በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ሀብት በመስጠት ይባርከናል?

አምላክ ሀብት በመስጠት ይባርከናል?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

አምላክ ሀብት በመስጠት ይባርከናል?

“የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች፣ ኀዘንንም ከእርስዋ ጋር አይጨምርም።”—ምሳሌ 10:22

ከላይ የተጠቀሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አምላክ አገልጋዮቹን ቁሳዊ ሀብት በመስጠት እንደሚባርካቸው ያሳያል? እንዲህ ብለው የሚያምኑ አንዳንድ ሰዎች አሉ። አንድ አውስትራሊያዊ የጰንጠቆስጤ እምነት ሰባኪና ደራሲ ምን እንዳሉ ተመልከት:- “በመጽሐፌ ላይ ተጨማሪ ገንዘብ የሚያስፈልጋችሁ ለምን እንደሆነና ተጨማሪ ገንዘብ እንዴት ማግኘት እንደምትችሉ እገልጽላችኋለሁ። . . . አስተሳሰባችሁን መለወጥ ከቻላችሁና ለገንዘብ ተገቢውን አመለካከት ካዳበራችሁ በአምላክ በረከትና ብልጽግና ስለምትኖሩ ዳግመኛ የገንዘብ ችግር እንደማይገጥማችሁ አምናለሁ።”

ይሁንና እንዲህ ብሎ መናገር አምላክ ድሆችን አልባረከም ከማለት ተለይቶ አይታይም። ቁሳዊ ብልጽግና በእርግጥ አምላክ እንደባረከን የሚያሳይ ነው?

አምላክ አንዳንድ ሰዎችን የባረከበት ምክንያት

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹን ሀብት በመስጠት እንደባረካቸው የሚገልጹ ታሪኮችን ይዟል። ለምሳሌ ያህል ያዕቆብ ከቤተሰቡ ተለይቶ ሲሄድ በትሩን ብቻ ይዞ እንደወጣና ከ20 ዓመታት በኋላ በሁለት ወገን ከተከፈሉ ብዙ በጎች፣ ከብቶችና አህዮች ጋር እንደተመለሰ ተገልጿል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው የያዕቆብ ብልጽግና ከአምላክ ያገኘው ስጦታ ነበር። (ዘፍጥረት 32:10) ሌላው ምሳሌ ኢዮብ ሲሆን ንብረቱን ሁሉ አጥቶ ነበር። ይሖዋ ግን በኋላ “አሥራ አራት ሺህም በጎች፣ ስድስት ሺህም ግመሎች፣ አንድ ሺህም ጥማድ በሬዎች፣ አንድ ሺህም እንስት አህዮች” በመስጠት ባርኮታል። (ኢዮብ 42:12) ይሖዋ ለንጉሥ ሰሎሞንም ዝናው እስከዛሬ ያልጠፋ ከፍተኛ ሀብት ሰጥቶታል።—1 ነገሥት 3:13

በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ድሃ የነበሩ የብዙ ታማኝና ታዛዥ የአምላክ አገልጋዮችን ታሪክ ይዟል። እርግጥ አምላክ አንዳንዶቹን በብልጽግና ሲባርክ ሌሎችን በድህነት እየቀጣቸው አልነበረም። ታዲያ አምላክ አንዳንድ ሰዎችን ሀብት በመስጠት የባረከበት ዓላማ ምን ነበር?

መልሱ እንደየሁኔታው የተለያየ ነው። ያዕቆብ በቁሳዊ ሀብት መባረኩ ተስፋ የተገባው መሲሕ የሚመጣበትን ብሔር ለማደራጀት የሚያስችል መሠረት ጥሏል። (ዘፍጥረት 22:17, 18) የኢዮብ ብልጽግና መከራ ያመጣበት ማን እንደሆነ በግልጽ ያመላከተ ስለነበር የይሖዋን ስም አስቀድሷል። (ያዕቆብ 5:11) ሰሎሞንም በአምላክ እርዳታ ካገኘው ሀብት ውስጥ አብዛኛውን ዕጹብ ድንቅ የሆነ ቤተ መቅደስ ለመገንባት ተጠቅሞበታል። (1 ነገሥት 7:47-51) ትኩረት የሚያሻው ሌላው ጉዳይ ግን ሰሎሞን ሀብት ያለው ጥቅም ውስን መሆኑን ከግል ተሞክሮው በመነሳት እንዲጽፍ ይሖዋ የተጠቀመበት መሆኑ ነው።—መክብብ 2:3-11፤ 5:10፤ 7:12

አምላክ እኛን የሚባርከን እንዴት ነው?

