በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የትኛውም ዓይነት የተፈጥሮ አደጋ ሊያጠፋው የማይችል ነገር

የትኛውም ዓይነት የተፈጥሮ አደጋ ሊያጠፋው የማይችል ነገር

የትኛውም ዓይነት የተፈጥሮ አደጋ ሊያጠፋው የማይችል ነገር

ጀርመን፣ ኦስትሪያ፣ ሜክሲኮ እና ኮሪያ የሚገኙ የንቁ! መጽሔት ዘጋቢዎች እንደጻፉት

በ2002 በብዙ አገሮች በአየር መዛባት ምክንያት ብዙ አደጋ ደርሶ ነበር። አውሮፓ በተከታታይ በአደገኛ ጎርፍ ተመትታለች። በሌላው የዓለም ክፍል የምትገኘው ሜክሲኮ አውዳሚ በሆነ አውሎ ነፋስ፣ ኮሪያ ደግሞ ነፋስ በቀላቀለ ዶፍ ዝናብ ተመትተዋል። እነዚህ ክስተቶች በእጅጉ የሚያሳዝኑ ቢሆኑም በእውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል ያለውን የፍቅር ሰንሰለት ግን ይበልጥ እንዲጠናከር አድርገዋል።

በአውሮፓ የደረሰውን ጎርፍ ተከትሎ የምዕራብ ጀርመን ቻንስለር የነበሩት ሄልሙት ሽሚት የአደጋው ተጎጂዎች ምን ዓይነት እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተጠይቀው ነበር። “ሰዎቹ ምግብ፣ መጠለያ፣ ገንዘብና መንፈሳዊ እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል” ሲሉ መልሰዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ለጎርፉ ተጎጂዎች ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ እርዳታ በማድረግ ረገድ የማይናቅ ድርሻ አበርክተዋል። በጀርመን፣ በኦስትሪያ፣ በሜክሲኮ እና በኮሪያ ያከናወኑትን የመልሶ ማቋቋም ሥራ እንመልከት።

ፈቃደኛ ሠራተኞች በጀርመን

የጎርፍ አደጋ እንደሚመጣ በታወቀ ጊዜ በጀርመን አገር የሚኖሩ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ሕዝቡ በአጠቃላይ ጎርፉን ለመቆጣጠር ያደርግ ከነበረው ጥረት ጋር መተባበር ጀመሩ። የድረስደን ከተማ ነዋሪ የሆነችው የ19 ዓመቷ ካትሊን “እጄን አጣጥፌ መቀመጥ አልቻልኩም። ያላቸውን ሁሉ የማጣት አደጋ የተደቀነባቸው ሰዎች መኖራቸውን እንደሰማሁ እርዳታ ለመስጠት ራሴን አቀረብኩ” ብላለች።

የጀርመን ምሥክሮች አፋጣኝና ቀልጣፋ እርዳታ ለመስጠት በሚያስችላቸው መንገድ መደራጀት ጀመሩ። ክርስቲያኖች እንደመሆናቸው መንፈሳዊ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን የመርዳት ግዴታ እንዳለባቸው ተሰማቸው። ለጎረቤቶቻቸው ያላቸውንም ፍቅር አሳይተዋል። (ማርቆስ 12:31) ከ2000 የሚበልጡ ፈቃደኛ ሠራተኞች 8 እና 12 ሰዎች በሚገኙባቸው ቡድኖች ተከፋፈሉና እያንዳንዱ ቡድን አደጋው በደረሰበት አካባቢ የሚያከናውነው የተለየ ሥራ ተሰጠው። በዘልተርስ፣ ጀርመን በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ስለ አደጋውና ምን መርዳት እንደሚችሉ ለመጠየቅ ስልክ የሚደውሉ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን መልእክት ለመቀበል ብቻ 13 የስልክ መስመሮች ተዘጋጁ።

ራኒ እና ዲና ወዳጆቻቸውና ጎረቤቶቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች እንዲያውቁ የሚረዱ የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ናቸው። ጎርፉ እየቀረበ መምጣቱን እንደሰሙ ወደ ድረስደን ማዘጋጃ ቤት ሕንፃ ሄዱና ታሪካዊ የሆነውን ይህን ሕንፃ ለማዳን በሚደረገው የሞት ሽረት ትግል የበኩላቸውን እርዳታ ሰጡ። ጎርፉ ጎደል ማለት እንደ ጀመረ ራኒ እና ዲና ከሌሎች ምሥክሮች ጋር በመሆን በቆሻሻ ጎርፍ ተጥለቅልቆ የነበረውን የፍራይታል የመንግሥት አዳራሽ ማጽዳት ጀመሩ። ከዚያም ቡድኑ ጎረቤቶቻቸውን መርዳት ጀመረ። ከአዳራሹ ፊት ለፊት የሚገኝ የአንድ ምግብ ቤት ባለቤት ምሥክሮቹ በምድር ቤቱ ውስጥ የተከመረውን ጭቃና ጥራጊ ስላጸዱለት አመስግኗል።

ዚግፍሪት እና ሃነሎረ የሚኖሩት ከደቡባዊ ምሥራቅ ድረስደን 40 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ኮልምኒትዝ የምትባል መንደር ነው። መንደራቸውን ለሁለት ሰንጥቆ ያልፍ የነበረው ወንዝ አለወትሮው ሞልቶ ዳርቻውን ጥሶ በመውጣቱ ቤታቸውና አትክልታቸው በጎርፍ ተጥለቀለቀ። ጎርፉ ጎደል እንዳለ የዚያ አካባቢ ነዋሪ ያልሆኑ 30 የሚያክሉ ምሥክሮች መጥተው ቤታቸውን በማጽዳት ሲረዷቸው ዚግፍሪት እና ሃነሎረ በጣም ተገረሙ። ቡድኑ በመቀጠል በአካባቢው ያሉትን ሌሎች ግቢዎች ማጽዳት ጀመረ። በርካታ የመንደሩ ነዋሪዎች አይተው የማያውቋቸውን ሰዎች ለመርዳት ሲሉ 100 ኪሎ ሜትር ያህል ተጉዘው እንዲመጡ ያነሳሳቸው ምን እንደሆነ ምሥክሮቹን ጠይቀዋቸዋል። በዚህም የተነሣ ምሥክሮቹ ለኮልምኒትዝ የጎርፍ ተጎጂዎች መንፈሳዊ ማጽናኛ ሊሰጡ ችለዋል።

በዊትንበርግ ከተማ ዳርቻ የሚገኙ ቤቶችም በጎርፉ ተጎድተዋል። ፍራንክ እና ኤልፍሪደ የሚባሉ የይሖዋ ምሥክር ባልና ሚስቶች ጎርፉ ከመምጣቱ ከበርካታ ቀናት በፊት ጀምሮ ወንዙ ዳርቻውን ሰብሮ እንዳይፈስ አሸዋ የተሞሉ ጆንያዎች እየደረደሩ ድንበሩን ሲያጠናክሩ ሰንብተዋል። ጎርፉ መጉደል እንደጀመረም ፍራንክና ኤልፍሪደ ምግብና ማጽናኛ በመስጠት በጎርፉ የተጎዱትን ሰዎች መጎብኘት ጀመሩ። ፍራንክ እንዲህ በማለት ያስታውሳል:- “አንዲት የጠየቅናት ሴት ከዚህ በፊት የማታውቀን ሰዎች ምንም ገንዘብ ሳንጠይቃት ምግብ ሠርተን ስለወሰድንላት ልታምን አልቻለችም። ከራሷ ቤተ ክርስቲያን አንድም ሰው መጥቶ እንዳልጠየቃት ነገረችን። ምግብ ያመጣላት ድርጅትም ቢሆን ባመጣ ቁጥር ገንዘብ አስከፍሏታል። የይሖዋ ምሥክሮች በፊት እንደሚያደርጉት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ሳይሆን ምግብ ይዘው ሲመለከቱ ብዙ ሰዎች ተደንቀዋል።”

