በራሴ ማንነት ሳይሆን በወላጆቼ ዝና የምታወቀው እስከመቼ ነው?
የወጣቶች ጥያቄ . . .
በራሴ ማንነት ሳይሆን በወላጆቼ ዝና የምታወቀው እስከመቼ ነው?
“አባቴን ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ያውቁታል። ለእርሱ ከፍተኛ አክብሮት ቢኖረኝም በሄድኩበት ቦታ ሁሉ የእገሌ ልጅ ተብዬ መታወቄ አንዳንድ ጊዜ ቅር ያሰኘኛል።”—ላሪ *
“አባቴ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ሽማግሌ ስለሆነ ሁሉም ከእኔ ብዙ እንደሚጠብቁ ይሰማኛል፤ በዚህም ምክንያት ራሴን ሆኜ ለመገኘት ተቸግሬ ነበር።”—አሌክሳንደር
እያደግህ ስትሄድ የተወሰነ ነፃነት እንዲኖርህ መመኘትህ ወይም በአንተነትህ ለመታወቅ መፈለግህ ያለ ነገር ነው። ስትወለድ ወላጆችህ ደስ ያላቸውን ስም አወጡልህ። እየጎረመስህ ስትሄድ ግን ለራስህ “ስም” ለማውጣት ማለትም የራስህን ዝና ለማትረፍ ትፈልጋለህ።
ንጉሥ ሰሎሞን “መልካም ስም ከብዙ ባለጠግነት ይሻላል፣ መልካምም ሞገስ ከብርና ከወርቅ ይበልጣል” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 22:1) በመሆኑም ገና ወጣት ብትሆንም በራስህ ማንነት ለመታወቅ ትፈልግ ይሆናል።
በወላጆችህ ማንነት መታወቅ
እንደ ላሪና አሌክሳንደር ሁሉ አንዳንድ ወጣቶችም በሌሎች ዘንድ የሚታወቁት በወላጆቻቸው ስም ወይም ዝና እንደሆነ ይሰማቸዋል። ምናልባት ወላጆቻቸው በሥራቸው ወይም በትምህርት ደረጃቸው በማኅበረሰቡ ውስጥ ስመ ጥር ይሆኑ ይሆናል። ወይም ደግሞ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የታወቁ ሊሆኑ ይችላሉ። ያንተም ወላጆች በእነዚህ ወይም በሌሎች ምክንያቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ የታወቁ ከሆኑ የሰዎች ትኩረት በአንተ ላይ እንደሚያርፍና የምታደርገው ነገር ሁሉ ፈጽሞ ከእይታ እንደማያመልጥ ይሰማህ ይሆናል። በወላጆችህ ማንነት ምክንያት ሰዎች የተወሰነ ዓይነት ባሕርይ የሚጠብቁብህ መሆኑ ቅር ያሰኝህ ይሆናል።
ለምሳሌ ያህል የኢቫን አባት በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ በሽማግሌነት ያገለግላል። ኢቫን እንዲህ ይላል:- “አባቴ በብዙዎች ዘንድ የታወቀና የተከበረ በመሆኑ በቤትም ሆነ በትምህርት ቤት ምሳሌ መሆን እንዳለብኝ ሁልጊዜ ይሰማኝ ነበር። ሌሎች ወላጆች ከልጆቻቸው በሚጠብቁት የሥነ ምግባር ደረጃ ረገድ እኔን በአርዓያነት እንደሚጠቅሱኝ አስብ ነበር። ይህ በአንድ በኩል የሚያስደስት ቢሆንም በባሕርዬ ለሌሎች ምሳሌ ለመሆን የማደርገው ጥረት ከፍተኛ ጫና ፈጥሮብኝ ነበር። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ጊዜ ልኬን ማወቅ ይሳነኝና ያለብኝን የባሕርይ ጉድለት እንኳን መቀበል ይከብደኝ ነበር።” አሌክሳንደር ደግሞ እንዲህ ይላል:-
