በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተለዋዋጭ የሆነው የፋሽን ገጽታ

ተለዋዋጭ የሆነው የፋሽን ገጽታ

ተለዋዋጭ የሆነው የፋሽን ገጽታ

አወቅንም አላወቅን፣ በየዕለቱ የምንለብሰው ልብስ በመጠኑም ቢሆን የሚወሰነው በፋሽን ነው። ገበያ ላይ የምንገዛውን የልብስ ዓይነት በአብዛኛው የሚወስነው የፋሽኑ ዓለም ነው።

በአሁኑ ጊዜ እንደተራ የምንቆጥራቸው የልብስ ዓይነቶች እንኳን በአንድ ወቅት ጊዜ አመጣሽ ፋሽኖች ነበሩ። ለምሳሌ ያህል ወንዶች የሚለብሱት ሸሚዝና ክራባት ከአንድ መቶ ዓመት በፊት አዲስ ፋሽን ነበር። የሴቶች ሹራብም በ1920ዎቹ ዓመታት ተወዳጅነት ያተረፈ ፋሽን ነበር።

የፋሽኑን ኢንዱስትሪ የሚያንቀሳቅሱት ሁለት መሠረታዊ ፍላጎቶች ናቸው። እነርሱም ዘመናዊ ሆኖ የመታየትና ከሌሎች ጋር የመመሳሰል ፍላጎቶች ናቸው። አዲስ ነገር መልበስ የማይወድ ሰው የለም ለማለት ይቻላል። አንዳንድ ጊዜ ያለን ልብስ ሳያረጅብን እንዲሁ ለለውጥ ያህል ብቻ አዲስ ልብስ የምንገዛው በዚህ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም። ከዚህም በላይ ኋላ ቀር ሆነን መታየት ስለማንፈልግ በመጠኑም ቢሆን ባልንጀሮቻችን ከሚለብሱት ጋር የሚመሳሰል ልብስ እንለብሳለን። ባለፉት መቶ ዘመናት የልብሱ ኢንዱስትሪ ሸማችን ለመሳብና አንዳንድ ጊዜም አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ሲጥር የኖረው ይህን ዘመናዊ ሆኖ የመታየትና ከሌሎች ጋር የመመሳሰል ፍላጎትን በመጠቀም ነው።

የፋሽን አጀማመር አጭር ታሪክ

ፋሽን አውጪዎች አዲስ ፋሽን ለመፍጠር አምስት መሠረታዊ ነገሮችን ይጠቀማሉ። እነርሱም ቀለም፣ ቅርጽ፣ አወራረድ፣ የጨርቁ ልስላሴ ወይም ሻካራነትና በጨርቁ ላይ የሚገኙ መስመሮች አቀማመጥ ናቸው። ፋሽን አውጪዎችና ልብስ ሠፊዎች በእነዚህ በአምስቱ ዘርፎች ያላቸው ምርጫ ባለፉት ዘመናት በሙሉ እየጨመረ መጥቷል። ለምሳሌ ያህል በጥንቷ ግብጽ በአገሩ ይመረት የነበረው ስስ ሊኖ (ከተልባ ጭረት የሚሠራ) ጨርቅ ለሞቃቱ የአየር ጠባይ በጣም ተመራጭ ነበር። ይሁን እንጂ ሊኖን በቀላሉ ማቅለም ስለማይቻል አብዛኛውን ጊዜ ይለበስ የነበረው ነጭ ቀለም ያለው ልብስ ብቻ ነበር። ቢሆንም ግብጻውያን ፋሽን አውጪዎች ልብሶቻቸው የሚያምር ቅርጽና አወራረድ እንዲኖራቸው ጨርቁን ሽንሽን አድርገው መስፋት ጀመሩ። በዚህ መንገድ ዛሬ በመላው ዓለም ታዋቂነት ያተረፈ ጥንታዊ ፋሽን ተፈጠረ።

በአንደኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ አዳዲስ የጨርቅ ዓይነቶችና ቀለሞች ብቅ ማለት ጀመሩ። ሮማውያን ባለጠጎች ከቻይናና ከሕንድ ሐር ያስመጡ ነበር። የማጓጓዣው ወጪ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ የጨርቁ ዋጋ የወርቅ ያህል ይወደድ ነበር። ሌላው ተወዳጅ ጨርቅ ባለቀለም የጢሮስ ሱፍ ሲሆን አንድ ኪሎ የሚመዝን ሱፍ 2,000 ዲናር ማለትም የአንድ ተራ ሠራተኛ የስድስት ዓመት ደመወዝ ያህል ነበር። አዲሶቹ ቀለሞችና ጨርቆች ባለጠጋ ሮማውያን ወይዛዝርት ከሕንድ ሰማያዊ ጥጥና ከቻይና ቢጫ ሐር የተሠራ ረዥምና የተንዘረፈፈ ልብስ እንዲለብሱ አስችለዋቸዋል።

በጥንቶቹ ዘመናት አዳዲስ ፋሽኖች በየጊዜው ብቅ ማለታቸው ባይቀርም አንድ ውድ ልብስ ወረቱ ሳያልፍበት ዕድሜ ልክ ይቆይ ነበር። ለውጦቹ የሚመጡት ቆይተው ሲሆን በለውጦቹ የሚነኩት ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ መኳንንቱ ነበሩ። ከኢንዱስትሪ አብዮት በኋላ ግን ተራውም ሰው ፋሽን መከተል ጀመረ።

በአሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመን ለባለጠጎችም ሆነ ለድሆች ልብስ የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ተቋቋሙ። በማሽን የሚንቀሳቀሱ የጥጥ እንዲሁም የሱፍ መፍተያና መሸመኛ መሣሪያዎች በመስፋፋታቸው የጨርቃ ጨርቅ ዋጋ እየወረደ መጣ። የልብስ ስፌት መኪናዎች በመገኘታቸውም በአነስተኛ ወጪ ልብሶችን ማዘጋጀት ተቻለ። አዳዲስ ሰው ሠራሽ ቀለሞች በመሠራታቸውም ሠፊ የሆነ የቀለም ምርጫ ሊገኝ ቻለ።

ማኅበራዊና ቴክኖሎጂያዊ ለውጦች በብዙኃኑ ላይ ከዚህም የበለጠ ለውጥ አስከትለዋል። በምዕራብ አውሮፓና በሰሜን አሜሪካ የተራ ሰዎች ገቢ ማደግ ጀመረ። በ1850ዎቹ ዓመታት የሴቶች መጽሔቶች መውጣት ሲጀምሩ ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ትላልቅ የገበያ አዳራሾች የተሰፉ ልብሶችን መሸጥ ጀመሩ። በተጨማሪም በ19ኛው መቶ ዘመን ቻርልስ ፍሬድሪክ ወርዝ የደንበኞቹን የመግዛት ፍላጎት ለመቀስቀስ ሲል የፋሽን ትርዒት ለማሳየት የመጀመሪያው ሰው ሆነ።

በሃያኛው መቶ ዘመን እንደ ናይለንና ፖሊስተር የመሰሉት ሰው ሠራሽ ጨርቆች በመገኘታቸው ልብስ አምራቾች ሠፊ የምርጫ ዕድል አገኙ። በኮምፒውተር አማካኝነት አዳዲስ ፋሽኖችን በቀላሉ ማውጣት ከመቻሉም በላይ አሁን አሁን አንድ ፋሽን በአንድ ጊዜ በቶኪዮ፣ በኒው ዮርክ፣ በፓሪስና በሳኦ ፓውሎ ጎዳናዎች ላይ ሊታይ ይችላል። በዚሁ ጊዜ ፋሽን አውጪዎችና ልብስ አምራቾች ምርቶቻቸውን የሚያስተዋውቁባቸው አዳዲስ መንገዶች አግኝተዋል።

