በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የብዙ ዓመት ልምድ ካለው አብራሪ የተገኙ የአውሮፕላን ጉዞ ምክሮች

የብዙ ዓመት ልምድ ካለው አብራሪ የተገኙ የአውሮፕላን ጉዞ ምክሮች

የብዙ ዓመት ልምድ ካለው አብራሪ የተገኙ የአውሮፕላን ጉዞ ምክሮች

በአውሮፕላን መጓዝ በጣም እወዳለሁ። የአውሮፕላን ጉዞ በጣም ፈጣን ከመሆኑም በላይ ደመናማ በሆነ ቀን ደመናውን አቋርጦ ለመውጣትና ፀሐያማ በሆነ ቀንም ደማቅ የፀሐይ ብርሃን ለማየት ያስችላል። ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮፕላን የተጓዝኩት ገና ልጅ ሳለሁ በ1956 ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በአውሮፕላን መጓዝ ያስደስተኛል። በዚህም ምክንያት አውሮፕላን አብራሪነት ሞያዬ እንዲሆን መረጥኩ። የአውሮፕላን አደጋ መርማሪ ሆኜ የሠራሁበት ጊዜም አለ።

በአውሮፕላን መጓዝ ምን ያህል አስተማማኝ ነው? በአውሮፕላን የመጓዝ አጋጣሚ በሚኖርህ ጊዜ ምን ዓይነት ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብሃል?

አስተማማኝ የሆነውን መጓጓዣ ይበልጥ አስተማማኝ ማድረግ

በመላው ዓለም በሺህ የሚቆጠሩ የአውሮፕላን ማረፊያዎች በየዓመቱ 18, 000 የሚያክሉ የአውሮፕላን ጉዞዎችን እያስተናገዱ ከ1.6 ቢልዮን የሚበልጡ መንገደኞችን ያጓጉዛሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ብዙ አደጋ አይፈጠርም። እንዲያውም ሎይድ የተባለው የለንደን እውቅ የኢንሹራንስ ኩባንያ በመኪና ከመጓዝ ይልቅ በአውሮፕላን መጓዝ 25 እጥፍ አስተማማኝ እንደሆነ ገምቷል። ስለዚህ በስታትስቲክስ መረጃዎች መሠረት ይበልጥ አደገኛ የሆነው የጉዞህ ክፍል ወደ አውሮፕላን ማረፊያ ለመሄድና ከአውሮፕላን ማረፊያ ለመመለስ በመኪና የምታደርገው ጉዞ ነው። ቢሆንም ጥቂት ጥንቃቄዎችን ብታደርግ ይህ አስተማማኝ የሆነ መጓጓዣ ይበልጥ አስተማማኝ ሊሆንልህ ይችላል።

የምትጓዝበትን አየር መንገድ በጥንቃቄ ምረጥ:- በአስተማማኝነታቸው ሁሉም አየር መንገዶች እኩል አይደሉም። በአጠቃላይ ሲታይ የታወቁ አየር መንገዶች ይበልጥ አስተማማኝ ናቸው። የሚያበሯቸው አውሮፕላኖች ይበልጥ ዘመናዊ ከመሆናቸውም በላይ በአስተማማኝነታቸውና በጥገና ሥራቸው ጥሩ ስም ያተረፉ ናቸው።

የምትለብሰውን ልብስ በጥንቃቄ ምረጥ:- ከተከሰከሰ አውሮፕላን በሕይወት የተረፉ ሰዎች በቃጠሎና በጭስ የመሞት አደጋ ይገጥማቸዋል። ስለዚህ ረዥም እጅጌ ያለው ልብስና ሙሉውን እግር የሚሸፍን ሱሪ ወይም ረዥም ቀሚስ መልበስ ቆዳ በእሳት ወላፈንና በትኩሳት እንዳይጎዳ ይከላከላል። እንደ ናይለን ያሉ ከሰው ሠራሽ ጨርቆች የሚሠሩ ልብሶች ሙቀት ሲያገኛቸው ተጨማትረውና ቀልጠው ቆዳን ይበልጥ ሲያቆስሉ እንደ ጥጥና ሱፍ ያሉ ከተፈጥሮ ጭረት የተሠሩ ጨርቆች ከቃጠሎ ይከላከላሉ። የቆዳ ልብስም እሳት ሲነካው ሊኮማተር ስለሚችል ጥሩ አይደለም። አንድ ልብስ ብቻ ከመልበስ ይልቅ ደራርቦ መልበስ ይበልጥ ከቃጠሎ ይከላከላል። በተጨማሪም ጠቆር ካሉ ልብሶች ይልቅ ነጣ ያሉ ልብሶች ሙቀት አንጸባርቀው ይመልሳሉ። ሶላቸው ጠፍጣፋ የሆኑና ማሠሪያ ያላቸው ጫማዎች ከእግር ሳይወልቁ የመቆየትና እግርህን ከቃጠሎና ከመቆረጥ አደጋ የመጠበቅ ችሎታ አላቸው። የሱፍ የእግር ሹራቦች ከናይለን ከተሠሩ የእግር ሹራቦች የተሻሉ ናቸው።

አደጋ ሲያጋጥም ምን ማድረግ እንደሚገባ የሚሰጠውን ማሳሰቢያ በሚገባ አዳምጥ:- የበረራ ሠራተኞች አውሮፕላኑ ከመነሣቱ በፊት አደጋ ቢከሰት እንዴት ራስን ማዳን እንደሚቻል የሚገልጽ ማብራሪያ ይሰጣሉ። አደጋ ድንገት ቢፈጠር ራስህን ከአውሮፕላኑ እንዴት ማውጣት እንደምትችል የሚጠቅምህን ሐሳብ የምታገኘው በዚህ ወቅት ከሚሰጠው መግለጫ ነው። ስለዚህ የሚናገሩትን በጥንቃቄ አዳምጥ። በካናዳ አውሮፕላን ተጓዦች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት ከመንገደኞች መካከል ራስን እንዴት ማዳን እንደሚቻል የሚገልጸውን ካርድ ያነበቡት ወይም የተመለከቱት 29 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። ጊዜ ወስደህ እነዚህን መመሪያ የያዙ ካርዶች አንብብ። በተለይ ደግሞ ቀድመህ የምትደርሰው አንተ ልትሆን ስለምትችል የአደጋ ጊዜ መውጫውን እንዴት እንደምትከፍት የሚያሳየውን ክፍል በጥሞና ተመልከት። ጨለማ ቢሆን ወይም በጭስ ተጋርደህ አጥርተህ ማየት ቢያቅትህ የአደጋ ጊዜ መውጫውን እንዴት ልታገኝ እንደምትችል አስብ። በአንተና በአደጋ ጊዜ መውጫው መካከል ስንት ረድፍ መቀመጫ እንዳለ መቁጠር አንዱ ቀላል ዘዴ ነው። ይህን ካስታወስክ በጨለማ ውስጥ እንኳን ብትሆን የአደጋ ጊዜ መውጫውን ፈልገህ ማግኘት አያስቸግርህም።

በእጅ የሚያዝ ጓዝ አታብዛ:- “በሰላማዊ ጉዞ ወቅት እንኳን ሳይቀር በደንብ ያልተቀመጡ ወይም በመንገደኞች ተከፍተው የተተዉ ዕቃዎች ወድቀው በአናታቸው ላይ ከባድ ጉዳት የሚደርስባቸው ከዚያም አልፎ እስከ መሞት የሚደርሱ መንገደኞች ብዙ ናቸው” ይላል ፍላይት ኢንተርናሽናል የተባለው መጽሔት። ስለዚህ በእጅ የሚያዙ ከባድ ሻንጣዎች አደጋ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አስታውስ። ስለሆነም በአደጋ ጊዜ ዕቃህን ይዘህ ለመውጣት አትሞክር። ሕይወትህን ብቻ አድን ! ሕይወትህ ከተረፈ ጓዝህን መተካት ትችላለህ።

አደጋ በሚያጋጥምበት ጊዜ

በአደጋ ጊዜ እሳት፣ ወላፈንና ጢስ ካለ ከአውሮፕላን ውስጥ መውጣት በጣም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። አንድ የአደጋ ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “አውሮፕላኑ መሬት እንዳረፈ የአውሮፕላኑ ክፍሎች በጭስ ስለተሸፈኑ ከወለሉ አንድ ጫማ ያህል ከፍ ብሎ ያለን ነገር ሁሉ ማየት አይቻልም ነበር። ከጥፋቱ የተረፉት ሰዎች ወደ መውጫው በር ለመሄድ ድፍረት አጥተው እንደነበር ተናግረዋል።” በሕይወት መትረፋቸው የተመካው ከአውሮፕላኑ ፈጥነው በመውጣታቸው ላይ ነበር።

የአውሮፕላኑ ሠራተኞች አደጋ ከደረሰበት አውሮፕላን እንዴት ፈጥኖ መውጣት እንደሚቻል በቂ ሥልጠና ያገኙ ናቸው። ስለዚህ የሚሰጡትን መመሪያ በፍጥነት ተከተል። እርግጥ ነው ሁኔታዎቹ ሁልጊዜ እንደታቀደው ላይሆኑ ይችላሉ። የመነጋገሪያ መሣሪያዎች ሊበላሹ፣ ሠራተኞቹ ላይ ጉዳት ሊደርስ፣ ግራ መጋባት ወይም ጫጫታ እንዲሁም እሳትና ጭስ የሚፈጥረው ችግር የአውሮፕላኑ ሠራተኞች የሚያደርጉትን ጥረት ሊያደናቅፍ ይችላል። የመረጥከው አየር መንገድ የሚጠቀምበትን ቋንቋ የማትችል ከሆነም የአውሮፕላኑ ሠራተኞች የሚሉትን መረዳት ሊያስቸግርህ ይችላል።

የአደጋ ምርመራዎች እንደሚያሳዩት ከአደጋ መትረፍህ በአብዛኛው የሚመካው ለመትረፍ ባለህ ቁርጠኝነት ላይ ነው። ምን እንደምታደርግ በግልጽ ማወቅና ለመዳን የቻልከውን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆን ይኖርብሃል። አብረውህ የሚጓዙ ካሉ በተለይ ሕፃናትና አረጋውያን ከሆኑ እነርሱንም በእቅድህ ውስጥ ማስገባትና በምትወጡበት ጊዜ እንዳትለያዩ ጥረት ማድረግ ይገባሃል። ፍላይንግ ሴፍቲ የተባለው መጽሔት “በጭስ ውስጥ አልፋችሁ የምትወጡ ከሆነ እርስ በርሳቸው እንዲያያዙ አድርግ። ቀበቶህን እንዲይዙ ማድረግ ጥሩ ዘዴ ይሆናል” ይላል። አደጋ ቢያጋጥም ምን ልታደርግ እንዳሰብክ አብረውህ ለሚጓዙ ሰዎች ንገራቸው።

ሁሉም የመጓጓዣ ዓይነቶች የየራሳቸው አደጋ ሊኖራቸው ቢችልም ዘመናዊዎቹ የመንገደኛ አውሮፕላኖች ከብዙ አደጋዎች እንድንጠበቅና ብዙ ሳንደክምና ሳንሰላች ለሥራም ሆነ ለመዝናናት ካሰብንበት ቦታ እንድንደርስ ይረዱናል። አደጋ ቢፈጠር ምን ማድረግ እንደምትችል ሁልጊዜ ዝግጁ ሆነህ መቆየት ቢኖርብህም መጨነቅ ግን አያስፈልግህም። ዘና በልና በጉዞህ ተደሰት።​—⁠ተጽፎ የተላከልን

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአደጋ ጊዜ ከአውሮፕላን እንዴት መውጣት እንደሚቻል የሚገልጽ ሥልጠና

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአደጋ ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለብህ የሚሰጠውን መግለጫ በጥንቃቄ አዳምጥ