በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጅነት ሲባክን

ልጅነት ሲባክን

ልጅነት ሲባክን

“ልጅነት መሠረታዊ ከሆኑት የሕፃናት ሰብዓዊ መብቶች አንዱ ነው።”ዘ ሃሪድ ቻይልድ”

ልጆች በልጅነት ዕድሜያቸው የሚያስጨንቃቸውና የሚያሳስባቸው ነገር ሳይኖር እንደልባቸው ተጫውተው ማደግ አለባቸው ብትባል እንደምትስማማ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ብዙ ልጆች ይህን የመሰለ የልጅነት ጊዜ ሳያገኙ ማደጋቸው በእጅጉ የሚያሳዝን ነው። ልጆች የጦርነት ተጠቂዎች በሚሆኑበት ጊዜ ስንቶቹ የወደፊት ምኞታቸውና ተስፋቸው መና ሆኖ እንደሚቀርባቸው አስብ። በተጨማሪም በባርነትና በሚፈጸምባቸው ግፍ ምክንያት ሕይወታቸው የሚበላሽባቸው ልጆች ምን ያህል እንደሚሆኑ ገምት።

አንድ ልጅ ከወላጆቹ ቤት ጎዳና እንደሚሻለው አስቦ የጎዳና ተዳዳሪ በሚሆንበት ጊዜ ምን እንደሚሰማው መገመት ለአብዛኞቻችን አስቸጋሪ ይሆንብናል። እንደነዚህ ያሉት ልጆች በፍቅርና በእንክብካቤ ተከብበው መኖር በሚገባቸው ዕድሜ ሊበዘብዟቸውና ሊጠቀሙባቸው የሚፈልጉ ግፈኞችን እንዴት ተቋቁመው መኖር እንደሚችሉ ለመማር ይገደዳሉ። ይህ የምንኖርበት አስጨናቂ ዘመን በልጅነት ሕይወት ላይ ብዙ ጉዳት እያደረሰ እንዳለ በተደጋጋሚ የሚታይ ነው።

“ተመልሼ ልጅ በሆንኩ ብዬ እመኛለሁ”

የሃያ ሁለት ዓመቷ ካርመን የልጅነት ዕድሜዋን በሙሉ ያሳለፈችው በብዙ ችግር ነበር። * እርሷና እህቷ ከአባታቸው ጭካኔና ከእናታቸው ግድየለሽነት ለማምለጥ ሲሉ የጎዳና ተዳዳሪዎች ለመሆን ተገደዱ። ይህ ኑሯቸው ለብዙ አደጋ የሚያጋልጣቸው ቢሆንም ከቤታቸው የኮበለሉ ልጆች የሚያጋጥሟቸውን ብዙ ችግሮች ተከላክለው ለማደግ ችለዋል።

ካርመን እንደ ልጅ ሆና የኖረችበት ጊዜ ትዝ ስለማይላት የልጅነት ዕድሜዋ እንዲሁ ባክኖ ማለፉ በጣም ያሳዝናታል። “22 ዓመት እስኪሆነኝ ድረስ መላው ሕይወቴን ያሳለፍኩት በመከራና በችግር ነው” በማለት ታማርራለች። “አሁን አግብቼ የራሴ ልጅ አለኝ። ቢሆንም በአሻንጉሊት እንደመጫወት ያሉትን ትናንሽ ልጆች የሚያደርጓቸውን ነገሮች ማድረግ በጣም ያምረኛል። ወላጆች እንዲያቅፉኝና እንዲስሙኝ እፈልጋለሁ። ተመልሼ ልጅ በሆንኩ ብዬ እመኛለሁ።”

የካርመንንና የእህቷን የመሰለ ችግር ያጋጠማቸው ልጆች በጣም ብዙ ናቸው። ልጅነታቸውን ተነጥቀው ጎዳና ተዳዳሪዎች ሆነዋል። ብዙዎቹ ኑሯቸውን ለማሸነፍ በወንጀል ድርጊቶች ይካፈላሉ። ልጆች ወንጀል መሥራት የሚጀምሩበት ዕድሜ ከጊዜ ወደ ጊዜ በጣም እያነሰ እንደሄደ የዜና ዘገባዎችና አኃዛዊ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህንኑ ችግር የሚያባብስ ሌላ ተጨማሪ ችግር ደግሞ አለ። ብዙ ሴቶች ልጆች ልጅነታቸውን ሳይጠግቡ በአሥራዎቹ ዕድሜ ራሳቸው ወላጆች ይሆናሉ።

ስውር ማኅበራዊ ቀውስ

ለማደጎ የሚሰጡ ልጆች ቁጥር በጣም እየጨመረ መጥቷል። ዊክኤንድ አውስትራሊያን በተባለ ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ርዕሰ አንቀጽ እንዲህ ይላል:- “ለማደጎ በሚሰጡ ልጆች ረገድ አዲስ ችግር እያጋጠመን መጥቷል። በቤተሰብ መፈራረስ ምክንያት አለ አሳዳጊና አለ ተንከባካቢ የሚቀሩ ልጆች ቁጥር በጣም እየጨመረ መጥቷል።” በተጨማሪም ጋዜጣው “ለማደጎ የተሰጡ ብዙ ልጆች ጉዳያቸውን የሚከታተሉላቸው የማኅበራዊ ጉዳይ ሠራተኞች ሳይጠይቋቸው በርካታ ወራት እንዲያውም ዓመታት ያልፋሉ። ሌሎች ደግሞ ቋሚ ቤት ሳያገኙ ከአሳዳጊ ወደ አሳዳጊ ሲዘዋወሩ ይቆያሉ” ብሏል።

በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለ97 አሳዳጊዎች ስለተሰጠች የ13 ዓመት ልጃገረድ ሪፖርት ተደርጓል። በአንዳንዶቹ አሳዳጊዎች ቤት የቆየችበት ጊዜ ከአንድ ምሽት አይበልጥም። በዚያን ጊዜ ምን ያህል ተቀባይነት የማጣትና የሥጋት ስሜት ይሰማት እንደነበረ ታስታውሳለች። እንደ እርሷ ያሉ ለማደጎ የተሰጡ ብዙ ልጆች የልጅነት ጊዜያቸው ባክኖባቸዋል።

በዚህም የተነሳ በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሊቃውንት ልጅነታቸው ስለባከነባቸው ልጆች እየተናገሩ መሆናቸው አያስደንቅም። ወላጅ ከሆንክ እነዚህን አሳዛኝ ሁኔታዎች በመመልከት ለልጆችህ መኖሪያና ለሕይወታቸው የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማቅረብ በመቻልህ ራስህን ዕድለኛ እንደሆንክ አድርገህ ልትቆጥር ትችላለህ። ይሁን እንጂ ሌላም አደጋ አለ። በዛሬው ዓለም የሚያጋጥመው የልጅነት ዕድሜ መባከን ብቻ አይደለም። የልጅነት ዕድሜ አጭር የሚሆንበት ጊዜም አለ። እንዴት እንዲህ ሊሆን ይችላል? ምን ውጤትስ ያስከትላል?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 ስሟ ተለውጧል።