በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጉልበተኝነት—ዓለም አቀፍ ችግር

ጉልበተኝነት—ዓለም አቀፍ ችግር

ጉልበተኝነት—ዓለም አቀፍ ችግር

“ነገ ትምህርት ቤት ትመጪና እንገልሻለን።”—ክሪስቲን የተባለች አንዲት ካናዳዊት ልጅ ማንነቷን ከማታውቃት ልጅ በስልክ የደረሳት መልእክት። *

“በቀላሉ የምናደድ ሰው እንኳን አልነበርኩም። ቢሆንም ትምህርት ቤት መሄድ እስከመጥላት ደርሻለሁ። ሆዴን ይቆርጠኛል እንዲሁም ቁርስ ከበላሁ በኋላ ያስመልሰኛል።”—በጃፓን የምትኖር ሂሮሚ የተባለች ወጣት ጉልበተኞች ያደረሱባትን ችግር ስታስታውስ።

ጉልበተኞች አስቸግረውህ ያውቃሉ? አብዛኞቻችን አንድ ወቅት ላይ አጋጥሞን ይሆናል። በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታ አሊያም በአሁኑ ጊዜ የኃይል ጥቃት እየተስፋፋ በመጣበት በቤት ውስጥም ሊያጋጥም ይችላል። ለምሳሌ ያህል አንድ የብሪታንያ ምንጭ ለአካለ መጠን ከደረሱ ሰዎች መካከል 53 በመቶ የሚሆኑት ከትዳር ጓደኛቸው ወይም አብሯቸው ከሚኖር ሰው የሚያናድዱ ቃላት እንደሚሰነዘርባቸው ገምቷል። ጉልበተኞችም ሆኑ ለዚህ ጥቃት የሚዳረጉ ሰዎች ወንድ ወይም ሴት፣ በሁሉም የዓለም ክፍል የሚኖሩና በየትኛውም የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሊሆኑ ይችላሉ። *

ጉልበተኝነት ሲባል ምን ማለት ነው? የኃይል ወይም የጉልበት ጥቃት በመሰንዘር ብቻ የሚወሰን አይደለም። በአንድ ወቅት ብቻ ሳይሆን በረዥም ጊዜ ውስጥ የሚፈጸሙ የበርካታ ጥቃቅን ድርጊቶች ጥርቅም ነው። በጉልበተኝነት ላይ ጥናት በማድረግ ተቀዳሚ የሆኑት የሥነ አእምሮ ሊቅ ዳን ኦልቫውስ ጉልበተኝነት ከሚገለጥባቸው የጋራ ባሕርያት መካከል ሆን ብሎ ጠብ መፈለግና ብዙውን ጊዜ አቅም በሌላቸው ሰዎች ላይ መፈጸሙ እንደሆነ ተናግረዋል።

የጉልበተኝነትን የተለያዩ ገጽታዎች አጠቃልሎ የሚይዝ አንድ ፍቺ ለመስጠት ባይቻልም “በአንድ ወንድ/ሴት ላይ ጉዳት ለማድረስ ወይም ጭንቀት ለመፍጠር በማሰብ ሆን ተብሎ የሚፈጸም ድርጊት” ሊባል ይችላል። ጭንቀቱ የሚፈጠረው አንድ ሰው ችግሩ ስለደረሰበት ብቻ ሳይሆን ወደፊት ይደርስብኝ ይሆናል ብሎ ስለሚፈራም ጭምር ነው። አንድ ሰው ሌሎችን በማብሸቅ፣ ሁልጊዜ አቃቂር በማውጣት፣ በመሳደብ፣ በማማትና ተገቢ ያልሆነ ነገር እንዲደረግለት በመጠየቅ ጉልበተኝነቱን ሊያሳይ ይችላል።—በገጽ 18 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።

በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችው ክርስቲን በትምህርት ቤት ባሳለፈቻቸው ዓመታት በአብዛኛው የጉልበተኞች ዒላማ ሆና ቆይታለች። የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለች ጉልበተኞች ፀጉሯ ላይ ማስቲካ ይለጥፉባት፣ በመልኳ ይቀልዱባትና እንመታሻለን እያሉ ያስፈራሯት ነበር። ሁለተኛ ደረጃ ስትገባ ደግሞ ሁኔታው ተባብሶ እንገድልሻለን የሚል ዛቻ በስልክ እስከመስማት ደረሰች። አሁን 18 ዓመት የሞላት ሲሆን “ትምህርት ቤት የመማሪያ ቦታ መሆን ሲገባው የግድያ ዛቻ የሚሰማበትና እንግልት የሚፈጸምበት ቦታ ሆኗል” በማለት ታማርራለች።

አንድ የአእምሮ ጤና ባለሙያ “አሳዛኝ ግን የተለመደ የሰዎች የሕይወት ክፍል ሆኗል። አንዳንድ ሰዎች ሌላውን ማዋረድ ያስደስታቸዋል” ብለዋል። እንዲህ ያለው ድርጊት እየተባባሰና እየተካረረ ሲሄድ ከባድ የሆነ የበቀል ድርጊት እንዲያውም አሳዛኝ ክስተት እስከመፈጸም ሊያደርስ ይችላል። ለምሳሌ ያህል በሕዝብ ትራንስፖርት ድርጅት ተቀጥሮ የሚሠራ አንድ ሰው ኮልታፋ በመሆኑ ምክንያት የሥራ ባልደረቦቹ እያሾፉ ያበሽቁታል። በዚህ የተመረረው ይህ ሰው ራሱን ጨምሮ አራቱን በጥይት ገድሏል።

ጉልበተኝነት በሁሉም የዓለም ክፍል የሚገኝ ችግር ነው

የተማሪዎች ጉልበተኝነት በሁሉም የዓለም ክፍሎች የሚገኝ ችግር ነው። ፔድያትሪክስ ኢን ሪቪው የተባለ መጽሔት ባወጣው አንድ ጥናት በኖርዌይ 14 በመቶ የሚሆኑ ልጆች ጉልበተኞች አሊያም ጉልበተኞች የሚያስቸግሯቸው እንደሆኑ ተረጋግጧል። በጃፓን ከአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች መካከል 15 በመቶ የሚሆኑት ጉልበተኞች እንዳስቸገሯቸው ሲናገሩ በአውስትራሊያና በስፔይን 17 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች የችግሩ ተጠቂዎች ሆነዋል። በብሪታንያ አንድ ባለሙያ 1.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ልጆች በጉልበተኝነት ድርጊት እንደተካፈሉ ገልጸዋል።

የኤሜክ ኢዝርኤል ኮሌጅ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር አሞስ ሮሊደር በ21 ትምህርት ቤቶች በሚገኙ 2,972 ተማሪዎች ላይ ጥናት አድርገዋል። ዘ ጀሩሳሌም ፖስት እንደዘገበው ፕሮፌሰሩ “65 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው በጥፊና በእርግጫ እንደመቷቸው፣ እንደገፈተሯቸው ወይም እንዳበሳጯቸው ተናግረዋል።”

በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች አማካኝነት የሚፈጸም አዲስና ስውር ዓይነት የጉልበተኝነት ድርጊትም ተጀምሯል። የሚያስፈራሩና የሚያሸብሩ የጽሑፍ መልእክቶች በሞባይል ስልኮችና በኮምፒውተሮች አማካኝነት ይላካሉ። በተጨማሪም ወጣቶች አንድን ግለሰብ የሚያበሽቅ መረጃ የሚያስተላልፉበት የኢንተርኔት ገጽ ይፈጥራሉ። በካናዳ የኩዊንስ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ወንዲ ክሬግ እንዳሉት እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ለማብሸቅ ተብሎ የሚደረግ ሲሆን “እንዲበሽቅ በሚደረገው ልጅ ላይ የሚደርሰው ጉዳት በጣም ከፍተኛ ነው።”

