በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወንጀል ይህን ያህል የተስፋፋው ለምንድን ነው?

ወንጀል ይህን ያህል የተስፋፋው ለምንድን ነው?

ወንጀል ይህን ያህል የተስፋፋው ለምንድን ነው?

ማንኛውም ወንጀል ቢሆን ርኩስ ድርጊት ነው። አላንዳች ዓላማ ወይም ግብ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ደግሞ እንዲህ ናቸው ብሎ መግለጽም ያዳግታል። አላንዳች ግልጽ ዓላማና ምክንያት የሚፈጸሙ በመሆናቸው ወንጀል መርማሪዎችን ግራ አጋብቷቸዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመገናኛ ብዙኃን ይበልጥ እየተቀላጠፉ በመምጣታቸው እንደነዚህ ያሉት አስደንጋጭ ወንጀሎች በተፈጸሙ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ በሚሊዮን ከዚያም አልፎ በቢሊዮን ወደሚቆጠሩ ሰዎች ጆሮ ይደርሳሉ። የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው ዘገባ “ወንጀል ያልዳሰሰው አንድም አህጉር፣ አገር ወይም ማኅበረሰብ አይገኝም” ብሏል።

በቀደሙት ዓመታት ብዙ ወንጀል አይሰማባቸውም ይባሉ የነበሩ አካባቢዎች እንኳን በቅርቡ ብዙ የእብደት ወንጀሎች የሚፈጸሙባቸው ቦታዎች ሆነዋል። ለምሳሌ ያህል ጃፓን እምብዛም ወንጀል ከማይፈጸምባቸው አገሮች መካከል አንዷ ነበረች። ይሁን እንጂ በሰኔ ወር 2001 በኢከዳ ከተማ አንድ የሥጋ መቁረጫ ቢላ የያዘ ሰው ወደ አንድ ትምህርት ቤት ዘው ብሎ ከገባ በኋላ ያገኘውን ሁሉ መውጋትና መቆራረጥ ጀመረ። በ15 ደቂቃ ውስጥ 8 ሕፃናት ገድሎ ሌሎች 15 አቆሰለ። ይህን የመሰለ ወንጀልና ወጣቶች የማያውቁትን ሰው ለቀልድ ሲሉ ብቻ እንደሚገድሉ ሲሰማ በጃፓን አገር ያለው ሁኔታ እንደተለወጠ በግልጽ ያሳያል።

ወንጀል በከፍተኛ መጠን በሚፈጸምባቸው አገሮች እንኳን ለብዙ ሰዎች የሚዘገንኑ የእብደት ድርጊቶች ተፈጽመዋል። መስከረም 11, 2001 በኒው ዮርክ በሚገኘው የዓለም ንግድ ማዕከል ላይ የተፈጸመው አደጋ ይህን የሚመስል ነበር። ጀራርድ በልስ የተባሉት የሥነ አእምሮ ሊቅ “ይህ ጥቃት ዓለማችንን ነገ ምን እንደሚሆን ልናውቅ የማንችልባት አደገኛና እንግዳ ቦታ አድርጓታል” ብለዋል።

እንዲህ የሚያደርጉት ለምንድን ነው?

ለሁሉም የእብደት ወንጀሎች ምክንያቱ ይህ ነው ብሎ የተለየ ምክንያት መጥቀስ አይቻልም። አንዳንድ ወንጀሎችን ለመረዳት አስቸጋሪ የሚያደርጋቸው ያለ ምንም ምክንያት የሚፈጸሙ መሆናቸው ነው። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው ጨርሶ ወደማያውቀው ሰው ቀርቦ በጩቤ የሚወጋበትን ወይም ወደ አንድ ቤት ተጠግቶ በዚያ የሚያገኘውን ሰው ተኩሶ የሚገድልበትን ምክንያት ለመረዳት በጣም ይከብዳል።

ጠበኝነት የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባሕርይ ነው የሚሉ አሉ። የእብደት ወንጀል ልናመልጠው የማንችል የሰው ልጅ ተፈጥሮ አንድ ክፍል ሊሆን አይችልም ብለው የሚከራከሩም አሉ።—“ጭካኔ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባሕርይ ነውን?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

