በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአየሩ ጠባይ እንዲህ የሚለዋወጠው ለምንድን ነው?

የአየሩ ጠባይ እንዲህ የሚለዋወጠው ለምንድን ነው?

የአየሩ ጠባይ እንዲህ የሚለዋወጠው ለምንድን ነው?

“በአሁኑ ጊዜ እያጋጠመን ያለው ጎርፍና ከባድ ዝናብ ቶሎ ቶሎ መከሰታቸውን ይቀጥላሉ።”—ቶማስ ሎስተር፣ በአየር መለዋወጥ ምክንያት የሚደርሱ አደጋዎች ስፔሽያሊስት

እውነት በአየሩ ጠባይ ላይ የተፈጠረ ችግር ይኖር ይሆን? አዎን፣ በእርግጥ ችግር አለበት ብለው የሚሰጉ ብዙ ሰዎች አሉ። የፖትስዳም የአየር ንብረት ውጤቶች ጥናት ተቋም ባልደረባ የሆኑት ሜትሮሎጂስቱ ዶክተር ፒተር ቨርነር “አለመጠን የሚወርደውን ዝናብ፣ ጎርፍ፣ ድርቅና ዶፍ በአጠቃላይ ዓለም አቀፉን የአየር ጠባይና አካሄዱን ልብ ብለን ስንመለከት እነዚህ እየከፉ የሄዱ ሁኔታዎች ባለፉት 50 ዓመታት በአራት እጥፍ ጨምረዋል ለማለት እንችላለን” ብለዋል።

ብዙዎች ያልተለመደ ዓይነት የአየር ጠባይ የሚታየው ከምድር በሚወጣው የተቃጠለ አየር ምክንያት የከባቢ አየሩ ሙቀት በመጨመሩ ነው ይላሉ። ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው ኢንቫይሮመንታል ፕሮቴክሽን ኤጀንሲ እንደሚከተለው በማለት ይገልጻል:- “ግሪን ሃውስ ኢፌክት የሚባለው፣ በከባቢ አየር ውስጥ የሚገኙ እንደ ተን፣ የተቃጠለ አየር፣ ናይትረስ ኦክሳይድና ሜተን ያሉ አንዳንድ ጋዞች ከፀሐይ የሚመጣውን ሙቀት አምቀው በማቆየታቸው ምክንያት የምድራችን ሙቀት ከፍ ሲል ነው። እነዚህ ጋዞች ባይኖሩ ኖሮ የፀሐይ ሙቀት ወደ ሕዋው ይመለስና የምድር አማካይ ሙቀት በ33 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይቀንስ ነበር።”

ይሁን እንጂ ብዙዎች እንደሚሉት ይህን የተፈጥሮ ሂደት ባለማወቅ ያባባሰው የሰው ልጅ ነው። የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የበረራና ሕዋ አስተዳደር በኢንተርኔት በሚያሰራጨው ኧርዝ ኦብዘርቫተሪ የተባለ መጽሔት ላይ የወጣ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “በአሥራዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ሰዎች የሠሯቸው ፋብሪካዎችና መኪኖች በቢሊዮን ቶን የሚመዘን የግሪንሃውስ ጋዞችን ወደ ከባቢው አየር ሲተፉ ቆይተዋል። . . . ብዙ ሳይንቲስቶች የግሪንሃውስ ጋዞች መጠን መጨመር ብዙ ሙቀት ከምድር ከባቢ አየር እንዳይወጣ አድርጓል ብለው ይሰጋሉ። የመኪና መስተዋት ወደ መኪናው የሚገባውን የፀሐይ ሙቀት አፍኖ እንደሚያቆይ ሁሉ እነዚህም ጋዞች ወደ ምድር ከባቢ አየር የገባውን ሙቀት አምቀው ይይዛሉ ማለት ነው።”

ይህን የማያምኑ ሊቃውንት በሰዎች ምክንያት ወደ ከባቢ አየር የገባው የጋዝ መጠን በጣም አነስተኛ ነው ይላሉ። ኢንተርገቨርንመንታል ፓነል ኦን ክላይመት ቼንጅ (IPCC) የተባለው በዓለም ሜትሮሎጂ ድርጅትና በተባበሩት መንግሥታት አካባቢ ፕሮግራም በጋራ የሚተዳደር የምርምር ድርጅት “ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የታየው የምድር ሙቀት መጨመር በአብዛኛው ሰዎች በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ምክንያት የተፈጠረ መሆኑን የሚያረጋግጡ አዳዲስና ጠንካራ ማስረጃዎች ተገኝተዋል” ይላል።