በሥራ ቦታ

በመሥሪያ ቤቶች ከሚፈጸሙና በጣም እየተስፋፉ ከመጡት የኃይል ጥቃቶች አንዱ ጉልበተኝነት ነው። እንዲያውም አንዳንድ አገሮች ሪፖርት እንደሚያደርጉት ጉልበተኝነት ከዘር መድልዎም ሆነ በጾታ ከመደፈር ይበልጥ የተለመደ ሆኗል። በዩናይትድ ስቴትስ በየዓመቱ ከአምስት ሠራተኞች አንዱ ጉልበተኞች ጥቃት ይፈጽሙበታል።

በብሪታንያ የማንቸስተር ዩኒቨርሲቲ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋም ባወጣው የ2000 ሪፖርት በ70 ድርጅቶች ውስጥ ከሚሠሩ 5,300 ሠራተኞች መካከል 47 በመቶ የሚሆኑት ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ጉልበተኞች ጥቃት ሲፈጽሙ እንደተመለከቱ ገልጿል። የአውሮፓ ኅብረት በ1996 በ15ቱ አባል አገራት 15,800 በሚያክሉ ቃለ ምልልሶች አማካኝነት ባደረገው ጥናት 12 ሚሊዮን የሚያክሉ ሠራተኞች ጉልበተኞች እንዳስፈራሯቸው አረጋግጧል።

የጉልበተኝነት ድርጊት በትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ይፈጸም ወይም በሥራ ቦታ አንድ የጋራ ባሕርይ አለው። እርሱም ጉልበት ተጠቅሞ ሌላውን ሰው መጉዳት ወይም ማዋረድ ነው። ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች ጉልበተኛ የሚሆኑት ለምንድን ነው? ይህስ ምን ጉዳት ያስከትላል? ለመከላከልስ ምን ማድረግ ይቻላል?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 አንዳንድ ስሞች ተለውጠዋል።

^ አን.4 በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ጉልበተኞች አብዛኛውን ጊዜ በተባዕታይ ጾታ የሚጠቀሱ ቢሆንም መሠረታዊ ሐሳቡ ለአንስታይ ጉልበተኞችም ይሠራል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የጉልበተኝነት ዓይነቶች

በኃይል የሚፈጸም:- ይህ በግልጽ የሚታወቅ የጉልበተኝነት ዓይነት ነው። ጉልበተኞች በመማታት፣ በመገፍተር፣ በመራገጥ ወይም ንብረትን በማውደም ቁጣቸውን ይገልጻሉ።

በቃል የሚፈጸም:- አንዳንዶች ስም በማጥፋት፣ በመሳደብ ወይም አለማቋረጥ በማሾፍ እንዲሁም የሚጎዳና የሚያዋርድ ቃል በመናገር ጉልበተኛ መሆናቸውን ያሳያሉ።

ስም በማጉደፍ የሚፈጸም:- ስለ አንድ ግለሰብ መጥፎ ወሬ ይነዛሉ። እንዲህ ያለውን ጠባይ የሚያሳዩት ብዙውን ጊዜ ሴት ጉልበተኞች ናቸው።

አጸፋ የሚመልሱ:- በጉልበተኞች ጥቃት ይደርስባቸው የነበሩ አንዳንዶች እነርሱ ራሳቸው ጉልበተኞች ይሆናሉ። እርግጥ ነው፣ ከዚህ ቀደም ተጠቂ መሆናቸው የአሁኑን ድርጊታቸውን ትክክል አያደርገውም።

[ምንጭ]

ጊሰል ላጅዋ፣ አላሳን ማክሌን እና ሲንዲ ሴዶ ካዘጋጁት ቴክ አክሽን አጌንስት ቡሊይንግ ከተባለው ጽሑፍ የተወሰደ።