ከፆታ ጋር በተያያዘ ሰዎች የፈለጉትን አኗኗር ቢመርጡ አምላክ ይቀበለዋል?
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
ከፆታ ጋር በተያያዘ ሰዎች የፈለጉትን አኗኗር ቢመርጡ አምላክ ይቀበለዋል?
“ከፆታ ጋር በተያያዘ የትኛውን አኗኗር መምረጥ እንዳለብኝ የማውቀው ስንት ዓመት ሲሞላኝ ነው?” ለወጣቶች ምክር ለሚሰጥ አንድ አምድ ይህን ጥያቄ የላከችው አንዲት የ13 ዓመት ልጅ ናት። ይህ ጥያቄዋ ፆታን በተመለከተ የፈለግኩትን አኗኗር መምረጥ እችላለሁ ብለው የሚያስቡትን የብዙዎችን አመለካከት የሚያስተጋባ ነው።
አንዳንድ ሰዎች የፆታ ስሜታቸውን በተመለከተ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ ይጋባሉ። ሌሎች ደግሞ እንደ ግብረ ሰዶም ያሉ ከተፈጥሮ ውጪ የሆኑ ልማዶችን እንደ አማራጭ አድርገው ይከተላሉ። አንዳንዶች በአለባበሳቸው ወይም በአኳኋናቸው ሴቶቹ እንደ ወንድ፣ ወንዶቹ ደግሞ እንደ ሴት ለመሆን ሲጥሩ ይታያሉ፤ አልፎ ተርፎም በሕክምና ፆታቸውን የሚቀይሩም አሉ። ከሕፃናት ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸም ምንም ስህተት የለበትም ብለው የሚከራከሩም አልታጡም።
ፆታንና ወሲብን በተመለከተ አንድ ሰው የፈለገውን መምረጥ ይችላል? የአምላክ ቃል ይህን በሚመለከት ምን ይላል?
“ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው”
በዘፍጥረት መጽሐፍ ዘገባ መሠረት ሰዎችን ወንድና ሴት አድርጎ የፈጠረው አምላክ ራሱ ነው። ዘገባው እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ . . . ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። እግዚአብሔርም ባረካቸው፣ እንዲህም አላቸው:- ብዙ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም።”—ዘፍጥረት 1:27, 28
አምላክ ሰዎችን የፈጠራቸው የፈለጉትን መምረጥ እንዲችሉ አድርጎ ሲሆን በዚህ ነፃነታቸው የሚጠቀሙበት አጋጣሚም ሰጥቷቸዋል። (መዝሙር 115:16) ሰው በምድር ላይ ያሉትን እንስሳት ሁሉ የመንከባከብ ኃላፊነት የተሰጠው ከመሆኑም በላይ ተስማሚ ስም እንዲያወጣላቸውም ተደርጎ ነበር። (ዘፍጥረት 2:19) ከፆታ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ረገድ ግን አምላክ የማያሻሙ መመሪያዎችን ሰጥቷል።—ዘፍጥረት 2:24
በአዳም አለመታዘዝ ምክንያት ሁላችንም አለፍጽምናን ወርሰናል። ስለዚህ ከአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ ጋር የማይጣጣሙትን ሥጋዊ ድክመቶቻችንንና ፍላጎቶቻችንን መዋጋት አለብን። አምላክ በሙሴ በኩል በሰጠው ሕግ ላይ የሚጠላቸውን የወሲብ ድርጊቶች የዘረዘረ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ምንዝር፣ በዘመዳሞች መካከል የሚደረግ የፆታ ግንኙነት፣ ግብረ ሰዶምና ከእንስሳት ጋር የሚፈጸም ግንኙነት ይገኙበታል። (ዘሌዋውያን 18:6-23) በተጨማሪም አምላክ ከሥነ ምግባር ውጪ ለሆነ ዓላማ ወንድ ሴትን፣ ሴት ደግሞ ወንድን እንዳይመስሉ አስጠንቅቋል። (ዘዳግም 22:5) አምላክ የሚደግፈው የፆታ ግንኙነት በሕግ በተጋቡ ወንድና ሴት መካከል የሚደረገውን ብቻ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። (ዘፍጥረት 20:1-5, 14፤ 39:7-9፤ ምሳሌ 5:15-19፤ ዕብራውያን 13:4) አምላክ ያወጣቸው እንደነዚህ ያሉት የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ትክክል ናቸው?
