በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

አዎንታዊ አመለካከት ዕድሜ ያስረዝማል

አንድ በቅርቡ የተጠናቀቀ ጥናት ስለ ሕይወትና እርጅና ይበልጥ አዎንታዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች “ያነሰ አዎንታዊ አመለካከት ካላቸው ሰዎች የበለጠ 7.5 ዓመት እንደሚኖሩ” ማረጋገጡን ጆርናል ኦቭ ፐርሰናሊቲ ኤንድ ሶሻል ሳይኮሎጂ በተባለ መጽሔት ላይ የወጣ የጥናት ጽሑፍ ገልጿል። 660 በሚያክሉ 50 ዓመትና ከዚያ በላይ በሆናቸው ሰዎች ላይ ለ23 ዓመታት የተደረገው ይህ ጥናት ሁለት ነገሮችን ማለትም ስለ እርጅና አዎንታዊ አመለካከት አለመያዝ “ዕድሜ ሊያሳጥር” እንደሚችልና አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ደግሞ “ዕድሜ ሊያስረዝም እንደሚችል” ሊያረጋግጥ ችሏል። እንዲያውም አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ከተስተካከለ የኮሌስትሮል መጠንና የደም ግፊት ይበልጥ ለዕድሜ መርዘም አስተዋጽኦ ያደርጋል። ጽሑፉ ኅብረተሰቡ አረጋውያንን በተለያዩ እንቅስቃሴዎች በማሳተፍና “አፍራሽ ለሆኑ የእርጅና አመለካከቶች ብዙ ግምት ባለመስጠት” ይበልጥ አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረው በመምከር አስተያየቱን ደምድሟል።

ጊዜ ማብቃቃት

በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት “ጊዜ የለኝም እያሉ የሚያማርሩ ሰዎች ራሳቸውን ያታልላሉ” ከሚል መደምደሚያ ላይ እንደደረሰ ዘ አውስትራሊያን ዘግቧል። ጋዜጣው የኒው ሳውዝ ዌልስ ዩኒቨርሲቲና የአውስትራሊያ ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ ያደረጉትን ጥናት በመጥቀስ “ብዙዎቻችን በመሥሪያ ቤታችንና በቤታችን በሥራ የምናሳልፈው ጊዜ ከሚያስፈልገው በላይ ብዙ ነው” ብሏል። ተመራማሪዎቹ ልጅ የሌላቸው ሠራተኛ ባልና ሚስቶች ለሕይወት የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ብቻ ለማግኘት ምን ያህል ሰዓት መሥራት እንደሚኖርባቸው አስልተዋል። ከዚያም እነርሱ አስልተው ያገኙትን የጊዜ መጠን እነዚህ ባልና ሚስቶች በሥራ ከሚያሳልፉት ጊዜ ጋር አወዳደሩ። ሥራ የሚውሉና ልጅ የሌላቸው ባልና ሚስቶች “በሳምንት ውስጥ 79 ሰዓት በሥራ ቦታ፣ 37 ሰዓት በቤት ውስጥ ሥራና 138 ሰዓት ለገዛ ሰውነታቸው እንክብካቤ በማድረግ ያሳልፋሉ። ይሁን እንጂ በሳምንት ውስጥ በሥራ ቦታ መሥራት የሚያስፈልጋቸው 20 ሰዓት (እያንዳንዳቸው 10 ሰዓት)፣ ቤት ውስጥ ደግሞ 18 ሰዓት እንዲሁም ለግል ሰውነታቸው እንክብካቤ ለማድረግ የሚያስፈልጋቸው 116 ሰዓት ብቻ ነው” ይላል ጋዜጣው። አንድ ባልና ሚስት ኑሯቸውን ቢያቀልሉና በሥራ የሚያሳልፉትን ጊዜ ቢቀንሱ በሳምንት 100 ሰዓት የሚያክል ነጻ ጊዜ ያገኙ ነበር። ዘ አውስትራሊያን እንደገለጸው ጥናቱ ልጅ የሌላቸው ሠራተኛ ባልና ሚስቶች “ከማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ያነሰ የጊዜ ችግር ያለባቸው እነርሱ ሆነው ሳለ ጊዜ በጣም እንደሚያጥራቸው ሆኖ የሚሰማቸውም እነርሱ ናቸው” ብሏል።

