በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ጃንጥላህን እንዳትረሳ!”

“ጃንጥላህን እንዳትረሳ!”

“ጃንጥላህን እንዳትረሳ!”

ብሪታንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

በብሪታንያ ብዙ ሰዎች ጃንጥላ ይይዛሉ። ዝናብ አይመጣም ብሎ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ከቤት ስንወጣ “ጃንጥላህን እንዳትረሳ” እንባባልና አውቶቡስ ወይም ባቡር ላይ ወይም ሱቅ ውስጥ ረስተነው እንመለሳለን። አዎን፣ ይህን ተንቀሳቃሽ መጠለያችንን በቀላሉ መግዛት ስለምንችል እንደ አልባሌ ነገር እንቆጥረዋለን። ይሁን እንጂ ጃንጥላ እንደ ቀላል ነገር የማይታይበት ጊዜ ነበር።

ታላቅ ታሪክ

የመጀመሪያዎቹ ጃንጥላዎች ከዝናብ ጋር ምንም ዓይነት ዝምድና አልነበራቸውም። በጣም ታላላቅ ለሆኑ ሰዎች ብቻ የተወሰኑ የማዕረግና የክብር ምልክቶች ነበሩ። ከአሦር፣ ከግብጽ፣ ከፋርስና ከሕንድ የተገኙ ሐውልቶችና ሥዕሎች አገልጋዮች ገዥዎቻቸውን ከፀሐይ ለመከላከል ጃንጥላ ይይዙላቸው እንደነበረ ያሳያሉ። በአሦር ጃንጥላ መያዝ የሚችለው ንጉሡ ብቻ ነበር።

በታሪክ ዘመናት በሙሉ በተለይ በእስያ ጃንጥላ የሥልጣን ምልክት ሆኖ አገልግሏል። የአንድ ገዥ ክብር ባሉት ጃንጥላዎች ቁጥር ይለካ ነበር። የአንድ የበርማ ንጉሥ የሃያ አራቱ ጃንጥላዎች ጌታ ተብሎ የተጠራው በዚህ ምክንያት ነበር። አንዳንድ ጊዜ በጃንጥላው ላይ የሚኖሩት የደረጃዎች ብዛት ትርጉም ይኖረዋል። የቻይና ንጉሠ ነገሥት ጃንጥላ አራት ደረጃዎች ሲኖሩት የሲያም (የጥንቷ ታይላንድ) ንጉሥ ጃንጥላ ደግሞ ሰባት ወይም ዘጠኝ ደረጃዎች ነበሩት። ዛሬም እንኳን ጃንጥላን ሥልጣንንና ክብርን ለማመልከት የሚገለገሉባቸው አንዳንድ የሩቅ ምሥራቅና የአፍሪካ አገሮች አሉ።

ሃይማኖታዊ ጃንጥላዎች

ጃንጥላ ከሃይማኖት ጋር መዛመድ ከጀመረ ረዥም ዘመን ሆኖታል። የጥንት ግብጾች ኑት የተባለችው ሴት አምላክ መላውን ምድር በራሷ አካል እንደ ጃንጥላ እንደምታጠላ ያምኑ ነበር። ስለዚህ ሰዎች የዚህችን አምላክ ጥበቃ ለማግኘት የየራሳቸውን ተንቀሳቃሽ “ጣሪያ” ይዘው ይዘዋወሩ ነበር። በሕንድና በቻይና የተዘረጋ ጃንጥላ የሰማይን ጠፈር እንደሚያመለክት ይታመን ነበር። የጥንት ቡድሂስቶች ጃንጥላን የቡድሃ ምልክት አድርገው ሲጠቀሙ በሕንጻዎቻቸው ጉልላት ላይም ጃንጥላ ያደርጉ ነበር። በሂንዱ ሃይማኖትም ጃንጥላዎች የራሳቸው ቦታ ነበራቸው።

ጃንጥላዎች በ500 ከዘአበ ወደ ግሪክ የተዛመቱ ሲሆን በሃይማኖታዊ በዓሎች ላይ በወንድና በሴት አማልክት ምስሎች ላይ ይደረጉ ነበር። አገልጋዮቻቸውን ጃንጥላ አስይዘው የሚዟዟሩ አቴናውያን ሴቶች ነበሩ። ጃንጥላ የሚይዙ ወንዶች ግን እምብዛም አልነበሩም። ይህ ልማድ ከግሪክ ወደ ሮም ተዛመተ።

የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ክብረ በዓሎቿን በጃንጥላ ታደምቅ ነበር። ሊቀ ጳጳሱ በቀይና ብጫ ሽንትሮች ባጌጠ ጃንጥላ ሥር ሆኖ ሲታይ ጳጳሳቱና ካርዲናሎቹ ግን አረንጓዴ ቀለም ያለው ጃንጥላ ይያዝላቸው ነበር። ዛሬም ቢሆን በታላላቅ አብያተ ክርስቲያናት በሊቀ ጳጳሳቱ መንበር ላይ ከአልባሳቱ ጋር የሚመሳሰል ቀለም ያለው ጃንጥላ ይደረጋል። አንድ ሊቀ ጳጳሳት ሞቶ ሌላ አዲስ ሊቀ ጳጳሳት እስኪመረጥ ድረስ በጊዜያዊነት የሚሠራው ካረዲናልም መለያ የሚሆነው ጃንጥላ ይደረግለታል።

