በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአየሩ ጠባይ ላይ የተፈጠረ ችግር ይኖር ይሆን?

በአየሩ ጠባይ ላይ የተፈጠረ ችግር ይኖር ይሆን?

በአየሩ ጠባይ ላይ የተፈጠረ ችግር ይኖር ይሆን?

“ሁለት እንግሊዛውያን ሲገናኙ ወሬያቸውን የሚጀምሩት ስለ አየሩ ጠባይ በመነጋገር ነው።” ይህን ቀልድ የተናገረው ዝነኛው ደራሲ ሳሙኤል ጆንሰን ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የአየሩ ጠባይ የውይይት መክፈቻ በመሆን ብቻ አልተወሰነም። በመላው ዓለም የሚኖሩ ሰዎችን በእጅጉ የሚያሳስብ ጉዳይ ሆኗል። ለምን? ወትሮውንም ተለዋዋጭ የነበረው የአየር ሁኔታ ይበልጥ ተለዋዋጭ እየሆነ በመምጣቱ ነው።

ለምሳሌ ያህል በ2002 የበጋ ወራት አውሮፓ ታይቶ የማይታወቅ ዶፍ ዝናብ ወርዶባት ነበር። በዚህም ምክንያት “መካከለኛው አውሮፓ ከመቶ ዓመት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ጎርፍ ተጥለቅልቋል።” የሚከተሉትን የዜና ዘገባዎች ልብ በል:-

ኦስትሪያ:- “በጣም ከባድ በሆነ ዶፍ ዝናብ ይበልጥ የተጎዱት የዛልስቡርግ፣ የካርንቲያ እና የቲሮል ክፍለ አገሮች ናቸው። ብዙ መንገዶች እስከ 15 ሜትር ጥልቀት ባለው ጭቃ፣ ደለልና ቆሻሻ ክምር ተውጠዋል። በቪየና ደቡባዊ ባቡር ጣቢያ የወረደው ዶፍ በባቡር ላይ አደጋ አድርሶ ብዙ ሰዎች ተጎድተዋል።”

ቼክ ሪፑብሊክ:- “ለፕራግ ነዋሪዎች በጣም የሚያስፈራ ጊዜ ነበር። ይሁን እንጂ በየክፍለ አገሩም የባሰ አሳዛኝ አደጋ ደርሷል። ሁለት መቶ ሺህ የሚያክሉ ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለዋል። ሙሉ በሙሉ በጎርፍ የተዋጡ ከተሞች ነበሩ።”

ፈረንሣይ:- “ሃያ ሦስት ሰዎች ሞተዋል፣ ዘጠኙ የደረሱበት አልታወቀም፣ በሺህ የሚቆጠሩ ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። . . . ሰኞ ዕለት በወረደው ዶፍ ሦስት ሰዎች በመብረቅ ተመትተው ሞተዋል። . . . አንድ የእሳት አደጋ ሠራተኛ መኪናቸው ውስጥ እንዳሉ በጎርፍ የተወሰዱ ባልና ሚስቶችን ካዳነ በኋላ ሞቷል።”

ጀርመን:- “በፌደራላዊ ሪፑብሊኳ ታሪክ በዚህ ‘በክፍለ ዘመኑ ጎርፍ’ የታየውን ያህል ከተሞችና መንደሮች ባዶ የቀሩበት ጊዜ የለም። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መንደራቸውን ጥለው ተሰድደዋል። ብዙዎቹ የተሰደዱት ለጥንቃቄ ሲሉ ነበር። አንዳንዶቹ ግን ነፍሳቸው ሊተርፍ የቻለው በመጨረሻው ደቂቃ በጀልባዎችና በሄሊኮፕተሮች እርዳታ ነው።”

ሩማንያ:- “ከሐምሌ አጋማሽ ጀምሮ በወረደው ከባድ ዝናብ ምክንያት [አሥራ ሁለት] የሚያክሉ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።”

ሩሲያ:- “በጥቁር ባሕር ዳርቻ ላይ ቢያንስ 58 ሰዎች ሞተዋል። . . . ነፋስ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ እንደሚመጣ ማስጠንቀቂያ ከተነገረ በኋላ ባሕሩ ውስጥ የሰመጡ 30 መኪኖች ፈላጊ ሳያገኙ እዚያው ቀርተዋል።”

በአውሮፓ ብቻ የተወሰነ አይደለም

ሱድዶቸ ጻይቱንግ የተባለው የጀርመን ዕለታዊ ጋዜጣ እንደዘገበው “በእስያ፣ በአውሮፓና በደቡብ አሜሪካ እንደ አዲስ ያገረሸው ዶፍ ዝናብ ብዙ ጉዳት አስከትሏል። ረቡዕ ዕለት በኔፓል በደረሰው የመሬት መደርመስ ቢያንስ 50 ሰዎች ሞተዋል። በቻይና ደቡባዊ ክፍል የደረሰው ከባድ አውሎ ነፋስ ለስምንት ሰዎች መሞት ምክንያት ከመሆኑም በላይ በመካከለኛው ቻይና ከባድ ዝናብ እንዲዘንብ አድርጓል። በቻይና በደረሰው ጎርፍ ምክንያት የሚኮንግ ወንዝ በ30 ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ መጠን በመሙላቱ በሰሜናዊ ምሥራቅ ታይላንድ ከ100 የሚበልጡ ቤቶች ሰምጠዋል። . . . በአርጀንቲና ቢያንስ አምስት ሰዎች በከባዱ ዝናብ ምክንያት ሰምጠዋል። . . . በቻይና በበጋ የወረደው ዶፍ ዝናብ ከአንድ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችን ገድሏል።”