የቤተሰብ መፈራረስ የቤት እጥረት አስከተለ

በዩናይትድ ስቴትስ፣ የሚቺጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ በሆኑት በዶክተር ጅያንጉ ሊው የተመራ አንድ አለም አቀፋዊ ጥናት የሕዝብ ብዛት እየቀነሰ በሚገኝባቸው አገሮች ሳይቀር ቤተሰቦች በመፈራረሳቸውና ልጆች ጎጆ በመውጣታቸው ምክንያት የአባወራዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። ለእነዚህ ሁሉ በቂ መኖሪያ ቤት ለማግኘት ሲባል ከተሞች አለ ልክ እየሰፉና በአካባቢ ደህንነት ላይ ትልቅ ውድመት እየደረሰ መጥቷል። “ለምሳሌ ያህል አንድ ባለ ሦስት መኝታ ቤት ሕንጻ የሁለት ሰዎች መኖሪያም ሆነ የአራት የሚፈልገው የግንባታ ዕቃና ቦታ እንዲሁም የሚፈጀው ማገዶ ያው እኩል ነው” ይላል ኒው ሳይንቲስት። ተመራማሪዎቹ ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ እስከ 2015 ድረስ 233 ሚሊዮን የሚያክሉ ተጨማሪ አባወራዎች እንደሚኖሩ ተንብየዋል።

ኮረዳ እናቶች

በሜክሲኮ ከ10 እስከ 19 ባለው የዕድሜ ክልል የሚያረግዙ ሴቶች ቁጥር “ባለፉት ሦስት አሥርተ ዓመታት 50 በመቶ ጨምሯል” ይላል ካምቢዮ የተባለው የሜክሲኮ ሲቲ መጽሔት። ይህን የሚያክል ጭማሪ የተገኘው በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚሰጠው የቤተሰብ ምጣኔና የጾታ ትምህርት በጨመረበት ጊዜ ነው። በጤና ባለ ሥልጣናት የሚደረጉ ጥናቶች “የሚያጨሱ፣ የአልኮል መጠጥ የሚጠጡ ወይም ሕገወጥ ዕፆችን የሚወስዱ ልጆች ገና በልጅነታቸው ሩካቤ ሥጋ የመፈጸም ዕድላቸው አራት እጥፍ እንደሚበልጥ” ያመለክታሉ። በተጨማሪም በአሥራዎቹ ዕድሜ ልጅ ከሚወልዱ እናቶች መካከል 30 በመቶ የሚሆኑት የመጀመሪያ ልጃቸውን በወለዱ በአንድ ዓመት ጊዜ ሳያስቡት ሁለተኛ ልጅ ሲወልዱ 50 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁለተኛ ልጅ ይወልዳሉ። ከእነዚህ ወጣት እናቶች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት ልጃቸውን የሕፃኑ አባት ሳይረዳቸው ብቻቸውን ለማሳደግ የሚገደዱ መሆናቸው የወጣት እርጉዞችን ችግር አባብሶታል።

