በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ብነቀስ ምን አለበት?

ብነቀስ ምን አለበት?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

ብነቀስ ምን አለበት?

“አንዳንድ ንቅሳቶች ያምራሉ። ዓይን የሚስብ ውበት አላቸው።”ጄሊን *

“ከመነቀሴ በፊት ለሁለት ዓመት ያህል ሕልሜ ይኸው ነበር።”—መሼል

ንቅሳት ተወዳጅ ነገር የሆነ ይመስላል። የሮክ አቀንቃኞች፣ ታዋቂ ስፖርተኞች፣ የፋሽን ሞዴሎችና የፊልም ተዋንያን የሰውነት ንቅሳቶቻቸውን በኩራት ያሳያሉ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ብዙ ወጣቶችም እነርሱን በመኮረጅ በትከሻቸው፣ በእጆቻቸው፣ በወገባቸውና በቁርጭምጭሚታቸው ላይ በመነቀሳቸው ይኩራራሉ። አንድሩ “ንቅሳት የዘመናዊነት ምልክት ነው። መነቀስ አለመነቀስ የግል ምርጫ ነው” በማለት ተናግሯል።

ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዳለው “ንቅሳት በገላ ላይ የማይጠፋ ምልክት የማበጀት ልማድ ነው። ንቅሳት የሚከናወነው ተፈጥሮአዊ ማቅለሚያ በተነከረ እሾህ፣ ሹል አጥንት ወይም መርፌ ቆዳን በመጨቅጨቅ ነው።”

ትክክለኛ አኃዛዊ መረጃ ማሰባሰብ አስቸጋሪ ቢሆንም በዩናይትድ ስቴትስ ከሚኖሩ ከ15 እስከ 25 ዓመት ያሉ ወጣቶች ውስጥ 25 በመቶዎቹ ንቅሳት እንዳላቸው አንድ ምንጭ ገምቷል። ሳንዲ “ንቅሳት ከፍተኛ ተወዳጅነት ያለው ነገር ነው” ትላለች። አንዳንድ ወጣቶች ንቅሳትን ይህን ያህል የሚወድዱት ለምንድን ነው?

ንቅሳት ተወዳጅ የሆነው ለምንድን ነው?

አንዳንድ ወጣቶች የሚነቀሱት አንድን ሰው ምን ያህል እንደሚወዱት ለመግለጽ ነው። መሼል “ወንድሜ በቁርጭምጭሚቱ ላይ ጓደኛው የነበረችውን ልጃገረድ ስም አስነቅሶ ነበር” ትላለች። ይህ ምን ችግር አስከተለ? “አሁን ግንኙነታቸው ተቋርጧል።” ቲን የተባለው መጽሔት እንደገለጸው “ንቅሳታቸውን ለማጥፋት ከሚመጡ ሰዎች መካከል ከ30 በመቶ የሚበልጡት የቀድሞ የወንድ ጓደኛቸውን ስም ለማጥፋት የሚፈልጉ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ልጃገረዶች ናቸው።”

አንዳንድ ወጣቶች ንቅሳት የሚያምር ጌጥ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሌሎች ደግሞ በራስ የመመራት መግለጫ እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩታል። ጆዚ “ሕይወቴን የምመራው ራሴ ነኝ” ትላለች። አክላም መነቀስ “በሕይወቴ ያደረግሁት የመጀመሪያው ትልቅ ውሳኔ ነው” ብላለች። አንዳንድ ወጣቶች መነቀስ አዲስ ነገር የመሞከር አጋጣሚ እንደሚሰጣቸው ይሰማቸዋል። በመሆኑም በሰውነታቸው ላይ የፈለጉትን ማድረግ እንደሚችሉ ሞክረው ማየት ይፈልጋሉ። ንቅሳት የዓመፀኝነት ወይም ለየት ያለ አኗኗር መግለጫ በመሆንም ሊያገለግል ይችላል። በመሆኑም አንዳንድ ንቅሳቶች ጸያፍ ቃላትና ሥዕሎች ወይም የሌሎችን ስሜት የሚጎዱ አባባሎች የያዙ ናቸው።

ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ወጣቶች የሚነቀሱት እንዲሁ ፋሽን ስለሆነ ብቻ ነው። ታዲያ ሰው ሁሉ እየተነቀሰ ነው በሚል ብቻ አንተም መነቀስ ይኖርብሃል?