“ምን ጊዜም ከሰው ትኩረት ማምለጥ እንደማልችልና ትንሽ ስህተት ብሠራ እንኳ ማንም እንደማያልፈኝ ይሰማኝ ነበር።”በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ላሪ የአባቱን ስም በመደበቅ ከሰዎች ትኩረት ለማምለጥ ይሞክር ነበር። እንዲህ ይላል:- “በማኅበራዊ ግብዣዎች ላይ ከሰዎች ጋር ስተዋወቅ የአባቴን ስም ሳልጠቅስ ‘ላሪ እባላለሁ’ ብቻ እላለሁ። አንዳንድ ጊዜ ስፈርም እንኳን የሚቻል ከሆነ የራሴን ስም ብቻ እጠቀማለሁ። ሰዎች አባቴ ማን መሆኑን ካወቁ ለእኔ ያላቸው አመለካከት ይለወጣል ብዬ እፈራለሁ። ሌሎች እንደማንኛውም ሰው እንዲያዩኝ እፈልግ ነበር።”
አባትህ ክርስቲያን ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ ከሆነ ሌሎች ከአንተ ብዙ መጠበቃቸው ያለ ነገር ነው። ደግሞም እንዲህ ያለ ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች ‘ልጆቻቸውንና የራሳቸውን ቤቶች በመልካም የሚገዙ’ መሆን አለባቸው። (1 ጢሞቴዎስ 3:5, 12) በመሆኑም ሰዎች መልካም አርዓያ እንድትሆን ቢጠብቁብህ አያስገርምም። ይሁን እንጂ ሰዎች ከአንተ መልካም አርዓያ እንድትሆን መጠበቃቸው ቅር የሚያሰኝ ነው? አይደለም። ወጣት ክርስቲያን የነበረው የጢሞቴዎስ ታሪክ ይህን ያሳየናል። ጢሞቴዎስ ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ክልል እያለ ሳይሆን አይቀርም ጳውሎስ የጉዞ ጓደኛው እንዲሆንና በአገልግሎቱ ጠቃሚ ሥራ እንዲያከናውን መርጦት ነበር። (1 ተሰሎንቄ 3:1-3) ስለዚህ አባትህ የጉባኤ ሽማግሌ ሆነም አልሆነ ምሳሌ ለመሆን ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል።
ማመጽ አያዋጣም
ያም ሆኖ አንዳንድ ወጣቶች የወላጆቻቸው ማንነት ከሚያስከትልባቸው ኃላፊነት ለመሸሽ ሲሉ ያምጻሉ። ኢቫን እንዲህ ይላል:- “ለሌሎች ምሳሌ መሆን እንደሚጠበቅብኝ ሳስብ የምበሳጭበት ጊዜ ነበር። ሰዎች አፍ አውጥተው እስኪነግሩኝ ድረስ ሆን ብዬ ፀጉሬን በማሳደግ የዓመጸኝነት መንፈስ አሳይ ነበር።”
የንጉሥ ዳዊት ልጅ የነበረው አቤሴሎም የዓመጸኝነት አካሄድ ተከትሏል። አባቱ ለይሖዋ ያደረ ከመሆኑም በላይ በእሥራኤል ብሔር ውስጥ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ ነበር። አቤሴሎም የዳዊት ልጅ እንደመሆኑ መጠን ብዙ ይጠበቅበት ነበር። ይሁን እንጂ እንደሚጠበቅበት ሆኖ በመገኘት ፈንታ በአባቱ ላይ በማመጽ የራሱን ስም ለማስጠራት ፈለገ። ዳዊት በይሖዋ የተሾመ ንጉሥ ስለሆነ አቤሴሎም ያመጸው በይሖዋ ላይ ነበር። ይህ ድርጊቱ በቤተሰቡ ላይ ኀፍረት ያስከተለ ሲሆን በራሱም ላይ ጥፋት አምጥቷል።—2 ሳሙኤል 15:1–15፤ 16:20–22፤ 18:9-15
ነህምያ 6:13 አ.መ.ት) አንተም ማመጽህ ከሰዎች አእምሮ በቀላሉ የማይፋቅ መጥፎ ስም ሊያሰጥህ ይችላል።