ከፀሐይ መከለያነት ወደ ዝናብ መጠለያነት

በአሁኑ ጊዜ የፀሐይን ትኩሳት እንዲከላከልልን እንዲሁም ከዝናብ ለመጠለል ጃንጥላ እንይዛለን። መጀመሪያ ላይ ግን ከዝናብ ለመጠለል ተብሎ ጃንጥላ አይያዝም ነበር። የወረቀት ጃንጥላዎቻቸውን ዘይትና ሰም ቀብተው ለዝናብ መጠለያነት መጠቀም የጀመሩት ቻይናውያን ወይም የጥንቷ ሮም ሴቶች ሳይሆኑ አይቀሩም። ይሁን እንጂ በ16ኛው መቶ ዘመን ኢጣሊያውያን በኋላም ፈረንሣውያን መጠቀም እስከ ጀመሩበት ጊዜ ድረስ ለፀሐይ ወይም ለዝናብ ተብሎ ጃንጥላ የመያዝ ሐሳብ ጠፍቶ ቆየ።

አሥራ ስምንተኛው መቶ ዘመን ላይ የብሪታንያ ሴቶች ጃንጥላ መያዝ ቢጀምሩም ወንዶቹ ግን የሴት ጌጥ ነው ብለው ስለናቁት አይዙትም ነበር። ከዚህ ለየት ያለ አቋም የያዙት ደንበኞቻቸውን ዝናብና የፀሐይ ትኩሳት እንዳይነካቸው ጃንጥላ ይዘው ሠረገሎቻቸው ዘንድ ማድረስ የሚኖረውን ጥቅም ያስተዋሉት የቡና ቤት ባለቤቶች ነበሩ። ቀሳውስትም በቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ የቀብር ሥነ ሥርዓት ሲያካሂዱ የሚወርድባቸውን ዝናብ ለመከላከል እንደሚጠቅማቸው ተገንዝበዋል።

በእንግሊዝ አገር የጃንጥላ ታሪክ እንዲለወጥ ያደረገው ተጓዥና በጎ አድራጊ የሆነው ጆናስ ሃንዌይ ነበር። በለንደን አደባባዮች ጃንጥላ ይዞ ለመዘዋወር የደፈረ የመጀመሪያው ሰው እርሱ እንደሆነ ይነገራል። በባሕር ማዶ ባደረጋቸው ጉዞዎች ወንዶች ጃንጥላ አድርገው ተመልክቶ ስለነበረ ሆን ብለው ውኃ የሚረጩበትን የሠረገላ ነጂዎች ቁጣ ተቋቁሞ ጃንጥላ ዘርግቶ ለመዘዋወር ቆረጠ። ሃንዌይ ለ30 ዓመታት ሳያቋርጥ ጃንጥላ ይዞ የተዘዋወረ ሲሆን በሞተበት ጊዜ ማለትም በ1786 የእሱን ፈለግ ተከትለው ጃንጥላ የሚይዙ ብዙ ወንዶችና ሴቶች ነበሩ።

በዚያ ዘመን በዝናብ ጃንጥላ መያዝ በጣም አስቸጋሪ ነበር። ጃንጥላዎቹ በጣም ትልቅ፣ ከባድና ለመያዝ የማይመቹ ነበሩ። ሽፋናቸው ከሐር ወይም ከሸራ የተሠራና ዘይት የተቀባ በመሆኑና የውስጥ መወጠሪያቸውና እጀታቸው ከመቃ ወይም ከዓሣ ነባሪ አጥንት የተሠራ ስለነበረ በዝናብ በሚርሱበት ጊዜ ለመክፈትና ለመዝጋት በጣም ያስቸግሩ ነበር። ዝናብም ያስገቡ ነበር። ይሁን እንጂ በተለይ ዝናብ በሚዘንብበት ጊዜ ሠረገላ ከመከራየት ጃንጥላ መጠቀም ገንዘብ የሚቆጥብ በመሆኑ ተወዳጅነታቸው እየጨመረ ሄደ። ጃንጥላ ሠሪዎችና ሻጮች በጣም ከመብዛታቸውም በላይ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ሰዎች የጃንጥላን አሠራር ለማሻሻል ተነሳሱ። በ19ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ ሳሙኤል ፎክስ ቀላልና ጠንካራ መወጠሪያ ብረት ያለውን ፓራጎን የተባለ የጃንጥላ ሞዴል የፈጠራ ባለቤትነት መብት ወሰደ። እንደ ሐር፣ ጥጥና ሰም የተነከረ ሊኖ የመሰሉ ቀላል ጨርቆች የቀድሞዎቹን ዘይት የተቀቡ ሸራዎች ተኩ። ዘመናዊው ጃንጥላ ብቅ አለ ማለት ነው።

