በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፍጽምና የመጠበቅ ዝንባሌን ማስወገድ የምችለው እንዴት ነው?

ፍጽምና የመጠበቅ ዝንባሌን ማስወገድ የምችለው እንዴት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

ፍጽምና የመጠበቅ ዝንባሌን ማስወገድ የምችለው እንዴት ነው?

“ፍጽምና የመጠበቅ ዝንባሌ መላ ሕይወቴን ተቆጣጥሮታል።”—ካርሊ

ፍጽምና የመጠበቅ ዝንባሌ ማለትም አንድ ሰው የሚሠራው ነገር ሁሉ እንከን የለሽ መሆን አለበት የሚለው አመለካከት የበርካታ ወጣቶችን አስተሳሰብ ይቆጣጠራል።

ፐርፌክሽኒዝም—ዋትስ ባድ አባውት ቢይንግ ቱ ጉድ? የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ጥራት ያለው ነገር የማከናወን ተገቢ ፍላጎት በማሳደርና የማይደረስበትን ነገር ለማግኘት ከአቅም በላይ የሆነ ጥረት በማድረግ መካከል ከፍተኛ ልዩነት አለ። ጥራት ያለው ሥራ ማከናወን የሚፈልጉ ሰዎች ነገሮች ሥርዓትና መልክ እንዲኖራቸው በጥብቅ የሚፈልጉና ለራሳቸው የላቀ ግብ የሚያወጡ ቢሆኑም እንኳ ስህተታቸውን አምነው ይቀበላሉ ከዚያም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያውቃሉ። . . . በአንጻሩ ደግሞ ፍጽምና የሚጠብቁ ሰዎች እንዳልሳሳት የሚል ጭንቀት ሕይወታቸውን ይቆጣጠረዋል። ከአቅም በላይ የሆኑ መሥፈርቶች ያወጣሉ።”

እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ይታይብሃል? የማይደረስበት መሥፈርት የምታወጣ ከሆነ በቀላሉ ተሳስረህ ቁጭ ልትል ትችላለህ። ከዚህ ቀደም ሠርተኸው የማታውቀውን ነገር ከመጀመር ትሸሽ ይሆናል። ወይም ደግሞ እንዳልሳሳት በሚል ፍራቻ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን በይደር ማቆየት ትመርጥ ይሆናል። አልፎ ተርፎም የአንተን መሥፈርቶች ከማያሟላ ሰው ጋር ላለመቀራረብ ትመርጥ ይሆናል። ከዚህም የተነሳ ጓደኛ ልታጣ ትችላለህ።

ከላይ የቀረበው መግለጫ በአንተ ላይ የሚታይ ከሆነ ለመክብብ 7:16 ትኩረት ልትሰጥ ይገባል:- “እጅግ ጻድቅ አትሁን፣ እጅግ ጠቢብም አትሁን፣ እንዳትጠፋ።” አዎን፣ ፍጽምና የሚጠብቅ ሰው ራሱን ‘ለጥፋት’ ሊዳርግ ይችላል! እንዲያውም ፍጽምና የመጠበቅ ዝንባሌ የምግብ ፍላጎት ማጣትንና ከልክ በላይ መብላትን የመሳሰሉ ለሕይወት አስጊ የሆኑ የአመጋገብ ልማዶችን ሊያስከትልም ይችላል። *

‘ፍጽምና የመጠበቅ ዝንባሌን ማስወገድ የምችለው እንዴት ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። በዚህ ረገድ የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል አይካድም። በአምላክ እርዳታ ግን ይቻላል። እንግዲያው አምላክ ፍጽምናን ስለመጠበቅ ያለውን አመለካከት እስቲ እንመልከት።

ፍጽምና—ሊደረስበት የሚችል ግብ ነው?