ብዙዎቹ የዓለም ክፍሎች በዝናብ ሲጥለቀለቁ ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ በከባድ ድርቅ ትጠቃ ነበር። የሚከተለው ሪፖርት ቀርቦ ነበር:- “የውኃ ጉድጓዶች መድረቅና መሟጠጥ፣ ብዙ ወንዞች ለብዙ ዘመናት ታይቶ በማይታወቅ መጠን መቀነሳቸውና በደኖች ላይ ይደርስ የነበረው ሰደድ እሳት ከወትሮው ከእጥፍ በላይ መጨመሩ በአገሪቱ በሙሉ እጅግ አሳሳቢ ሆኖ ነበር። በአዝርዕትና በግጦሽ ሣር ላይ የደረሰው ጥፋት፣ የመጠጥ ውኃ መቀነስ፣ ሰደድ እሳትና አቧራ ያስነሳው አውሎ ነፋስ ያደረሰው ጉዳት ሲታሰብ ድርቁ በ2002 ያደረሰው ኪሣራ በቢሊዮን ዶላር የሚገመት እንደሚሆን ሊቃውንት ይገምታሉ።”

የሰሜናዊ አፍሪካ አንዳንድ ክፍሎች ከ1960ዎቹ ዓመታት ጀምሮ በከፍተኛ ድርቅ ተመትተዋል። ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት “የሚጥለው ዝናብ መጠን በ20ኛው መቶ ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ይጥል ከነበረው ከ20 እስከ 49 በመቶ በመቀነሱ መጠነ ሰፊ ረሃብና ሞት አስከትሏል።”

በምሥራቃዊ ፓስፊክ ውቅያኖስ መሞቅ ምክንያት የሚፈጠረው ኤል ኒኞ የተባለ የአየር ሁኔታ ክስተት በሰሜንና በደቡብ አሜሪካ ጎርፍና ሌላ ዓይነት የአየር ሁኔታ መዛባት ሲያስከትል ኖሯል። * ሲ ኤን ኤን የተባለው የዜና አገልግሎት የ1983/84ቱ ኤል ኒኞ “1,000 ለሚያክሉ ሰዎች መሞት ምክንያት ሲሆን በሁሉም አህጉራት ላይ ማለት ይቻላል ከአየር ጠባይ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው አደጋዎች በማስከተል በንብረትና በከብቶች ላይ 10 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ውድመት አድርሷል” ሲል ዘግቧል። ይህ የአየር ሁኔታ ክስተት ከታወቀበት ከ19ኛው መቶ ዘመን ወዲህ በተወሰነ የዓመታት ልዩነት (በየአራት ዓመቱ) ብቅ ሲል ቆይቷል። ይሁን እንጂ ኤል ኒኞ የሚመጣበትን የጊዜ ልዩነት እንዳሳጠረና ወደፊትም ቶሎ ቶሎ እንደሚከሰት የሚያምኑ ሊቃውንት አሉ።

በዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የበረራና ሕዋ አስተዳደር የተዘጋጀ አንድ ጽሑፍ እንዲህ በማለት ሊያረጋጋን ይሞክራል:- “ሲያጋጥመን የቆየው እንግዳ የሆነ የአየር ጠባይ ማለትም ታይቶ የማይታወቅ የበልግ ንዳድ ወይም ዶፍ ዝናብ የዘነበበት የክረምት ወራት በአየር ሁኔታ ላይ በደረሰ ጤናማ አካባቢያዊ ለውጥ ምክንያት የሚመጣ ነው።” ይሁን እንጂ ከባድ ችግር ሊኖር እንደሚችል የሚጠቁሙ ምልክቶች አሉ። የአካባቢ ደህንነት ተሟጋች የሆነው ግሪንፒስ የተባለ ድርጅት “በጣም ኃይለኛ የሆኑ አውሎ ነፋሶችንና ከባድ ዝናቦችን ጨምሮ አደገኛ የሆኑ የአየር ጠባዮች በመላው ዓለም ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ይቀጥላሉ። ይበልጥ ከባድ የሆኑ ድርቆችና ጎርፎች የምድርን ገጽ ቃል በቃል በመለወጥ በባሕር ዳርቻ በሚገኙ አካባቢዎችና በደኖች ላይ ከፍተኛ ውድመት ያስከትላሉ” ብሏል። ይህ አባባል ተጨባጭ ማስረጃ ይኖረው ይሆን? ከኖረውስ “የእነዚህ አደገኛ የአየር ጠባዮች” መንስኤ ምንድን ነው?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.14 በግንቦት 2000 የንቁ! እትም ላይ የወጣውን “ኤል ኒኞ ምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 2 እና 3 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በጀርመን (ከላይ) እና በቼክ ሪፑብሊክ (በስተ ግራ) የደረሰ የጎርፍ መጥለቅለቅ