በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወንጀል እየተባባሰ የመጣው ለምንድን ነው?

ወንጀል እየተባባሰ የመጣው ለምንድን ነው?

ወንጀል እየተባባሰ የመጣው ለምንድን ነው?

ፍራንክ እና ጋብርዬላ ማለዳ ላይ የምትወጣውን ጀምበር እየተመለከቱ በዩናይትድ ስቴትስ ኦሪገን በሚገኝ አንድ የባሕር ዳርቻ ላይ እየተንሸራሸሩ ነበር። አደጋ ይደርስብናል ብለው ቅንጣት ታክል እንኳን አላሰቡም። በጥቂት ደቂቃ ውስጥ ሁለቱም ከቅርብ ርቀት በተተኮሰባቸው ጥይት ጭንቅላታቸው ላይ ተመትተው ሞቱ። የተገደሉበት ምክንያት በቀል ነው? ወይስ ምቀኝነት? ሁለቱም አይደለም። ተኳሹ ሰው ፈጽሞ የማያውቃቸው ሲሆን ይህን ያደረገው መግደል ምን ስሜት እንደሚያሳድር ለማወቅ ስለፈለገ ብቻ ነበር።

“ማርቲን ብራያንት እሁድ ዕለት ሚያዝያ 28 ቀን 1996 የምዕራቡን ዓለም ሙሉ ትኩረት በመሳብ የዕድሜ ልክ ምኞቱን እውን አደረገ። በታስማንያ፣ ፖርት አርተር ከተማ እየተዘዋወረ ባገኘው ሁሉ ላይ በመተኮስ ጉልበተኝነቱን ሲያሳይና ሲፈነጥዝ ዋለ።” (በፊሊፕ አትኪንሰን የተዘጋጀው ኤ ስተዲ ኦፍ አወር ዲክላይን) እግረ መንገዱን ለ35 ሰዎች ሞት ምክንያት ሆነ!

በካናዳ የሚኖሩ አንድ የ65 ዓመት አረጋዊ በብስክሌት ለመንሸራሸር ማለዳ ላይ ወጣ አሉ። መንገዱን እንደ ጀመሩ ከበስተኋላቸው የመጣ አሽከርካሪ ገጫቸውና ጥሏቸው ሄደ። መኪናው ብስክሌቱን 700 ሜትር ያህል ርቀት እየጎተተ ወሰደው። መጀመሪያ ላይ ሁሉም ሰው ድንገተኛ አደጋ እንደደረሰና ገጪውም እንዳይያዝ ያመለጠ መስሏቸው ነበር። ተጨማሪ ምርመራ ሲደረግ ግን መኪና ሰርቆ እንደ ልቡ በሚጋልብ ሰው እንደተገጩ ታወቀ። ብስክሌተኛውን መግጨት “የደስታው” አንዱ ክፍል ነበር።

በዓይነቱ ልዩ የሆነ ወንጀል?

ወንጀል ለበርካታ መቶ ዓመታት አብሮን የኖረ ቢሆንም ከላይ ያየናቸው የወንጀል ዓይነቶች ግን ብዙዎች “ሰው ይህን ያደርጋል? እንዲህ ያለውን ነገር እንዴት ማሰብ እንኳን ይቻላል?” ብለው እንዲጠይቁ አድርጓቸዋል። እንደ ስርቆትና ማጭበርበር የመሰሉ ተራ ወንጀሎች የብዙ ሰዎችን ትኩረት የማይስቡ ቢሆኑም የመገናኛ ብዙሐንን ትኩረት የሚስቡና ብዙ ሰዎች ‘ምን ዓይነት እብደት ነው! ዓለም ምን እየሆነች ነው?’ እንዲሉ የሚያደርጉ በርካታ ድርጊቶች ይፈጸማሉ።

እነዚህ ወንጀሎች በዓይነታቸው ልዩ ናቸው። በባሕርያቸውም አሰቃቂና አስደንጋጭ ናቸው። ከላይ እንደተመለከትናቸው ምሳሌዎችም አብዛኛውን ጊዜ ወንጀሎቹ የሚፈጸሙት ንጹሐኑ ሰዎች ፈጽሞ በማያውቋቸው ግለሰቦች ነው። በተጨማሪም እንደነዚህ ያሉትን ወንጀሎች የሚፈጽሙት ሰዎች እንዲህ እንዲያደርጉ የሚያነሳሳቸውን ዓላማ ወይም ግብ ይህ ነው ብሎ መናገርም አይቻልም። አለአንዳች ዓላማና ግብ የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶችን ዘርዝረን መጨረስ አንችልም።

