በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውን ሊሆን የሚችል መፍትሔ ማግኘት ይቻላል?

እውን ሊሆን የሚችል መፍትሔ ማግኘት ይቻላል?

እውን ሊሆን የሚችል መፍትሔ ማግኘት ይቻላል?

ወንጀል ምንጊዜም ከዘመናዊው ማኅበረሰብ ጋር አብሮ የሚኖር ችግር ይመስላል። የማኅበራዊ ኑሮ ሠራተኞች፣ ሕግ አስከባሪዎች፣ የወንጀለኞች ማረሚያ ቤት ሠራተኞች ምንም ያህል ጥረት ቢያደርጉ ዓለማችን እያደር በጣም አደገኛ እየሆነች መሄዷ አልቀረም። ታዲያ መፍትሔ ይገኝ ይሆን?

መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ትልቅ ለውጥ እንደተቃረበ ያመለክታል። ይህ ለውጥ የሚመጣው በሰብዓዊ መንግሥታት ጥረት አይደለም። ሁሉም ሰብዓዊ ገዥዎች ምንም ያህል ክቡር ዓላማና ግብ ቢኖራቸው አቅማቸው ውስን ነው። የወንጀልን ምክንያቶች ከሥራቸው ለመንቀልም ሆነ ዘላቂነት ያለው አስተማማኝ ሥርዓት ለማቋቋም አቅምና ችሎታ የላቸውም።

መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገርለትን ለውጥ የሚያመጣውና ሥራ ላይ የሚያውለው ፈጣሪያችን ነው። እርሱ የአጽናፈ ዓለሙ ፈጣሪ በመሆኑ የሰው ልጆች ሊያደርጉ የማይችሉትን ለመፈጸም የሚያስችል አቅምም ሆነ ሕጋዊ ሥልጣን አለው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፈጣሪ ሲናገር “አለቆችንም እንዳልነበሩ፣ የምድርንም ፈራጆች እንደ ከንቱ ነገር የሚያደርጋቸው እርሱ ነው።” በኃይልም ‘የበረታ’ ነው። (ኢሳይያስ 40:23-26) ታዲያ አምላክ ቃል የገባልን እንዴት ያሉ ለውጦች እንደሚኖሩ ነው? እነዚህስ ለውጦች የተሻለ ዓለም ይመጣል ብለን ተስፋ እንድንጥል የሚያደርጉን እንዴት ነው?

መዝሙር 37:10 አምላክ የሰጠውን ተስፋ ሲናገር “ገና ጥቂት፣ ኃጢአተኛም አይኖርም፤ ትፈልገዋለህ ቦታውንም አታገኝም” ይላል። አምላክ አንገታቸውን ያደነደኑና ለመለወጥ ፈቃደኛ ያልሆኑ ክፉ አድራጊዎችን ጨርሶ ለማስወገድ አቅዷል። ይሁን እንጂ ሁሉንም ሰዎች አያጠፋም። የዋህ፣ ትሁትና ሰላማዊ ለመሆን ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች መዝሙራዊው “እግዚአብሔርን ደጅ ጥና፣ መንገዱንም ጠብቅ፣ ምድርንም ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፤ ኃጢአተኞችም ሲጠፉ ታያለህ” ብሏል። ክፉዎች ከተወገዱ በኋላ በሕይወት የሚቀሩት ሰዎች ከማንኛውም ወንጀል በጸዳ ዓለም ውስጥ ‘በብዙ ሰላም ደስ ይላቸዋል።’—መዝሙር 37:11, 34

የአእምሮና የልብ ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋል

ክፉዎችን ከጥሩ ሰዎች ለይቶ ማጥፋቱ ብቻውን የወንጀልን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አያስወግድም። አብዛኛውን ጊዜ ወንጀል የሚመነጨው በተሳሳተ መንገድ ከሠለጠነ ልብና አእምሮ ነው። የአምላክ መንግሥት ከሌሎች መንግሥታት ብልጫ የሚኖረው በዚህ ረገድ ነው። ሰዎች ጽድቅን የሚወድዱ እንዲሆኑ ለማሠልጠን ተግባራዊ የሆነ ትምህርትና መመሪያ ይሰጣቸዋል። ኢሳይያስ 54:13 “ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፣ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል” ይላል።

በዚህ መንገድ የሚገኘው ውጤት በእርግጥም የሚያረካ ይሆናል! መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ወቅት የአራዊት ዓይነት ጠባይ የነበራቸው ሰዎች ምን ዓይነት ለውጥ እንደሚያደርጉ ሥዕላዊ በሆነ መንገድ ይገልጻል። እንዲህ ይላል:- “ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር ይቀመጣል፣ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፤ ጥጃና የአንበሳ ደቦል ፍሪዳም በአንድነት ያርፋሉ፤ ታናሽም ልጅ ይመራቸዋል።” ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? “ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለች።” (ኢሳይያስ 11:6, 9) ይሁን እንጂ አንተም ሆንክ ቤተሰብህ ይህን የመሰለውን ለውጥ ለማየት የወደፊቱን ጊዜ መጠበቅ አያስፈልግህም። እንዴት?

አሁንም ቢሆን ጥቅም ማግኘት ትችላለህ

በአሁኑ ጊዜ ከወንጀል በጸዳ ዓለም ውስጥ ለመኖር የሚያስፈልገውን ለውጥ በማድረግ ላይ የሚገኙ ሰዎች አሉ። አሁንም እንኳን አምላክ በአዲሱ ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ የሚፈልጋቸው ሰዎች ሊኖራቸው የሚገባውን አዲስ ስብዕና በመልበስ ላይ ናቸው። (2 ጴጥሮስ 3:13) ይህንንም የሚያደርጉት በሕይወታቸው ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ በማዋል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን የሚከተለውን መግለጫ ልብ በል:- “በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፣ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።”—ኤፌሶን 4:23, 24

ቆላስይስ 3:12-14 ብዙ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በአሁኑ ጊዜ በመኮትኮት ላይ ስለሚገኙት መልካም ባሕርያት ተጨማሪ መግለጫ ይሰጣል። እንዲህ ይላል:- “እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፣ ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፣ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፤ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት።”

አዲሱን ክርስቲያናዊ ባሕርይ ለመልበስ የሚያስችል እርዳታ ማግኘት ትፈልጋለህ? በመላው ዓለም የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በይሖዋ ምሥክሮች እርዳታ ይህን ባሕርይ በመልበስ ላይ ናቸው። በጣም ከባድ ወንጀለኞች የነበሩ ሰዎች እንኳ ሳይቀሩ የይሖዋ ምሥክሮች በየሳምንቱ በሚያደርጓቸው መደበኛ ስብሰባዎችና በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ እንዴት ሰላማውያን መሆን እንደሚችሉ እየተማሩ ነው። * እንዲህ ካለው ግሩም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ፕሮግራም ጥቅም ማግኘት ከፈለግህ ይህን መጽሔት ከሚያዘጋጁት ሰዎች ጋር ለመገናኘት ወደኋላ አትበል። ወደፊት ከወንጀል በጸዳ የአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር በአሁኑ ጊዜ በመዘጋጀት ላይ ከሚገኙት ሰዎች አንዱ እንድትሆን በደስታ ይረዱሃል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.12 ግንቦት 2001 ንቁ! ገጽ 8-10 ላይ የሚገኘውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከወንጀል በጸዳ ዓለም ውስጥ ለመኖር የሚያስችላቸውን ትምህርት እየቀሰሙ ነው