ብዙ ሊቃውንት ሰዎች ዘግናኝ የሆኑ ወንጀሎችን እንዲፈጽሙ የሚያነሳሷቸው በርካታ ምክንያቶችና ሁኔታዎች እንዳሉ ያምናሉ። በዩናይትድ ስቴትስ የኤፍ ቢ አይ (የፌዴራል ምርመራ ቢሮ) አካዳሚ ያወጣው ሪፖርት “ነፍስ ግድያ ጤናማ አእምሮ ያለው ግለሰብ የሚፈጽመው ወንጀል አይደለም” እስከ ማለት ደርሷል። አንዳንድ ባለ ሥልጣናት በዚህ አባባል እንደማይስማሙ ቢናገሩም ብዙዎቹ አባባሉ ከሚኖረው አንድምታ ጋር ይስማማሉ። ያለ ምክንያት ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎች አስተሳሰብ ጤናማ አይደለም። አስተሳሰባቸው በአንድ ነገር በመዛባቱ ለማሰብ እንኳን የሚከብድ ድርጊት ይፈጽማሉ። ሰዎች እንደነዚህ ያሉትን ድርጊቶች እንዲፈጽሙ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? ሊቃውንቱ ከሚጠቅሷቸው በርካታ ምክንያቶች መካከል የተወሰኑትን እንመልከት።

የቤተሰብ መፈራረስ

የፊሊፒንስ ብሔራዊ የምርመራ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ የሆኑት ማሪያኒቶ ፓንጋኒባን ከባድ ወንጀሎችን የሚፈጽሙ ሰዎች ምን ዓይነት አስተዳደግ እንዳላቸው የንቁ! ፀሐፊ ጠይቋቸው ነበር። “በፈረሰ ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ ናቸው። ፍቅርና እንክብካቤ አላገኙም። አመራር ባለማግኘታቸው ምክንያት ስለሚባዝኑ የሥነ ምግባር ጥንካሬ የላቸውም” በማለት መልሰዋል። በርካታ ተመራማሪዎች ብዙ ወንጀለኞች ጥሩ የቤተሰብ ዝምድና ያልነበራቸውና ጠበኛ በሆነ ቤት ውስጥ ያደጉ እንደሆኑ ይናገራሉ።

የዩናይትድ ስቴትስ የወንጀል ምርመራ ብሔራዊ ማዕከል በትምህርት ቤት የግድያ ወንጀል ሊፈጽሙ የሚችሉ ወጣቶች ተለይተው ሊታወቁ የሚችሉባቸውን መንገዶች ዘርዝሯል። የሚከተሉት የቤተሰብ ሁኔታዎች በዝርዝሩ ውስጥ ተካትተዋል:- ከወላጆቹ ጋር ጥሩ መግባባት ያልነበረው ልጅ፣ ወላጆቹ ችግር እንዳለው ያልተረዱለት ልጅ፣ ከወላጆቹ ጋር ተቀራርቦ ያላደገ ልጅ፣ በቂ ቁጥጥር ወይም ገደብ ያልተደረገበት ልጅ፣ በጣም ድብቅ የሆነ ልጅ፣ የሕይወቱን አንድ ክፍል ከወላጆቹ ደብቆ ሁለት ዓይነት አኗኗር ሲኖር የቆየ ልጅ።

በዛሬው ጊዜ ብዙ ልጆች በፈረሰ ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ ከወላጆቻቸው ጋር ብዙ ጊዜ ያላሳለፉ ናቸው። በሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች በቂ የሥነ ምግባርና የቤተሰብ አመራር ሳያገኙ ያድጋሉ። እንዲህ ያለው አስተዳደግ ልጆች ከሌሎች ጋር ጥሩ ዝምድናና ግንኙነት እንዳይፈጥሩ እንዲሁም በሌሎች ሰዎች ላይ ወንጀል ፈጽመው ምንም ፀፀት እንዳይሰማቸው እንደሚያደርግ አንዳንድ ሊቃውንት ያምናሉ።