ተጠምቀዋል፣ ግን የሃይማኖቱ ተከታዮች አይደሉም

ኤል ፓይስ የተባለው የስፔይን ጋዜጣ “ስፔይን አሁንም የተጠመቁ ካቶሊኮች አገር ትሁን እንጂ ከዓመት ወደ ዓመት የካቶሊኮች ቁጥር እየተመናመነ ሄዷል” ይላል። በጄኔራል ፍራንኮ የአምባገነን ዘመነ መንግሥት “የካቶሊክ እምነት የአገሪቱ ኦፊሴላዊ ሃይማኖት ሆኖ የቆየ ሲሆን ሌሎቹ ሃይማኖቶች በሙሉ በሕግ ታግደው ስደት ይደርስባቸው ነበር። በገጠር አካባቢዎች እሁድ እሁድ ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ማስቀደስ ግዴታ ሲሆን ይህን የቤተ ክርስቲያን ሥልጣን ለመጋፋት የደፈረ ሰው ቅጣት ይደርስበት ነበር” ይላል ጋዜጣው። ዛሬ ግን ሁኔታው በእጅጉ ተለውጧል። የማኅበረሰባዊ ምርምር ማዕከል ያደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው አዘውትረው የሚያስቀድሱ ስፔናውያን ከጠቅላላው ሕዝብ መካከል 18.5 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። “የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በእርስ በርስ ጦርነትና በፍራንኮ አምባገነናዊ ሥርዓት ተባባሪ በመሆን ከፈጸመችው ወንጀል ለማምለጥ ብትችልም ሊቀለበስ በማይችል የውድቀት ጎዳና ላይ እንደምትገኝ የማኅበረሰባዊ ምርምር ማዕከል ጥናት ያሳያል” ብሏል ኤል ፓይስ።

ወጣቶችን የሚያሳስቧቸው ነገሮች

የለንደኑ ዘ ታይምስ መጽሔት “ወላጆች በአፍላ ጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻቸው ዕፅ መውሰድ ይጀምሩ ይሆናል ብለው በጣም ስለሚሰጉ ልጆቻቸውን የሚያስጨንቋቸውን የስሜትና የአእምሮ ችግሮች ማየት አቅቷቸዋል” ብሏል። ከ500 በሚበልጡ ወላጆችና 500 ገደማ በሚሆኑ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ በሚገኙ ልጆች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት 42 በመቶ የሚያክሉ ወላጆች ልጆቻቸውን የሚያጋጥማቸው ትልቁ ችግር አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ ነው ብለው እንደሚያምኑ ያመለክታል። በዚህ የሚስማሙት ወጣቶች ግን ከ19 በመቶ አይበልጡም። ሠላሳ አንድ በመቶ የሚያክሉትን ወጣቶች በይበልጥ የሚያሳስባቸው ከጓደኞቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ሲሆን 13 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በጣም የሚያሳስቧቸው ትምህርት ቤት የሚያስቸግሯቸው ጉልበተኞች ናቸው። ጥናቱን ያካሄደው ጌት ኮነክትድ የተባለው ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት ጀስቲን አርዊን ወላጆች በአፍላ ጉርምስና ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆቻቸው ስለሚያጋጥሟቸው ስሜታዊና ሥነ ልቦናዊ ችግሮች ቸልተኞች መሆናቸው በጣም እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል። ወላጆችን አጥብቀው ሲመክሩ “የግምት ስጋታችሁን ተዉ። እውነታው ይታያችሁ” ብለዋል።

