በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዘር ጥላቻ ትክክል የሚሆንበት ጊዜ አለ?

የዘር ጥላቻ ትክክል የሚሆንበት ጊዜ አለ?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

የዘር ጥላቻ ትክክል የሚሆንበት ጊዜ አለ?

በዘርህ ምክንያት ብቻ ሰዎች ተንኮለኛ፣ ጨካኝ፣ ደደብ ወይም ግብረ ገብነት የጎደለህ እንደሆንክ አድርገው ቢገምቱህ ምን ይሰማሃል? በጣም እንደምታዝን አያጠራጥርም። የሚያሳዝነው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። ከዚህም በላይ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ንጹሐን ሰዎች የአንድ ዓይነት ዘር ወይም ብሔር አባል ስለሆኑ ብቻ ግፍ ተፈጽሞባቸዋል፤ አልፎ ተርፎም ተገድለዋል። እንዲያውም በጊዜያችን ከሚደረጉት ደም አፋሳሽ ጦርነቶች ውስጥ አብዛኞቹ መንስኤያቸው የዘር ጥላቻ ነው። ያም ሆኖ እነዚህን ግጭቶች ከሚደግፉት መካከል ብዙዎቹ በአምላክና በመጽሐፍ ቅዱስ እናምናለን የሚሉ ናቸው። ሌሎች ደግሞ ዘረኝነት የሰዎች የተፈጥሮ ባሕርይ ስለሆነ መቼም ቢሆን ሊቀር አይችልም ይላሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነቱን የዘር ጥላቻ ይደግፋልን? ከእኛ የተለየ ባሕል ወይም ዘር ያላቸውን ሰዎች መጥላት ትክክል የሚሆንበት ጊዜ አለ? የዘር ጥላቻ የማይኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?

የተፈረደባቸው በሥራቸው ነው

በጥንት ጊዜ አምላክ ከሰው ዘር ጋር ስለነበረው ግንኙነት ቁንጽል እውቀት ያለው ሰው አምላክ የዘር ጥላቻን ይደግፋል የሚል የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ሊደርስ ይችላል። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች አምላክ አንዳንድ ጎሳዎችንና ብሔራትን ጠራርጎ እንዳጠፋ ይናገሩ የለምን? ቢሆንም ዘገባዎቹን በጥልቀት ከተመለከትናቸው አምላክ እነዚህን ሕዝቦች ያጠፋው በዘራቸው ሳይሆን ለመለኮታዊ ሕጎች አክብሮት ስላልነበራቸው እንደሆነ እንገነዘባለን።

ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ አምላክ ከነዓናውያንን እንዲጠፉ የፈረደባቸው ልቅ የጾታ ብልግናና አጋንንታዊ የአምልኮ ሥርዓቶች ይፈጽሙ ስለነበረ ነው። ልጆቻቸውን እንኳን ለሐሰት አማልክት መስዋዕት አድርገው ያቃጥሉ ነበር። (ዘዳግም 7:5፤ 18:9-12) ይሁን እንጂ አንዳንድ ከነዓናውያን በአምላክ ላይ እምነት እንዳላቸው አሳይተው ንስሐ በመግባታቸው ይሖዋ ከጥፋት ያዳናቸው ከመሆኑም በላይ ባርኳቸዋል። (ኢያሱ 9:3, 25-27፤ ዕብራውያን 11:31) እንዲያውም ረዓብ የተባለች አንዲት ከነዓናዊት ሴት ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ ማለትም የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያት ሆናለች።—ማቴዎስ 1:5

ይሖዋ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ሕግ የማያዳላ አምላክ መሆኑን ያሳያል። እንዲያውም ለሁሉም ሰዎች ደህንነት ከልብ ያስባል። በዘሌዋውያን 19:33, 34 ላይ አምላክ የሚከተለውን ርኅራኄን የሚያንጸባርቅ ሕግ ሰጥቷቸው ነበር:- “በአገራችሁ ውስጥ ከእናንተ ጋር እንግዳ ቢቀመጥ ግፍ አታድርጉበት። እናንተ በግብፅ ምድር እንግዶች ነበራችሁና ከእናንተ ጋር የሚቀመጥ እንግዳ እንደ አገር ልጅ ይሁንላችሁ፣ እርሱንም እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።” በዘጸአትና በዘዳግም መጻሕፍት ውስጥም ተመሳሳይ ትእዛዛት ተመዝግበው እናገኛለን። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋ የዘር ጥላቻን አይደግፍም። ሁሉም ዘሮች ተስማምተው እንዲኖሩ ይፈልጋል።