ጥላቻ ያደረባቸው ቡድኖችና መናፍቃን

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አንዳንድ ጥላቻ ያደረባቸው ቡድኖች ወይም መናፍቃን ለአንዳንድ ወንጀሎች መፈጸም አስተዋጽኦ አድርገዋል። በኢንድያና፣ ዩናይትድ ስቴትስ አንድ የ19 ዓመት ጥቁር ወጣት ከገበያ አዳራሽ ወደ ቤቱ እየተመለሰ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጭንቅላቱን በጥይት ተመትቶ መንገድ ዳር ተዘረረ። የተኮሰበት በአጋጣሚ ብቻ የተመለከተው አንድ ሌላ ወጣት ነበር። ለምን ገደለው? ገዳዩ የነጮችን የበላይነት በሚያራምድ ድርጅት ውስጥ ተቀባይነት እንዲያገኝና ጥቁር በመግደል የሚገኘውን የሸረሪት ድር ንቅሳት እንዲደረግለት ስለፈለገ ነበር።

በ1995 በቶክዮ የምድር ውስጥ መጓጓዣ የደረሰው የነርቭ ጋዝ ጥቃት፣ በጆንስታውን፣ ጉያና በቡድን ራሳቸውን ያጠፉት ሰዎች፣ በስዊዘርላንድ፣ በካናዳና በፈረንሣይ የሶላር ቴምፕል ሃይማኖታዊ ቡድን 69 አባላት ላይ የደረሰው ሞት በመናፍቃን ጠንሳሽነት የተፈጸሙ ናቸው። እነዚህ ምሳሌዎች አንዳንድ ቡድኖች የሌሎችን አስተሳሰብ እንዴት ሊያጣምሙ እንደሚችሉ ያሳያሉ። ከፍተኛ የማሳመን ችሎታ ያላቸው መሪዎች ሰዎችን አንዳንድ ጥቅም ታገኛላችሁ ብለው በማባበል “ለማሰብ እንኳን የሚከብድ” ነገር እንዲፈጽሙ ያደርጓቸዋል።

መገናኛ ብዙኃንና የጭካኔ ድርጊቶች

አንዳንዶች የተለያዩ የዘመናችን መገናኛ ብዙኃን ዓመፅ ሊያነሳሱ እንደሚችሉ ይናገራሉ። በቴሌቪዥን፣ በፊልሞች፣ በቪዲዮ ጨዋታዎችና በኢንተርኔት የሚታየውን ዓመፅ አዘውትሮ መመልከት የሰዎች ሕሊና ለጭካኔ ድርጊቶች እንዲደነዝዝና ለወንጀል እንዲነሳሱ እንደሚያደርግ ይነገራል። የአሜሪካ የሥነ አእምሮ ሕክምና ማኅበር ፕሬዚደንት የሆኑት ዳንኤል ቦረንስታይን “በአሁኑ ጊዜ በመገናኛ ብዙኃን በሚታዩ የጭካኔ ድርጊቶችና አንዳንድ ሕፃናት በሚያሳዩት የዓመፀኝነት ባሕርይ መካከል የምክንያትና የውጤት ዝምድና እንዳለ የሚያመለክቱ ከ30 ዓመታት በላይ በተደረጉ ምርምሮች ላይ የተመሠረቱ ከ1,000 የሚበልጡ ጥናቶች አሉ” ብለዋል። ዶክተር ቦረንስታይን ለዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ኮሚቴ በሰጡት የምሥክርነት ቃል “በማንኛውም መልክ ለመዝናኛ ተብሎ ለሚቀርብ የዓመፅ ድርጊት በተደጋጋሚ መጋለጥ በጤና ላይ ጉልህ የሆነ አደጋ እንደሚያስከትል እርግጠኛ ሆነናል” ብለዋል።—“የዓመፅ ድርጊትን የሚያበረታቱ የኮምፒውተር ጨዋታዎች—አንድ ዶክተር የሰጡት አስተያየት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

