ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
በተረፈ ምርት የሚነዳ መኪና
በአሁኑ ሰዓት አንድ የፊንላንድ ገበሬ ከተረፈ ምርት በሚወጣ ጋዝ የሚንቀሳቀስ መኪና አለው። ሱዎመን ሉዎንቶ የተባለው የፊንላንድ ጋዜጣ “መኪናው በነዳጅነት የሚጠቀመው በመኪናው ባለቤት እርሻ ላይ በሚገኝ የባዮጋዝ ማመንጫ ውስጥ ከሚጨመር ተረፈ ምርት የወጣውን ባዮጋዝ ነው” ሲል ዘግቧል። ባዮጋዝ በአሁኑ ጊዜ ለመኪና አገልግሎት ከሚውሉት የነዳጅ ዓይነቶች በሙሉ በደንብ በመቃጠልና አካባቢ ባለመበከል ረገድ ተወዳዳሪ አልተገኘለትም። እንዲያውም ከባዮጋዝ ተረፈ ምርቶች አንዱ በጣም ጠቃሚ የሆነ የእርሻ ማዳበሪያ ነው። በተፈጥሮ ጋዝ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች በሙሉ (በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም በተፈጥሮ ጋዝ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ሁለት ሚሊዮን እንደሚደርሱ ይገመታል) በባዮጋዝም ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ። በስዊድን ብዙ የከተማ አውቶቡሶች የሚንቀሳቀሱት በባዮጋዝ ሲሆን አንዳንድ የነዳጅ ማደያ ጣቢያዎችም ከሌሎች ነዳጆች በተጨማሪ ባዮጋዝ መሸጥ ጀምረዋል። ጽሑፉ የባዮጋዝ የመጨረሻው ጥቅም ደግሞ “ከቤንዚንም ሆነ ከናፍጣ በጣም ርካሽ መሆኑ ነው” ይላል።
የደቡብ አፍሪካ ወጣት ሰካራሞች
ዘ ስታር የተባለው የጆሃንስበርግ ጋዜጣ “ሕፃናት ከለጋ ዕድሜያቸው ጀምረው አልኮል አላግባብ መጠጣት ስለ ጀመሩ ደቡብ አፍሪካ የሰካራሞች አገር ልትሆን ነው” ሲል ያስጠቅቃል። የዘጠኝ ዓመት ልጆች ከስካራቸው ሙሉ በሙሉ ሳይነቁ ትምህርት ቤት መሄድ ጀምረዋል። ብዛታቸውም እያሻቀበ መጥቷል። እንዲህ ያለ ችግር ሊፈጠር የቻለው ለምንድን ነው? ፖሊሶች “ማስታወቂያዎች ስካርን ለወጣቶች እንደ ዘመናዊነት አድርገው ስለሚያሳዩ ነው” ይላሉ። ጋዜጣው የአልኮል መጠጥ እንደ ልብ መገኘት፣ የአልኮል መጠጥ ማኅበራዊ ተቀባይነት ማግኘቱ፣ የወላጆች ቁጥጥር መላላት፣ የዛሬዎቹ ልጆች ብዙ ነጻነትና ገንዘብ የሚያገኙ መሆናቸውን እንደ ተጨማሪ ምክንያቶች አድርጎ አቅርቧል። አንድ የሥነ አእምሮ ሐኪም “በተጨማሪም የወላጆች ቁጥጥር መላላትና ሥልጣንን ያለማክበር ዝንባሌም በሰፊው ይታያል። ይህ ደግሞ የማኅበራዊ መዋቅር መፈራረስ ምልክት ነው” ብለዋል።
የቪዲዮ ጨዋታዎች የሚያስከትሉት የጤንነት ችግር
የቪዲዮ ጨዋታዎች በልