በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከጠበቀችው በላይ አገኘች

ከጠበቀችው በላይ አገኘች

ከጠበቀችው በላይ አገኘች

በጀርመን የምትኖረው የ17 ዓመቷ ሬቤካ “ምክንያቱ ባይገባኝም የታሪክ መምህራችን የይሖዋ ምሥክሮችን እንደማይወድ አውቃለሁ” በማለት ተናግራለች። በመሆኑም መምህሩ ለክፍሉ ተማሪዎች ንግግር ለማቅረብ ፈቃደኛ የሆነ ተማሪ እንዳለ ሲጠይቅ ሬቤካ በአጋጣሚው ለመጠቀም አመነታች። ቢሆንም እንደ ምንም ራሷን አደፋፍራ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች በናዚ አገዛዝ ስለደረሰባቸው ስደት ንግግር ለማቅረብ እንዲፈቅድላት ጠየቀችው። መምህሩም ሐሳቧን በደስታ ተቀበለው።

የክፍሉ ተማሪዎች ሬቤካ ባቀረበችው ንግግር የተደሰቱ ከመሆኑም በላይ ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር የሚዛመድ ሐሳብ የያዙ 44 መጽሔቶችና ቡክሌቶችን ልታበረክትላቸው ችላለች። ከዚያም ሬቤካ የይሖዋ ምሥክር ባልሆኑ ሰዎች የተዘጋጁ በርካታ መጽሐፎችንና ቪዲዮዎችን ጨምሮ የንግግሩን አስተዋጽኦ ለመምህሯ ሰጠችው። ከቪዲዮዎቹ መካከል አንዱ የይሖዋ ምሥክሮች በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት በምሥራቅ ጀርመን የደረሰባቸውን ስደት የሚዘግብ ነበር። መምህሩ ስለዚህ ጉዳይ ምንም የሚያውቀው ነገር ስላልነበር ከሌሎቹ ይበልጥ ትኩረቱን ሳበው።

ከዚያም ሬቤካ መምህሯ የይሖዋ ምሥክሮችን የማይወደው ለምን እንደሆነ ተገነዘበች። ተማሪ እያለ አንድ የይሖዋ ምሥክር አብሮት ይማር እንደነበር ነገራት። ልጁ ስለ እምነቱም ሆነ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ሕይወት ምንም ነገር ነግሮት አያውቅም ነበር። በመሆኑም መምህሩ የይሖዋ ምሥክሮች ነገረ ሥራቸው ሁሉ የማይታወቅ ሰዎች ናቸው የሚል ድምዳሜ ላይ በመድረሱ ከእነርሱ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ላለመመሥረት ወሰነ። ይሁን እንጂ ሬቤካ ያቀረበችው ንግግር አመለካከቱን እንዲለውጥ አደረገው። ሬቤካ እንዲህ ትላለች:- “አሁን ከመምህሬ ጋር ከበፊቱ የተሻለ ግንኙነት አለኝ። በተጨማሪም እኛ ወጣቶች ስለ እምነታችን ለሌሎች በግልጽ መናገር እንዳለብን ትምህርት አግኝቻለሁ።”

ሆኖም ሬቤካ ያገኘችው ውጤት በዚህ አያበቃም። መምህሩ ሬቤካ ስላቀረበችው ግሩም ንግግር ለሥራ ባልደረቦቹ ነገራቸው። ከጥቂት ቀናት በኋላ የግብረገብ መምህሩ ንግግሩን በድጋሚ እንድታቀርብ ጠየቃት። በዚህ ወቅት ግን ንግግሩን የምታቀርበው ለአንድ ክፍል ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ትምህርት ቤቱ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ በኦሽዊትዝ ማጎሪያ ካምፕ የነበሩ እስረኞች ነፃ የወጡበትን ዓመታዊ በዓል በሚያከብርበት ዝግጅት ላይ ነበር። ወደ 360 የሚጠጉ ተማሪዎችና 10 የሚያህሉ መምህራን ንግግሩን አዳመጡ። ንግግሩ ካበቃ በኋላ የዝግጅቱ ተሳታፊዎች 50 ቡክሌቶችን የወሰዱ ሲሆን ትምህርት ቤቱም በሌላ ጊዜ የሚያሰራጨው 150 ተጨማሪ ቅጂዎች እንዲላኩለት ጠይቋል።

ሬቤካ ያገኘችው ውጤት ከጠበቀችው በላይ ነበር። ለክፍሏ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን በትምህርት ቤት ላሉት ባጠቃላይ ስለ እምነቷ ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት ችላለች። እንዲሁም መምህሯ ቀደም ሲል ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የነበረውን ጥርጣሬ እንዲያስወግድ ረድታዋለች።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሄንሪክ ፉንዲስ በናዚዎች እጅ አንገቱ ተቆርጦ ተገድሏል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ተገድለዋል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች እምነታቸውን መካዳቸውን ለመግለጽ እዚህ ሰነድ ላይ ከፈረሙ ከእስር ሊፈቱ እንደሚችሉ ተነግሯቸው ነበር

[ምንጭ]

Courtesy of United States Holocaust Memorial Museum

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንደ ቤርቶሆልት ሜቪስ ያሉ ትናንሽ ልጆች ከወላጆቻቸው ተለይተው ተወስደው ነበር

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይህ ቪዲዮ በናዚ ጀርመን ውስጥ የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች ያስመዘገቡትን ድፍረት የተሞላበት ታሪክ ይዘግባል

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮችን ለመለየት በወኅኒ ቤት ልብሳቸው ላይ ወይን ጠጅ ቀለም ያለው ባለ ሦስት ማዕዘን ጨርቅ ይሰፋ ነበር

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

JEHOVAH’S WITNESSES STAND FIRM AGAINST NAZI ASSAULT