ይህ እውነት መሆኑን የሚያሳዩ የተለያዩ ምሳሌዎች ተጠቅሰዋል። ባለፈው ርዕስ የተጠቀሱትን በባሕር ዳርቻ ጀምበር ስትወጣ ይመለከቱ የነበሩትን ባልና ሚስት የገደለው ግለሰብ ለግድያ የተነሳሳው የዓመፅ ፊልሞችን በተደጋጋሚ ከተመለከተ በኋላ እንደሆነ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ከሳሾቹ አቅርበዋል። አሥራ አምስት ሰዎች በተገደሉበት የትምህርት ቤት ተኩስ ደግሞ ሁለቱ ተኳሽ ተማሪዎች በየቀኑ ለበርካታ ሰዓታት የዓመፅ ቪዲዮ ጨዋታዎች ይጫወቱ እንደነበረ ታውቋል። በተጨማሪም ጭካኔ የሞላባቸውንና ግድያን የሚያሞግሱ ፊልሞችን በተደጋጋሚ አይተዋል።

አደንዛዥ ዕፆች

በዩናይትድ ስቴትስ አፍላ ወጣቶች የሚፈጽሙት ግድያ መጠን በስምንት ዓመት ጊዜ ውስጥ በሦስት እጥፍ አድጓል። ባለ ሥልጣናት እንደ ምክንያት አድርገው ከሚጠቅሷቸው ነገሮች አንዱ ምንድን ነው? ወንጀለኛ ቡድኖች በተለይም ክራክ ኮኬይን የተባለውን አደንዛዥ ዕፅ የሚወስዱና የሚያሰራጩ ቡድኖች ተጠቃሽ ናቸው። በሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ ከተፈጸሙት ከ500 የሚበልጡ የነፍስ ግድያ ወንጀሎች መካከል “ፖሊስ እንደገለጸው 75 በመቶ የሚሆኑት ከወንጀለኛ ቡድኖች ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው።”

የአሜሪካ የፌዴራል ምርመራ ቢሮ አካዳሚ ያወጣው ሪፖርት “በነፍስ ግድያ ተጠርጥረው ከሚያዙ ሰዎች መካከል በጣም ብዙዎቹ አደንዛዥ ዕፅ ሲወስዱ የነበሩ ወይም በዕፅ አዘዋዋሪነት ተወንጅለው የሚያውቁ ናቸው” ይላል። አንዳንድ በዕፅ አስተሳሰባቸው የተዛባባቸው ሰዎች በወሰዱት ዕፅ ተገፋፍተው የነፍስ ግድያ ወንጀል ይፈጽማሉ። ሌሎች ደግሞ ዕፅ የማዘዋወር ሥራቸው እንዳይታወቅባቸው ሲሉ ዓመፅ ይፈጽማሉ። አደንዛዥ ዕፆች ሰዎችን ዘግናኝ ድርጊት እንዲፈጽሙ እንደሚያነሳሱ ግልጽ ነው።

የአጥፊ መሣሪያዎች እንደልብ መገኘት

ባለፈው ርዕስ እንደተገለጸው አንድ ሰው ብቻውን በታስማንያ አውስትራሊያ 35 ሰዎችን ገድሏል። ሌሎች 19 ሰዎችን አቁስሏል። ሰውየው ወታደሮች የሚታጠቁት ዓይነት አውቶማቲክ ጠመንጃ ይዞ ነበር። በዚህም የተነሳ ብዙዎች ለነፍስ ግድያ ወንጀል መብዛት አንደኛው ምክንያት የመሣሪያዎች እንደ ልብ መገኘት እንደሆነ ይሰማቸዋል።

በ1995 በጃፓን አገር በጦር መሣሪያ የተፈጸሙ ነፍስ ግድያዎች 32 ብቻ እንደሆኑና አብዛኞቹም የተፈጸሙት በወንጀለኛ ቡድኖች መካከል እንደሆነ አንድ ሪፖርት ያመለክታል። በአንጻሩ ደግሞ በዩናይትድ ስቴትስ 15,000 የሚያክሉ በጦር መሣሪያዎች የተፈጸሙ ግድያዎች ነበሩ። በሁለቱ አገሮች መካከል ይህን የሚያክል ልዩነት ሊኖር የቻለው ለምንድን ነው? አንዳንዶች የጦር መሣሪያ መያዝን በጥብቅ የሚከለክለውን የጃፓን ሕግ እንደ ምክንያት አድርገው ይጠቅሳሉ።