በዛሬው ጊዜ ፋሽን በማሳደድ ረገድ በጥንቶቹ ባለጠጋዎች እግር የተተኩት ወጣቶች ናቸው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በእያንዳንዱ ወር አዳዲስ ልብሶች ሲገዙ የልብሱ ኢንዱስትሪ ደግሞ በየዓመቱ በመቶ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ልብስ ያመርታል። * ይሁን እንጂ ይህ የተሰወረ ወጥመድ ይኖረው ይሆን?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.12 በአንድ የቅርብ ዓመት የተመረቱት ልብሶች 335 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያወጡ ተገምቷል።

[በገጽ 4, 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ፋሽን ጀማሪዎች

ለብዙ መቶ ዘመናት ለአለባበስ እንደመሪ ሆነው ይታዩ የነበሩት ነገሥታትና መኳንንት ነበሩ። በአሥራ ሰባተኛው መቶ ዘመን የፈረንሣዩ ንጉሥ ሉዊ 13ኛ የራሱን በራነት ለመሸፈን ሲል ሰው ሠራሽ ፀጉር ወይም ዊግ ማድረግ ጀመረ። ወዲያው የአውሮፓ መኳንንት ፀጉራቸውን እየተላጩ ሰው ሠራሽ ፀጉር ማድረግ ጀመሩ። ይህ ፋሽን ከአንድ መቶ ዓመት በላይ ቆይቷል።

በአሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመን የሴቶች መጽሔቶች የፋሽን አቅጣጫዎችን ከመጠቆም አልፈው ሴቶች የራሳቸውን ልብስ ሰፍተው እንዲለብሱ ቀላል የልብስ ቅዶችን ማውጣት ጀመሩ። ፊልሞችና ቴሌቪዥን በጣም በተስፋፋበት በሃያኛው መቶ ዘመን የፊልም ተዋንያን ዓለም አቀፍ አድናቆት በማትረፋቸው የፋሽን ጀማሪዎች ሆኑ። በተጨማሪም ተወዳጅ ሙዚቀኞች ያልተለመደ ዓይነት አለባበስ በመልበስ የወጣቶችን ቀልብ መሳብ ጀመሩ። ዛሬም ቢሆን ሁኔታው ያው ነው። አስተዋዋቂዎች በፋሽን ትርዒቶች፣ ዓይን በሚስቡ መጽሔቶች፣ መንገድ ላይ በሚለጠፉ ማስታወቂያዎች፣ በሱቆችና በቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች አማካኝነት የሰዎችን አዳዲስ ልብስ የመግዛት ፍላጎት ይቀሰቅሳሉ።

[ሥዕል]

ንጉሥ ሉዊ 13ኛ

[ምንጭ]

The Historian’s History of the World ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይህ የጥንቷ ግብጽ የሊኖ ልብስ ለረዥም ዘመን ጸንተው ከቆዩት የዓለም ፋሽኖች አንዱ ሆኖ ነበር

[ምንጭ]

Photograph taken by courtesy of the British Museum

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጥንቷ ሮም ሴቶች ረዥምና የተንዘረፈፈ ልብስ ይለብሱ ነበር

[ምንጭ]

From the book Historia del Traje, 1917

[በገጽ 4 እና 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኪሞኖ ከ650 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ጀምሮ እስከ አሁን የቆየ ፋሽን ሆኗል

[ምንጭ]

From the newspaper La Ilustración Artística, Volume X, 1891

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቀደሙት ዓመታት አንድ ውድ ልብስ ፋሽኑ ሳያልፍበት ዕድሜ ልክ ይቆይ ነበር

[ምንጭ]

EclectiCollections

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኢንዱስትሪው አብዮት ተራ ሰዎች ፋሽን ተከታዮች እንዲሆኑ አድርጓል

[ምንጭ]

EclectiCollections