ኦስትሪያ—ለድንገተኛ አደጋ የተሰጠ አፋጣኝ ምላሽ

ጎርፍ በኦስትሪያም ብዙ ጉዳት አድርሷል። የእርዳታውን ሥራ በበላይነት የሚመሩ ሦስት ኮሚቴዎች ተቋቋሙ። ከባድ ጉዳት የደረሰባቸውን ሦስት የመንግሥት አዳራሾች ለመጠገኑ ሥራ ቅድሚያ ተሰጠ። በተጨማሪም ከይሖዋ ምሥክሮች መካከል 100 የሚያክሉ ቤተሰቦች በጎርፉ ሲጎዱ 50 የሚያክሉ ቤቶች ተጥለቅልቀዋል። አንዳንዶቹ ከለበሱት ልብስ ሌላ የቀራቸው ምንም ነገር አልነበረም። የኦስትሪያ ቅርንጫፍ ቢሮ ስለደረሰው ሁኔታ ለአገሩ ጉባኤዎች ካሳወቀ በኋላ እርዳታ ማሰባሰብ ጀመረ። እስከ መስከረም ድረስ 270,000 ብር የሚያክል ገንዘብ ሊሰበሰብ ችሏል።

አንዲት እናት እንደሚከተለው ስትል ጽፋለች:- “የስምንት ዓመት ልጄ በጣም ገንዘብ ቆጣቢ ነው። ሠላሳ ብር ያህል አጠራቅሞ ነበር። አንዳንድ ወንድሞቻችን ንብረታቸውን በሙሉ እንዳጡ በሰማ ጊዜ ግን ያጠራቀመውን ገንዘብ በሙሉ ለእርዳታ መዋጮ ሰጠ።”

የይሖዋ ምሥክሮችን የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ሥራ በሚከታተለው የአካባቢ ሕንፃ ሥራ ኮሚቴ ተቆጣጣሪነት በጎርፉ የተጎዱ ቤቶችን የሚያድሱ ቡድኖች ተደራጁ። አንድ ታዛቢ “እናንተ የምታከናውኑትን ይህን ሥራ ጋዜጦች መዘገብ ነበረባቸው” ብሏል። እንዲያውም አንዳንዶች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የነበራቸውን አመለካከት ለመለወጥ ተገድደዋል። አንድ ምሥክር ወላጅ “እስካሁን ድረስ የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ልጆቼ ስለ እምነቴ ልነግራቸው ስጀምር ሊያዳምጡኝ አይፈልጉም ነበር። አሁን ግን ለመጀመሪያ ጊዜ መስማት ጀምረዋል” ብላለች።

ምሥክሮች ያልሆኑ በርካታ ሰዎችንም ለመርዳት ጥረት ተደርጓል። ለምሳሌ አንዲት ሴት አንድ የይሖዋ ምሥክር ጠዋት በ1:30 ቤቷ ድረስ መጥቶ እርዳታ ያስፈልጋት እንደሆነ ሲጠይቃት ልቧ በጣም ተነክቷል። ሴቲቱ ቤቷ በጎርፍ መጥለቅለቅ ጀምሮ ስለነበረ ቤቷን ጥላ መውጣት ነበረባት። ስትመለስ ግን ምሥክሮቹ የተዉትን ማስታወሻ አጥሯ ላይ አገኘች። “እርዳታ የሚያስፈልግሽ ከሆነ ቶሎ ብለሽ ንገሪን” የሚል ነበር። ምሥክሮቹ ቤቷንና ግቢዋን ከጭቃና ከፍርስራሽ በማጽዳት ረድተዋታል።

አንድ መቶ ምሥክሮች የሚገኙበት አንድ ቡድን በአካባቢው የሚኖሩ ምሥክሮችንና ጎረቤቶቻቸውን ለመርዳት አው ወደሚባል ከተማ ተጉዞ ነበር። የቡድን መሪዎቹ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ እርዳታ ይፈልጉ እንደሆነ ነዋሪዎቹን ጠየቋቸው። ምሥክሮቹ እንደ ፓምፕ፣ መጥረጊያና አካፋ የመሰሉ ውኃ ማስወገጃና ማጽጃ መሣሪያዎች ይዘው ሲያዩ ብዙ ሰዎች ተደንቀዋል። ለባለቤቶቹ ሳምንት ያህል ሊወስድ ይችል የነበረ ሥራ በሰዓታት ጊዜ ውስጥ ሊጠናቀቅ ችሏል። ሰዎቹ ዓይናቸው እንባ እያቀረረ ነበር የተመለከቱት።

በእርዳታው ሥራ የተካፈሉት ምሥክሮች ቁጥር 400 እንደሚደርስ ሲገመት አብዛኛውን ጊዜ ቀንና ሌሊት ሠርተዋል። ተመልካቾች እውነተኛ ክርስትና ምን ያህል ኃይል እንዳለው ለማየት ችለዋል።

