በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጉልበተኝነት—አንዳንዶች ጉልበተኛ የሚሆኑት ለምንድን ነው? ይህስ ሌሎችን የሚጎዳው እንዴት ነው?

ጉልበተኝነት—አንዳንዶች ጉልበተኛ የሚሆኑት ለምንድን ነው? ይህስ ሌሎችን የሚጎዳው እንዴት ነው?

ጉልበተኝነት—አንዳንዶች ጉልበተኛ የሚሆኑት ለምንድን ነው? ይህስ ሌሎችን የሚጎዳው እንዴት ነው?

አንድ ልጅ ጉልበተኛ እንዲሆን የሚያደርገው ምንድን ነው? ጉልበተኛ ሰው አስቸግሮህ የሚያውቅ ከሆነ “የራሱ ጉዳይ ነው! እንዲህ ያለውን ድርጊት ለመፈጸም የሚያበቃ ምንም ዓይነት ምክንያት ሊኖር አይችልም” ብለህ ትመልስ ይሆናል። ትክክል ልትሆንም ትችላለህ። ይሁን እንጂ አንድ ልጅ ጉልበተኛ የሆነበትን ምክንያት ለመረዳት መሞከር ድርጊቱን አቃልሎ መመልከት ማለት አይደለም። አንድ ልጅ ጉልበተኛ እንዲሆን ያደረጉትን ምክንያቶች ማወቃችን መጥፎ ጠባይ የኖረው ለምን እንደሆነ እንድንረዳ ያስችለን ይሆናል እንጂ ለመጥፎ ጠባዩ ሰበብ ሊሆን አይችልም። ይህን ዓይነቱን ማስተዋል ማግኘታችን ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። እንዴት?

አንድ የጥንት ምሳሌ “ሰውን ጠቢብ አእምሮው ከቁጣ ያዘገየዋል” ይላል። (ምሳሌ 19:11) ጉልበተኛው በፈጸመው ድርጊት መቆጣት ብዙ ነገር እንዳይታየን፣ በብስጭትና በጥላቻ እንድንሞላ ሊያደርገን ይችላል። እንዲህ ያለ ጠባይ ለምን እንደኖረው ጠለቅ ብለን ማስተዋላችን ግን ንዴታችንን ቀዝቀዝ እንድናደርግ ሊረዳን ይችላል። ይህ ደግሞ በተራው መፍትሔ የምናገኝበትን መንገድ አጥርተን እንድንመለከት ይረዳናል። ስለዚህ እንዲህ ላለው አጉል ጠባይ መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉትን አንዳንድ ምክንያቶች እንመልከት።

ለጉልበተኝነት መንስኤው ምንድን ነው?

አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያለ ጠባይ የሚጠናወተው ሰው በቂ የወላጆች እንክብካቤና ጥሩ ምሳሌነት ሳያገኝ ያደገ ነው። ብዙ ጉልበተኞች የወላጅ ፍቅር ያላገኙና ከወላጆቻቸው ጋር ቅርርብ ያልነበራቸው እንዲሁም ወላጆቻቸው ችግሮችን በጉልበት ወይም በጠብ እንዲፈቱ ያስተማሯቸው ናቸው። እንዲህ ባለው አካባቢ ያደጉ ልጆች ምንም ዓይነት የቃላትም ይሁን የአካል ጥቃት ቢሰነዝሩ እንደ ጉልበተኝነት ላይቆጥሩት ይችላሉ። እንዲያውም ጠባያቸው ትክክለኛና ተቀባይነት ያለው ሆኖ ሊታያቸው ይችላል።

ጉልበተኛ በነበረ የእንጀራ አባቷና ትምህርት ቤት ጉልበተኛ በነበሩ ጓደኞቿ መከራዋን ታይ የነበረች አንዲት የ16 ዓመት ልጃገረድ ሰባተኛ ክፍል ስትደርስ እርሷም ጉልበተኛ እንደሆነች ተናግራለች። “መሠረታዊው ምክንያት በውስጤ ሲጠራቀም የኖረው ቁጣ ነው። ያገኘሁትንና ያጋጠመኝን ሁሉ መልከፍ ጀመርኩ። በስሜት መቁሰል የሚያስከትለው ውጤት በጣም ከባድ ነው። አንዴ ከቆሰላችሁ እናንተም ሌላውን ለማቁሰል ትፈልጋላችሁ።” ሁሉም ሴት ጉልበተኞች እንዲህ ያለው አዝማሚያ አላቸው ባይባልም ሁሉም ማለት ይቻላል ጉልበተኛ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ምክንያት የታመቀ ንዴት ነው። *

