በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በካውካሰስ የደረሰውን የጎርፍ መጥለቅለቅ መቋቋም

በካውካሰስ የደረሰውን የጎርፍ መጥለቅለቅ መቋቋም

በካውካሰስ የደረሰውን የጎርፍ መጥለቅለቅ መቋቋም

ሩሲያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ባለፈው ዓመት የሩሲያ ክፍል በሆነችው በደቡባዊ ካውካሰስ አካባቢ ለሁለት ቀን ከባድ ዝናብ ጥሎ ነበር። በዚህ ሁለት ቀን ውስጥ የጣለው የዝናብ መጠን በሌላው ጊዜ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ከሚጥለው ዝናብ ጋር የሚመጣጠን ነበር። ከአፍ እስከ ገደፋቸው የሞሉ ብዙ ወንዞች አካባቢያቸውን አጥለቀለቁ። ትናንሽ ጅረቶችም እንኳን ኃይለኛ ወራጅ ውኃ በመሆን በመንገዳቸው ላይ ያገኙትን ሁሉ እየጠራረጉ ወሰዱ። ግድቦች ፈራረሱ፣ ቤቶችና ሌሎች ተቋሞችም ወደሙ። በድንገት በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ቤት አልባ ሆኑ። ከቤታቸው ፈጥነው መውጣት ያልቻሉ እዚያው ሞቱ። ሞገደኛው ጎርፍ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ጠርጎ ሲወስድባቸው ከማየት የበለጠ ምንም ማድረግ ሳይችሉ የቀሩም ነበሩ።

በነቪኖሚስክ ከተማ አንድ ቤተሰብ በእርሻ መኪናቸው ላይ ሆነው ለማምለጥ ሞክረው ነበር። ሆኖም ኃይለኛ ሞገድ ትራክተሩን ገለበጠውና መላው ቤተሰብ አለቀ። ሌሎችን ለማዳን ሲሞክሩ የሞቱም ነበሩ። በይፋ በተሰጠ ግምት መሠረት 335,000 ሰዎች በጎርፉ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ከ200 የሚበልጡ ሞተዋል እንዲሁም ሌሎች ብዙዎች የደረሱበት ሳይታወቅ ቀርቷል።

በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች በጎርፉ ተጥለቅልቀዋል። የውኃ ቧንቧዎችና የቆሻሻ ፍሳሽ ማስወገጃዎች ወድመዋል። ጎርፉ በአባ ሰንጋ በሽታ የሞቱ እንስሳት ሬሳዎችን ጨምሮ አስከሬኖችን ከመቃብራቸው አውጥቷል። ጎርፉ ያስከተለው ኪሣራ በገንዘብ ሲሰላ 16 ቢሊዮን ሩብል ወይም 500 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሆነ ይገመታል።

በየዘፈኑና በየግጥሙ የሚወደሰው ይህ ውብና ለም ምድር ለማየት በሚያሳዝን መንገድ እንዳልነበር ሆነ! ሆኖም ጎርፉ እውነተኛ የጎረቤት ፍቅርን አላጠፋም።

እርዳታ በፍጥነት ቀረበ

መጀመሪያ ላይ ንጹሕ የመጠጥ ውኃ፣ የኤሌክትሪክ መብራት፣ ጋዝና የስልክ አገልግሎት ተቋርጦ ነበር። ሰዎች እርስ በርስ መገናኘት አልቻሉም። ከ3,000 በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች በጎርፍ በተጥለቀለቀው አካባቢ የሚኖሩ ሲሆን ከ700 በላይ የሚሆኑት በነቪኖሚስክ ከተማ ውስጥና አካባቢ የሚገኙ ነበሩ። የጎርፍ መጥለቅለቁ ዜና እንደተሰማ ምሥክሮቹ በጎርፍ የተጠቁትን ለመርዳት የሚያስችሉ ኮሚቴዎች በፍጥነት አቋቋሙ። እነዚህ ኮሚቴዎች ሥራ የጀመሩት የመንግሥት ሕይወት አድን ሠራተኞች ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ነበር።