ሜክሲኮ በኢሲዶር አውሎ ነፋስ ተመታች

ኢሲዶር የተባለው አውሎ ነፋስ የተነሳው ከቬነዙዌላ በስተ ሰሜን ነበር። ይህ አውሎ ነፋስ ሜክሲኮ የሚገኘውን የዩካታን ባሕረ ገብ መሬት የመታው መስከረም 22, 2002 ነበር። በከባድ ዝናብ የታጀበውና በሰዓት 190 ኪሎ ሜትር ፍጥነት የነበረው ይህ አውሎ ነፋስ ዩካታን እና ካምፔቺ በሚባሉት የሜክሲኮ ክፍለ ሀገራት ላይ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ከባድ ውድመት ሲያደርስ በኪንታና ሩ ክፍለ ሀገር ደግሞ መጠነኛ ጉዳት አድርሷል። በዩካታን ብቻ 95,000 በሚያክሉ ቤቶች ላይ ከባድ ጉዳት ሲደርስ 500,000 የሚያክሉ ሰዎች ደግሞ በአደጋው ተነክተዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች ያደረጉት የመልሶ ማቋቋም ሥራ በጣም የተቀላጠፈ በመሆኑ በሰሜናዊ ሜክሲኮ የሚታተም አንድ ጋዜጣ “የይሖዋ ምሥክሮች ለነፍስ አድን እርዳታ ደርሰዋል” የሚል ርዕስ አውጥቷል። አውሎ ነፋሱ ከመድረሱ በፊት የእርዳታ ኮሚቴ ተቋቋመ። በብዙ መቶዎች ለሚቆጠሩ ምሥክሮች ጊዜያዊ መጠለያ ተዘጋጀ። አጎራባች ጉባኤዎች የድንገተኛ እርዳታ መዋጮ አቀረቡ። ልብስ፣ መድኃኒትና ከ220 ኩንታል የሚበልጥ ምግብ ምሥክር ያልሆኑ ብዙ ሰዎችን ጨምሮ በአውሎ ነፋሱ ለተጎዱ ሰዎች ተከፋፈለ። የአካባቢው ሽማግሌዎች የአደጋውን ተጠቂዎች እንዲጎበኙና እንዲያጽናኑ ተደረገ።

አውሎ ነፋሱ ካለፈ በኋላ የእርዳታ ኮሚቴዎች ተደራጅተው የጠፉ ምሥክሮችን መፈለግ ጀመሩ። ብዙዎች በየደኑና በየጥሻው ውስጥ ያለምግብና ውኃ ሦስት ቀን ያህል ቆይተው ተገኙ። በአንዳንድ አካባቢዎች ጎርፉ በጣም በመሙላቱ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ተውጠው ነበር። በዚህም ምክንያት የጠፉ ሰዎችን ፈልጎ ለማግኘት፣ ከአደጋው አካባቢ አጓጉዞ ለማውጣትና ምግብ ለማቅረብ በሞተር ጀልባዎች መጠቀም አስፈልጎ ነበር።

የአካባቢው ባለ ሥልጣናት ሌሎች ወዳልደፈሩባቸው ቦታዎች ለመሄድ ፈቃደኛ ለሆኑ ምሥክሮች ጀልባዎችንና ሌሎች መሣሪያዎችን አውሰዋል። በመጀመሪያ አንድ የጦር ሠራዊት መኮንን ምሥክሮቹ እንዲህ ያለውን አደገኛ ፍለጋ እንዳያደርጉ ተቃውሞ ነበር። ደፋሮችና መንፈሰ ጠንካሮች መሆናቸውን ከተመለከተ በኋላ ግን “ሰዎቻችሁን ለማዳን ስትሉ አስፈላጊ ከሆነ በሄሊኮፕተር እንኳን ለመሄድ ወደኋላ እንደማትሉ ተመልክቻለሁ። ተሽከርካሪዎቻችን ወደፈለጋችሁበት ቦታ ሊወስዷችሁ ዝግጁ ናቸው” ብሏል።

