በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የብልግና ሥዕሎች ይህን ያህል የተስፋፉት ለምንድን ነው?

የብልግና ሥዕሎች ይህን ያህል የተስፋፉት ለምንድን ነው?

የብልግና ሥዕሎች ይህን ያህል የተስፋፉት ለምንድን ነው?

የፆታ ስሜት የሚቀሰቅሱ የብልግና ሥዕሎች መታየት ከጀመሩ በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት አስቆጥረዋል። ይሁን እንጂ በእነዚህ የታሪክ ዘመናት በሙሉ የብልግና ሥዕሎችን ማዘጋጀት ቀላል ስላልነበረ እነዚህን ሥዕሎች አግኝተው ማየት የሚችሉት ባለጠጋዎችና የገዢ መደብ አባላት ብቻ ነበሩ። ብዙ ቅጂዎችን በአንድ ጊዜ ማተምና ተንቀሳቃሽ ሥዕሎችን ማዘጋጀት መቻል ይህን ለረዥም ዓመት የቆየ ሁኔታ እንዲቀየር አደረገ። በዚህም የተነሳ የብልግና ሥዕሎች ብዙ ገንዘብ የማይጠይቁና ማንም ሰው በቀላሉ ሊያገኛቸው የሚችሉ ሆኑ።

የቪዲዮ መፈልሰፍም ይህ አዝማሚያ ይበልጥ እንዲፋጠን አድርጓል። የቪዲዮ ካሴቶች እንደ ፊልም ጥቅልሎችና እንደ አሮጌ ፎቶግራፎች ለማስቀመጥ፣ ለማባዛትም ሆነ ለማሠራጨት የሚያስቸግሩ ሆነው አልተገኙም። በተጨማሪም በቤት ውስጥ በምሥጢር ሊታዩ ይችላሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን መቀበል የሚያስችሉ አንቴናዎችና ኢንተርኔት የብልግና ሥዕሎች ይበልጥ እንዲስፋፉና የትም ቦታ በቀላሉ እንዲገኙ አስችሏል። ቪዲዮ ቤት ገብቼ የብልግና ፊልም ስዋስ ብታይስ ብሎ ይፈራ የነበረ ሰው ዛሬ “የኬብል ወይም የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያውን በመክፈት ብቻ እቤቱ ቁጭ ብሎ ማየት ይችላል” ይላሉ የመገናኛ ብዙኃን ተንታኝ የሆኑት ደኒስ ማክአልፓይን። እንዲህ ያለውን ፕሮግራም በቀላሉ ማግኘት መቻል ማክአልፓይን እንደሚሉት የብልግና ሥዕሎች “የበለጠ ተቀባይነት እንዲያገኙ አስተዋጽኦ አድርጓል።”

የብልግና ሥዕሎች ነውር መሆናቸው እየቀረ መጥቷል

ብዙ ሰዎች የብልግና ሥዕሎች እንደነውር መታየታቸው እየቀረ በመምጣቱ ግራ መጋባት ጀምረዋል። ጀርመይን ግሪር “አሁንም እንኳን ኦፔራዎች፣ ባሌ ዳንሶች፣ ቲያትሮች፣ ሙዚቃዎችና ሥነ ጥበባት አንድ ላይ ሆነው ከሚያሳድሩት ባሕላዊ ተጽዕኖ ይልቅ የብልግና ሥዕሎች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ የበለጠ ነው” ብለዋል። ብዙ ታዋቂ የሙዚቃ ሰዎች የዝሙት አዳሪዎችን አለባበስ መከተላቸው እንዲሁም የሙዚቃ ፊልሞችና የንግድ ማስታወቂያዎች ወሲባዊ እንቅስቃሴዎችን የሚያሳዩ መሆናቸው ሰዎች ለብልግና ሥዕሎች ያላቸው አመለካከት እየተለወጠ መምጣቱን ያሳያል። ማክአልፓይን አስተያየታቸውን ሲያጠቃልሉ “ኅበረተሰቡ ያጎረሱትን በሙሉ በመቀበል ላይ ነው። . . . ይህም የቀረበለትን ሁሉ ጥሩ ነው ብሎ እንዲቀበል እያደረገው ነው” ብለዋል። በዚህም የተነሣ “ሰዎች የሚዘገንናቸው ነገር እየጠፋ ነው” ሲሉ ደራሲው አንድርያ ድዎርኪን ያማርራሉ። “ለምንም ነገር ግድ የላቸውም።”

ለብልግና ሥዕሎች ጥሩነት የሚሰጡ ምክንያቶች

ሮጀር ያንግ የተባሉት የቀድሞ የአሜሪካ የፌደራል ምርመራ ቢሮ (FBI) አባል የደራሲ ድዎርኪንን አመለካከት በማስተጋባት ብዙ ሰዎች “በብልግና ምክንያት የሚመጡት ችግሮች አይታዩአቸውም” ብለዋል። አንዳንዶች የብልግና ሥዕሎች በሰዎች ላይ ጉዳት እንደሚያስከትሉ የሚያረጋግጥ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም በማለት የብልግና ሥዕሎች ጠበቆች በሚያሰሙት ክርክር ተታልለዋል። ኤፍ ኤም ክሪሰንሰን የተባሉት ደራሲ “የብልግና ሥዕሎች እኮ ከአእምሮ አልፈው የማይሄዱ ቅዠቶች ናቸው። ተቃዋሚዎች መረዳት ያቃታቸው ይህንን ነው” ብለዋል። ይሁን እንጂ በአእምሮ ውስጥ የሚፈጠር ቅዠት ምንም ዓይነት ኃይል ከሌለው ማስታወቂያዎች የሚለፈፉት ለምንድን ነው? በሰዎች ላይ የሚያስከትሉት ዘላቂ ተጽዕኖ ከሌለ የንግድ ድርጅቶች የማስታወቂያ ፊልሞችንና የማስታወቂያ ወረቀቶችን ለማዘጋጀት በሚሊዮን የሚቆጠር ብር የሚያፈሱት ለምንድን ነው?