ከነቪኖሚስክ ደቡብ ምሥራቅ 60 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ኦርቤልያኖቭካ በምትባል ትንሽ ከተማ የውኃው መጠን በፍጥነት ይጨምር ነበር። ሁለት እህቶችን ጨምሮ ስምንት ሰዎች ከጎርፍ ለመሸሽ ወደ አንድ ትንሽ ኮረብታ አናት ላይ ወጡ። ከእነርሱ ሌላ ትናንሽ እንስሳትና ብዙ እባቦችም ወደዚያው ሸሹ። በዚያ ረዥም ሌሊት ሊነድፏቸው ከሚሞክሩ እባቦች ጋር ሲታገሉ አደሩ።

በቀጣዩ ቀን ጠዋት የአካባቢው ምሥክሮች በሞት አፋፍ ላይ የሚገኙትን ሁለት ክርስቲያን እህቶቻቸውን ለማዳን ዘዴ እየፈለጉ ነበር። በመጨረሻም ቀትር ላይ አንዲት ትንሽ ጀልባ አገኙ። ይሁን እንጂ ምሥክሮቹ እህቶችን ለማዳን ከመሄዳቸው በፊት በጀልባው ተጠቅመው ሽባ የሆኑ አንድ በዕድሜ የገፉ አረጋዊ ሰው አዳኑ። ከዚያም በኋላ እህቶችን እያጓጓዙ ሳለ አንድ ሄሊኮፕተር መጣና በኮረብታው ላይ የሚገኙትን የቀሩትን ሰዎች ወሰደ።

በዚያው ቀን ትንሽ ቆየት ብሎም ምሥክሮቹ በጀልባዋ አማካኝነት ሌሎች ተጨማሪ ሰዎችን ማዳን ችለው ነበር። ምሥክሮቹ “እኛ እነማን እንደሆንን አውቃችሁናል?” ብለው ሲጠይቁ ሰዎቹ “የድንገተኛ አደጋ ሚኒስቴር ሠራተኞች ናችኋ” ብለው ይመልሱ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን ሲረዱ ግን በጣም ተገርመው ነበር።

በነቪኖሚስክ ከተማ ያሉ ምሥክሮች ተንቀሳቃሽ ማእድ ቤት ገዙና ምግብ እያዘጋጁ ችግር ላይ ለወደቁት ሁሉ ሰጧቸው። ከምግብ በተጨማሪ ውኃ፣ ልብስና መድኃኒት ያቀርቡላቸው ነበር። ምሥክሮቹ በቡድን በቡድን እየተደራጁ ቤቶችን አጽድተዋል እንዲሁም ፍርስራሾችን ከግቢ ጠራርገው አስወግደዋል።

በዘሊዮኖኩምስክ የሚኖሩ አንድ ነጋዴ የይሖዋ ምሥክር ባልና ሚስት ውኃ፣ ምግብና ልብስ በጅምላ እየገዙ በመኪናቸው ያመላልሱ ነበር። ሚስትየዋን የሚያውቋት ሰዎች ይህን ሁሉ የሚገዙት ለማን እንደሆነ ሲጠይቋት በጎርፍ አደጋው ለተጎዱት መሰል አማኞች መሆኑን ገለጸችላቸው። በዚህ ድርጊቷ ልባቸው በመነካቱ እነሱም የእርዳታ እጃቸውን ለመዘርጋት ፈለጉ። አንድ ነጋዴ ትልቅ ጆንያ መኮረኒ፣ ሌላው ደግሞ ትልቅ እሽግ ሣሙና ሌሎች ደግሞ ጆንያ ሙሉ ስኳር ለግሰዋል።