ለመሆኑ በተሟላ መልኩ ፍጹም መሆን ይቻላል? መጽሐፍ ቅዱስ እንደማይቻል ይገልጻል:- “ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ . . . ሁሉ ተሳስተዋል፣ በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል።” (ሮሜ 3:10-12) ይህ ልናስብበት የሚገባ ጥቅስ አይመስልህም? ሙሉ በሙሉ ፍጹም ለመሆን ጥረት የሚያደርግ ማንኛውም ሰው እንደማይሳካለት ያሳያል።

በመንፈሳዊ አቋሙ የላቀ ምሳሌ የሆነውን ሐዋርያው ጳውሎስን ተመልከት። እርሱም እንኳ ሳይቀር አምላክን ፍጹም በሆነ መንገድ ማገልገል አልቻለም። እንዲህ ሲል ሳይሸሽግ ተናግሯል:- “መልካሙን አደርግ ዘንድ ስወድ በእኔ ክፉ እንዲያድርብኝ ሕግን አገኛለሁ። በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፣ ነገር ግን በብልቶቼ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ።” (ሮሜ 7:21-23) ጳውሎስ በክርስትና ጎዳና በታማኝነት ሊጸና የቻለው አምላክ ስለረዳው ነው።

አምላክ ከማናችንም የተሟላ ፍጽምና የማይጠብቅና እንዲህ እንድናደርግ የማያስገድደን መሆኑ ያስደስታል። “እርሱ አፈጣጠራችንን ያውቃልና፤ ትቢያ መሆናችንንም ያስባል።” (መዝሙር 103:14 አ.መ.ት) የሰው ልጆች ፍጽምና ደረጃ ላይ መድረስ የሚችሉት በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ብቻ ነው።

አመለካከትህን አስተካክል

እስከዚያ ድረስ ግን ሙሉ በሙሉ ፍጹም እሆናለሁ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። እንዲያውም አልፎ አልፎ ስህተት ልትሠራ እንደምትችል መጠበቅ አለብህ። (ሮሜ 3:23) ለነገሩ መሳሳታችንን እንኳ ልብ የማንልባቸው ጊዜያት አሉ! መዝሙር 19:12 “የራሱን ስሕተት የሚያይ ማንም የለም” ይላል። (የ1980 ትርጉም) ማቲው የሚባል አንድ ወጣት እንዲህ ብሏል:- “በምድር ላይ ፍጹም የሆነ አንድም ሰው የለም። ከራስህ ፍጽምና የምትጠብቅ ከሆነ መቼም ቢሆን ደስተኛ አትሆንም። . . . ፍጽምና መጠበቅ የማይመስልና የማይቻል ነገር ነው።”

ይህን በአእምሮህ ይዘህ አመለካከትህን ለማስተካከል ለምን ጥረት አታደርግም? ለምሳሌ ያህል አንድን ነገር ከማንም በላቀ መንገድ ካልሠራሁ በሚል ራስህን ታደክማለህ? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነት አድካሚ ጥረት ማድረግ ‘ከንቱና ነፋስን እንደ መከተል’ መሆኑን ይናገራል። (መክብብ 4:4) የላቁ ሆነው በመገኘት የሚሳካላቸው በጣም ጥቂቶች እንደሆኑ ግልጽ ነው። አንድ ሰው የመጀመሪያውን ደረጃ ለመያዝ ቢሳካለትም እንኳ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ከእርሱ የተሻለ መምጣቱ አይቀርም።

ሐዋርያው ጳውሎስ “እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ . . . እናገራለሁ” የሚል ምክር ሰጥቷል። (ሮሜ 12:3) ሐቁን ተቀበል! ያሉህን ችሎታዎችም ሆነ የአቅም ገደቦች ግምት ውስጥ በማስገባት አመለካከትህን አስተካክል። ጥራት ያለው ሥራ ለማከናወን ሞክር፤ ፍጽምና ግን አትጠብቅ። በግልጽ የተቀመጠ ሆኖም ሊደረስበት የሚቻል ግብ አውጣ።

