በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የልጅነት ዕድሜን በአግባቡ ማጣጣም

የልጅነት ዕድሜን በአግባቡ ማጣጣም

የልጅነት ዕድሜን በአግባቡ ማጣጣም

ጥሩ የልጅነት ዕድሜ በአብዛኛው የተመካው በወላጆች አያያዝ ላይ ነው። ይሁን እንጂ ጥሩ አያያዝ ምን ነገሮችን ያጠቃልላል? በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰጡ ምክሮችን ሳትሰማ አትቀርም። ለልጆችህ በቂ ጊዜ መድብ። አዳምጣቸው። ጠንከር ያለ አመራር ስጣቸው። ራስህን በእነርሱ ቦታ አድርገህ በመመልከት ደስታቸውንም ሆነ ሐዘናቸውን ተካፈል። የወላጅነት ኃላፊነትህን ሳትዘነጋ ጥሩ ጓደኛ ሁናቸው። እነዚህ በተደጋጋሚ የሚሰሙ ምክሮች ወላጆች ኃላፊነታቸውን በጥሩ ሁኔታ እንዲወጡ ይረዳሉ። ይሁን እንጂ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ መሠረታዊና አስፈላጊ የሆነ አንድ ነገር አለ።

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወላጆች ለጥሩ ወላጅነት ቁልፉ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተል እንደሆነ ተገንዝበዋል። ለምን? ይህ የሆነበት ምክንያት የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ የሆነው ይሖዋ አምላክ የቤተሰብ ዝግጅትም ፈጣሪ በመሆኑ ነው። (ዘፍጥረት 1:27, 28፤ 2:18-24፤ ኤፌሶን 3:15) ስለዚህ ስለ ልጆች አስተዳደግ ከሁሉ የተሻለ አመራር የምናገኘው ይሖዋ በመንፈሱ ካስጻፈው ቃሉ መሆኑ ተገቢ ነው። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስን የመሰለ ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረ መጽሐፍ በዘመናችን ለሚታየው ልጆች የልጅነት ጊዜያቸውን ሳያጣጥሙ በፍጥነት እንዲያልፉ ለሚያደርገው ዝንባሌ ጠቃሚ ምክር ሊሰጥ የሚችለው እንዴት ነው? በዚህ ጉዳይ ላይ አግባብነት ያላቸውን በቅዱስ ጽሑፉ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ መሠረታዊ መመሪያዎችን እንመልከት።

“በሕፃናቱ እርምጃ መጠን”

የይስሐቅ ልጅ ያዕቆብ ከአሥራ ሁለት የሚበልጡ ልጆች ነበሩት። መጽሐፍ ቅዱስ ያዕቆብ ቤተሰቡ ስላደረገው ጉዞ የተናገረውን የጥበብ ቃል መዝግቦ ይዞልናል። “ልጆቹ ደካሞች እንደ ሆኑ ታውቃለህ . . . ጌታዬ ከባሪያው ፊት ቀድሞ ይለፍ፤ እኔም . . . በሕፃናቱ እርምጃ መጠን በዝግታ እከተላለሁ።”—ዘፍጥረት 33:13, 14

ያዕቆብ ልጆቹ ትናንሽ አዋቂ ሰዎች እንዳልሆኑ አውቋል። “ደካሞች” ማለትም በአቅማቸው፣ በመጠናቸውና በጉልበታቸው ከትልቅ ሰው ያነሱ ነበሩ። ልጆቹ ከእርሱ እኩል እንዲሄዱ ከማስገደድ ይልቅ የራሱን ፍጥነት በመቀነስ ከልጆቹ ጋር እኩል ተጉዟል። በዚህ ረገድ አምላክ ለሰብዓዊ ልጆቹ የሚያሳየውን ጥበብ አንጸባርቋል። ሰማያዊው አባታችን አቅማችንን ያውቅልናል። ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር አይጠብቅብንም።—መዝሙር 103:13, 14