በሚያዝያ ወር 1999 በኮሎራዶ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ሁለት ተማሪዎች 12 ተማሪዎችንና አንድ መምህር ተኩሰው ከገደሉ በኋላ የራሳቸውን ሕይወት አጥፍተዋል። በ1982 በካሊፎርንያ የሚገኝ አንድ ሰው በገዛው መድኃኒት ላይ ሌላ ሰው ስትሪክኒን የተባለ መርዝ ጨምሮበት ለሞት ዳርጎታል። በ1993 በእንግሊዝ አገር፣ በቡትል ሜርሲሳይድ ሁለት የአሥር ዓመት ልጆች እናቱ ሥጋ ለመግዛት ዞር ስትል ጀምስ በልገር የሚባል የሁለት ዓመት ልጅዋን ከነበረበት የገበያ አዳራሽ አባብለው አወጡት። ከዚያም ወደ አንድ የባቡር ሐዲድ ወስደው ቀጥቅጠው ገደሉት።

በ1995 በቶኪዮ ከምድር በታች ባለ መጓጓዣ እንደተፈጸመው ግድያ ያሉት አንዳንድ ድርጊቶች ከአሸባሪነት ሊፈረጁ የሚችሉ ናቸው። አንድ የመናፍቃን ቡድን የመርዝ ጋዝ አፈንድቶ 12 ሰዎች በመሞታቸውና በሺህ የሚቆጠሩ በመጎዳታቸው መላው የጃፓን ሕዝብ በድንጋጤ ተውጦ ነበር። ለ3,000 ሰዎች መሞት ምክንያት የሆነውን በኒው ዮርኩ የዓለም ንግድ ማዕከልና በዋሽንግተን ዲ ሲ በፔንታጎን ላይ የደረሰውን እንዲሁም አምና በባሊ ኢንዶኔዥያ 200 ሰዎችን ለሕልፈተ ሕይወት የዳረገውን ፍንዳታ መርሳት አይቻልም።

እንደነዚህ ያሉት ወንጀሎች በጣም እየተስፋፉ እንደመጡ ግልጽ ነው። ችግሩ መላውን ዓለም የዳሰሰ፣ ብዙ ብሔራትንና ሕዝቦችን የጎዳ ነው።

በአንድ በኩል ሲታይ ወንጀለኞቹ የበለጠ አስደንጋጭ ወንጀል የሚሠራው ማን ነው ብለው የሚወዳደሩ ይመስላሉ። ከዚህም በላይ በጥላቻ ምክንያት የሚፈጸሙ ወንጀሎች በጣም እየተስፋፉ መጥተዋል። እንደነዚህ ያሉ ጭካኔ የተሞላባቸው ወንጀሎች የሚፈጸምባቸው ሰዎች “በደላቸው” ምንድን ነው? የሌላ ዘር፣ ሃይማኖት ወይም ጎሣ አባል መሆናቸው ነው። በ1994 በሩዋንዳ 800,000 በሚያክሉ ቱትሲዎች ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ይህን የመሰለ ነበር።

በዚህም የተነሳ ብዙ ሰዎች ‘ይህ ሁሉ የሚሆነው ለምንድን ነው? ድሮም ሁኔታው እንዲሁ ነበርን? እንደነዚህ ካሉት አሰቃቂ ወንጀሎች በስተጀርባ ያለው ምን ሊሆን ይችላል? እንደነዚህ ያሉት አስከፊ ወንጀሎች ይቀንሳሉ ወይም ይወገዳሉ ብሎ ለማመን የሚያስችል ተስፋ ይኖራልን?’ ብለው ይጠይቃሉ። የሚከተሉት ርዕሶች ለእነዚህና ለሌሎች ጥያቄዎች መልስ ይሰጣሉ።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ወንጀሎች አብዛኛውን ጊዜ የሚፈጸሙት በአጋጣሚ በተገኙ ሰዎች ላይ እንዲሁም አለምንም ግልጽ ምክንያትና ዓላማ ነው