በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጅነት አጭር ሲሆን

ልጅነት አጭር ሲሆን

ልጅነት አጭር ሲሆን

ሰማዩ ጭጋጋማ ነበር። ባለ አንድ ሞተሯ ትንሽ አውሮፕላን ፍጥነቷን እየጨመረች ሄዳ ከማኮብኮቢያው መስመር ብድግ ማለት ጀመረች። በብዙ መገናኛ ብዙኃን የተሰራጨና የበርካታ ካሜራዎችንና ጋዜጠኞችን ትኩረት የሳበ ብዙ ውዳሴ የተዥጎደጎደለት ድርጊት ነበር። ይህን ሁሉ ትኩረት የሳበው ማን ነበር? በአውሮፕላኗ ላይ ተሳፍሮ የነበረው የአውሮፕላን አብራሪም ሆነ ብቸኛው ወንድ መንገደኛ አልነበረም። ይህ ሁሉ ትኩረት ያረፈው አብራቸው በነበረችው የመንገደኛው ሴት ልጅ ላይ ነበር። የሰባት ዓመት ልጅ ነበረች።

አውሮፕላኑን የምታበርረው ትንሿ ልጅ ነች። አንድ ዓይነት ሪኮርድ እንድትሰብርና የወጣላትን ፕሮግራም ሳታዛንፍ እንድትከተል ይጠበቅባት ነበር። በምታርፍበት ቦታ ላይ ጋዜጠኞች አፋቸውን ከፍተው ይጠብቋታል። አየሩ ጭጋጋማ ቢሆንም እንኳ ሦስቱም ወደ አውሮፕላኗ ገቡና ትንሿ ልጅ የበረራ መሣሪያዎቹን ማየት እንድትችል የመቀመጫ ትራስ፣ እግሯ ደግሞ ወለሉ ላይ ደርሶ ፔዳሎቹን መርገጥ እንድትችል የእግር ማራዘሚያ ተደርጎላት ቁጭ አለች።

በረራው የቆየው ለአጭር ጊዜ ነበር። ከባድ የሆነ ድንገተኛ ውሽንፍር መጣና አውሮፕላኗ አቅጣጫዋን እንድትቀይር አደረጋት። በኋላም ከቁጥጥር ውጭ ሆነችና ተከሰከሰች። በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት ሦስቱም ተሳፋሪዎች ሞቱ። መገናኛ ብዙኃን የውዳሴ ቃላት ሳይሆን ሐዘን ማስተጋባት ጀመሩ። ለዚህ አሳዛኝ ክስተት የመገናኛ ብዙኃን እጅ ይኖርበት ይሆን ብለው ያሰቡ ዜና ዘጋቢዎችና ጋዜጣ አዘጋጆች ነበሩ። ብዙ ሰዎች ሕፃናት አውሮፕላን እንዳያበሩ መከልከል አለባቸው ብለው መከራከር ጀመሩ። በዩናይትድ ስቴትስ ይህንኑ የሚከለክሉ ሕጎች ወጡ። ይሁን እንጂ ከነበረው የስሜት መጋጋልና ውጪያዊ መፍትሔ በስተጀርባ ጠለቅ ያሉ አሳሳቢ ጉዳዮች ነበሩ።

ይህ አሳዛኝ ገጠመኝ አንዳንድ ሰዎች በጊዜያችን እየተስፋፋ ስለሄደ አንድ አዝማሚያ በጥሞና እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። በአሁኑ ጊዜ ልጆች ልጅነታቸውን ቶሎ እንዲጨርሱና ገና በልጅነታቸው የትላልቅ ሰዎችን ሥራ እንዲሠሩ ግፊት ይደረግባቸዋል። ይህ ሁኔታ ሁልጊዜ ይህን የመሰለ አሳዛኝ ውጤት ላያስከትል እንደሚችል የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ሥር የሰደደና ዘላቂ የሆነ ውጤት ማስከተሉ አይቀርም። የልጅነት ዕድሜን ከሚያሳጥሩ ምክንያቶች መካከል አንዳንዶቹን እስቲ እንመልከት።