አንዳንድ እንስሳት እንኳን አምላክ በፍጥረታቸው ጠቢባን ስላደረጋቸው ይህ ዓይነቱ ጥበብ አላቸው። (ምሳሌ 30:24) ለምሳሌ ያህል የተፈጥሮ ተመራማሪዎች አንድ የዝሆኖች መንጋ በውስጡ አዲስ የተወለደ ዝሆን በሚኖርበት ጊዜ ሕፃኑ ዝሆን ጉልበቱ ጠንቶ ከመንጋው ጋር እኩል መሄድ እስኪጀምር ድረስ የጉዞውን ፍጥነት እንደሚቀንስ አስተውለዋል።

አንዳንድ ዘመናውያን ይህን አምላካዊ ጥበብ ችላ ብለዋል። አንተ ግን እነርሱን መከተል አይኖርብህም። ልጅህ የትላልቅ ሰዎችን ሸክምና ኃላፊነት ሊሸከም የማይችል ‘ደካማ’ መሆኑን አትዘንጋ። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ የግል ችግሮች ያሉብህና ለብቻህ ልጆችህን የምታሳድግ ከሆንክ ለልጅህ ምሥጢር ማዋየት እንዳለብህ የሚገፋፋህን ስሜት ተቋቁመህ ማሸነፍ አለብህ። ከዚህ ይልቅ ከተቻለ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክሮች ተጠቅመህ ችግሮችህን እንድትፈታ ሊረዳህ ለሚችል የጎለመሰ ወዳጅ አማክር።—ምሳሌ 17:17

እንዲሁም ልጅህ በልጅነት ዕድሜው የሚጫወትበትና የሚደሰትበት ጊዜ እስኪያጣ ድረስ ጊዜው በሙሉ የተጣበበና በሥራ የተያዘ እንዲሆን አታድርግ። የዘመናዊው ዓለም ኑሮ ከሚጠይቀው የጥድፊያ ፕሮግራም ጋር ሳይሆን ከልጅህ አቅም ጋር የሚመጣጠን ፕሮግራም አውጣ። መጽሐፍ ቅዱስ “ይህን ዓለም አትምሰሉ” በማለት የሚሰጠውን ምክር በመከተል በዙሪያህ ያለው ዓለም እንዳይቀርጽህ ተጠንቀቅ!—ሮሜ 12:2

“ለሁሉ ዘመን አለው”

ሌላው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ደግሞ “ለሁሉ ዘመን አለው፣ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው” ይላል። እርግጥ ነው፣ ለመሥራትም ጊዜ አለው። ልጆች ደግሞ የትምህርት ቤት፣ የቤት ውስጥና መንፈሳዊ የሆኑ ብዙ ሥራዎች አሏቸው። ይሁን እንጂ ይኸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል “ለመሳቅም ጊዜ አለው” “ለመጨፈርም ጊዜ አለው” [NW] ይላል።—መክብብ 3:1, 4

ልጆች መጫወት፣ መሳቅና እንደ ልባቸው መቦረቅ ይኖርባቸዋል። የየቀኑ ውሏቸው በትምህርት ቤት፣ ከትምህርት ሰዓት ውጭ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎችና በሌሎች ኃላፊነቶች የተያዘ ከሆነ የመጫወት ፍላጎታቸው ሳይሟላላቸው ይቀራል። ይህ ደግሞ ለብስጭትና ለምሬት ሊዳርጋቸው ይችላል።—ቆላስይስ 3:21

ይህንኑ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት እንዴት በሌሎች መንገዶች ሥራ ላይ ማዋል እንደሚቻል እንመልከት። ለምሳሌ ያህል ለሁሉ ነገር ጊዜ ከኖረው የልጅነት ጊዜም ልጅ የሚኮንበት ጊዜ መሆን አይገባውም? አዎን ብለህ ትመልስ ይሆናል። ልጆችህ ግን ሁልጊዜ በዚህ አይስማሙም። አብዛኛውን ጊዜ ትናንሽ ልጆች ትላልቅ ሰዎች ሲያደርጉ ያዩትን ሁሉ ማድረግ ይፈልጋሉ። ለምሳሌ ያህል ሴት ልጆች እንደ ትላልቅ ሴቶች ለመልበስና ለመኳኳል ይፈልጉ ይሆናል። ቶሎ ብለው መጎርመሳቸው ትልቅ ሆነው መታየት እንዲፈልጉ ተጽዕኖ ሊያሳድርባቸው ይችላል።

ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች የዚህን አዝማሚያ አደገኛነት ያስተውላሉ። የዚህ ርካሽ ዓለም አንዳንድ መዝናኛዎችና ማስታወቂያዎች ልጆች ወሲባዊ ፍላጎት እንዳላቸውና ከዕድሜያቸው በፊት የበሰሉ እንደሆኑ አድርገው ያሳያሉ። ትናንሽ ልጆች መኳኳያዎችን፣ ጌጣ ጌጦችንና የፆታ ስሜት የሚቀሰቅሱ ልብሶችን ማዘውተር ጀምረዋል። ይሁን እንጂ ልጆችን ሊደፍሯቸው ለሚፈልጉ ምግባረ ብልሹ ሰዎች ማራኪ አድርጎ ማቅረብ የሚፈልግ ማን አለ? ወላጆች ልጆቻቸው ለዕድሜያቸው የሚመጥን ልብስ እንዲለብሱ ሲያደርጉ “ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ሥራ ላይ አዋሉ ማለት ነው።—ምሳሌ 27:12

ሌላ ምሳሌ እንውሰድ:- አንድ ልጅ ለስፖርት ቅድሚያ እንዲሰጥ ከተደረገ ለሁሉ ጊዜ መስጠት ያቅተውና መላ ሕይወቱ የተዛባ ይሆንበታል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰውነትን ለሥጋዊ ነገር ማስለመድ ለጥቂት ይጠቅማልና፤ እግዚአብሔርን መምሰል ግን የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው፣ ለነገር ሁሉ ይጠቅማል” በማለት የጥበብ ምክር ይሰጣል።—1 ጢሞቴዎስ 4:8

ልጆችህ “ማሸነፍ ወይም ሞት” የማለት ዝንባሌ እንዲቀረጽባቸው አትፍቀድ። ብዙ ወላጆች በልጆቻቸው ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የፉክክርና አሸናፊ የመሆን መንፈስ እንዲሰርጽ በማድረግ ከስፖርትና ከጨዋታዎች ማግኘት የሚገባቸውን ደስታ እንዳያገኙ ያደርጋሉ። በዚህ የተነሣ አንዳንድ ልጆች አሸናፊ ለመሆን ሲሉ ያጭበረብራሉ ወይም በሌሎች ተወዳዳሪዎች ላይ ጉዳት ያደርሳሉ። ሆኖም አሸናፊነት ይህን ያህል መሥዋዕትነት ሊከፈልለት የሚገባ ነገር አይደለም።

ራስ መግዛትን መለማመድ

ለሁሉ ጊዜ እንዳለው መማር ለልጆች ቀላል አይደለም። የሚፈልጉትን ነገር እስኪያገኙ ድረስ በትዕግሥት መጠበቅ ሊያስቸግራቸው ይችላል። ይባስ ብሎ ደግሞ ሰብዓዊው ማኅበረሰብ የፈለገውን ሁሉ ወዲያው የማግኘት ፍላጎት ተጠናውቶታል። መገናኛ ብዙኃን አብዛኛውን ጊዜ “የምትፈልገውን ነገር አሁኑኑ አግኝ” የሚል መልእክት ያስተላልፋሉ።