አንድ ባለ ሱቅ አንዳንድ ምሥክሮች የታሸገ ውኃ ለምን በብዛት እንደሚገዙ ለማወቅ ፈለገ። ለመንፈሳዊ ወንድሞቻቸውና ችግር ላይ የወደቁ ሌሎች ሰዎችን ለመርዳት እንደሆነ ነገሩት። ሰውየው በሱቁ የነበረውን የታሸገ ውኃ በሙሉ በነጻ ሊሰጣቸው ወሰነ። በማግስቱም ተጨማሪ ብዙ ውኃ ሰጣቸው። በሌላ ሱቅ ደግሞ አንድ የሱቁ ደንበኛ ምሥክሮቹ ይህን ያህል ምግብ የሚገዙት ለምን እንደሆነ ጠየቃቸው። የአውሎ ነፋስ አደጋ ለደረሰባቸው ሰዎች እንደሆነ ሲነግሩት ተጨማሪ ምግብ እንዲገዙበት የገንዘብ እርዳታ አደረገ።

በኢሲዶር ምክንያት የንብረት ጥፋት የደረሰባቸው የይሖዋ ምሥክር ቤተሰቦች 3,500 ቢሆኑም የጠፋ ወይም ሕይወቱን ያጣ አንድም ምሥክር አልነበረም። ይሁን እንጂ 331 የሚያክሉ የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶች በጣም ተጎድተው ወይም ወድመው ስለነበረ የመልሶ ግንባታ ፕሮግራም አስፈልጓል። የግንባታ ሥራ ልምድ ያላቸው ምሥክሮች እያንዳንዱን ቤትና የመንግሥት አዳራሽ ጎብኝተው የደረሰውን የጉዳት መጠን አስልተዋል። እስካሁን ድረስ 258 ቤቶች የታደሱ ሲሆን 172 አዳዲስ ቤቶች ተገንብተዋል። በተጨማሪም ጉዳት የደረሱባቸው 19 የመንግሥት አዳራሾች በመጠገን ላይ ናቸው።

በዩካታን ክፍለ ሀገር የሚገኝ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እንደሚከተለው ለማለት ተገፋፍቷል:- “በሌሎች አገሮች ስለተደረጉ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች በጽሑፎቻችን ላይ አንብቤያለሁ። በራስ ላይ ሲደርስ መመልከት ግን የተለየ ነው። የይሖዋ ድርጅትና ውድ ወንድሞቻችን እንዴት ባለ ፍጥነትና አሳቢነት እንደደረሱልን መመልከት የራሴንም ሆነ የብዙ ወንድሞቻችንን እምነት አጠንክሯል።”

አንዲት ሴት “የእኔም ቤተ ክርስቲያን እንደናንተ የይሖዋ ምሥክሮች እርዳታ ቢሰጥ ደስ ይለኝ ነበር” ብላለች። ምሥክሮች ያዳኗት አንዲት ሴት ደግሞ “ዕድሜ ለይሖዋ ምሥክሮች ከሞት ተርፈናል። ቤታችንን ጎርፍ ጠርጎ በወሰደው ጊዜ የራሳቸውን ሕይወት አደጋ ላይ ጥለው እኛን በማዳን ፍቅራቸውን አሳይተውናል” ብላለች።

ኮሪያ በኃይለኛ ውሽንፍር ተመታች

ነሐሴ 31 እና መስከረም 1, 2002 ሩሳ የተባለው ውሽንፍር በኮሪያ ምድር ላይ ከፍተኛ ውድመት አድርሷል። ሶንግፒል ቾ የተባለ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ “በገላ መታጠቢያ ቧንቧ ሥር የቆምን ያህል ነበር። ዝናቡ አለማቋረጥ ዘነበ” ብሏል። ከ24 ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ 870 ሚሊ ሜትር መጠን ያለው ዝናብ ወረደ። ይህን የሚያክል ዝናብ በአንድ ቀን ውስጥ ዘንቦ አያውቅም።

ዘ ኮሪያ ሄራልድ እንዳለው ከሆነ በመላው አገሪቱ 28,100 የሚያክሉ ቤቶችና 85,000 ሄክታር የሚደርስ ማሳ በውኃ ተጥለቀለቀ። ሰባ ሺህ የሚያክሉ ሰዎች ቤታቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገድደዋል። ውሽንፍሩ 301,000 የሚያክሉ የቁም ከብቶችን ሲገድል 126 መርከቦችን አስጥሟል። በመቶ የሚቆጠሩ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎችን ገንድሷል። ከ180 የሚበልጡ ሰዎች እንደሞቱ ወይም የደረሱበት እንዳልታወቀ ተዘግቧል። ከእነዚህ መካከል ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ።