ከሩቅ የመጣ እርዳታ

በሩሲያ የሚኖሩ ብዙ ምሥክሮች የጎርፍ ሰለባዎቹን እንዴት መርዳት እንደሚችሉ ለማወቅ ስለ ፈለጉ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የሚላክ ገንዘብ ማሰባሰብ ጀመሩ። በሩሲያ፣ በሴንት ፒተርስበርግ አቅራቢያ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ያሉ ፈቃደኛ ሠራተኞችም ሳይቀር እርዳታ አቀረቡ። አንዳንዶቹ አዳዲስ ነገር ገዝተው በጎርፉ ለተጠቁት ላኩላቸው። አንዲት ሴት “ካለኝ ሁሉ ምርጡን መስጠት የቻልኩት ትንሽም ቢሆን ስለኖረኝ ነው። በጎርፉ የተጠቁት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ግን ያላቸውን ሁሉ አጥተዋል” ብለዋል።

ቅርንጫፍ ቢሮው ወንድሞች ገንዘብ፣ ምግብና ልብስ እንዴት ማዋጣት እንደሚችሉ የሚያብራራ ደብዳቤ ሴንት ፒተርስበርግ እና ሞስኮ ለሚገኙ 150 ጉባኤዎች ላከ። የሩሲያ የኢኮኖሚ ሁኔታ ዝቅተኛና የአብዛኞቹ ምሥክሮች ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ ቢሆንም የላኩት መዋጮ ግን የተትረፈረፈ ነበር። ሁኔታው በመቄዶንያ የነበሩት በድህነት የተጠቁ ክርስቲያኖች በይሁዳ ለነበሩ ችግረኛ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ያሳዩትን የልግስና መንፈስ የሚያስታውስ ነበር።—2 ቆሮንቶስ 8:1-4

የተዋጡት ቁሳቁሶች በአንድ ማዕከላዊ ሥፍራ በዓይነት በዓይነታቸው ከተለዩ በኋላ በመኪና ተጭነው አደጋው ወደደረሰበት ቦታ ተወሰዱ። በመዋጮ ከተሰበሰቡት ቁሳቁሶች በተጨማሪም ቅርንጫፍ ቢሮው አሥር ቶን ምግብ፣ 500 ጥንድ አንሶላና ለማጽጃ የሚያገለግሉ ኬሚካሎች እንዲሁም ከአደጋው በኋላ ለጽዳት ሥራው የሚውሉ መሣሪያዎችና የሥራ ልብሶች ገዝቶ ላከ። በጠቅላላው 50 ቶን የሚይዙ ስድስት የጭነት መኪናዎች የእርዳታ ቁሳቁሶችን ጭነው ወደ ሰሜናዊው የካውካሰስ ክልል ተጓዙ።

ልግስናው ምሥክርነት ሰጠ

የጎርፍ አደጋው በተከሰተበት አካባቢ በተደረገው የጽዳት ሥራ ወቅት ምሥክሮቹ ያከናወኑት ሥራ ሳይስተዋል አላለፈም። ከ300 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች በሚኖሩባት ውቧ የመዝናኛ ከተማ በኪስሎቮድስክ የሆነውን እንመልከት። ምሥክሮቹ በጽዳቱ ለመካፈል ለከተማው አስተዳደር አመለከቱና የሚያጸዱት አካባቢ ተሰጣቸው።

ሰኔ 28 ከጠዋቱ 2 ሰዓት ላይ ከመላው ቤተሰባቸው ጋር የመጡትን ጨምሮ 150 የሚያህሉ ምሥክሮች የጽዳት ዕቃዎቻቸውን ይዘው ለሥራ ተሰናዱ። አንዳንዶቹ በዚህ ጽዳት ለመካፈል ሲሉ ከመደበኛ የሥራ ቦታቸው ደመወዝ የማይጠይቁበት ዕረፍት የወሰዱ ነበሩ። ከዚያም ወዲያው አንድ መኪና መጥቶ ቆመና የከተማው ምክትል ከንቲባ ከመኪናው ወረዱ። “እነዚህ እነማን ናቸው?” ብለው ጠየቁ።

“የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው” ተብሎ ተነገራቸው። “ከአደጋው በኋላ ከተማዋን ሊያጸዱ የመጡ ናቸው።”

ምክትል ከንቲባው ይህን ያህል ብዙ ሰዎች በማየታቸው ተገርመው “ጎሽ! እናመሰግናችኋለን! ግሩም ነው!” አሉ።

ከምሳ ጥቂት ቀደም ብሎ ሌላ የከተማው ባለ ሥልጣን በመኪናቸው መጡ። ከመኪናቸው ወርደው ወደ ምሥክሮቹ መጡ። “ሥራችሁን እያየን ነበር፤ በጣም ገርሞናል” አሉ። “እንደናንተ የሚሠሩ ሰዎች አላየንም። ገና ከአሁኑ ብዙ ሥራ ሠርታችኋል!”

በዚሁ ጊዜ በዕድሜ የገፉ አንዲት ሴት በዚያ በኩል ሲያልፉ ቆም ብለው “እነዚህ ሰዎች እንደዚህ የሚለፉት ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁ። የይሖዋ ምሥክሮች በጽዳቱ ሥራ ለመካፈል ወደ ከተማው እንደመጡ ሲነገራቸው ዓይናቸው እንባ አቀረረ። “እናንተ እውነተኛ አማኞች ናችሁ” አሉ። “የሰዎች ማንነት የሚለየው በችግር ጊዜ ነው።” ሌላዋ ሴት ደግሞ “በጣም የሚያስደንቅ ነው! በዚህ ሁሉ ዘመን እንዲህ ዓይነት ሥራ አይቼ አላውቅም” በማለት ተናገሩ።

በቀጣዩ ቀን ና ቮዳክ የተባለ የአካባቢው ጋዜጣ የይሖዋ ምሥክሮች ከ100 ቶን የሚበልጥ ደለል ከከተማዋ እንዳስወገዱ በመግለጽ አመስግኗቸዋል። የኪስሎቮድስክ ከተማ ባለ ሥልጣኖች ለምሥክሮቹ የምስጋና ደብዳቤ በመጻፍ “ያደረጋችሁት በገንዘብ የማይተመን እርዳታ ከተማይቱን ወደ ቀድሞ ውበቷ መልሷታል። . . . ከሁሉ የላቀው ሽልማታችሁ ከተማችንን ለመጎብኘት ከሚመጡት እንግዶች የሚሰነዘሩት ብዙ የምስጋና ቃላት እንደሚሆን እሙን ነው” ብለዋል።

ሰሜናዊውን ካውካሰስ የመታው የተፈጥሮ አደጋ ብዙ ኪሳራና መከራ ያስከተለ ቢሆንም የይሖዋ ምሥክሮች ለመሰል አማኞችና ለጎረቤቶቻቸው ፍቅር ለማሳየት በመቻላቸው ደስተኞች ናቸው። በተለይ ደግሞ እንዲህ ያሉት የፍቅር መግለጫዎች ለፈጣሪያችን ለይሖዋ ክብር እንደሚያመጡ ማወቃቸው ደስታቸውን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ካርታዎች]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ጥቁር ባሕር

ካውካሰስ ተራራዎች

ነቪኖሚስክ

ኪስሎቮድስክ

ዘሊዮኖኩምስክ

ኦርቤልያኖቭካ

ካስፒያን ባሕር

[ምንጭ]

Globe: Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ምሥክሮቹ ይህን ተንቀሳቃሽ ማእድ ቤት ገዝተው ለተቸገሩት ምግብ አዘጋጁላቸው

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይህች እህት በቤተሰቧ መኪና ምግብና ሌሎች ቁሳቁሶችን አጓጉዛለች

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ምሥክሮቹ የኪስሎቮድስክ ከተማን ወደ ቀድሞ ውበቷ ለመመለስ ላደረጉት እርዳታ ባለ ሥልጣኖች አመስግነዋቸዋል