በናሽናል ኦሽኒክ ኤንድ አትሞስፌሪክ አድሚንስትሬሽን የአየር ንብረት ተመራማሪ የሆኑት ፒተር ታንስ “በአኃዝ እንዳስቀምጥ ብጠየቅ 60 በመቶው በእኛ ጥፋት የተፈጠረ ሲሆን . . . በተፈጥሮ ምክንያቶች የተፈጠረው 40 በመቶ ቢሆን ነው” ብለዋል።

በምድር ሙቀት መጨመር ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ ውጤቶች

ታዲያ ሰዎች በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ምክንያት በከባቢ አየር ውስጥ የሚገኘው የጋዝ ክምችት ምን ውጤት አስከትሏል? በአሁኑ ጊዜ የምድር ሙቀት እንደጨመረ አብዛኞቹ ሳይንቲስቶች ይስማማሉ። ይህ ጭማሪ ምን ያህል ከፍተኛ ነው? አይ ፒ ሲ ሲ የተባለ ድርጅት ያወጣው የ2001 ሪፖርት “ከ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ወዲህ የምድር ሙቀት ከ0.4 እስከ 0.8 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሚደርስ ጭማሪ አሳይቷል” ይላል። ብዙ ተመራማሪዎች ይህን የሚያክል አነስተኛ ጭማሪ በአየር ንብረታችን ላይ በጣም ከፍተኛ ለውጥ ሊያስከትል እንደሚችል ያምናሉ።

የምድር የአየር ጠባይ እጅግ በጣም ውስብስብ መሆኑና የምድር ሙቀት መጨመር ምን ዓይነት ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል ሳይንቲስቶች እንኳ በእርግጠኝነት መናገር አለመቻላቸው የሚካድ ነገር አይደለም። ይሁን እንጂ ብዙዎች እንደሚያምኑት የምድር ሙቀት መጨመር በሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ የሚጥለው ዝናብ እንዲጨምር፣ በእስያና በአፍሪካ ድርቅ እንዲበዛ፣ በፓስፊክ አካባቢ ደግሞ የኤል ኒኞ ክስተት እንዲባባስ አድርጓል።

ዓለም አቀፍ መፍትሔ ማግኘት ያስፈልጋል

ይህ ችግር ሰው ሠራሽ እንደሆነ ብዙዎች የሚያምኑ ከሆነ ታዲያ የሰው ልጅ ችግሩን ሊፈታው አይችልም? ከመኪናዎችና ከፋብሪካዎች የሚወጡት በካይ ጋዞች እንዲቀነሱ የሚያስገድዱ ሕጎች ያወጡ አንዳንድ አገሮች አሉ። ይሁን እንጂ ይህ ጥረታቸው የሚመሰገን ቢሆንም ያስገኘው ውጤት ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። የአየር መበከል ዓለም አቀፍ ችግር እንደመሆኑ መፍትሔውም ዓለም አቀፋዊ መሆን ይኖርበታል። በ1992 በሪዮ ደ ጀኔይሮ ስለ ምድር ሥነ ምህዳር የሚነጋገር ስብሰባ ተደርጎ ነበር። በጆሃንስበርግ፣ ደቡብ አፍሪካ ከአሥር ዓመት በኋላ ቀጣይነት ስላለው እድገት የሚነጋገር ዓለም አቀፍ ስብሰባ ተደርጓል። በዚህ በ2002 ተደርጎ በነበረው ስብሰባ ላይ 100 የሚያክሉ የብሔራት መሪዎችን ጨምሮ 40,000 የሚያክሉ ተወካዮች ተገኝተው ነበር።

እንደነዚህ ያሉት ስብሰባዎች ሳይንቲስቶች ወደ አንድ አጠቃላይ የመግባቢያ ሐሳብ ላይ እንዲደርሱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ደር ታገሽፒገል የተባለው የጀርመንኛ ጋዜጣ “በዚያ ጊዜ [በ1992] አብዛኞቹ ሳይንቲስቶች ግሪንሃውስ ስለሚያስከትለው ውጤት ጥርጣሬ የነበራቸው ሲሆን ዛሬ ግን አጠራጣሪ መሆኑ ቀርቷል” ብሏል። ቢሆንም የጀርመን የአካባቢ ሚኒስትር የሆኑት ዮርገን ትሪቲን ችግሩ እንዴት እንደሚወገድ በትክክል የሚያውቅ የለም ይላሉ። ስለዚህ “የጆሃንስበርጉ ስብሰባ የቃል ብቻ ሳይሆን የተግባርም መሆን” እንደሚገባው አበክረው ተናግረዋል።

በአካባቢ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ማስቆም ይቻላል?

