በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥርስ መፋቂያ እንጨት

ጥርስ መፋቂያ እንጨት

ጥርስ መፋቂያ እንጨት

ዛምቢያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

አፍሪካውያን የጥርስ ብሩሽ እምብዛም ባይጠቀሙም ጥርሶቻቸው ነጫጭና የሚያማምሩ ናቸው። ይህ ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው? ብዙዎቹ ጥርሳቸውን ለማጽዳት እንጨት ወይም መፋቂያ ስለሚጠቀሙ ነው።

በድሮ ጊዜ ባቢሎናውያን ቆየት ብሎ ደግሞ ግብጻውያን፣ ግሪኮችና ሮማውያን ጥርሳቸውን ለማጽዳት መፋቂያ ይጠቀሙ ነበር። የእስልምና ሃይማኖት ከመመሥረቱ በፊት አረቦችም ከእንጨት ቁራጭ በሚሠሩ “የጥርስ ብሩሾች” ጥርሳቸውን ማጽዳታቸው የተለመደ ነበር። የእንጨት መፋቂያ በአውሮፓ የነበረውን ተወዳጅነት የዛሬ 300 ዓመት ገደማ ቢያጣም በአፍሪካ፣ በእስያና በመካከለኛው ምሥራቅ አሁንም በሰፊው ጥቅም ላይ ይውላል።

በመካከለኛው ምሥራቅ በብዛት ጥቅም ላይ የሚውለው የጥርስ መፋቂያ ሶልትቡሽ ወይም የጥርስ ብሩሽ ዛፍ ተብሎ የሚጠራው የዛፍ ዓይነት ነው። በምዕራብ አፍሪካ የሎሚና የብርቱካን ዛፍ ቅርንጫፎችን በመፋቂያነት የሚጠቀሙ ሲሆን በሕንድ ደግሞ በዋነኛነት የኒም ዛፍን ይጠቀማሉ። በምሥራቅ አፍሪካ ደግሞ ወደ 300 የሚጠጉ የዛፍ ዓይነቶችና ቁጥቋጦዎች ለጥርስ መፋቂያነት ያገለግላሉ። የእንጨት መፋቂያ ጥርስ የሚያጸዳው እንዴት ነው?

የእንጨቱ አንደኛው ጫፍ ሲታኘክ እንደ ጥርስ ብሩሽ ሻካራ ይሆናል። መፋቂያውን ማኘክ በጥርሶች መካከል የቀረውን ምግብ ለማውጣት የሚያስችል ሲሆን በድድ ውስጥ ያለውን የደም ዝውውር ከፍ ያደርገዋል። ከዚህም በተጨማሪ በአፍ ውስጥ የሚኖረው የምራቅ መጠን እንዲጨምር ያደርጋል። ምራቅ ደግሞ ባክቴሪያዎችን አጥቦ ያስወግዳል፤ እንዳይራቡም ያደርጋል። *

ይሁን እንጂ የመፋቂያ እንጨት ጥርስን ከማጽዳት የበለጠ ጥቅም አለው። የአንዳንድ ተክሎች ቀንበጥና ሥራ ሥሮች በጥርስ ላይ ልማም ወይም የጥርስ ቆሻሻ እንዳይፈጠር የሚከላከሉ ኬሚካሎች አሏቸው። ከአንዳንድ የእንጨት ዓይነቶች የሚወጣው ፈሳሽ የፀረ ባክቴሪያነትና የፀረ ፈንገስነት ጠባይ እንዳለው ተረጋግጧል። ቀደም ብለን የጠቀስነው ሶልትቡሽ የተባለው ዛፍ ቀንበጦች የቆላ ቁስል እንዳይፈጠር ይከላከላሉ። በናሚቢያ ሙታላ ከተባለው ተክል ላይ የሚቆረጥ እንጨት የጥርስ መበስበስን፣ የድድ በሽታንና የጉሮሮ ቁስለትን የሚያስከትሉ ተህዋስያንን እድገት እንደሚቀንስ ይታወቃል። ይህ ተፈጥሯዊ የጥርስ ማጽጃ የጥርስ መቦርቦርን ይከላከላል፤ እንዲሁም የጥርስን ሥርና ድድን ያጠነክራል። በአሁኑ ወቅት አንዳንድ የጥርስ ሳሙና አምራች ኩባንያዎች በምርቶቻቸው ውስጥ የእነዚህን ተክሎች ቃጫና ሙጫ ይጨምራሉ።

እርግጥ አንዳንዶች ዘመናዊውን የጥርስ ብሩሽ ለመጠቀም ይመርጣሉ። አንተ የምትጠቀመው ጥንታዊውን የእንጨት መፋቂያም ይሁን ዘመናዊውን የጥርስ ብሩሽ የጥርስህን ንጽሕና መጠበቅህ ለጤንነትህ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ ምንም አያጠያይቅም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 እርግጥ፣ ለጥርስ ንጽሕና አመጋገብም ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አይካድም። በአፍሪካ በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በከተማ ከሚኖሩት የበለጠ ያልተፈተጉ እህሎችንና አትክልቶችን ይመገባሉ። እንዲሁም ስኳርን፣ የፋብሪካ ምግቦችንና ለስላሳ መጠጦችን የመሳሰሉ ለጥርስ መበላሸት በዋነኛነት ምክንያት የሚሆኑትን ነገሮች በብዛት አይጠቀሙም።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለጥርስ መፋቂያነት ከሚያገለግሉት ዛፎች መካከል አንዱ የኒም ዛፍ ነው

[ምንጭ]

William M. Ciesla, Forest Health Management International, www.forestryimages.org