ጥንታዊ ልማድ የሆነው ንቅሳት

መነቀስ በዚህ ዘመን የተጀመረ ልማድ እንዳልሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። ከክርስቶስ ልደት በፊት በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት አስቀድሞ የነበሩ በመድኃኒት ተጠብቀው የቆዩ ንቅሳት ያለባቸው አስከሬኖች በግብፅና በሊቢያ ተገኝተዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ የተጠበቁ ንቅሳት ያለባቸው አስከሬኖች በደቡብ አሜሪካም ተገኝተዋል። ንቅሳት ያለባቸው ብዙዎቹ ምስሎች ከአረማውያን የጣዖት አምልኮ ጋር በቀጥታ የተያያዙ ነበሩ። እስቲቭ ጊልበርት የተባሉ ተመራማሪ እንደገለጹት “በጥንታዊነቱ የሚታወቀው ንቅሳት ግልጽ ያልሆነ ንድፍ ሳይሆን የአንድን ነገር ምስል የያዘ ማለትም ቤስ የተባለውን ጣዖት የሚወክል ነው። በግብፃውያን አፈ ታሪክ መሠረት ቤስ የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ የፈንጠዝያ አምላክ ነው።”

የሙሴ ሕግ የአምላክን ሕዝቦች እንዳይነቀሱ የከለከላቸው መሆኑ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ነው። ዘሌዋውያን 19:28 “ስለ ሞተውም ሥጋችሁን አትንጩ፣ ገላችሁንም አትንቀሱት፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ” ይላል። እንደ ግብፃውያን ያሉ አረማውያን አምላኪዎች የአማልክቶቻቸውን ስም አለዚያም ምስል በጡታቸው ወይም በእጆቻቸው ላይ ያስነቅሱ ነበር። እስራኤላውያን ይሖዋ የሰጣቸውን እንዳይነቀሱ የሚከለክለውን ሕግ በማክበር ከሌሎች አሕዛብ የተለዩ ሆነው ይታዩ ነበር።—ዘዳግም 14:1, 2

በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር ባይሆኑም በንቅሳት ላይ የተጣለውን እገዳ በቁም ነገር ሊመለከቱት ይገባል። (ኤፌሶን 2:15፤ ቆላስይስ 2:14, 15) ክርስቲያን ከሆንክ በገላህ ላይ ከአረማዊ እምነት ወይም ከሐሰት አምልኮ ጋር የሚዛመዱ ምልክቶችን ለጊዜውም ቢሆን ማድረግ እንደማትሻ የታወቀ ነው።—2 ቆሮንቶስ 6:15-18

ንቅሳት በጤና ላይ የሚያስከትለው ጠንቅ

ልታስብበት የሚገባው ሌላው ነገር በጤና ላይ የሚያስከትለው ጠንቅ ነው። የቆዳ ሕክምና ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ሮበርት ቶምሲክ እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “ንቅሳት ሲባል ቆዳን እየበሱ ማቅለም ማለት ነው። መርፌው ወደ ውስጥ ዘልቆ ባይገባም ቆዳችሁ የተበሳበት ቦታ ሁሉ በባክቴሪያ ወይም በቫይረስ ለሚመጡ በሽታዎች ሊጋለጥ ይችላል። በአጠቃላይ ሲታይ [መነቀስ] የሚያስከትለው ጠንቅ ያለ ይመስለኛል።” ዶክተር ቶምሲክ በመቀጠል “ከተነቀሳችሁ በኋላ በባክቴሪያ ወይም በቫይረስ በሚመጡ በሽታዎች ባትያዙም እንኳ ቆዳችሁ እንዲቀላ፣ እንዲያብጥና እንዲገለፈፍ እንዲሁም እንዲያሳክካችሁ የሚያደርግ የቆዳ ሽፍታ፣ ሕመምና መቆጣት መከሰቱ አይቀርም” ብለዋል።

ንቅሳቶች ዘላቂ እንዲሆኑ ታስበው የሚደረጉ ቢሆንም ለማስለቀቅ በሚደረግ ጥረት የሚሠራባቸው የተለያዩ ዘዴዎች አሉ። እነዚህም ንቅሳቱን በጨረር ማቃጠል፣ በቀዶ ሕክምና ማስወገድ፣ በሽቦ ብሩሽ የተነቀሰውን ቆዳ ፈግፍጎ ማስወገድ፣ የተነቀሰውን ቆዳ በጨዋማ ፈሳሽ መዘፍዘፍና ንቅሳቱን በፈሳሽ አሲድ አጥፍቶ ቦታው ጠባሳ እንዲሆን ማድረግ ናቸው። እነዚህ ዘዴዎች ብዙ ወጪ የሚጠይቁና ሥቃይ የሚያስከትሉ ናቸው። ቲን የተባለው መጽሔት እንደገለጸው “ንቅሳቱን በጨረር ማስወገድ ከመነቀሱ ይበልጥ ያሳምማል።”