ሐቁ የብልግና ሥዕሎች ዋነኛ ዓላማ እንደማንኛውም ውጤታማ ማስታወቂያ ከዚህ ቀደም ያልነበረን ፍላጎት መፍጠር ነው። ስቲቨን ሂል እና ኒና ሲልቨር የተባሉት ተመራማሪዎች “የብልግና ሥዕሎች ዓላማ ቀላልና ግልጽ ነው። ትርፍ ከማስገኘት ሌላ ምንም ዓይነት ዓላማ የላቸውም” ብለዋል። “በዚህ በተመሰቃቀለ የንግድ ዓለም ማንኛውም ነገር በተለይ ደግሞ የሴቶች ገላና ወሲብን የሚያሳዩ ሥዕሎች የሚታዩት ከሚያስገኙት ገቢና ትርፍ አንጻር ነው።” ግሪር የብልግና ሥዕሎችን ምንም ዓይነት ገንቢ ንጥረ ነገር ከሌላቸው፣ ሱስ ከሚያስይዙና ኬሚካላዊ ማጣፈጫዎች ከተጨመሩባቸው አሸርባሸር ምግቦች ጋር አመሳስለዋቸዋል። “ሸቀጥ ሆኖ የቀረበ ወሲብ የውሸት ወሲብ ነው . . . ገንቢ ያልሆኑ መናኛ ምግቦች በምግብ ማስታወቂያዎች አማካኝነት ይሸጣሉ። የወሲብ ማስታወቂያዎችም የቅዠት ወሲብ ያሻሽጣሉ” ብለዋል።

አንዳንድ ዶክተሮች የብልግና ሥዕሎች ከአደንዛዥ ዕፆች የከፋና ለመተው የሚከብድ ሱስ ሊያስይዙ እንደሚችሉ ይናገራሉ። አብዛኛውን ጊዜ የአደንዛዥ ዕፅ ሱስ ያለባቸውን ሰዎች ከሱስ ለማላቀቅ ሰውነታቸው ውስጥ የገባው ዕፅ በሕክምና እንዲወጣ ይደረጋል። ይሁን እንጂ የብልግና ሥዕሎችን ሱስ በተመለከተ የፔንሲልቫንያ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ሜሪ አን ለይደን እንደሚሉት “በአንጎል ውስጥ ሊፋቅ በማይችል ሁኔታ ይታተምና ከሱሰኛው አንጎል ጋር ተዋህዶ ይኖራል።” ሰዎች ከብዙ ጊዜ በፊት የተመለከቱትን የብልግና ሥዕል ዛሬም በሚገባ የሚያስታውሱት በዚህ ምክንያት ነው። “ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ የገጠመን ከሰውነት ተጣርቶ ሊወጣ የማይችል ሱስ የሚያስይዝ ዕፅ ነው” ብለዋል። ታዲያ እንዲህ ሲባል ከብልግና ሥዕሎች ሱሰኝነት ፈጽሞ መላቀቅ አይቻልም ማለት ነው? የብልግና ሥዕሎች የሚያስከትሉት ጉዳትስ ምንድን ነው?

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ስለ ኢንተርኔት የብልግና ሥዕሎች አንዳንድ መረጃዎች

ከኢንተርኔት የብልግና ሥዕሎች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት የሚዘጋጁት በዩናይትድ ስቴትስ ሲሆን ወደ 15 በመቶ የሚጠጉ ደግሞ በአውሮፓ ነው።

በሳምንት 70 ሚሊዮን የሚያክሉ ሰዎች የብልግና ሥዕሎችን በኢንተርኔት ይመለከታሉ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል 20 ሚሊዮን የሚያክሉት የሚኖሩት በካናዳና በዩናይትድ ስቴትስ ነው።

በቅርብ ጊዜ በአንድ ወር ውስጥ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው በኢንተርኔት የብልግና ሥዕሎች ተመልካቾች ብዛት ከአውሮፓ የአንደኛነቱን ቦታ የያዘችው ጀርመን ስትሆን ታላቋ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ፣ ኢጣሊያና ስፔይን ተከታዮቹን ቦታዎች ይዘዋል።

በጀርመን የኢንተርኔት የብልግና ሥዕሎችን የሚመለከቱ ሰዎች በወር 70 ደቂቃ ያህል የብልግና ሥዕሎችን በመመልከት ያሳልፋሉ።

በአውሮፓ የኢንተርኔት የብልግና ሥዕሎችን ከሚመለከቱ ሰዎች መካከል ኢንተርኔት በመመልከት ብዙ ሰዓት የሚያሳልፉት ከ50 ዓመት በላይ የሆናቸው ትላልቅ ሰዎች ናቸው።

አንድ የመረጃ ምንጭ እንዳመለከተው 70 በመቶ የሚሆኑት የኢንተርኔት የብልግና ሥዕሎችን የሚመለከቱት በቀን ነው።

መቶ ሺህ የሚያክሉ የኢንተርኔት ገጾች የሕፃናት የብልግና ሥዕሎችን እንደሚያሳዩ አንዳንዶች ይገምታሉ።

ከሕፃናት የብልግና ሥዕሎች መካከል 80 በመቶ የሚሆነው የሚዘጋጀው በጃፓን ነው።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የብልግና ሥዕሎች የትም ቦታ በቀላሉ የሚገኙ ሆነዋል