የምድር ሙቀት መጨመር በሰው ልጅ ፊት ከተጋረጡት በርካታ አካባቢያዊ ችግሮች መካከል አንዱ ብቻ ነው። ውጤታማ እርምጃ የመውሰዱ ጉዳይ የመናገሩን ያህል ቀላል አይደለም። እንግሊዛዊቷ የእንስሳት ባሕርይ ተመራማሪ ጄን ጉዳል “በአካባቢያችን ላይ ያደረስነውን አስከፊ ጉዳት አሁን በስተመጨረሻ ከተገነዘብን በኋላ ቴክኖሎጂያዊ መፍትሔ ለማግኘት ባለን አቅም ሁሉ ቀን ከሌት እየሠራን ነው” ብለዋል። ይሁን እንጂ “ቴክኖሎጂ ብቻውን በቂ አይሆንም” በማለት ያስጠነቅቃሉ። “ልባችንንም መስጠት ይኖርብናል።”

የምድር ሙቀት ስለ መጨመሩ በድጋሚ እንመልከት። የአካባቢ ብክለትን ለማስወገድ የሚወሰዱ እርምጃዎች ብዙ ወጪ የሚጠይቁ በመሆናቸው አብዛኛውን ጊዜ ከድሃ አገሮች አቅም በላይ ናቸው። በዚህም የተነሳ በኃይል አጠቃቀም ላይ የሚጫኑ ገደቦች ኢንዱስትሪዎች የበለጠ አትራፊ ወደሚሆኑባቸው ድሃ አገሮች እንዲሸሹ ያደርጓቸዋል ብለው የሚሰጉ ሊቃውንት ብዙ ናቸው። በዚህ ምክንያት ከልባቸው የተነሳሱ መሪዎች ሳይቀሩ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል። የአገሮቻቸውን የኢኮኖሚ ጥቅም ቢያስቀድሙ አካባቢያቸው ይበደላል። የአካባቢ ጥበቃን ቢያስቀድሙ ደግሞ ኢኮኖሚያቸው አደጋ ላይ ይወድቃል።

በጆሃንስበርግ የተደረገው ዓለም አቀፍ ጉባኤ አማካሪ ቡድን አባል የነበሩት ሰቨርን ከሊስ-ሱዙኪ ለውጡ የሚመነጨው ግለሰቦች በተናጠል ከሚወስዷቸው እርምጃዎች መሆን አለበት ብለው ይከራከራሉ። “እውነተኛ የሆነ የአካባቢ ሁኔታ መለወጥ በእያንዳንዳችን ላይ የተመካ ነው። መሪዎቻችን ላይ ጥለን ዝም የምንለው ነገር አይደለም። ሁላችንም ባሉብን ኃላፊነቶችና ለውጡን ልናመጣ በምንችልባቸው መንገዶች ላይ ማተኮር ይኖርብናል።”

ሰዎች ለአካባቢያቸው አክብሮት ያሳያሉ ብሎ መጠበቅ ምክንያታዊ ነው። በአኗኗራቸው ረገድ አስፈላጊውን ለውጥ ማድረግ ግን ቀላል አይደለም። ነገሩን ለማስረዳት መኪናዎች ለምድር ሙቀት መጨመር አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ አብዛኞቹ ሰዎች ይስማማሉ። ስለዚህ አንድ ሰው በመኪና የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለመቀነስ ወይም ጨርሶ በመኪና መሄድ ለማቆም ይፈልግ ይሆናል። ይሁን እንጂ እንዲህ ማድረግ ቀላል ላይሆን ይችላል። የዉፐርታል ከተማ አየር ንብረት፣ አካባቢና ኃይል ተቋም ባልደረባ የሆኑት ቮልፍጋንግ ዛክስ እንዳሉት “በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻችን የምንሄድባቸው ቦታዎች በሙሉ (መሥሪያ ቤት፣ መዋዕለ ሕፃናት፣ ትምህርት ቤት ወይም የገበያ ማዕከል) በጣም ተራርቀው የሚገኙ በመሆናቸው አለመኪና ምንም ማድረግ አይቻልም። . . . እኔ በግሌ መኪና መፈለጌና አለመፈለጌ የሚያመጣው ለውጥ የለም። አብዛኞቹ ሰዎች ሌላ ምርጫ የላቸውም።”