ምርጫው የማን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ሰው በፈጣሪው ፊት ያለውን ቦታ በሸክላ ሠሪ እጅ ካለ ጭቃ ጋር ያመሳስለዋል። እንዲህ ይላል:- “አንተ ሰው ሆይ፣ ለእግዚአብሔር የምትመልስ ማን ነህ? ሥራ ሠሪውን:- ስለ ምን እንዲህ አድርገህ ሠራኸኝ ይለዋልን?” (ሮሜ 9:20) የወንድና የሴት አፈጣጠር ራሱ እርስ በርስ በፆታ መፈላለጋቸው ተፈጥሯዊ መሆኑን ያሳያል። ስለሆነም ከተመሳሳይ ፆታ፣ ከእንስሳ ወይም ከሕፃን ጋር ወሲብ የመፈጸም ፍላጎት ከተፈጥሮ ውጪ ነው።—ሮሜ 1:26, 27, 32
በዚህም ምክንያት እንዲህ ያለ ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ የወሲብ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች አምላክን እየተቃወሙ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ከሠሪው ጋር ለሚታገል ወዮለት! በምድር ሸክላዎች መካከል ያለ ሸክላ ነው። ጭቃ ሠሪውን:- ምን ትሠራለህ? ወይስ ሥራህ:- እጅ የለውም ይላልን?” የሚል ማስጠንቀቂያ ይዞአል። (ኢሳይያስ 45:9) ከዚህ አንጻር ሰዎችን የሠራ ፈጣሪ ፆታን በሚመለከት መመሪያ መስጠቱ ተገቢ ነው። ሰዎችም እንደዚህ ያለውን መመሪያ የመከተል ግዴታ አለባቸው።
የራስን ዕቃ በቅድስናና በክብር መያዝ
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ጳውሎስ ፆታን በሚመለከት ለክርስቲያኖች መመሪያ በሰጠ ጊዜ ተመሳሳይ አገላለጽ ተጠቅሟል። ‘ከእናንተ እያንዳንዱ የራሱን ዕቃ በፍትወት ምኞት ሳይሆን በቅድስናና በክብር ያገኝ ዘንድ ይወቅ’ ብሏል። (1 ተሰሎንቄ 4:4, 5) ጳውሎስ የአንድን ሰው አካል ከዕቃ ጋር አመሳስሎታል። ይህንን ዕቃ በቅድስናና በክብር መያዝ ሲባል አስተሳሰብንና ፍላጎትን ከአምላክ የሥነ ምግባር ሕጎች ጋር ማስማማት ማለት ነው።
እርግጥ ይህ ቀላል ላይሆን ይችላል። በሕፃንነቱ በፆታ የተነወረ፣ በወላጆቹ ወይም በአሳዳጊዎቹ መጥፎ ባሕርይ ምክንያት ስለ ወንድነት ወይም ስለ ሴትነት የተዛባ አመለካከት የተቀረጸበት አሊያም ገና በለጋ ዕድሜው ለብልግና ሥዕሎች የተጋለጠ ሰው በዚህ ረገድ ሊቸገር ይችላል። የዘር ውርስ፣ የሆርሞን መዛባትና የሥነ ልቦና ችግሮችም አንድ ሰው ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ የፆታ ስሜት እንዲኖረው ሊያደርጉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ፈጣሪያችን ይህን ችግር ለመወጣት እገዛ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ እርዳታና ድጋፍ የሚሰጥ መሆኑን ማወቅ የሚያጽናና ነው።—መዝሙር 33:20፤ ዕብራውያን 4:16
ታላቁ ሸክላ ሠሪ እንዲቀርጽህ ፍቀድለት
አንድ ሸክላ ሠሪ ጭቃውን ቅርጽ ማስያዝ ከመጀመሩ በፊት በሸክላ መሥሪያው መዘውር መሃል ላይ ያስቀምጠዋል። ከዚያም መዘውሩ ሲሽከረከር ጥበብ በተካኑ ጣቶቹ ጭቃውን ጫን ጫን እያደረገ የሚፈለገውን ቅርጽ ያስይዘዋል። እኛም አምላክ ደስ የሚሰኝብን ዓይነት ሰዎች ሆነን ለመቀረጽ እንድንችል ሕይወታችንን ጊዜ ከማይሽራቸው የአምላክ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ሕጎች ጋር ማስማማት ይኖርብናል። የሚፈለግብንን ጥረት ማድረግ ከጀመርን አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በቅዱስ መንፈሱና በክርስቲያናዊ የወንድማማች ማኅበር አማካኝነት ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ይቀርጸናል። በዚህ ጊዜ አምላክ በግለሰብ ደረጃ እየተንከባከበን እንዳለ ይሰማናል።
እርግጥ ነው፣ ፈጣሪያችን ለእኛ የሚበጀንን እንደሚያውቅ በመተማመን በእርሱ ጥበብ ላይ ትምክህት ማዳበር ይኖርብናል። በጸሎትና መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት በማጥናት እንዲህ ያለውን ትምክህት ማዳበር እንችላለን። ተገቢ ያልሆነ የፆታ ፍላጎት የሚያስቸግረው ሰው ይሖዋ ለእርሱ የሚበጀውን እንደሚያውቅ የሚተማመን ከሆነ አመለካከቱን በማስተካከል በፈጣሪው እጅ በቀላሉ ሊቀረጽ ይችላል። አንደኛ ጴጥሮስ 5:6, 7 “እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት” ይላል።
መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን ማንበባችን ተስፋ ሳይቆርጡ ከነበረባቸው የሥጋ ፍላጎት ጋር ትግል ካደረጉ በርካታ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ጋር እንድንተዋወቅ ይረዳናል። እነዚህ የታማኝነት ምሳሌዎች እንዴት የሚያበረታቱ ናቸው! ሐዋርያው ጳውሎስ “እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?” ብሎ ሲናገር ሮሜ 7:24, 25