ሰዎች የኑሮን ውጣ ውረድ ለመቋቋም አለመቻላቸው

አንዳንድ ሰዎች አንድ አሰቃቂ ወንጀል እንደተፈጸመ ሲሰሙ ‘ድርጊቱን የፈጸመው ሰው ለመሆኑ ጤነኛ ነው?’ ይላሉ። ይሁን እንጂ እንደነዚህ ያሉትን ወንጀሎች የሚፈጽሙ ሁሉ የአእምሮ ችግር ያለባቸው ናቸው ማለት አይቻልም። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ የኑሮን ውጣ ውረዶች መቋቋም የተሳናቸው ናቸው። የጠባይ ጉድለት ወደ መጥፎ ድርጊት ሊመራ እንደሚችል የሚናገሩ ሊቃውንት አሉ። ከእነዚህ ጉድለቶች አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው:- የመማርና ከሰዎች ጋር ተግባብቶ የመኖር ችግር፣ አካላዊ ወይም ወሲባዊ ጥቃት የሚያስከትለው አሉታዊ ተጽእኖ፣ ፀረ ማኅበራዊ ጠባዮች፣ እንደ ሴቶች ባሉ አንዳንድ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ ጥላቻ ማሳደር፣ ጥፋት ሲሠራ አለመጸጸት፣ ሌሎችን ጨቁኖ የመቆጣጠር ፍላጎት።

ችግሩ ምንም ይሁን ምን አንዳንዶች መላ አስተሳሰባቸው እስኪዛባ ድረስ በችግራቸው ይዋጡና እንግዳ የሆነ ድርጊት ይፈጽማሉ። አንዲት የሰዎችን ትኩረት የማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት ያደረባት ነርስ ለዚህ ምሳሌ ትሆናለች። ትናንሽ ሕፃናትን ጡንቻዎችን የሚያልፈሰፍስና በዚህም ምክንያት መተንፈስ እንዲያቅታቸው የሚያደርግ መድኃኒት ትወጋ ነበር። ከዚያ በኋላ ሕፃናቱን “ለማዳን” በምትሯሯጥበት ጊዜ በሚሰጣት ትኩረት በጣም ትደሰታለች። የሚያሳዝነው ግን ለመመለስ የቻለችው የሁሉንም ሕፃናት ትንፋሽ አልነበረም። በግድያ ወንጀል ተከስሳ ተፈረደባት።

ከላይ ልንመለከት እንደቻልነው ሰዎች ወንጀል ለመፈጸም የሚነሳሱባቸው ምክንያቶች በርካታ እንደሆኑ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ በጣም አስፈላጊ የሆነ አንድ ምክንያት ሳንጠቅስ ብናልፍ ለወንጀለኝነት መስፋፋት ምክንያት ስለሚሆኑ ነገሮች የሰጠነው ዝርዝር የተሟላ አይሆንም።

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

መጽሐፍ ቅዱስ በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸሙ ያሉትን ሁኔታዎችና ሰዎች በጣም አግባብ ያልሆነ ነገር የሚያደርጉበትን ምክንያት እንድንረዳ ያስችለናል። በዛሬው ጊዜ ተስፋፍተው የሚገኙትን ዝንባሌዎች በትክክል ይገልጻል። ለምሳሌ ያህል 2 ጢሞቴዎስ 3:3, 4 ሰዎች የተፈጥሮ “ፍቅር” የሌላቸው፣ “ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣” “በትዕቢት የተነፉ” እንደሚሆኑ ይናገራል። በሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ደግሞ ኢየሱስ “ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች” እንዳለ ተጠቅሷል።—ማቴዎስ 24:12