ኢየሱስ የተለያዩ ዘሮች ተቻችለው እንዲኖሩ አስተምሯል

ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት አይሁዳውያንና ሳምራውያን እርስ በርሳቸው ይናናቁ ነበር። እንዲያውም በአንድ አጋጣሚ በሳምራውያን መንደር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም የሚያቀና አይሁዳዊ በመሆኑ ብቻ ሳይቀበሉት ቀርተዋል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥምህ ምን ታደርግ ነበር? የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “ጌታ ሆይ፣ . . . እሳት ከሰማይ ወርዶ ያጥፋቸው እንል ዘንድ ትወዳለህን?” ብለው መጠየቃቸው በወቅቱ የነበረው ጭፍን ጥላቻ ተጽዕኖ አሳድሮባቸው ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል። (ሉቃስ 9:51-56) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ያንጸባረቁት ዝንባሌ ተጽዕኖ አሳድሮበት ይሆን? በፍጹም። ደቀ መዛሙርቱን ገሠጻቸውና ሁኔታውን በሰላም ለመፍታት ወደ ሌላ መንደር አቀና። ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ ምሳሌ የተናገረው ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ነበር። ይህ ምሳሌ አንድ ሰው ከአንድ ጎሳ የመጣ መሆኑ ብቻውን ጠላት እንደማያሰኘው አጉልቶ ያሳያል። እንዲያውም ጥሩ ወዳጅ ሊሆን ይችላል።

የተለያዩ ዘሮችን ያቀፈው የክርስቲያን ጉባኤ

ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ደቀ መዛሙርት ለማፍራት ይጥር የነበረው በዋነኛነት ከራሱ ብሔር ነበር። ሆኖም ወደፊት ከሌሎች ብሔራት የመጡ ሰዎችም የእርሱ ተከታዮች እንደሚሆኑ ጠቁሟል። (ማቴዎስ 28:19) አምላክ ከሁሉም ዓይነት ዘሮች የመጡ ሰዎችን ይቀበላልን? እንዴታ! ሐዋርያው ጴጥሮስ “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ” በማለት ተናግሯል። (ሥራ 10:34, 35) ሐዋርያው ጳውሎስም ከጊዜ በኋላ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው አንድ ሰው የመጣበት ዘር እንዳልሆነ በግልጽ በመናገር ይህንን ሐሳብ አጠናክሮታል።—ቆላስይስ 3:11

አምላክ ከሁሉም ዘሮች የመጡ ሰዎችን እንደሚቀበል የሚጠቁም ሐሳብ በራእይ መጽሐፍ ውስጥም እናገኛለን። ሐዋርያው ዮሐንስ አምላክ እንዲያይ ባደረገው ራእይ ላይ መዳንን ከአምላካቸው እንዳገኙ የሚናገሩ “ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ [የመጡ] እጅግ ብዙ ሰዎች” ተመልክቶ ነበር። (ራእይ 7:9, 10) ከተለያዩ ጎሳዎችና ብሔራት የመጡ ሕዝቦች ለአምላክ ባላቸው ፍቅር አንድ ሆነው በሰላም ለሚኖሩበት ለአዲሱ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ መሠረት የሚሆኑት እነዚህ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ናቸው።

እስከዚያው ድረስ ግን ሰዎችን ከእኛ የተለየ ዘር ስላላቸው ብቻ ላለመጥላት ጥረት ማድረጋችን የተገባ ነው። ሰዎችን አምላክ በሚያያቸው መንገድ ይኸውም በዘራቸው ሳይሆን በማንነታቸው መመልከታችን ፍትሕንና ፍቅርን የሚያንጸባርቅ ነው። አንተስ ሰዎች በዚህ መንገድ ቢመለከቱህ አትደሰትም? ኢየሱስ “እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው” ብሎ ማሳሰቡ ተገቢ ነው። (ማቴዎስ 7:12) የዘር ጥላቻ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ መኖር የሚያስደስት ነው። ውስጣዊ ሰላም እንዲኖረንና ከሌሎችም ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንድንመሠርት ያስችለናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የማያዳላውን ፈጣሪያችንን ይሖዋ አምላክን እንድንመስለው ይረዳናል። በእርግጥም የዘር ጥላቻ ትክክል አይደለም የምንልበት በቂ ምክንያት አለን!