ቶሎ ብሎ ትምህርት መጨረስ

ወላጆች ልጆቻቸው ጥሩ ውጤት ላይ እንዲደርሱ መጓጓታቸው የሚጠበቅ ነገር ነው። ይህ ጉጉታቸው ከመጠን ያለፈ በሚሆንበት ጊዜ ግን ልጆቻቸውን ከመጠን በላይ ሊጫኗቸውና ቶሎ ብለው ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ ሊጠብቁባቸው ይችላሉ። እንዲህ ያለውን አመለካከት የሚያዳብሩት ሳያውቁት ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል ልጆች ከትምህርት ሰዓታቸው ውጭ ስፖርትንና ሙዚቃን ጨምሮ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች እንዲካፈሉ ማድረግ በጣም እየተለመደ መጥቷል። አብዛኛውን ጊዜ የተለዩ አስተማሪዎች ይቀጠሩላቸዋል።

እርግጥ አንድ ልጅ የተፈጥሮ ችሎታውን ወይም ፍላጎቱን እንዲያዳብር ማበረታታት ምንም ስህተት የለውም። ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ ተባብሶ አደገኛ ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል? አንዳንድ ልጆች በትላልቅ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ያህል ጫና በሚያጋጥማቸው ጊዜ ሁኔታው አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው። ታይም መጽሔት እንዲህ ይላል:- “ልጆች በልጅነት ጨዋታዎች ተጠምደው መዋላቸው ቀርቶ ዛሬ የሚጨነቁት የተመደበላቸውን ሥርዓተ ትምህርት ስለማጠናቀቃቸው ሆኗል። በወጣትነት ጉልበት መቦረቅና መሯሯጣቸው ቀርቶ ዛሬ የሚያስቡት ስለ ወደፊት ኑሯቸው ሆኗል።”

አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው በአትሌቲክስ፣ በሙዚቃ ወይም በተዋናይነት ሙያ ተሰማርተው ተደናቂ ሰዎች እንዲሆኑ ይመኛሉ። ልጆቻቸውን ገና ከመወለዳቸው በፊት በአንዳንድ የሙያ መስኮች የተሻለ ዕድል እንዲኖራቸው ልዩ ሥልጠና በሚሰጡ ተቋሞች የሚያስመዘግቡ ወላጆች አሉ። በተጨማሪም አንዳንድ እናቶች ገና በማኅፀን ውስጥ ላሉ ልጆች የሙዚቃ ትምህርት በሚሰጡ “ቅድመ ልደት ዩኒቨርሲቲዎች” ይገባሉ። ይህ ሁሉ የሚደረገው የልጆቹን የአእምሮ እድገት ለማፋጠን ነው።

በአንዳንድ አገሮች ልጆች ገና ስድስት ዓመት ሳይሞላቸው የማንበብና የሂሣብ ችሎታቸው ይገመገማል። እንዲህ ያለው ልማድ የስሜት ቀውስ ያስከትልባቸዋል ተብሎ ተሰግቷል። ለምሳሌ ያህል በመዋዕለ ሕፃናት የሚገኝ ልጅ ፈተና “ወድቀሃል” ሲባል ምን ይሆናል? ዘ ሃሪድ ቻይልድ የተባለው መጽሐፍ ደራሲ የሆኑት ዴቪድ ኤልኪንድ ትምህርት ቤቶች ልጆችን በአንድ የተወሰነ ምድብ ውስጥ ለመመደብ ይቸኩላሉ ብለዋል። ይህንንም የሚያደርጉት ይላሉ ኤልኪንድ ልጆችን በተቀላጠፈ መንገድ ለማስተማር ብለው ሳይሆን በአስተዳደራዊ ምክንያቶች የተነሳ ነው።

ልጆችን አለጊዜያቸው ብቃት ያላቸው ትናንሽ አዋቂ ሰዎች ለማድረግ የሚደረገው ጥረት የሚያስከትለው ጉዳት ይኖራል? ኤልኪንድ ማኅበረሰቡ ልጆች የትላልቅ ሰዎችን ሸክም እንዲሸከሙ ለማስቻል የሚያደርገው ጥረት በእጅጉ አሳስቧቸዋል። እንዲህ ይላሉ:- “በዛሬዎቹ ልጆች ላይ እየጨመረና እየተባባሰ የመጣውን ጫና እንደ ‘ጤናማ’ ነገር አድርገን የመመልከት ዝንባሌ ያለን ይመስላል።” ለልጆች ጤናማ ናቸው ስለሚባሉ ነገሮች ያለን አመለካከት በእርግጥም እየተለወጠ መጥቷል።