በብዙ ትምህርት ቤቶች የተለያየ አስተዳደግ ያላቸው በርካታ ተማሪዎች ይሰበሰባሉ። አንዳንድ ልጆች የጉልበተኝነት ድርጊት መፈጸም የሚቀናቸው ሌሎችን ማስፈራራትና መሳደብ የፈለጉትን ለማግኘት የሚያስችል ዘዴ እንደሆነ ተምረው ስለሚያድጉ ነው።

ይህ ዘዴያቸው አብዛኛውን ጊዜ ውጤታማ ሆኖ መገኘቱ በእጅጉ ያሳዝናል። በካናዳ የብሪቲሽ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ተባባሪ ዲን የሆኑት ሸሊ ሂመል ለሃያ ዓመታት የልጆችን ባሕርይ አጥንተዋል። እንዲህ ይላሉ:- “የገዛ ፍላጎታቸውን የሚያሳኩበትን ዘዴ አጥብቀው የሚፈልጉ ልጆች አሉን። ለዚህ ደግሞ ሁልጊዜም ውጤታማ ሆኖ የሚያገኙት ጉልበተኝነትን ነው። የፈለጉትን ሁሉ ይኸውም ሥልጣንን፣ አክብሮትንና ትኩረትን ያገኛሉ።”

ጉልበተኝነት እንዲስፋፋ ያደረገው ሌላ ምክንያት ደግሞ የቁጥጥር መላላት ነው። ብዙዎቹ ተጠቂዎች የሚደርስላቸው ሰው እንደሌለ ይሰማቸዋል። በእርግጥም አብዛኛውን ጊዜ የሚደርስላቸው አይኖርም። በቶሮንቶ ከተማ በዮርክ ዩኒቨርሲቲ የላማርሽ የጠብና የግጭት ማስወገጃ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ደብራ ፔፕለር በተማሪዎች ላይ ጥናት አድርገው በትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ከሚፈጸሙት የጉልበተኝነት ድርጊቶች መካከል አስተማሪዎች ደርሰው ሊያስቆሙ የቻሉት 4 በመቶ የሚሆነውን ብቻ እንደሆነ ተገንዝበዋል።

ይሁን እንጂ ጣልቃ ገብቶ መዳኘት ወሳኝነት እንዳለው ፔፕለር ያምናሉ። “የጉልበትና የኃይል ጉዳይ ስለሆነ ልጆች ችግሩን ሊፈቱት አይችሉም። ጉልበተኛው በተጣላ ቁጥር ተሰሚነቱና ጉልበተኝነቱ እየተጠናከረ ይሄዳል” ይላሉ።

ታዲያ የጉልበተኝነት ድርጊቶች ሪፖርት የማይደረጉት ለምንድን ነው? ተጠቂዎቹ ችግሩን ሪፖርት ቢያደርጉ ከማባባስ በስተቀር የሚያገኙት መፍትሔ እንደሌለ ስለሚያውቁ ነው። በዚህ የተነሣ ብዙ ወጣቶች የትምህርት ዘመናቸውን በጭንቀትና በፍርሃት ይጨርሳሉ። እንዲህ ያለው አኗኗር ምን ዓይነት ውጤት ያስከትላል?

አካላዊና ስሜታዊ ጉዳት

ናሽናል አሶሲዬሽን ኦፍ ስኩል ሳይኮሎጂስትስ ኢን ዘ ዩናይትድ ስቴትስ ያወጣው አንድ ሪፖርት በዩናይትድ ስቴትስ በየቀኑ 160,000 ልጆች ጉልበተኞችን በመፍራት ከትምህርት ቤት ይቀራሉ። የጉልበተኞች ዒላማ የሆኑ ልጆች ስለ ትምህርት ቤት ወይም ስለ አንድ የትምህርት ዓይነት ወይም የትምህርት እንቅስቃሴ ማውራት ያቆሙ ይሆናል። ሁልጊዜ አርፍደው ለመድረስ ወይም በአንዳንድ ክፍለ ጊዜያት ላለመግባት እንዲያውም ከትምህርት ቤት ጨርሶ ለመቅረት ሊሞክሩ ይችላሉ።

