በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“የመጽሐፍ ቅዱስ ዓመት”

“የመጽሐፍ ቅዱስ ዓመት”

“የመጽሐፍ ቅዱስ ዓመት”

ኦስትሪያ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመንና ስዊዘርላንድ 2003ን “የመጽሐፍ ቅዱስ ዓመት” ብለው ሰይመውታል። ፍራንክፈርተር አልጌማይነ ጻይቱንግ የተባለው የጀርመን ዕለታዊ ጋዜጣ እንዲህ ብሏል:- “ከአሁን ቀደም የመጽሐፍ ቅዱስ ዓመት የተከበረው በ1992 ብቻ ሲሆን እንደዚያን ጊዜው ሁሉ በዚህ ዓመትም [አብያተ ክርስቲያናት] ሕዝቡ ስለዚህ ‘የሕይወት መጽሐፍ’ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግና መጽሐፍ ቅዱስ በዘመኑ የነበረውን ባሕል በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ለማስገንዘብ ግብ አውጥተዋል።”

ቢብልሪፖርት በሰኔ 2002 እትሙ እንደዘገበው መጽሐፍ ቅዱስ ቢያንስ የተወሰነው ክፍሉ በ2,287 ቋንቋዎች ተተርጉሟል። ከዚህም በላይ እስካሁን ድረስ ወደ አምስት ቢሊዮን የሚጠጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች እንደተሰራጩ ይገመታል። መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች እጅ እንዲገባ እንደዚህ ያለ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ መደረጉ ሰዎች ለዚህ መጽሐፍ ትልቅ ግምት እንዳላቸው በግልጽ ያሳያል።

በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ለዘመናችን የሚሆን መጽሐፍ እንዳልሆነ ይሰማቸው ይሆናል። በእርግጥም፣ ብዙዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጊዜ ያለፈባቸውና ከእውኑ ዓለም የራቁ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዓመት በጀርመን ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ሁለት ነገሮችን ለማከናወን አቅደዋል። እነዚህም፣ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ጋር ይበልጥ ተስማምተው እንዲኖሩ ማበረታታትና ከቤተ ክርስቲያን የራቁ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ማነሳሳት ናቸው።

መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር አንብቦ መጨረስ ቀላል ነገር ባይሆንም በውስጡ የሰፈሩትን ዋና ዋና ነጥቦች ለመጨበጥ የሚያስችል ግሩም መንገድ እንደሆነ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተሟላ ጥቅም ማግኘት የሚፈልግ ሰው በ2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ሐሳብ ልብ ሊለው ይገባል:- “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።”

ጀርመናዊው ገጣሚ ዮሃን ቮልፍጋንግ ፎን ጎተ (1749-1832) “አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ በተረዳ መጠን ከበፊቱ ይበልጥ እየወደደውና እያደነቀው እንደሚሄድ አምናለሁ” ብሏል።  በእርግጥም፣ ከየት መጣን? የመኖራችን ዓላማ ምንድን ነው? የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዟል? ለሚሉት ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ማግኘት የምንችለው ከአምላክ ቃል ብቻ ነው!—ኢሳይያስ 46:9, 10

[በገጽ 29 ላይ የሚገኙ የሥዕሎቹ ምንጮች]

Bildersaal deutscher Geschichte ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