራው ይህ 30 ወራት የፈጀ ጥናት በተጀመረበት ወቅት 12 እና 13 ዓመት በሆናቸው 700 በሚያክሉ ተማሪዎች ላይ ክትትል አድርጎ ነበር። “ይህ ጥናት ከመደረጉ በፊት ልጆች የትንባሆ ሱሰኛ ለመሆን ለሁለት ዓመት ያህል በየቀኑ ቢያንስ ግማሽ ፓኮ ሲጋራ ማጨስ ይኖርባቸዋል ተብሎ ይገመት ነበር” ይላሉ ዲፍራንሳ። “ከእነዚህ ልጆች መካከል አንዳንዶቹ ሱስ የያዛቸው ማጨስ በጀመሩ ጥቂት ቀናት ውስጥ ነው . . . አብዛኛውን ጊዜ የኒኮቲን ሱስ የሚይዘው ከመጀመሪያዋ ሲጋራ ጀምሮ ነው የሚል ጥርጣሬ አለኝ” ብለዋል። በተለይ ወጣቶች አንጎላቸው ገና በማደግ ላይ ስለሆነ በሱስ የመጠቃት ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ ዲፍራንሳ ያምናሉ። “በትንባሆ መጫወት አትችሉም የሚለው መልእክት ለልጆች በግልጽ እንዲደርስ እፈልጋለሁ። ትንባሆ እያጨሱ ጉዳት አይደርስብኝም ማለት ፈጽሞ አይቻልም። አንድ ሲጋራ እንኳን መሞከር የዕድሜ ልክ ሱሰኛ ሊያደርግ እንደሚችል ልጆችን ማሳመን ያስፈልገናል” ይላሉ ዲፍራንሳ።

የስኳር በሽታ በሕንድ አገር እየተስፋፋ መጥቷል

የዓለም ጤና ድርጅት በመላው ዓለም 170 ሚልዮን የሚያክሉ የስኳር ሕመምተኞች እንዳሉ ገምቷል። በስኳር ሕመምተኞች ብዛት የአንደኛነቱን ቦታ የያዘችው አገር ሕንድ ስትሆን 32 ሚልዮን የሚያክሉ ሕመምተኞች አሏት። ይህ አኃዝ እስከ 2005 ድረስ ከ57 ሚልዮን እንደሚበልጥ ዴካን ሄራልድ ጋዜጣ ዘግቧል። ለዚህ ከፍተኛ ጭማሪ ምክንያቱ የአመጋገብና የአኗኗር ስልት መለወጥ፣ ውጥረት፣ የዘር ውርሻ፣ በአነስተኛ ክብደት መወለድና የጨቅላ ሕፃናት ከልክ በላይ መመገብ እንደሆነ እስያ ውስጥ ያለውን የስኳር በሽታ በተመለከተ በስሪ ላንካ ተደርጎ በነበረ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ተካፍለው የነበሩ ሊቃውንት አስታውቀዋል። በሕንድ አገር ለስኳር ሕመም መታከሚያ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን በዓለም በጣም ዝቅተኛ ነው ከሚባለው የሚመደብ ነው። ቢሆንም ከስኳር ሕመም ጋር ተዛማጅነት ያላቸው የጤና ችግሮችና በዚሁ ሳቢያ የሚደርሰው ሞት በጣም ከፍተኛ ነው። ይህም የሆነው ከግንዛቤ እጦትና በሽታው በጊዜው ካለመታወቁ የተነሳ ነው። በዋና ዋናዎቹ የሕንድ ከተሞች የተደረገ አንድ ጥናት ለአካለ መጠን ከደረሱ ሰዎች መካከል 12 በመቶ የሚሆኑት የስኳር ሕመምተኞች ሲሆኑ 14 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የስኳር በሽታ ከመታየቱ በፊት የሚታየው ግሉኮስን በአግባቡ ለመጠቀም ያለመቻል ችግር አለባቸው።