በአውሮፓና በሜክሲኮ እንደተደረገው እዚህም የይሖዋ ምሥክሮች በፍጥነት ተንቀሳቅሰዋል። የእርዳታ መዋጮ በአገሪቱ በሙሉ ከሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጎረፈ። ልብሶች፣ ብርድ ልብሶችና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶች ተሰባሰቡ። አንዳንድ የጉባኤ አባሎች ግን የሚኖሩት በቀላሉ ሊደረስባቸው በማይችሉ ራቅ ባሉ አካባቢዎች ነበር። መንገዶቹ ፈራርሰዋል፣ ድልድዮቹም ተጠርገው ሄደዋል። የኤሌክትሪክም ሆነ የስልክ አገልግሎት የለም። ስለዚህ እንደምንም በእግራቸው ተጉዘው እርዳታ የሚያደርሱ ቡድኖች ተደራጁ። ከአንደኛው የእርዳታ ቡድን ጋር ይሠራ የነበረው ሶንግፒል ቾ እርዳታ ስላደረሱበት አንድ አካባቢ እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “ሰባት ድልድዮችና አብዛኛው የመንገዱ ክፍል ተጠራርጎ ተወስዷል። ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ወደ ከተማው ስንደርስ የፈራረሱና የወላለቁ ቤቶች በያሉበት ይታዩ ነበር። የሞቱ እንስሳት በየቦታው ወድቀው ስለነበረ አካባቢው በመጥፎ ሽታ ተሞልቷል። ስድስቱን ክርስቲያን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በማግኘታችን ግን በጣም ተደሰትን! ንብረታቸውን በሙሉ ቢያጡም ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው አግኝተናቸዋል።”

የይሖዋ ምሥክሮች አደጋው ከመድረሱ በፊት ቅድመ ዝግጅት አድርገው ነበር። የክረምቱ ዝናብ በሚጥልበት ጊዜ ጎርፍ መከሰቱ የማይቀር በመሆኑ በሴውል አካባቢ የሚገኘው የአካባቢ ሕንፃ ሥራ ኮሚቴ እርዳታ ለማቅረብ የሚያስችለውን ቅድመ ዝግጅት አድርጓል። አደጋ በሚደርስበት ጊዜ ፈጣን እርዳታ ለማድረስ እንዲቻል ከ1997 ጀምሮ በየዓመቱ ለፈቃደኛ ሠራተኞች ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቷል።

የአካባቢ ሕንፃ ሥራ ኮሚቴ የእርዳታ ሠራተኞች ካንግኑንግ በምትባለው ምሥራቃዊ የወደብ ከተማ የደረሱት መስከረም 2 ቀን ሲሆን ጽሕፈት ቤታቸውን አካባቢው በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የስብሰባ አዳራሽ አቋቋሙ። ቅድሚያ የሚሰጠው ሥራ ምን ነበር? ከአደጋው ለተረፉት ሰዎች ንጹሕ ውኃ ማቅረብ ነበር። ከባድ ጎርፍ ሲደርስ አብዛኛውን ጊዜ በውኃ ቧንቧዎች ላይ ጉዳት ይደርሳል። የጎርፍ ውኃ ደግሞ በጣም የተበከለ ነው። የአካባቢ ሕንፃ ሥራ ኮሚቴው በውኃ የተሞሉ ትላልቅ የውኃ ማጠራቀሚያ ገንዳዎች ጉዳት ወደደረሰባቸው አካባቢዎች እንዲሄዱ አደረገ።

ጎርፉ ሲጎድል ሁሉ ነገር መጥፎ ሽታ ባለው ጭቃ ተመረገ። ይሁን እንጂ ውጤታማ የሆነ የማጽጃ ዘዴ ተፈጥሮ ነበር። በአካባቢው የሚገኙ ቤቶች በሙሉ በሲሚንቶ የተሠሩ ስለነበሩ ግድግዳዎቹ የተሸፈኑባቸውን ወረቀቶች ካስወገዱ በኋላ ኃይለኛ ግፊት ያለው ውኃ በመርጨት ማጽዳት ተችሏል።