የፋሽን ክፍል ሆነ

በዚህ ጊዜ ጃንጥላ አምረው ለመታየት ለሚፈልጉ የእንግሊዝ ወይዛዝርት የአለባበስ ፋሽን ክፍል ሆነ። ፋሽኖች በተለዋወጡ ቁጥር የጃንጥላዎችም ስፋት ይጨምርና የጨርቆቹም ዓይነትና ድምቀት ይለዋወጥ ነበር። ከልብሶቻቸው ጋር በሚስማማ መንገድ በተለያዩ ዘርፎች፣ ጌጦች፣ ጥልፎችና ላባዎች ሳይቀር ያጌጡ ነበር። እስከ 20ኛው መቶ ዘመን ድረስ ፊቷ በፀሐይ እንዳይመታ የምትፈልግ ወይዘሮ ሁሉ ጃንጥላ አይለያትም ነበር።

በ1920ዎቹ ዓመታት ፀሐይ መትቶት የጠቆረ ቆዳ እንደ ጥሩ መልክ መቆጠር ስለጀመረ ፀሐይን ለመከላከል ጃንጥላ መያዝ ፈጽሞ እየቀረ መጣ። አሁን ደግሞ ሠፊ ባርኔጣ የሚያደርጉ፣ ጥቁርና የተጠቀለለ፣ በከዘራነትም የሚያገለግል ጃንጥላ የሚይዙ የከተማ ጨዋዎች ዘመን መጣ።

ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠረው አዲስ ቴክኖሎጂ የሚተጣጠፉና ዝናብ የማያስገቡ ከናይለንና ከፖሊስተር የሚሠሩ ፕላስቲክ መያዣ ያላቸው አዳዲስ ዓይነት ጃንጥላዎች ገበያ ውስጥ እንዲገቡ አስቻለ። አሁንም ቢሆን በእጅ የሚሠሩና ውድ የሆኑ የተራቀቁ ጃንጥላዎችን የሚሠሩ ጥቂት ሱቆች አሉ። ይሁን እንጂ ዛሬ በአብዛኛው ሠፋፊ ከሆኑት የመዝናኛ ጥላዎች አንስቶ የ15 ሳንቲ ሜትር ቁመት እስካላቸው በቦርሣ ውስጥ ሊያዙ የሚችሉ ትናንሽ ተጣጣፊ ጃንጥላዎች ድረስ የተለያየ መጠንና ቀለም ያላቸው ጃንጥላዎች በብዛትና በርካሽ የሚመረቱት በትላልቅ ፋብሪካዎች ነው።

ጃንጥላ እንደ ቅንጦት ዕቃና ክብርና ማዕረግ ማሳያ ይቆጠር የነበረበት ዘመን ቢኖርም ዛሬ ግን በቀላል ዋጋ የሚገዛና ከሚጠፉ ዕቃዎች መካከል የመጀመሪያውን ደረጃ የያዘ ሆኗል። በየትኛውም የዓለም ክፍል አስቸጋሪ የአየር ጠባዮችን ለመቋቋም የሚያስችል በጣም ጠቃሚ መሣሪያ ሲሆን፣ ለፀሐይ መጋለጥ አደገኛ እንደሆነ በሚነገርበት በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ፀሐይን ለመከላከል በአንዳንድ አገሮች እየተለመደ መጥቷል። ስለዚህ አንተም ዛሬ ከቤትህ ስትወጣ “ጃንጥላህን እንዳትረሳ” የሚል ማስጠንቀቂያ ትሰማ ይሆናል።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የጃንጥላ አገዛዝና አያያዝ

ቅልጥፍ ካለና ከጥንካሬ አንዱን መምረጥ ይኖርብሃል። ተጣጥፎ ኪስ ውስጥ ሊገባ የሚችለው ዓይነት ጃንጥላ ያሉት የመወጠሪያ ብረቶች ጥቂት በመሆናቸው ኃይለኛ ነፋስ ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ አይኖረውም። በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ከዘራ ያለው የተለመደ ጃንጥላ ወደድ ሊል ቢችልም አብዛኛውን ጊዜ የተለያዩ የአየር ጠባዮችን ሊቋቋምና ብዙ ጊዜ ሊቆይ ይችላል። በእርግጥም አንድ ጥሩ ጃንጥላ ብዙ ዓመት መቆየት ይችላል። የትኛውንም ዓይነት ጃንጥላ ብትመርጥ መልሰህ አጥፈህ ከማስቀመጥህ በፊት ተዘርግቶ ቆይቶ በደንብ እንዲደርቅ በማድረግ እንዳይሻግትና እንዳይዝግ ጠብቀው። በመሸፈኛው ውስጥ ማስቀመጥ አቧራ ሳይጠጣ ንፁሕ ሆኖ እንዲቆይ ያስችላል።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ አገልጋይ ለአሦራዊ ንጉሥ ጃንጥላ ይዞ

ጃንጥላ የያዘች አንዲት የጥንት ግሪካዊት ሴት

[ምንጭ]

የሥዕሎቹ ምንጭ:- The Complete Encyclopedia of Illustration/J. G. Heck

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የፀሐይ መከላከያ ጃንጥላ በ1900 ገደማ

[ምንጭ]

Culver Pictures