አሸናፊ ለመሆን መጣደፍ

ብዙ ወላጆች ልጆቻቸውን በተለይ በስፖርቱ ዓለም ከማሸነፍ የበለጠ ነገር እንደሌለ ማስተማር ተገቢና እንዲያውም አስፈላጊ እንደሆነ ያስባሉ። ዛሬ የኦሎምፒክ ሜዳልያዎች ብዙ ልጆች የሚጓጉላቸው ሽልማቶች ሆነዋል። አንዳንድ ልጆች ለጥቂት ጊዜ በሚቆይ ዝና ለመኩራራትና ጥሩ ኑሮ ለማግኘት ሲሉ የልጅነት ዕድሜያቸውን መሥዋዕት ያደርጋሉ።

ለምሳሌ ያህል የሴት ጅምናስቲክ ሠሪዎችን እንውሰድ። ገና ባልጠነከረ አካላቸው ላይ ከፍተኛ ጫና በሚያሳድር አድካሚ ሥልጠና የሚጠመዱት ከጨቅላነታቸው ጀምሮ ነው። ለኦሎምፒክ ውድድር ለበርካታ ዓመታት አእምሯዊና አካላዊ ዝግጅት ሲያደርጉ ይቆያሉ። አሸናፊ የሚሆኑት በጣም ጥቂቶቹ ብቻ እንደሆኑ የታወቀ ነው። ተሸናፊዎቹ ያን የሚያክል መሥዋዕትነት መክፈላቸው ተገቢ እንደነበረ ሆኖ ይሰማቸዋል? አሸናፊዎቹም ቢሆኑ ውሎ አድሮ ያን የሚያክል መሥዋዕትነት መክፈላቸው ተገቢ እንዳልነበረ ሳይሰማቸው አይቀርም።

እነዚህ ትናንሽ ልጃገረዶች ኮከብ አትሌቶች እንዲሆኑ በሚደርስባቸው ከፍተኛ ግፊት ምክንያት ልጅነታቸው ሳይታወቃቸው ሊያልፍባቸው ይችላል። አካላዊ እድገታቸው ግን እንዲህ ባለው ጠንካራ ልምምድ ምክንያት ሊቀጭጭ ይችላል። አንዳንዶቹ አጥንታቸው የሚገባውን ያህል ሳይዳብር ይቀራል። የአመጋገብ ቀውስም ያጋጥማቸዋል። ብዙውን ጊዜ ለአካለ መጠን የሚደርሱበት ዕድሜ ለበርካታ ዓመታት ይዘገያል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ በርካታ ልጆች የዚህ ተቃራኒ የሆነ ችግር ያጋጥማቸዋል። ገና በትንሽነታቸው ጉርምስና ይጀምራቸዋል።—ከላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።

ከልጅነት ሕይወት በስተቀር ሁሉ ነገር ያላቸው ልጆች

የመዝናኛው ዓለም የሚለውን ካመንክ ጥሩ የልጅነት ሕይወት ማለት ማንኛውንም ዓይነት ቅንጦት አግኝቶ ማደግ ማለት ነው። አንዳንድ ወላጆች የተመቻቸ ቤትን፣ ገደብ የለሽ መዝናኛዎችንና ውድ የሆኑ ልብሶችን ጨምሮ ልጆቻቸው የጠየቋቸውን ሁሉ ለማቅረብ ሲሉ ብዙ ይደክማሉ።

ይሁን እንጂ እንዲህ ባለ ሁኔታ አድገው ጠጪዎች፣ የዕፅ ሱሰኞችና ዓመፀኞች የሆኑ ልጆች ጥቂቶች አይደሉም። ለምን? ብዙዎቹ በቂ ትኩረት ሳይሰጣቸው እንዳደጉ ስለሚሰማቸው በወላጆቻቸው ላይ ከፍተኛ ቅሬታ ያሳድራሉ። ልጆች ወላጆቻቸው አጠገባቸው ሆነው ፍቅራቸውን እንዲገልጹላቸውና እንዲንከባከቧቸው ይፈልጋሉ። ይህን ለማድረግ ጊዜ የሚያጡ ወላጆች ጊዜ ያጣነው ልጆቻችንን ለማስደሰት ስንል ነው ይሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ የሚያደርጉት የዚህን ተቃራኒ ሊሆን ይችላል።