ልጆችህን በማቀማጠልና በማሞላቀቅ እንዲህ ላለው ተጽዕኖ አትሸነፍ። ዘ ቻይልድ ኤንድ ዘ ማሽን የተባለው መጽሐፍ “የተፈለገውን ነገር ለማግኘት ታግሦ መቆየት በስሜት የመብሰል ዋነኛ ምልክት ነው” ይላል። “ልጆች በትምህርት ቤት ውስጥም ሆነ ከትምህርት ቤት ውጭ ለሚያሳዩት የዓመፀኝነት ዝንባሌ መድኃኒቱ ተግሣጽና ማኅበራዊ ስምምነት ነው።” መጽሐፍ ቅዱስ “ባሪያውን ከሕፃንነቱ ጀምሮ በማቀማጠል የሚያሳድግ የኋላ ኋላ እንደ ጌታ ያደርገዋል” የሚል ጠቃሚ ምክር ይሰጣል። (ምሳሌ 29:21) ጥቅሱ በቀጥታ የሚናገረው ስለወጣት አገልጋዮች ቢሆንም መሠረታዊ ሥርዓቱ ለልጆችም እንደሚሠራ ብዙ ወላጆች ተገንዝበዋል።

ልጆች ከሚያስፈልጓቸው ነገሮች ተቀዳሚውን ቦታ የሚይዘው ‘የጌታ ምክርና ተግሣጽ’ ነው። (ኤፌሶን 6:4) በፍቅር የተሰጠ ተግሣጽና ምክር ልጆች እንደራስ መግዛትና ትዕግሥት የመሰሉትን ባሕርያት እንዲያዳብሩ ይረዳል። እነዚህ ባሕርያት ደግሞ በመላ ሕይወታቸው ደስታና እርካታ እንዲያገኙ ይረዷቸዋል።

በልጆች ላይ የሚጋረጡ አደጋዎች በሙሉ የሚወገዱበት ጊዜ

ይሁን እንጂ ‘እነዚህን ጠቃሚ መሠረታዊ ሥርዓቶች ያስጻፈው አፍቃሪና ጥበበኛ አምላክ ዓለማችን እንዲህ እንዳሁኑ እንድትሆን ዓላማው ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ‘ልጆች እንክብካቤ ከሚያገኙበት ቦታ ይልቅ ለአደጋ በሚያጋልጣቸው ዓለም ውስጥ እንዲያድጉ ዓላማው ነው?’ ይሖዋ አምላክና ልጁ ክርስቶስ ኢየሱስ በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ልጆችን ጨምሮ ለመላው የሰው ዘር ጥልቅ ፍቅር እንዳላቸው ማወቅህ ሊያጽናናህ ይችላል። ከጥቂት ጊዜ በኋላ መላዋ ምድር ከማንኛውም ክፋት የጸዳች እንድትሆን ያደርጋሉ።—መዝሙር 37:10, 11

ይህ ሰላማዊ የሆነ አስደሳች ጊዜ ምን ሊመስል እንደሚችል ማየት ትፈልጋለህ? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን የሚከተለውን ትንቢት በማንበብ ሁኔታው ምን ሊመስል እንደሚችል በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር:- “ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር ይቀመጣል፣ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፤ ጥጃና የአንበሳ ደቦል ፍሪዳም በአንድነት ያርፋሉ፤ ታናሽም ልጅ ይመራቸዋል።” (ኢሳይያስ 11:6) ልጅነትን በጭካኔ በሚያጠፋውና ልጆች በልጅነታቸው ማግኘት የሚገባቸውን ደስታ ሳያገኙ እንዲያድጉ በሚያደርገው በዚህ ዓለም ውስጥ እየኖርን አምላክ እንዲህ ያለ ኑሮ በምድር ላይ እንደሚያመጣ ማወቅ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ፈጣሪ የልጅነት ዕድሜ እንዲባክን ወይም እንዲያጥር ሳይሆን አስደሳችና ተገቢ እንክብካቤ የሚደረግለት ወቅት እንዲሆን እንደሚፈልግ ግልጽ ነው።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለልጅህ ችግሮችህን በማወያየት ሸክም እንዲጫንበት ከማድረግ ይልቅ ሌላ ትልቅ ሰው አማክር

[በገጽ 26 እና 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆች መጫወት ያስፈልጋቸዋል