በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጤንነትህና የምታደርጋቸው ምርጫዎች

ጤንነትህና የምታደርጋቸው ምርጫዎች

ጤንነትህና የምታደርጋቸው ምርጫዎች

ተገቢውን ዓይነት ምግብ እየተመገቡ ጤነኛ ሆኖ መኖር ብዙውን ጊዜ እንደሚታሰበው ቀላል አይደለም። ውጥረት በበዛበት በዚህ ጊዜ ብዙዎች ምግብ አብስለው ከመመገብ ይልቅ በፋብሪካ የሚመረቱ የታሸጉ ምግቦችን መመገብ እንዲሁም በትርፍ ጊዜያቸው አካላዊ እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ ይልቅ በቴሌቪዥን ወይም በኮምፒውተር ፊት ተቀምጦ መዋልን ይመርጣሉ። በዚህ ምርጫቸው የተነሳ ለከባድ የጤና ችግሮች እየተዳረጉ ያሉ አዋቂዎችና ትናንሽ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው።

ኤዢያዊክ የተባለው መጽሔት በእስያ ስላለው ሁኔታ ሲናገር “ስኳርና ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች ማዘውተርና ያለ እንቅስቃሴ ለረዥም ሰዓት ተቀምጦ መዋል የስኳር ሕመምተኞች ቁጥር እንዲያሻቅብ እያደረገ ነው” ብሏል። የሚያሳዝነው ትናንሽ ልጆች እንኳን የዚህ በሽታ ተጠቂዎች እየሆኑ ነው። ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው በካናዳ “ዕድሜያቸው ከ13 ዓመት በታች ከሆኑ ልጆች መካከል የሚያስፈልጋቸውን ያህል ፍራፍሬና አትክልት የሚመገቡት ከሰባቱ አንዱ ብቻ እንደሆኑና ሰውነታቸውን እስኪያልባቸው ድረስ የሚጫወቱት ደግሞ ከግማሽ ብዙም እንደማይበልጡ ተመራማሪዎች ደርሰውበታል።” እንዲህ ያለው የአኗኗር ዘይቤ እነዚህን ልጆች “ዕድሜያቸው ገና ከ30ዎቹ ሳያልፍ በልብ ሕመም እንዲጠቁ እንደሚያደርጋቸው” ዘገባው አክሎ ገልጿል።

በሌላ በኩል ደግሞ አዋቂዎች በየዕለቱ የስምንት ሰዓት እንቅልፍ ማግኘት እንደሚያስፈልጋቸውና ልጆች ደግሞ ከዚያ የበለጠ መተኛት እንዳለባቸው የእንቅልፍ ባለሞያዎች ይናገራሉ። እንዲያውም በቺካጎ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ለስድስት ተከታታይ ቀናት የአራት ሰዓት እንቅልፍ ብቻ ያገኙ ጤናማ ወንዶች በአብዛኛው በአረጋውያን ላይ የሚታዩ የጤና ችግሮች ታይተውባቸዋል። ምንም እንኳን ብዙ ሰዎች ውድ የሆነውን የእንቅልፍ ጊዜያቸውን መሥዋዕት የሚያደርጉት ለሥራ፣ ለትምህርት ወይም ለመዝናኛ ሲሉ ቢሆንም ምርታማነታቸው ግን ይቀንሳል። ኒው ዮርክ በሚገኘው ኮርኔል ዩኒቨርሲቲ የእንቅልፍ ተመራማሪ የሆኑት ጄምስ ማስ እንዲህ ብለዋል:- “ሥራን ማከናወን አንድ ነገር ነው፤ ንቁ ሆኖ የፈጠራ ችሎታን እየተጠቀሙ መሥራትና በእንቅልፍ ሳይቸገሩ መኪና ማሽከርከር ግን ሌላ ነገር ነው።”

እርግጥ በጤንነታችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ሌሎች ነገሮችም አሉ። ለምሳሌ ያህል ለነገሮች አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ጥሩ ጤንነት እንዲኖረን አስተዋጽኦ ያደርጋል። እንዲሁም የሕይወትን ዓላማ ማወቃችን ጤናማ ሆነን ለመኖር የሚረዱንን ውሳኔዎች እንድናደርግ ይገፋፋናል።