ዶክተር ጁዲት ፓፋዚ “ጥሩ የኑሮ ደረጃ ያላቸውና ሁለቱም ሥራ ውለው የሚገቡ ወላጆች ልጆቻቸውን የሚያንቀባርሩት ገንዘብ ለማግኘት የሚያደርጉት ልፋት ቤተሰባቸውን እንደሚጎዳ ስለሚሰማቸው ነው” ብለዋል። በእርሳቸው አመለካከት እንደነዚህ ያሉ ወላጆች “የወላጅነት ኃላፊነታቸውን በገንዘብ ለማካካስ ይሞክራሉ።”

አብዛኛውን ጊዜ ልጆቹ ከፍተኛ ጉዳት ይደርስባቸዋል። በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ብዙ የቅንጦች ዕቃዎች ሊኖሯቸው ቢችልም ለጥሩ የልጅነት ሕይወት አስፈላጊ የሆኑት የወላጆች ጊዜና ፍቅር ይጎድልባቸዋል። ጥሩ አመራር፣ ምክርና ሥልጠና ሳያገኙ ስለሚያድጉ በቂ ዝግጅት ሳይኖራቸው ትላልቅ ሰዎች የሚያጋጥሟቸው ጥያቄዎች ያፋጥጧቸዋል። ‘ዕፅ ልውሰድ? ወሲብ ልፈጽም? ስናደድ ልደባደብ?’ እንደሚሉ ያሉ ጥያቄዎች ያጋጥሟቸዋል። የራሳቸውን መልስ ከእኩዮቻቸው ወይም ከቴሌቪዥን አሊያም ከፊልም ለማግኘት ይገደዳሉ። የዚህ ውጤት አብዛኛውን ጊዜ ልጅነትን በአሳዛኝ ገጠመኝ የሚያስጨርስ ይሆናል።

የትልቅ ሰውን ቦታ መውሰድ

ቤተሰብ ድንገት በፍቺ፣ በመለያየት ወይም በሞት ምክንያት በአንድ ወላጅ ብቻ የሚተዳደር በሚሆንበት ጊዜ በልጆች ላይ ስሜታዊ ችግር ይፈጠራል። እርግጥ የተሳካ ኑሮ የሚመሩ በአንድ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች አሉ። በአንዳንድ ቤተሰቦች ግን ልጆቹ ልጅነታቸውን ሳይጨርሱ የትልቅ ሰው ቀንበር ለመሸከም ይገደዳሉ።

ቤተሰቡን ለብቻው የሚያስተዳድር አንድ ወላጅ የብቸኝነት ስሜት ሊያጠቃው ይችላል። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ወላጆች ልጃቸው በተለይም የመጀመሪያው ልጅ የሌላውን ወላጅ ቦታ እንዲተካ ያደርጋሉ። ወላጅየው የሚያደርገው ሲጠፋው ወንድ ወይም ሴት ልጁን ምሥጢረኛው በማድረግ ልጁ ሊሸከም የማይችለውን ሸክም ይጭንበታል። አንዳንድ ነጠላ ወላጆች ከሚገባው በላይ የልጆቻቸውን እርዳታ ይፈልጋሉ።

ሌሎች ወላጆች ደግሞ ኃላፊነታቸውን ሙሉ በሙሉ እርግፍ አድርገው በመተው ልጃቸው የእነርሱን ቦታ እንዲይዝ ያደርጋሉ። ቀደም ብለው የተጠቀሱት ካርመንና እህቷ የጎዳና ሕይወት የመረጡት እንዲህ ካለው ሁኔታ ለማምለጥ ብለው ነበር። ገና ልጆች ሳሉ ታናናሾቻቸውን የማሳደግ ቀንበር ተጫነባቸው። ይህ ሊሸከሙት የማይችሉት ቀንበር ነበር።

