ለፋሽን ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ
ለፋሽን ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ
መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ “ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው” ይላል። (መክብብ 3:11) በዙሪያችን ባለው ዓለም ውስጥ ውበት እንመለከታለን። በሰው ልጆችም ላይ ውበት እናያለን።
ፋሽን አውጪዎች ዓላማቸው በምንለብሳቸው ልብሶች አማካኝነት ይበልጥ ተውበን እንድንታይ ማድረግ ነው። ይሁን እንጂ ቀደም ባለው ርዕስ እንደተመለከትነው የፋሽኑ ኢንዱስትሪ ሰዎች ስለ ውበት የተዛባ አመለካከት እንዲኖራቸው አድርጓል። የሥነ ልቦና ፕሮፌሰር የሆኑት ሩት ስትሪገል ሙር “ዓይናችን በጣም ቀጫጭን ሴቶች ማየት ስለለመደ ከቅጥነት በስተቀር ውበት የለም ብለን ወደማሰብ ደርሰናል” ብለዋል።
ዓለም ስለ ውበት ያለው ወቅታዊ አመለካከት ተጽዕኖ እንዲያደርግብን መፍቀድ አይኖርብንም። ዶሪስ ፑዘር
ኦልዌይስ ኢን ስታይል በተባለው መጽሐፋቸው “የዛሬዋ ሴት አዳዲስ ‘ጥሩ ቁመና’ ብቅ ባለ ቁጥር ራሷን መለወጥ ወይም መደበቅ አያስፈልጋትም” ብለዋል። በእርግጥም መገናኛ ብዙኃን በራሳቸው መስፈርት እንዲቀርጹን ለምን እንፈቅዳለን? “ያለንን ለመለወጥ የሞት ሽረት ትግል ውስጥ ከመግባት ይልቅ ራሳችንን ብንሆን ምን ያህል ቀላል ይሆንልናል!” ይላሉ ፑዘር።ዕድሜ የማይሽረው ውበት
በራስ መተማመንና ከሕይወት እርካታ ማግኘት በጥሩ መልክ ላይ የተመካ አይደለም። የአኖሬክሲያ ሕመምተኛ የነበረችው ጁዲ ሳርጀንት “እውነተኛ ደስታ የሚመነጨው ከውስጥ ነው” ብላለች። “ኪሎ በመቀነስ የሚገኝ አይደለም።” መጽሐፍ ቅዱስ አንድ እርምጃ ወደፊት በመራመድ “ውበታችሁ በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ፣ ገርና ጭምት መንፈስ ያለበት፣ ምንጊዜም የማይጠፋ የውስጥ ሰውነት ውበት ይሁን” በማለት ይመክራል።—1 ጴጥሮስ 3:4 አ.መ.ት
ጴጥሮስ የተናገረለት ዕድሜ የማይሽረው ውበት የማይጠፋና በአምላክ ዓይን ከፍተኛ ዋጋ ያለው በመሆኑ ምክንያት ከአካላዊ ቁንጅና ብልጫ አለው። አንድ ጠቢብ ንጉሥ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት “ውበት ሐሰት ነው፣ ደም ግባትም ከንቱ ነው፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች” ብሎ ነበር።—ምሳሌ 31:30
በአሁኑ ጊዜ የብዙ ሰዎችን ቀልብ የሚስበው አካላዊ ውበት ቢሆንም ዛሬም ቢሆን ለክርስቲያናዊ ባሕርያት የበለጠ ቦታ የሚሰጡ ብዙ ሰዎች አሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ ቆላስይስ 3:10, 12
ክርስቲያኖችን “አዲሱን ሰው” ማለትም “ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ” ሲል መክሯል።—ፋሽን አላፊ ነው። በጣም አዲስ የተባለው ፋሽን እንኳን ሊያደምቀን የሚችለው ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው። ባሕርያችን እንደ ቁመናችን የማያምር ከሆነ ውበታችን ፈጥኖ መረሳቱ አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ “የመንፈስ ፍሬ” ብሎ የሚጠራቸው እንደ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ጥሩነትና ራስን መግዛት ያሉት ባሕርያት ጊዜ የሚሽራቸው ፋሽኖች አይደሉም።—ገላትያ 5:22, 23፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10
እንዲህ ሲባል ግን ለአለባበሳችን ተገቢውን ትኩረት መስጠት አይኖርብንም ማለታችን አይደለም። ፈረንሣዊቷ አሊን በዚህ ረገድ ሚዛንን መጠበቅ ቀላል አይደለም ብላለች። “ወጣት ሳለሁ ስለምለብሰው ልብስ በጣም እጨነቅ ነበር። በራሴ እንድተማመን ስለሚያስችለኝ አንድም አዲስ ፋሽን አያመልጠኝም ነበር። በታወቁ ፋሽን አውጪዎች የተሰፉ ልብሶች እንዲያመልጡኝ አልፈቅድም ነበር።”
አሊን በመቀጠል “ካደግሁ በኋላ ግን ገንዘቤን መቆጠብ እንደሚያስፈልገኝ ተማርኩ። በተጨማሪም አብዛኛውን ጊዜዬን በክርስቲያናዊ አገልግሎት ማሳለፍ ጀመርኩ። እንደአቅሜ መኖር ከፈልግኩ የፋሽን ተገዥ መሆን እንደማልችል ተገነዘብኩ። እንዲያውም ልብሶቼን በቅናሽ ዋጋ ከሚሸጡ ሱቆች መግዛት ጀመርኩ። እንደዚያም ሆኖ እንደ ቀድሞ ብዙ ገንዘብ ማውጣት ሳያስፈልገኝ ጥሩ መልበስ ችያለሁ። ሚስጥሩ ያለው ልካችሁ፣ ምቹ የሆነ፣ ካላችሁ ልብስ ጋር የሚሄደውና ፋሽኑ ቶሎ የማያልፈው ልብስ የትኛው እንደሆነ ለይታችሁ ማወቃችሁ ላይ ነው። በፋሽን ተመርቼ ከመግዛት ይልቅ የሚያምርብኝን ስታይል መግዛት ተምሬአለሁ። ስለ ልብስ ፈጽሞ ግድየለኝም ማለቴ አይደለም። ሆኖም ማንነቴ የሚለካው በቁመናዬ ወይም በመልኬ እንዳልሆነ አውቃለሁ።”
ክርስቲያኖች ከውስጣዊ ማንነት ይልቅ ለውጪያዊ መልክ ከፍተኛ ቦታ በሚሰጥ ማኅበረሰብ ውስጥ በሚኖሩበት ጊዜ “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፣ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ልብ ማለት ይገባቸዋል።—1 ዮሐንስ 2:16, 17
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እውነተኛ ውበት ከውስጥ የሚመነጭ እንጂ ከላይ በሚለበስ ልብስ የሚመጣ አይደለም
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሁልጊዜ ሊለበስ የሚችልና ካላችሁ ልብስ ጋር የሚሄድ ልብስ ምረጡ