ጎርፍ አብዛኞቹን በኤሌክትሪክ የሚሠሩ መሣሪያዎች ከጥቅም ውጭ ያደርጋል። ይሁን እንጂ በጥቂት ቀናት ውስጥ እንደ ማቀዝቀዣና ውኃ ማሞቂያ የመሳሰሉ መሣሪያዎች ችሎታ ባለው ሠራተኛ ተፈታትተው በደንብ ተጠርገው ከደረቁ በኋላ ተመልሰው ቢገጠሙ አብዛኛውን ጊዜ ሥራ ላይ ሊውሉ ይችላሉ። የአካባቢ ሕንፃ ሥራ ኮሚቴው ይህን ሥራ ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅት አድርጓል። መለወጥ የማያስፈልጋቸው ማሞቂያዎች ቤቱን ለማድረቅ ያገለግላሉ። ይህም ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንት ሊያቆይ ይችላል።

በጎርፍ የተጎዱ ልብሶችና ብርድ ልብሶችም ዳግመኛ አገልግሎት እንዲሰጡ ከተፈለገ በጥቂት ቀናት ውስጥ በደንብ መታጠብ አለባቸው። ከአካባቢው ጉባኤ የተውጣጡ ፈቃደኛ ሠራተኞች የክርስቲያን ወንድሞቻቸውን የቆሸሹ ልብሶች አንድ ላይ ሰበሰቡ። በጎርፉ ጭቃና ቆሻሻ ያደፉ ልብሶችን ማጠብ በጣም አስቸጋሪ ሲሆን የሚታጠቡት ደግሞ በጣም ቀዝቃዛ በሆነ ውኃ ነበር። አንድ የጋዜጣ ዘጋቢ ይህን የፍቅር ተግባር ከተመለከተ በኋላ በአካባቢው በሚታተም አንድ ጋዜጣ ላይ ልብስ የሚያጥቡ ምሥክሮች ሥዕል በትልቁ እንዲወጣ አድርጓል።

በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካና በእስያ የደረሰው ጎርፍ ቤቶችንና ንብረቶችን ከማውደሙም በላይ የብዙ ንጹሐን ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። እነዚህ ሁኔታዎች እጅግ የሚያሳዝኑ ይሁኑ እንጂ አስጨናቂ እንደሚሆን በተነገረለት በዚህ ‘የመጨረሻ ቀን’ የሚከሰቱ የተለመዱ ክስተቶች ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) በተጨማሪም እንደነዚህ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎች እውነተኛ ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸውም ሆነ ለጎረቤቶቻቸው የጠለቀ ፍቅር እንዳላቸው በገሐድ የሚያሳዩ ናቸው። እንዲህ ያለውን ራስ ወዳድነት የሌለበት ፍቅር የትኛውም ዓይነት የተፈጥሮ አደጋ ሊያጠፋው አይችልም።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጀርመን​—በጎርፍ የወደመ ቤት

[በገጽ 11 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ጀርመን​—ከ2000 የሚበልጡ ፈቃደኛ ሠራተኞች አፋጣኝ እርዳታ አድርገዋል

[በገጽ 12 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ኦስትሪያ​—በኦተንሺም የመንግሥት አዳራሻቸውን ሲጠግኑ

በስተ ግራ:- አንድ የፈቃደኛ ሠራተኞች ቡድን ለአካባቢው ምሥክሮችና ለጎረቤቶቻቸው እርዳታ ካደረገ በኋላ ከአው ሲመለስ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ሜክሲኮ​—በስተ ቀኝ:- የእርዳታ ኮሚቴው ከጎርፉ ለተረፉ ሰዎች የመጠጥ ውኃ ሲያቀርብ

በታች:- በአደጋው ለፈረሰ ምትክ የሚሆን ቤት ሲገነባ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ኮሪያ​—ከግራ ወደ ቀኝ:- በጎርፍ የተጥለቀለቀ አንድ የከተማ ክፍል፣ ከፍተኛ ግፊት ባለው ውኃ የማጽዳት ሥራ ሲከናወንና በአካባቢው በሚገኝ ወንዝ ልብስ ሲታጠብ