እንቅልፍ ማጣት የሚያስከትለው ጉዳት

ቭፕሮስት የተባለው የዋርሶ ሳምንታዊ ጋዜጣ “ዘጠኝ በመቶ የሚሆኑት ፖላንዳውያን በእያንዳንዱ ምሽት እንቅልፍ የሚተኙበት ጊዜ ከአምስት ሰዓት እንደሚያንስ” ዘግቧል። “ከአሜሪካውያንና ከብሪታንያ ሰዎች መካከል ደግሞ ከሦስቱ አንዱ በየምሽቱ እንቅልፍ የሚተኛው ከ6.5 ላልበለጠ ሰዓት ነው።” በፖላንድ የእንቅልፍ ክሊኒክ ባልደረባ የሆኑት ሚካል ስካልስኪ እንደሚሉት “በቂ እንቅልፍ የማያገኝ ሰው ሁልጊዜ በውጥረት ውስጥ ይኖራል።” በጃፓን የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው “አምስት ሰዓትና ከዚያ ያነሰ የሚተኙ ሰዎች በልብ ድካም የመሞታቸው ዕድል ስምንት ሰዓት ከሚተኙት በ50 በመቶ ይበልጣል” ሲል ቭፕሮስት ዘግቧል። በተጨማሪም በአሜሪካ የተደረጉ ጥናቶች እንቅልፍ ማጣት ከስኳር በሽታና ከሌሎች የጤና እክሎች ጋር ተዛማጅነት ሊኖረው እንደሚችል ያመለክታሉ። እንቅልፍ ማጣት “በሰውነት የግሉኮስ አጠቃቀም ላይ ለውጥ ከማስከተሉም በላይ አለመጠን ከመወፈርም” ጋር ግንኙነት እንዳለው ሪፖርቱ ይናገራል። አሜሪካን ፊትነስ የተባለው መጽሔት “በምትደክምበት ጊዜ ሰውነትህ ያጣውን አቅም ለማካካስ ይሞክራል። እንቅልፍ ያጡ ሰዎች ንቁ ሆነው ለመቆየት ሲሉ ብዙ ይበላሉ፣ ይጠጣሉ። ስለዚህ ጥቂት ኪሎዎች ቀንሰህ ከነበረና ውፍረቱ እንዳይመለስብህ ከፈለግህ የእንቅልፍ ሰዓትህን ጨምር” በማለት ይናገራል።

የአንድ ቀን ውሎ በመሥሪያ ቤቶች

ለንደን ማጋዚን ባካሄደው አንድ ጥናት 511 ሰዎችን ስለተለመደው ውሏቸው ጠይቋቸው ነበር። ግማሽ የሚሆኑት በሥራ ሰዓት አልኮል ጠጥተዋል፣ 48 በመቶ የሚሆኑት ሰርቀዋል እንዲሁም አንድ ሦስተኛ ያህል የሚሆኑት ሕገወጥ ዕፅ ወስደዋል ሲል ዘ ዴይሊ ቴሌግራፍ የተባለው የለንደን ጋዜጣ ዘግቧል። በተጨማሪም 42 በመቶ የሚሆኑት “አለቆቻቸውን ሲገድሉ ታይቷቸዋል።” አንድ ሦስተኛ ያህል የሚሆኑት ደግሞ “በኢንተርኔት የብልግና ሥዕሎችን ተመልክተዋል።” “62 በመቶ የሚያክሉት የሥራ ባልደረባቸው የወሲብ ጥያቄ ሲያቀርብላቸው አንድ አምስተኛ ያህል የሚሆኑት በቢሯቸው ውስጥ ወሲብ ፈጽመዋል።” ከእነዚህ ሠራተኞች መካከል 36 በመቶ የሚሆኑት ስለ ትምህርታቸውና የሥራ ልምዳቸው ዋሽተዋል። አሥራ ሦስት በመቶ የሚሆኑት የሥራ እድገት የሚያስገኝላቸው ከሆነ ከአለቃቸው ጋር ቢተኙ ቅር እንደማይላቸው ተናግረዋል። አርባ አምስት በመቶ የሚያክሉት እድገት የሚያስገኝላቸው ከሆነ ከባልደረባቸው ጀርባ የሚጎዳውን ነገር ያደርጋሉ። ፊሊፕ ሆድሰን የተባሉት የአእምሮ ሐኪም እንዳሉት እነዚህ ባሕርያት በአብዛኛው የሚመነጩት ባለ ሥልጣናትን ከመናቅና ከመጥላት ነው። “ከፍተኛ ቦታ ላይ ለመድረስ ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ፈቃደኞች ነን። ክብር፣ ማዕረግና ደረጃ ትልቅ ቦታ የምንሰጣቸው ነገሮች ናቸው።”