ሰዎች ለእናንተ የሚኖራቸው ግምት

ብዙ ሰዎች ለንቅሳት ጥሩ አመለካከት ስለሌላቸው መነቀሳችሁ በሌሎች ላይ ስለሚያሳድረው ስሜትም ማሰብ ይኖርባችኋል። (1 ቆሮንቶስ 10:29-33) በታይዋን የምትኖር ሊ የተባለች አንዲት ወጣት በስሜት ተነሳስታ በ16 ዓመቷ ተነቀሰች። አሁን 21 ዓመቷ ሲሆን የቢሮ ሠራተኛ ናት። “የሥራ ባልደረቦቼ ንቅሳቴን ትኩር ብለው ሲያዩት እሸማቀቃለሁ” በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች። የአእምሮ ጤና ባለሙያ የሆኑት ብሪታኒያዊው ቴዎዶር ዳልሪምፐል እንደተናገሩት ለብዙ ሰዎች ንቅሳት “አንድ ሰው . . . የአንድ ዓመፀኛ፣ ጨካኝ፣ ፀረ ኅብረተሰብና ወንጀለኛ ቡድን አባል እንደሆነ የሚያሳይ ምልክት ነው።”

አሜሪካን ዲሞግራፊክስ በተሰኘው መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስም በተመሳሳይ እንዲህ ይላል:- “ብዙዎቹ አሜሪካውያን በሚታይ ንቅሳት ማጌጥን ችግር እንደሚያስከትል ነገር አድርገው እንደሚቆጥሩት ግልጽ ነው። 85 በመቶ የሚሆኑት [ወጣቶች] ‘በሚታይ የሰውነት ክፍል ላይ ንቅሳት ያላቸው ሰዎች . . . ማንነታቸውን ለማሳወቅ የሚያደርጉት እንዲህ ዓይነቱ ጥረት በሥራቸው ወይም ከሰዎች ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ላይ እንቅፋት እንደሚፈጥር መገንዘብ ይኖርባቸዋል’ በሚለው አባባል ይስማማሉ።”

ክርስቲያን እንደመሆንህ መጠን፣ ንቅሳት ምን ዓይነት ስም ሊያተርፍልህ እንደሚችል አስብበት። ለሌሎች “ማሰናከያ” ሊሆን ይችል ይሆን? (2 ቆሮንቶስ 6:3) እርግጥ አንዳንድ ወጣቶች የሚነቀሱት ልብሳቸውን ካላወለቁ በስተቀር በማይታዩ የሰውነታቸው ክፍሎች ላይ ነው። በማይታይ ቦታ ላይ ስላሉት ስለ እነዚህ ንቅሳቶች ወላጆቻቸው እንኳን ላያውቁ ይችላሉ። ሆኖም ማንም አያውቅብኝም ብለህ አታስብ! ድንገተኛ ሁኔታ አጋጥሞህ ሐኪም ዘንድ ብትቀርብ ወይም ከስፖርት ክፍለ ጊዜ በኋላ በትምህርት ቤት መታጠቢያ ክፍል ገላህን ስትታጠብ ምሥጢሩ ገሃድ ሊወጣ ይችላል። ራስን ከማታለል ይልቅ ‘በነገር ሁሉ በሐቀኝነት መኖር’ የተሻለ ነው።—ዕብራውያን 13:18 NW

እንደ ማንኛውም ፋሽን ሁሉ ንቅሳቶችም ከጊዜ በኋላ ማራኪነታቸውን ሊያጡ ይችላሉ። በጣም የምትወዱትን ልብስ ለምሳሌ ጂንስ ሱሪ፣ ሸሚዝ ወይም ቀሚስ አሊያም ጫማ ዕድሜ ልካችሁን ለመልበስ ወይም ለማድረግ ትወስናላችሁ? እንደማታደርጉት የታወቀ ነው! የልብስ ፋሽኖች፣ ስፌቶችና ተወዳጅ የቀለም ዓይነቶች ይለወጣሉ። ንቅሳቶች ግን እንደ ልብስ በቀላሉ አይወገዱም። ከዚህም በላይ የ16 ዓመት ልጅ እያላችሁ ትወድዱት የነበረው ነገር 30 ዓመት ሲሆናችሁ የማይማርክ ሊሆንባችሁ ይችላል።

በሰውነታቸው ላይ ዘላቂ ለውጥ ያደረጉ ብዙ ሰዎች የኋላ ኋላ ተጸጽተዋል። ኤሚ እንዲህ ትላለች:- “የተነቀስኩት ይሖዋን ከማወቄ በፊት ነበር። በልብሴ ልደብቀው እሞክራለሁ። በጉባኤው ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ንቅሳቴን ድንገት ሲያዩት አፍራለሁ።” ነጥቡ ምንድን ነው? ከመነቀስህ በፊት ጉዳዩን በጥሞና አስብበት። የኋላ ኋላ የምትጸጸትበት ውሳኔ አታድርግ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ንቅሳት ያላቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ እንደ ዓመፀኛ ተደርገው ይቆጠራሉ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙ ሰዎች መነቀሳቸው የኋላ ኋላ ይጸጽታቸዋል

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከመነቀስህ በፊት ጉዳዩን በጥሞና አስብበት