በእርግጥም ልጆች ገና በለጋ ዕድሜያቸው ብዙ ቀንበር እንዲሸከሙ የማድረግ ልማድ በተቻለ መጠን ሊወገድ ይገባዋል። ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ አንድ ጥሩ የምሥራች አለ። ወላጆች ልጃቸው በልጅነት ዕድሜው ቦርቆ እንዲያድግ የሚያስችሉ አዎንታዊ እርምጃዎች ሊወስዱ ይችላሉ። እነዚህ እርምጃዎች ምንድን ናቸው? ባለፉት ዘመናት ሁሉ እውነት ሆነው የተገኙትን አንዳንድ እርምጃዎች እንመልከት።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ከዕድሜ በፊት መጎርመስ የሚያስከትለው ችግር

በአሁኑ ጊዜ ሴት ልጆች ከዕድሜያቸው በፊት እየጎረመሱ ነው? ለሳይንቲስቶች ይህ አወዛጋቢ ጉዳይ ሆኖባቸዋል። አንዳንዶች በ19ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ ሴት ልጆች ለጉርምስና የሚደርሱበት ዕድሜ በአማካይ 17 ዓመት ሲሆን ዛሬ ግን ከ13 ዓመት በታች እንደሆነ ይናገራሉ። በ1997 በዩናይትድ ስቴትስ 17,000 በሚያክሉ ሴት ልጆች ላይ የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው 15 በመቶ የሚሆኑት ነጭ አሜሪካውያን ልጃገረዶች እንዲሁም 50 በመቶ የሚሆኑት ጥቁር አሜሪካውያን ልጃገረዶች በስምንት ዓመት ዕድሜያቸው ላይ አንዳንድ የጉርምስና ምልክቶች ታይተውባቸዋል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ዶክተሮች ወላጆች በጣም የቀደመ እድገት “ጤናማ” ነው ብለው እንዳይቀበሉ ያስጠነቅቃሉ።

ያም ሆነ ይህ ሁኔታው በወላጆችም ሆነ በልጆች ላይ የሚፈጥረው ችግር አለ። ታይም መጽሔት የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል:- “ከዕድሜያቸው በፊት የሚጎረምሱ ልጆች ከሚያጋጥማቸው አካላዊ ለውጥ ይበልጥ አሳሳቢ የሚሆነው የተረት መጻሕፍት ከማንበብ ያልወጡ ሕፃናት ተኩላዎችን ለመከላከል መገደዳቸው የሚያስከትልባቸው ሥነ ልቦናዊ ችግር ነው። . . . የልጅነት ዕድሜ በራሱ በጣም አጭር ነው።” ይኸው ጽሑፍ የሚከተለውን አሳሳቢ ጥያቄ ያነሳል:- “የወጣት ልጃገረዶች አካል ልባቸውና አእምሮአቸው ከመዘጋጀቱ በፊት ትልቅ ሰው የሚያስመስላቸው ከሆነ ምን ዓይነት ዘላቂ ኪሣራ ይደርስባቸዋል?”

አብዛኛውን ጊዜ ለወሲብ መጠቀሚያ በሚያደርጓቸው ሰዎች ንጽሕናቸው ይደፈራል። አንዲት እናት ግልጹን ስትናገር “አለዕድሜያቸው ትልቅ መስለው የሚታዩ ልጃገረዶች [ለንቦች] እንደማር ናቸው። በዕድሜ ትላልቅ የሆኑ ወንዶች ልጆችን ይስባሉ” ብላለች። ገና በልጅነት ዕድሜ በግፊት ወሲብ መፈጸም የሚያስከትለው ኪሣራ በጣም ከፍተኛ ነው። አንዲት ወጣት ልጃገረድ ለራሷ ያላትን አክብሮት፣ ንጹሕ ሕሊናዋን እንዲሁም አካላዊና ስሜታዊ ጤንነቷን ጭምር ልታጣ ትችላለች።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆች በብዙ ፕሮግራሞች እንዲጣበቡ ማድረግ ችግር እንዲደርስባቸው ሊያደርግ ይችላል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በልጆች ውስጥ የፉክክር መንፈስ መትከል ከስፖርትና ከጨዋታዎች ደስታ እንዳያገኙ ሊያደርጋቸው ይችላል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቁሳዊ ነገሮችን በገፍ ማቅረብ ለጥሩ ወላጅነት ማካካሻ አይሆንም