ልጆች ጉልበተኞች ጥቃት እየሰነዘሩባቸው እንዳለ እንዴት ማወቅ ይቻላል? ቅብጥብጦች፣ ግልፍተኞችና ብስጩዎች ሊሆኑ ወይም የደከማቸው ሊያስመስሉና ከሰው መራቅ ሊጀምሩ ይችላሉ። ከጓደኞቻቸውና ቤታቸው ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር በትንሽ በትልቁ ሊጣሉ ይችላሉ። የጉልበተኝነት ድርጊት ሲፈጸም ከዳር ቆመው የሚመለከቱም ቢሆኑ የሚደርስባቸው ጉዳት ይኖራል። በውስጣቸው ፍርሃት እንዲያድርባቸው ስለሚያደርግ የመማር ችሎታቸው ይዳከማል።

ይሁን እንጂ ፔድያትሪክስ ኢን ሪቪው የተባለው መጽሔት “በጉልበተኞች የሚጠቁ ልጆች ራሳቸውንም ሆነ ሌላውን እስከ መግደል ይደርሳሉ። የሚሰማቸው የአቅመ ቢስነት ስሜት በጣም ከፍተኛ ስለሚሆን አንዳንዶቹ ራሳቸውን ያጠፋሉ ወይም አጥቂያቸውን በመግደል ይበቀላሉ።”

ተመራማሪ፣ ሳይንቲስትና በቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ኤድ አድለፍ “ጉልበተኞችም ሆኑ ጥቃቱ የሚሰነዘርባቸው ልጆች አሁንም ሆነ ወደፊት የስሜት ቀውስ ሳያጋጥማቸው አይቀርም” በማለት ፍርሃታቸውን ገልጸዋል። በ2001 የትምህርት ዘመን ከ225,000 በሚበልጡ የኦንታሪዮ ተማሪዎች ላይ ጥናት ተካሂዶ ከአንድ አራተኛ እስከ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት የጉልበተኝነት ጥቃት እንደፈጸሙ ወይም እንደተፈጸመባቸው ተረጋግጧል። ከእነዚሁ መካከል ከአሥሩ አንዱ ራሳቸውን ለማጥፋት አስበዋል።

አለማቋረጥ ጉልበተኞች ጥቃት የሚሰነዝሩበት ሰው በራስ የመተማመን ችሎታው ሊሸረሸርና የጤና ችግር ሊያጋጥመው እንዲያውም ከሥራ እስከመፈናቀል ሊደርስ ይችላል። ራስ ምታት፣ ፍርሃትና ጭንቀትም ሊያጋጥመው ይችላል። አንዳንዶቹ በከባድ የመንፈስ ጭንቀት እስከመያዝ ይደርሳሉ። አካላዊ ጥቃት የሚደርስበት ሰው ብዙዎች የሚያዝኑለትና የሚደግፉት ሲሆን የስሜት ጥቃት የሚደርስበት ግን ያን ያህል የሚያዝንለት ሰው አያገኝም። የሚደርስበት ጉዳት ግልጽ ሆኖ አይታይም። በዚህም የተነሣ ጓደኞቹና ቤተሰቦቹ ለእርሱ ከማዘን ይልቅ በሚያሰማው እሮሮ ሊሰላቹ ይችላሉ።

ጉልበተኝነት ጉልበተኛ በሆኑት ላይም ጉዳት ያደርሳል። ይህ ልማዳቸው በልጅነታቸው ካልተቀጨ ሲያድጉ በመሥሪያ ቤት ባልደረቦቻቸው ላይ ተመሳሳይ ጥቃት ይሰነዝራሉ። እንዲያውም አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ልጆች ሳሉ ጉልበተኞች የነበሩ አድገው ትልቅ ሲሆኑም ይኸው ጠባይ አልለቀቃቸውም። በተጨማሪም ወንጀል የመፈጸም አጋጣሚያቸው ጉልበተኞች ካልነበሩት የበለጠ ነው።

