በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አስደናቂ የሆነ የወፍ ትርዒት

አስደናቂ የሆነ የወፍ ትርዒት

አስደናቂ የሆነ የወፍ ትርዒት

ስፔይን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ጣዎሱ (ፒኮኩ) የአንድ አዲስ ትርዒት ዋና ተዋናይ ይመስል የተለያዩ ቀለማት ያሉት ባለ ግርማ መጋረጃ ፊት ቆሟል። የሰውነቱን አምስት እጥፍ ርዝመት ያላቸውና ከኋላው ወደ ላይ ቀጥ ብለው የተዘረጉት ያሸበረቁ ላባዎች የፀሐይ ብርሃን ሲያርፍባቸው ያብረቀርቃሉ።

ይህ ዓይን የሚማርክ ዕይታ ወንዱ ጣዎስ ሴቷን ለማማለል የሚያሳየው ትርዒት ነው። ትርዒቱ ወደ ማብቂያው ሲቃረብ ወፉ ላባውን ማርገብገብ ይጀምርና ይህ እንቅስቃሴ የሚፈጥረው ድምፅ ትርዒቱ በተሳካ ሁኔታ እንዲደመደም ድርሻ ያበረክታል። የወደፊት ተጓዳኙ ‘ቀልብ የሚማርክ የዓለማችን ቁጥር አንድ ማስታወቂያ’ ተብሎ ለተገለጸው ለዚህ ትርዒት እንዳትንበረከክ የሚያግድ ምን አቅም አላት?

ይሁን እንጂ ጣዎሱ ትርዒቱን ለተመልካቾችም ማሳየቱን ይቀጥላል። “ጣዎሶች ለተጓዳኝነት የሚፈልጓቸው እንስት ጣዎሶች ባሉበት ከሚያሳዩት ይልቅ ተሰብስበው በሚያዩአቸው ሰዎች ፊት በተደጋጋሚና ለረጅም ጊዜ ትርዒት እንደሚያሳዩ የሥነ ተፈጥሮ ተመራማሪዎች አረጋግጠዋል” ሲል ዎንደርስ ኦቭ ፒኮክስ የተባለው ጽሑፍ ገልጿል። ጣዎስ ኩሩ እንደሆነ የሚነገርለት የተንቆጠቆጡ ላባዎቹን ለማሳየት ያለውን ፍላጎት በመመልከት ሳይሆን አይቀርም።

እንዲህ ቢያደርግ ታዲያ ምን አለበት? ትርዒቱ ቢታይ የሚያስቆጭ አይደለም። የሚያብረቀርቅ የዓይን ቅርጽ ጣል ጣል ያለባቸው የጣዎሱ ረጃጅም ላባዎች የተለያየ ርዝመት ያላቸው በመሆኑ ቆንጆ የማራገቢያ ቅርጽ እንዲይዙ አስችሏቸዋል። የፀሐይዋ ጨረር ካረፈበት አቅጣጫ አንጻር ላባዎቹ የመዳብ፣ የነሐስና የወርቅ እንዲሁም ደማቅ ሰማያዊ፣ አረንጓዴና ሀምራዊ ቀለም ይኖራቸዋል።

የጣዎሶች ዋነኛ ተግባር ላባቸውን በኩራት ማሳየት እንደሆነ በሚታሰብበት በምዕራቡ ዓለም ሰዎች ይህ ወፍ ከዚህ ሌላ ያን ያህል ጠቀሜታ ያለው አይመስላቸውም። ይሁን እንጂ ዋነኛ መገኛው በሆነው በሕንድ ገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ትናንሽ እፉኝቶችንና ሌሎች መርዛማ እባቦችን አድኖ የሚገድል ኃይለኛ ወፍ አድርገው ይመለከቱታል። የእፉኝት መርዝ አንዳች ጉዳት የማያደርስበት መሆኑ ጣዎስ በሩቅ ምሥራቅ የመለኮትነትና ያለመሞት ባሕርይ ተምሳሌት ተደርጎ እንዲታይ አስችሎታል።

ከዛሬ 3,000 ዓመታት ገደማ በፊት ጣዎስ በመካከለኛው ምሥራቅ ከፍተኛ ተፈላጊነት ነበረው። ንጉሥ ሰሎሞን እንደ ‘ወርቅ፣ ብርና የዝሆን ጥርስ’ ከመሳሰሉ ውድ ዋጋ ከሚያወጡ ሸቀጦች በተጨማሪ ጣዎስንም ወደ አገሩ ያስመጣ ነበር። (1 ነገሥት 10:22) “የጣዎስ ዝርያ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሜድትራንያን አገሮች ሊገባ የቻለው ንጉሥ ሰሎሞን ወደ አገሩ በማስመጣቱ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም” በማለት ዘ ናቹራል ሂስትሪ ኦቭ ዘ ባይብል የተባለው መጽሐፍ ዘግቧል። ከጥቂት መቶ ዘመናት በኋላ ታላቁ እስክንድር ለእነዚህ ወፎች ካደረበት አድናቆት የተነሳ ወታደሮቹ ወፎቹን እንዳይገድሉ ትእዛዝ አውጥቶ ነበር።

በዛሬውም ጊዜ ቢሆን በጣዎስ ልዩ ትርዒት የማይማረክ ሰው የለም ለማለት ያስደፍራል። በሌላ በኩል ደግሞ የትርዒቱን አዘጋጅ መርሳት የለብንም። የአንድ አርቲስት ክህሎት በሥራው እንደሚታይ ሁሉ የአምላካችን የፈጠራ ሥራም ከፍጥረታቱ መካከል እጅግ ውብ በሆነው በዚህ ወፍ በግልጽ ተንጸባርቋል።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Cortesía del Zoo de la Casa de Campo, Madrid