ማመጽ በአንተም ላይ ተመሳሳይ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል። እስቲ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነህምያ ምን እንደሚል ተመልከት። አንዳንድ ጠላቶቹ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት እንዲፈጽም ሊያታልሉት ሞክረው ነበር። ዓላማቸው ምን ነበር? “መጥፎ ስም ሰጥተው ተቀባይነት እንዳይኖረኝ ለማድረግ ነው” በማለት ነህምያ ተናግሯል። (ግምት ውስጥ መግባት ያለበት ሌላው ነገር ደግሞ ማመጽ በሌሎች ላይ የሚያስከትለው መጥፎ ውጤት ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ወላጆችህን ታሳዝናለህ። (ምሳሌ 10:1) እንዲሁም ድርጊትህ በሌሎች ወጣቶች ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ኢቫን እንዲህ ብሏል:- “ጠባዬ በታናሽ ወንድሜ ላይ መጥፎ ውጤት አስከትሎ ነበር። ለተወሰነ ጊዜ ከክርስቲያን ጉባኤ ርቆ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር የማይስማሙ ድርጊቶችን ሲፈጽም ቆይቷል። ደግነቱ አሁን ወደ ልቦናው ተመልሶ ይሖዋን በደስታ እያገለገለ ነው።”
የተሻለ አማራጭ
የአቤሴሎም ወንድም የሆነው ሰሎሞን የተከተለው አካሄድ ከአቤሴሎም የተለየ ነበር። ከአባቱ ከዳዊት በትሕትና ለመማር ፈቃደኛ ሆኗል። (1 ነገሥት 2:1-4) ሰሎሞን የራሱን ክብርና ዝና ከመፈለግ ይልቅ በአምላክ ዘንድ ጥሩ ስም ለማትረፍ ይጥር ነበር። እንዲህ ባደረገበት ጊዜ ሁሉ ለቤተሰቡ ክብር ያመጣ ሲሆን ከእስራኤል ታላላቅ ነገሥታት አንዱ ለመሆን በቅቷል።—1 ነገሥት 3:4-14
የሰሎሞን ጥሩ ምሳሌነት ሁለት አስፈላጊ ቁም ነገሮችን ያጎላል:- በመጀመሪያ ደረጃ፣ በራስህ ማንነት መታወቅ የምትችለው ከቤተሰቦችህ በመራቅ ሳይሆን ከጠንካራ ጎኖቻቸው በመማር ነው። አዶለሰንስ የተሰኘ መጽሔት “የጉርምስና ዕድሜ ወጣቱ ማንነቱ ጎልቶ እንዲታወቅ ሲል ከወላጆቹ የሚለይበት ጊዜ መሆን የለበትም” ይላል። አክሎም “ከወላጆችህ የምታገኘው ድጋፍ” ማንነትህን ለማሳወቅ በምታደርገው ጥረት “እገዛ ያበረክትልሃል እንጂ እንቅፋት አይሆንብህም” ብሏል።
ሰሎሞን ራሱ “የወለደህን አባትህን ስማ፣ እናትህም ባረጀች ጊዜ አትናቃት” በማለት የሰጠው ማሳሰቢያ ልብ ሊባል የሚገባው ነው። (ምሳሌ 23:22) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሰሎሞን እንዲህ ያለው ለልጆች አይደለም። ምክንያቱም ወላጆች ሲያረጁ ልጆቹ ትልልቅ ሰዎች ይሆናሉ። ታዲያ የምሳሌው ፍሬ ነገር ምንድን ነው? ትልቅ ሰው ሆነህ የራስህን ቤተሰብ ከመሠረትክም በኋላ ከወላጆችህ የጥበብ ምክር ልትጠቀም ትችላለህ። ኢቫን የኋላ ኋላ ይህን ተገንዝቧል። እንዲህ ብሏል:- “እያደግሁ ስሄድ የወላጆቼን ስህተቶች ላለመድገም እየጣርኩ ጠንካራ ጎኖቻቸውን ለመኮረጅ እሞክራለሁ።”