መጽሐፍ ቅዱስ “በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን” እንደሚመጣ ይናገራል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) አዎን፣ አሁን የምናየው ሁሉ ይህ ሥርዓት በሚጠፋበት የመጨረሻ ቀን ውስጥ እንደምንኖር የሚያሳይ ማስረጃ ነው። የሰዎች ዝንባሌና የዓለም ሁኔታ በጣም እየተበላሸ ነው። ታዲያ ፈጣን መፍትሔ ይመጣል ብለን ልንጠብቅ እንችላለን? መጽሐፍ ቅዱስ “ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች፣ እያሳቱና እየሳቱ፣ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ” ይላል።—2 ጢሞቴዎስ 3:13

ታዲያ ይህ ሲባል የሰው ልጅ እየተባባሰ በሚሄድና መውጫ በሌለው አሰቃቂ ወንጀል እንደተተበተበ ይኖራል ማለት ነውን? ይህን ጥያቄ በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ እንመረምራለን።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ጭካኔ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባሕርይ ነውን?

አንዳንዶች ወንጀል የመሥራት ወይም የመግደል ዝንባሌ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባሕርይ ነው ብለው ይከራከራሉ። የዝግመተ ለውጥ አማኞች ሰዎች ከዱር አራዊት የመጡ ስለሆኑ የእነርሱን የጠበኝነት ባሕርይ ወርሰዋል ይላሉ። በዚህ ንድፈ ሐሳብ መሠረት ልናመልጥ ከማንችለውና ማለቂያ ከሌለው የወንጀል እሽክርክሪት ውስጥ ገብተናል ማለት ነው።

ይሁን እንጂ ይህ ትክክል አለመሆኑን የሚያረጋግጡ በርካታ ማስረጃዎች አሉ። ከላይ የተጠቀሰው ንድፈ ሐሳብ በተለያዩ ባሕሎች ውስጥ የወንጀል ድርጊት በእኩል መጠን የማይፈጸመው ለምን እንደሆነ አይገልጽም። በአንዳንድ ባሕሎች ለምን ጠበኝነት እንደሚበዛና በሌሎች ማኅበረሰቦች ደግሞ ከዚያ ያነሰ እንዲያውም ግድያ ተሰምቶ የማያውቅበት ምክንያት ምን እንደሆነ አያመለክትም። የሥነ አእምሮ ተንታኝ የሆኑት ኤሪክ ፍሮም የጠበኝነት ባሕርይ የወረስነው ከዝንጀሮ መሰል አራዊት ነው የሚለው ንድፈ ሐሳብ ስህተት የሚሆንበትን ምክንያት ሲያጋልጡ አካላዊ ችግር አጋጥሟቸው ወይም ራሳቸውን ከአደጋ ለማዳን ሲሉ ጠበኛ የሚሆኑ አንዳንድ አራዊት ቢኖሩም ደስታ ለማግኘት ብሎ ሌላውን የሚገድል ፍጡር ግን የሰው ልጅ ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል።

ፕሮፌሰር ጀምስ አለን ፎክስ እና ጃክ ለቪን ዘ ዊል ቱ ኪል—ሜኪንግ ሴንስ ኦፍ ሴንስለስ መርደር በተባለው መጽሐፋቸው “አንዳንድ ግለሰቦች ከሌሎች የበለጠ የጠበኝነት ዝንባሌ ቢኖራቸውም ሁሉም ምርጫ የማድረግ ነጻነት አላቸው። የመግደል ፍላጎት በበርካታ ውስጣዊና ውጪያዊ ኃይሎች የሚገዛ ቢሆንም የግለሰቡን ምርጫና ውሣኔ የሚጠይቅ በመሆኑ ተጠያቂነትና ተወቃሽነት ማስከተሉ አይቀርም” ብለዋል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የዓመፅ ድርጊትን የሚያበረታቱ የኮምፒውተር ጨዋታዎች —አንድ ዶክተር የሰጡት አስተያየት