ለምሳሌ ያህል ጢሞቴዎስ “የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ” እንዲሆን ጳውሎስ ማበረታቻ ሰጥቶታል። (2 ጢሞቴዎስ 2:15) አዎን፣ ጳውሎስ ጥራት ያለው ሥራ እንዲሠራ ቢያበረታታውም ፍጹም ለመሆን እንዲጥር ግን አልመከረውም። በተመሳሳይ አንተም ለራስህ ምክንያታዊ ግቦች አውጣ። “ምክንያታዊ” የሚባለው ምን ዓይነት ግብ እንደሆነ ማወቅ ካልቻልክ ደግሞ ጉዳዩን ከወላጆችህ ወይም ከምትተማመንበት በዕድሜ የበሰለ ሰው ጋር ተነጋገርበት።

እንዲያውም አንዳንዶች በደንብ የማትችለውን ነገር ሥራዬ ብሎ መሞከር ጥሩ መሆኑን ይናገራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ከዚህ ቀደም ሞክረህ የማታውቀውን ስፖርት ልትሠራ ወይም የሙዚቃ መሣሪያ ልትጫወት ትችላለህ። አዲስ ነገር ስትማር ብዙ ስህተት ልትሠራ እንደምትችል የታወቀ ነው። ይህ ግን ጠቃሚ ጎን ሊኖረው ይችላል። ምናልባትም መሳሳት የመማር ሂደት ክፍል መሆኑን እንድትገነዘብ ይረዳህ ይሆናል።

የቤት ሥራህን ስትሠራም ሆነ የሙዚቃ መሣሪያ ስትጫወት ወይም ማንኛውንም ሥራ ስታከናውን ሐዋርያው ጳውሎስ “ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ” ሲል የሰጠውን ተጨማሪ ምክር ማስታወስ ይኖርብሃል። (ሮሜ 12:11) አዎን፣ ባይሳካልኝስ በሚል ፍራቻ ሥራውን ለሌላ ጊዜ አታስተላልፍ ወይም ዛሬ ነገ እያልክ አታመንታ።

አንዲት ወጣት “ሁኔታዎችን ላመቻች” በሚል ሰበብ የሚሰጣትን የቤት ሥራ ለሌላ ጊዜ የማስተላለፍ ልማድ ነበራት። አንድን ሥራ ከመጀመር በፊት ዝግጅት ማድረግ ተገቢ ቢሆንም ዛሬ ነገ የማለት ልማድ እንዳይኖርህ ተጠንቀቅ። ይህች ተማሪ “መቶ በመቶ ያልረካችበትን የቤት ሥራ ከማስረከብና ጭራሽ ሳይሰጡ ከመቅረት አንዱን እንድትመርጥ በምትገደድበት ጊዜ የቤት ሥራውን ማስረከብ የተሻለ ምርጫ” እንደሆነ ከጊዜ በኋላ ተገንዝባለች።

ጎጂ አስተሳሰቦችን አስወግድ!

ግልጹን ለመናገር አንድን ሥራ እንከን የለሽ በሆነ መልኩ ልትሠራው እንደማትችል እየተሰማህ ሥራውን መጀመር ሊከብድህ ይችላል። አንዳንድ ስህተቶች መስራትህ ነቀፌታ አዘል የሆኑ ተስፋ አስቆራጭ አስተሳሰቦች ወደ አእምሮህ እንዲመጡ ያደርግ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ትችላለህ? አሉታዊ በሆኑ ሐሳቦች ላይ ማውጠንጠን ጎጂና ለሽንፈት የሚዳርግ መሆኑ አይካድም። በመሆኑም ስለራስህ ያለህን ምክንያታዊ ያልሆነ አስተሳሰብ ከአእምሮህ ለማስወጣት ብርቱ ጥረት አድርግ። በሠራኸው ስህተት በራስህ ላይ የመሳቅ ልማድ ይኑርህ። ደግሞም እኮ “ለመሳቅም ጊዜ አለው።” (መክብብ 3:4) ይሖዋ በራሳችን ላይ ቢሆንም እንኳ የስድብ ቃል እንድንናገር እንደማይፈቅድ መዘንጋት አይኖርብንም።—ኤፌሶን 4:31