በቤተሰብ ላይ የሚያሳድረው ጫና

በሥራ ቦታ የሚፈጸም ጉልበተኝነት የቤትን ሰላምና ፀጥታ ይረብሻል። ጥቃት የሚሰነዘርበት ሰው አለበቂ ምክንያት ከቤተሰቡ አባላት ጋር ለመጣላት ወይም በእነርሱ ላይ ጉዳት ለማድረስ ይነሳሳል። ከዚህም በላይ የትዳር ጓደኛው ወይም አንዱ የቤተሰብ አባል ጥቃት የሚሰነዘርበትን የቤተሰብ አባል የረዳ መስሎት ከጉልበተኛው ጋር እስከ መደባደብ ሊደርስ ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ይህን እርምጃ የወሰደው ሰው ለችግሩ ምክንያት የሆነው የትዳር ጓደኛው እንደሆነ ሊያስብ ይችላል። ይህን የመሰለው የጉልበተኝነት ድርጊት መፍትሔ ሳያገኝ ረዘም ላለ ጊዜ ሲቆይ ይደጋገፉ የነበሩ የትዳር ጓደኞች እንኳን ትዕግሥታቸው እንዳለቀ ታይቷል። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ቤተሰቡ ሊበታተን ይችላል።

የጉልበተኝነት ድርጊት ከሥራ እስከ መፈናቀል፣ መለያየትና መፋታት እንዲሁም ራስን እስከ መግደል ያደረሰበትም ጊዜ አለ። በመሥሪያ ቤታቸው ጉልበተኞች ጥቃት ከሰነዘሩባቸው አውስትራሊያውያን መካከል ከግማሽ እስከ ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ከትዳር ጓደኛቸው አሊያም እንደ ቤተሰብ አባል ካሉ የቅርብ ሰዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንደነካባቸው ተናግረዋል።

ጉልበተኝነት ብዙ ኪሣራ ያስከትላል

በሥራ ቦታ የሚፈጸም የጉልበተኝነት ድርጊት በአሠሪዎች ላይም የሚያስከትለው ኪሣራ አለ። የመሥሪያ ቤት ጉልበተኛ ተናዳፊ ምላስ ያለው አለቃ ወይም ተንኮለኛ የሥራ ባልደረባ አሊያም ወንድ ወይም ሴት ሊሆን ይችላል። እንደነዚህ ያሉት ሰዎች ጥቃቅኑን ነገር ሁሉ ይቆጣጠራሉ። የጥቃታቸው ዒላማ ያደረጉትን ሰው በአፍራሽ ንግግራቸውና በማያባራ ትችታቸው አብዛኛውን ጊዜ በሰዎች ፊት ያዋርዱታል። ጉልበተኞች ጨዋነት የጎደላቸው መሆናቸው አይታወቃቸውም። ይቅርታ መጠየቅም አይሆንላቸውም። አብዛኛውን ጊዜ ጥሩ ችሎታ ያላቸውን፣ ታማኝ የሆኑትንና በሌሎች ሠራተኞች የሚወደዱትን ሠራተኞች ያጠቃሉ።

የጉልበተኞች ዒላማ የሆኑ ሠራተኞች በሥራቸው ውጤታማ አይሆኑም። በተጨማሪም ጉልበተኞች የሚፈጽሙትን ድርጊት የሚመለከቱ ሠራተኞች ውጤታማነትም ይቀንሳል። በጉልበተኞች ጥቃት የሚደርስባቸው ሠራተኞች ለአለቆቻቸው ታማኝ እንዳይሆኑና ሥራቸውንም በቁርጠኝነት እንዳያከናውኑ ይደረጋሉ። አንድ ሪፖርት ጉልበተኞች በብሪታንያ ኢንዱስትሪ ላይ በየዓመቱ ሦስት ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ኪሣራ እንደሚያደርሱ ገልጿል። ከሠላሳ በመቶ በላይ ለሚሆኑ ከውጥረት ጋር ዝምድና ላላቸው ሕመሞች ምክንያቱ ይህ ድርጊት እንደሆነ ተገምቷል።

ጉልበተኞች በመላው ዓለም በሚኖሩ ማኅበረሰቦች ላይ ጫና እንደሚያሳድሩ ግልጽ ነው። ጥያቄው ይህን ችግር ለመግታትና ለማስወገድ ምን ማድረግ ይቻላል? የሚል ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 አብዛኛውን ጊዜ ሴት ጉልበተኞች የሚጠቀሙት እንደማግለልና ሐሜት እንደማስፋፋት ባሉት ዘዴዎች ነው። ይሁን እንጂ የኃይል ጥቃት እስከመሰንዘር የሚደርሱ ሴቶችም ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጉልበተኝነት ድርጊቶች በመሥሪያ ቤቶች ውስጥ ተስፋፍተዋል

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጉልበተኞች ጥቃት የሚደርስባቸው ሰዎች ሐዘንና ብቸኝነት ሊሰማቸው ይችላል