ኢየሱስ ተከታዮቹ መሠረታዊ ስለሆኑ ነገሮች ‘እንዳይጨነቁ’ በነገራቸው ጊዜ ስለ ገንዘብ ጤናማ አመለካከት እንዲኖራቸው አስተምሯቸዋል። ሰሎሞን እንኳን ያን ያህል ክብር ኖሮት የሜዳ አበቦችን ያህል እንዳልለበሰ አስረዳቸው። ሆኖም ኢየሱስ “እግዚአብሔር ግን . . . የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፣ እናንተ እምነት የጎደላችሁ እናንተንማ ይልቁን እንዴት?” ብሏል። ኢየሱስ ተከታዮቹ መንግሥቱንና ጽድቁን ካስቀደሙ የሚያስፈልጋቸውን ምግብ፣ ልብስና መጠለያ እንደሚያገኙ ለክርስቲያኖች ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 6:25, 28-33) ኢየሱስ የሰጠው ይህ ተስፋ የሚፈጸመው እንዴት ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር መከተል በተለይ መንፈሳዊ በረከቶችን ያስገኛል። (ምሳሌ 10:22) ይሁን እንጂ ሌላ ጥቅምም አለው። ለምሳሌ ያህል የአምላክ ቃል ክርስቲያኖችን “የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፣ . . . በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም” በማለት ያዛቸዋል። (ኤፌሶን 4:28) በተጨማሪም “የታካች እጅ ችግረኛ ታደርጋለች፤ የትጉ እጅ ግን ባለጠጋ ታደርጋለች” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 10:4) ይህን ምክር የሚከተሉ ሐቀኞችና ታታሪ ክርስቲያኖች ብዙውን ጊዜ በሥራው መስክ ተፈላጊነት አላቸው። ይህም በረከት ሊሆን ይችላል።

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ስግብግብነትን የሚያንጸባርቅ የጊዜ ማሳለፊያ ከሆነው ከቁማር፣ ሰውነትን ከሚያረክሰው ሲጋራ የማጨስ ሱስና በጣም ጎጂ ከሆነው የመጠጥ ሱስ እንዲርቁ ያስተምራል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ 2 ቆሮንቶስ 7:1፤ ኤፌሶን 5:5) ይህን ምክር ተግባራዊ የሚያደርጉ ሁሉ ወጪያቸው የሚቀንስ ከመሆኑም በላይ ጤንነታቸውም ይሻሻላል።

ከብር ወይም ከወርቅ የላቀ ዋጋ ያለው ነገር

የሆነ ሆኖ ቁሳዊ ብልጽግናን ብቸኛው የአምላክ ድጋፍና በረከት መግለጫ አድርጎ በማሰብ ትምክህት ሊጣልበት አይችልም። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ “ሀብታም ነኝና ባለጠጋም ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም የምትል ስለሆንህ፣ ጎስቋላና ምስኪንም ድሃም ዕውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ” በማለት በሎዶቅያ ጉባኤ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች አስከፊ በሆነ መንፈሳዊ ድህነት እንደተጠቁ አጋልጧል። (ራእይ 3:17) በተቃራኒው ደግሞ በቁሳዊ ድሃ ቢሆኑም ጥሩ መንፈሳዊ ሁኔታ ለነበራቸው በሰምርኔስ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ኢየሱስ “መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ፣ ነገር ግን ባለ ጠጋ ነህ” ብሏቸዋል። (ራእይ 2:9) እነዚህ ክርስቲያኖች በታማኝነት አቋማቸው ምክንያት አሳዳጆቻቸው ለገንዘብ ችግር ዳርገዋቸው ሊሆን ቢችልም ከብርና ከወርቅ እጅግ የላቀ ዋጋ ያለው ሀብት አግኝተዋል።—ምሳሌ 22:1፤ ዕብራውያን 10:34

ይሖዋ አምላክ ፈቃዱን ለማድረግ የሚጣጣሩ ሰዎችን ይባርካል። (መዝሙር 1:2, 3) መከራን ለመቋቋም፣ ለቤተሰቦቻቸው የሚያስፈልገውን ለማቅረብና መንግሥቱን ለማስቀደም የሚያስችላቸውን ጥንካሬና የገቢ ምንጭ ይሰጣቸዋል። (መዝሙር 37:25፤ ማቴዎስ 6:31-33፤ ፊልጵስዩስ 4:12, 13) በመሆኑም እውነተኛ ክርስቲያኖች አምላክ በዋነኝነት የሚባርካቸው ቁሳዊ ነገሮችን በመስጠት እንደሆነ አድርገው ከማሰብ ይልቅ “በበጎ ሥራ ባለጠጎች” ለመሆን ይጣጣራሉ። ክርስቲያኖች ከፈጣሪ ጋር የቅርብ ዝምድና በመመሥረት “ለሚመጣውም ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ” ይሰበስባሉ።—1 ጢሞቴዎስ 6:17–19፤ ማርቆስ 12:42-44