በጆርጅያ የቴክኖሎጂ ተቋም የምድርና የከባቢ አየር የሳይንስ ትምህርት ቤት ባልደረባ እንደሆኑት እንደ ፕሮፌሰር ሮበርት ዲክንሰን የመሰሉ አንዳንድ ሳይንቲስቶች ምድርን የሙቀት መጨመር ከሚያስከትለው ጥፋት ልናድን የምንችልበት ጊዜ አልፎብናል ብለው ይሰጋሉ። ዲክንሰን እንደሚያምኑት የምድር ብክለት ዛሬ ቢቆም እንኳን ባለፉት ዓመታት በከባቢ አየር ላይ ያደረስነው ጉዳት ቢያንስ ለሌላ 100 ዓመት ይቆያል።

መንግሥታትም ሆኑ ግለሰቦች በአካባቢያችን ላይ የተፈጠሩ ችግሮችን መፍታት ካልቻሉ ታዲያ ማን ሊፈታው ይችላል? ከጥንት ጀምሮ ሰዎች የአየሩን ሁኔታ በተመለከተ ችግር ሲያጋጥማቸው እርዳታ ለማግኘት ወደ ሰማይ ያንጋጥጣሉ። እንዲህ ማድረጋቸው ከጅልነት ሊቆጠር ቢችልም አንድ የሚያሳየን መሠረታዊ እውነት አለ። የሰው ልጅ ያጋጠሙትን ችግሮች ለመፍታት መለኮታዊ እርዳታ ያስፈልገዋል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የታየው የምድር ሙቀት መጨመር በአብዛኛው ሰዎች በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ምክንያት የተፈጠረ መሆኑን የሚያረጋግጡ አዳዲስና ጠንካራ ማስረጃዎች ተገኝተዋል”

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“የምድር ሙቀት መጨመር በጤና ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ይኖር ይሆን?”

በሳይንቲፊክ አሜሪካን ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ይህን አሳሳቢ ጥያቄ አቅርቧል። የምድር ሙቀት መጨመር “ብዙ ከባባድ በሽታዎች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በተደጋጋሚና በስፋት እንዲከሰቱ ምክንያት እንደሚሆን” ተንብዮአል። ለምሳሌ ያህል በአንዳንድ አካባቢዎች “በሙቀት ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በ2020 በእጥፍ እንደሚጨምር ተገምቷል።”

የምድር ሙቀት መጨመር በተዛማች በሽታዎች ስርጭት ላይ የሚያስከትለው ውጤት ብዙም አልታወቀም። “ትንኞች የአካባቢው ሙቀት በጨመረ መጠን በፍጥነት ስለሚራቡና ንክሻቸውም ስለሚጨምር በትንኝ የሚተላለፉ በሽታዎች በጣም ሊስፋፉ እንደሚችሉ ይገመታል። . . . የአካባቢ ሙቀት በጨመረ መጠን ትንኞች ከዚህ በፊት ደርሰው ወደማያውቁባቸው ክልሎች ዘልቀው እንዲገቡ ያስችላቸዋል።”

በመጨረሻም ጎርፍና ድርቅ የሚያስከትሉት ውጤት አለ። ሁለቱም ለውኃ ብክለት መንስኤ ይሆናሉ። የምድር ሙቀት መጨመር በቀላሉ የማይታይ ችግር እንደሆነ ግልጽ ነው።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የግሪንሃውስ ጋዞች በከባቢ አየር ውስጥ ያለው ሙቀት ወደ ሕዋ ከመሰራጨት ይልቅ ታምቆ እንዲቆይ ያደርጋሉ

[ምንጭ]

NASA photo

[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የሰው ልጅ ቢሊዮን ቶን የሚመዝኑ በካይ ነገሮችን ወደ ከባቢ አየር እንዲገቡ በማድረግ የግሪንሃውስ ጋዞች ውጤት እንዲባባስ አድርጓል