ነጋ ጠባ ራስህን ከመውቀስ ይልቅ ምሳሌ 11:17 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ አድርግ:- “ቸር ሰው ለራሱ መልካም ያደርጋል፤ ጨካኝ ግን ሥጋውን ይጐዳል።” እንግዲያው ይህን ጥያቄ አስብበት፣ ከአቅም በላይ የሆኑ መሥፈርቶችን ማውጣትህ በቀላሉ ወዳጆች እንድታፈራ አስችሎሃል? ይህ የማይመስል ነው። ምናልባትም እንደምትጠብቀው ሆነው ባለመገኘታቸው ምክንያት ያገለልካቸው ሰዎች ይኖሩ ይሆናል። ታዲያ ምን ማድረግ ትችላለህ?

“እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፣ ይቅር ተባባሉ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ በሥራ አውል። (ቆላስይስ 3:13) አዎን፣ ከሌሎች በምትጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ በመሆን ወዳጆች ማፍራት ትችላለህ!

‘ፍጽምና የምጠብቅ በመሆኔ ሰዎች ለምን ያገልሉኛል?’ ብለህ ትገረም ይሆናል። ከራስህ ብዙ እንደምትጠብቅ መናገርህ በሌሎች ላይ ምን ዓይነት ስሜት ሊያሳድር እንደሚችል አስብ። ዌን ፐርፌክት ኢዝንት ጉድ ኢነፍ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “መቶ በመቶ አልደፈንኩም በሚል ከሚገባው በላይ ቅሬታ ማሰማትህ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ከአንተ ያነሰ ውጤት ያገኙ ልጆችን ስሜት ሊጎዳ ይችላል።” እንግዲያው አሉታዊ አመለካከትህንና ስለ ራስህ ብቻ የማሰብን ዝንባሌ ለመዋጋት ጥረት አድርግ። እንዲህ ካደረግህ ሰዎች ከአንተ ጋር መሆን ይበልጥ ያስደስታቸዋል።

ወጣቷ ካርሊ “ፍጽምና የመጠበቅ ዝንባሌዬን እርግፍ አድርጌ መተው እንዳለብኝ ራሴን ማሳመን አስፈልጎኛል” በማለት ጉዳዩን ጠቅለል አድርጋ ገልጻዋለች። እንዲህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? አምላክ ለዚህ ጉዳይ ባለው አመለካከት ላይ አሰላስል። ያም ሆኖ አስተሳሰብህን ማስተካከል ካስቸገረህ ወላጆችህን ወይም በጉባኤህ የሚገኝን የጎለመሰ ክርስቲያን አነጋግር። ወደ አምላክ በጸሎት በመቅረብ አስተሳሰብህን ለመለወጥ እንዲረዳህ ጠይቀው። ፍጽምና የመጠበቅ ዝንባሌን በመዋጋት ረገድ ጸሎት ከፍተኛ እርዳታ ያበረክታል።—መዝሙር 55:22፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7

ይሖዋ በታማኝነት እንድናገለግለው እንጂ ፍጽምናን እንደማይጠብቅብን ፈጽሞ አትዘንጋ። (1 ቆሮንቶስ 4:2) ታማኝ ለመሆን ጥረት የምታደርግ ከሆነ ፍጹም ባትሆንም እንኳ በአንተነትህ ደስታ ሊሰማህ ይችላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 በነሐሴ 2003 እትማችን ላይ የወጣውን “መሳሳት እንደሌለብኝ የሚሰማኝ ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ባይሳካልኝስ የሚል ፍርሃት አሳስሮ ሊያስቀርህ ይችላል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አዳዲስ ነገሮችን ለመማር መሞከር ስህተት መሥራት የማይቀር ነገር መሆኑን እንድትገነዘብ ሊረዳህ ይችላል