በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የብልግና ሥዕሎችን በተመለከተ የሚሰነዘሩ እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ አመለካከቶች

የብልግና ሥዕሎችን በተመለከተ የሚሰነዘሩ እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ አመለካከቶች

የብልግና ሥዕሎችን በተመለከተ የሚሰነዘሩ እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ አመለካከቶች

“መኖር የማይገባውን ፍላጎት ይፈጥራል፣ መርካት የማይገባውን ስሜት ይቀሰቅሳል”—ቶኒ ፓርሰንስ፣ የጋዜጣ አምድ አዘጋጅ

ጆን በኢንተርኔት የሚቀርቡ የብልግና ሥዕሎችን በመመልከት ሱሰኛ የመሆን ሐሳብ አልነበረውም። * ብዙ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች እንደሚያጋጥማቸው እርሱም አንድ ቀን ኢንተርኔት እየተጠቀመ ሳለ ድንገት ስለ ወሲብ ከሚጨዋወቱ ሰዎች ጋር ተገናኘ። ወዲያው በኢንተርኔት በሚተላለፉ የብልግና ሥዕሎች ሙሉ በሙሉ ተማረከ። “ባለቤቴ ወደ ሥራ እስክትሄድልኝ እጠብቅና ወዲያው ከአልጋ ወጥቼ ለበርካታ ሰዓት ኮምፒውተሬ ላይ አፍጥጬ እቆያለሁ” በማለት ያስታውሳል። ለመብላትና ለመጠጣት ብሎ እንኳን አንዴም አያርፍም። “የረሐብ ስሜት ፈጽሞ አይሰማኝም” ይላል። በድብቅ ስለሚያደርገው እንቅስቃሴ ለሚስቱ መዋሸት ጀመረ። ሥራው ላይ ማተኮር እያቃተው ከመምጣቱም በላይ ያለምክንያት የፍርሃት ስሜት ይሰማው እንዲሁም በትዳሩ ውስጥም ችግር ይፈጠር ጀመር። በመጨረሻም ከኢንተርኔት የወሲብ ጓደኞቹ መካከል ከአንዷ ጋር በአካል ለመገናኘት ሲቀጣጠር ሚስቱ አወቀችበት። ዛሬ ጆን ከዚህ ሱስ ለመላቀቅ የሕክምና ክትትል እየተደረገለት ነው።

የብልግና ሥዕሎችን የሚቃወሙ ሰዎች እንደነዚህ ያሉትን ምሳሌዎች በመጥቀስ የብልግና ሥዕሎች ጎጂ መሆናቸውን ያስረዳሉ። በሰዎች መካከል የሚፈጠሩ መልካም ግንኙነቶችን ያበላሻል፣ ሴቶችን ያዋርዳል እንዲሁም በሕፃናት ላይ ግፍ እንዲፈጸም፣ ስለ ፆታ ጎጂና ጠማማ አመለካከት እንዲስፋፋ ያደርጋል ይላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የብልግና ሥዕል ደጋፊዎች ስሜትን በነጻ ለመግለጽ ያስችላል በማለት ተቃዋሚዎቹን ጠባብ አስተሳሰብ ያላቸውና አጉል ተቆርቋሪዎች እንደሆኑ ይናገራሉ። አንድ የብልግና ሥዕሎች ደጋፊ “ሰዎች ስለ ፆታ ባሕርያቸው ወይም ፍላጎታቸው እፍረት ሊሰማቸው አይገባም” ሲሉ ጽፈዋል። “የብልግና ሥዕሎች ስለ ፆታ ግልጽ የሆነ ውይይት ለማድረግ ሊያገለግሉ ይችላሉ።” እንዲያውም አንዳንዶች የብልግና ሥዕሎች መስፋፋት ግልጽና ጤናማ የሆነ ማኅበረሰብ መለያ ምልክት ነው እስከ ማለት ደርሰዋል። ብራያን ማክነር የተባሉ ጸሐፊ “ለአካለ መጠን የደረሱ ሰዎች ተፈቃቅደው የሚፈጽሙትን የፆታ ግንኙነት በገሀድ ለማየት የሚያስችል ብስለት ያለው ማኅበረሰብ ወንድ ከወንድና ሴት ከሴት ጋር የሚደረገውን ወሲብም ሆነ የሴቶችን እኩልነት መቀበል አያዳግተውም” ብለዋል።

ታዲያ በኅብረተሰቡ ውስጥ አንድ ወጥ የሆነ አመለካከት የሌለ መሆኑ የብልግና ሥዕሎች ተቀባይነት እንዲያገኙ ያስችላል ማለት ነው? ይህን ያህል የተስፋፉትስ ለምንድን ነው? የብልግና ሥዕሎችን መመልከት በእርግጥ አደገኛ ነው? የሚቀጥሉት ርዕሶች ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 ስሞቹ ተለውጠዋል።