ምን ተሰምቶት እንደሆነ መገመት እንችላለን። ሆኖም ጳውሎስ “በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን” በማለት ለራሱ ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ዋነኛውን የእርዳታ ምንጭ ጠቁሞናል።—ለውጥ ለማድረግ የሚረዳ ኃይል
የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ከሚያደርግልን እርዳታም ተጠቃሚዎች ልንሆን እንችላለን። መንፈስ ቅዱስ ለውጥ ለማድረግ የሚረዳ ከፍተኛ ኃይል ሊሆንልን ይችላል። መንፈስ ቅዱስ ‘አሮጌውን ሰው አስወግደን እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው እንድንለብስ’ እገዛ ያደርግልናል። (ኤፌሶን 4:22-24) በሰማይ የሚኖረው አፍቃሪው አባታችን ይህን ለውጥ ለማድረግ እንድንችል በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት እንዲረዳን የምናቀርብለትን ልባዊ ልመና ምንጊዜም ይሰማል። ኢየሱስ ‘በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱሱን ይሰጣቸዋል’ በማለት አረጋግጦልናል። (ሉቃስ 11:13) ቢሆንም ኢየሱስ “ለምኑ፣ ይሰጣችሁማል” በማለት እንደተናገረው አለማቋረጥ መጸለያችን አስፈላጊ ነው። (ማቴዎስ 7:7) በተለይ ኃይለኛ የወሲብ ፍላጎትን ተቆጣጥሮ ለማሸነፍ ጸሎት በጣም አስፈላጊ ነው።
በተጨማሪም አምላክ የተለያየ ዓይነት አስተዳደግ ያላቸውን ሰዎች ባቀፈው በእውነተኛው ክርስቲያናዊ የወንድማማች ማኅበር አማካኝነት ይረዳናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በቆሮንቶስ ጉባኤ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች በቀድሞ ሕይወታቸው “ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ” ነበሩ። ቢሆንም ተለውጠዋል። በክርስቶስ ደም ታጥበው ስለነጹ በአምላክ ፊት ተቀባይነት አግኝተዋል። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) ዛሬም ቢሆን አንዳንዶች ተመሳሳይ ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። እነዚህ ሰዎች ተገቢ ካልሆኑ ምኞቶች ጋር በሚያደርጉት ትግል ከክርስቲያን ጉባኤ ድጋፍ ሊያገኙ ይችላሉ።
ታዲያ አንድ ሰው ክርስቲያን ሲሆን ከተፈጥሮ ውጪ ከሆኑ ምኞቶቹ ወይም ፆታውን በሚመለከት ከሚሰማው ግራ መጋባት ወዲያውኑ ይላቀቃል ማለት ነው? ላይሆን ይችላል። አንዳንድ ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች አዘውትረው ተግባራዊ ማድረጋቸው ጤናማ ሕይወት እንዲኖሩ አስችሏቸዋል። ያም ሆኖ እነዚህ ክርስቲያኖች አብዛኛውን ጊዜ ተገቢ ያልሆኑ ምኞቶችን ለማሸነፍ የዕለት ተዕለት ትግል ማድረግ ግድ ሆኖባቸዋል። በመሆኑም አምላክን የሚያገለግሉት ምሳሌያዊ ‘የሥጋ መውጊያ’ እያለባቸው ነው ለማለት ይቻላል። (2 ቆሮንቶስ 12:7) ተገቢ ያልሆኑ ዝንባሌዎችን መዋጋታቸውን እስከቀጠሉና የሥነ ምግባር አቋማቸውን እስከጠበቁ ድረስ አምላክ ንጹሕ እንደሆኑ ታማኝ አገልጋዮቹ አድርጎ ይመለከታቸዋል። የሰው ዘር በሙሉ ‘ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት የሚደርስበትን’ ጊዜ በተስፋ ሊጠባበቁ ይችላሉ።—ሮሜ 8:21
እስከዚያው ድረስ ግን አምላክን ማስደሰት የሚፈልጉ ሁሉ እርሱ ያወጣቸውን የጽድቅ የአቋም ደረጃዎቹን የሙጥኝ ብለው መኖር አለባቸው። እውነተኛ ክርስቲያኖች የራስ ወዳድነት ዝንባሌዎቻቸውን ከመከተል ይልቅ አምላክን ለማገልገል ይመርጣሉ። በሁሉም የኑሮ ዘርፍ በትሕትና ራሳቸውን ለአምላክ ፈቃድ የሚያስገዙ ሁሉ ዘላለማዊ ፍስሃና ደስታ በማግኘት ይባረካሉ።—መዝሙር 128:1፤ ዮሐንስ 17:3
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ከፆታ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ረገድ አምላክ የማያሻሙ መመሪያዎችን ሰጥቷል
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በመጀመሪያው መቶ ዘመን አንዳንድ የቆሮንቶስ ጉባኤ ክርስቲያኖች በቀድሞ ሕይወታቸው “ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ” የነበሩ ቢሆንም ተለውጠዋል
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከፍተኛ የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን ለመጠበቅ ይረዳል