ሊታሰብበት የሚገባው ሁለተኛው ነጥብ ሰሎሞን ቅድሚያ የሰጠው የራሱን “ስም” ለማስጠራት ሳይሆን ይሖዋን ለማስደሰት መሆኑ ነው። እርግጥ ነው፣ የዳዊት ልጅ እንደመሆኑ መጠን ብዙ ይጠበቅበት ነበር። ይሁን እንጂ ሰሎሞን በይሖዋ ላይ መመካቱ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አስችሎታል። እንደ ሰሎሞን በይሖዋ ላይ የሚመካው አሌክሳንደር እንዲህ ይላል:- “ከሽማግሌዎች ልጆች ብዙ የሚጠበቅባቸው መሆኑን ተቀብያለሁ። ይህን ገንቢ በሆነ መንገድ ልጠቀምበት ወሰንኩ፤ እንዲህ ማድረጌ ጥበቃ ሆኖልኛል። ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ይሖዋ ለእኔ ያለው አመለካከት መሆኑን መገንዘብ ችዬአለሁ። ይሖዋ እኔን የሚያውቀኝ የእገሌ ልጅ ነው ብሎ ሳይሆን በእኔነቴ ነው።”
በጊልያድ የሚስዮናውያን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት * የተመረቀ አባት ያለው ዳረን የተባለ ወጣትም የታወቁ ወላጆች ያሉት መሆን የሚያስከትለውን ፈታኝ ሁኔታ እንዴት መቋቋም እንደሚቻል ተምሯል። እንዲህ ይላል:- “ራሴን ወስኜ የተጠመቅኩት ለይሖዋ እንጂ ለሌላ ለማንም አይደለም። ወላጆቼ ያከናወኑትን ያህል ማከናወን ባልችልም ራሴን ስወስን ከገባሁት ቃል ጋር ተስማምቼ ለመኖር የተቻለኝን ሁሉ የማደርግ ከሆነ ይሖዋ እንደሚደሰትብኝ ማወቄ ውስጣዊ ሰላም ይሰጠኛል።”
ንጉሥ ሰሎሞን “ሕፃን ቅንና ንጹሕ መሆኑ በሚያደርገው ሥራ ይታወቃል” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 20:11) ወደፊት በሰዎች ዘንድ የምትታወሰው በወላጆችህ ማንነት ሳይሆን በተናገርካቸውና ባደረግሃቸው ነገሮች ነው። “በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም በንጽሕናም ምሳሌ ሁን።” እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ሰዎች በአንተነትህ ይወዱሃል፣ ያከብሩሃልም!—1 ጢሞቴዎስ 4:12
ይሁን እንጂ ለሌሎች ወጣቶች ፈታኝ የሆነባቸው የላቀ ስኬት ባስመዘገቡ ወንድሞቻቸው ወይም እህቶቻቸው ዝና ሳይሆን በራሳቸው ማንነት ለመታወቅ የሚያደርጉት ጥረት ነው። ይህን ፈታኝ ሁኔታ እንዴት ማሸነፍ እንደሚቻል የሚገልጽ ርዕስ በሚቀጥለው እትም ላይ ይወጣል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተለውጠዋል።
^ አን.22 ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የሚተዳደረው በይሖዋ ምሥክሮች ነው።
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ማመጽ በወላጆችህ ላይ ሐዘን ከማምጣትና የአንተን መልካም ስም ከማጉደፍ ሌላ የሚፈይደው ነገር የለም
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥሩ ምሳሌነትህ ሌሎችን ሊጠቅም ይችላል