የአሜሪካ ሕክምና ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶክተር ሪቻርድ ኤፍ ኮርሊን በፊላደልፊያ፣ ፔንስልቬንያ አዲስ ለሚመረቁ ዶክተሮች ንግግር አድርገው ነበር። በዚህ ንግግራቸው ለዓመፅ ስለሚያደፋፍሩ የኮምፒውተር ጨዋታዎች ተናግረዋል። ከእነዚህ ጨዋታዎች አንዳንዶቹ በአካል ላይ ጉዳት ለሚያደርሱ የተወሰነ ነጥብ፣ የሰውነት ክፍሎችን ለይተው ለሚመቱ ተጨማሪ ነጥብ፣ ግንባር ላይ መትቶ ለሚገድል ደግሞ ከፍተኛ ነጥብ ይሰጣሉ። ደም እንደ ጎርፍ ይፈስሳል፣ አንጎል ተፈጥርቆ የትም ይበተናል።

ዶክተር ኮርሊን ልጆች አለ ዕድሜያቸው መኪና እንዳይነዱ፣ የአልኮል መጠጥ እንዳይጠጡና እንዳያጨሱ እንደሚከለከሉ ከተናገሩ በኋላ “ይሁን እንጂ ገና ስሜታቸውን እንኳን ለመቆጣጠር በማይችሉበትና የሚጫወቱባቸውን መሣሪያዎች በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችላቸውን ብስለትና ዲሲፕሊን ባላገኙበት ዕድሜ ላይ ተኩስ እናስተምራቸዋለን። . . . ማንኛውም የኃይል ድርጊት ምን ጊዜም ከባድ ጉዳት ማስከተሉ እንደማይቀር ለልጆቻችን ገና ከመጀመሪያው ማስተማር ያስፈልገናል” ብለዋል።

የሚያሳዝነው ግን ልጆች ወንጀል ጉዳት እንደሚያስከትል ከመማር ይልቅ ራሳቸው የወንጀል ተጠቂዎች መሆናቸው ነው። በዩናይትድ ስቴትስ በቀን ውስጥ አሥር ልጆች በጥይት እንደሚገደሉ አኃዛዊ መረጃዎች ያሳያሉ። ዶክተር ኮርሊን “ዩናይትድ ስቴትስ በጥይት በሚሞቱ ሕፃናት ብዛት ከመላው ዓለም የመሪነቱን ቦታ ይዛለች” ብለዋል። ታዲያ ምን መደምደሚያ ላይ ደረሱ? “በጦር መሣሪያ የሚፈጸም ወንጀል የአገራችንን ሕዝብ ደህንነት አደጋ ላይ ጥሏል። ይህ ልንክደው የማንችል ሐቅ ነው” በማለት ተናግረዋል።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለወንጀል አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ምክንያቶች

የሚከተሉት አለምክንያት ለሚፈጸሙ ወንጀሎች አስተዋጽኦ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ብዙ ሊቃውንት ያምናሉ:-

የቤተሰብ መፈራረስ

በጥላቻ የተነሳሱ አክራሪ ቡድኖች እና ጽንፈኞች

አደገኛ መናፍቃን

የዓመፅ መዝናኛዎች

ለጭካኔ ድርጊት መጋለጥ

አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ

ችግሮችን ለመቋቋም አለመቻል

የአጥፊ መሣሪያዎች እንደ ልብ መገኘት

አንዳንድ የአእምሮ በሽታዎች

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቢያንስ 12 ሰዎችን ገድሎ ሌሎች ከ80 በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ካቆሰሉት አምስት የቦንብ ፍንዳታዎች አንዱ። ክዌዘን ሲቲ፣ ፊሊፒንስ

[ምንጭ]

AP Photo/Aaron Favila ታኅሣሥ 30, 2000

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሁለት ተማሪዎች በኮሎራዶ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ኮለምባይን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ አንድ መምህር፣ 12 ተማሪዎችንና ራሳቸውን ገደሉ

[ምንጭ]

AP Photo/Jefferson County Sheriff’s Department ሚያዝያ 20, 1999

[በገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መኪና ውስጥ የተጠመደ አንድ ቦምብ በባሊ፣ ኢንዶኔዥያ በአንድ የምሽት ክበብ ውስጥ የነበሩ 182 ሰዎችን ገድሎ 132 ሰዎችን አቁስሏል

[ምንጭ]

Maldonado Roberto/GAMMA ጥቅምት 12, 2002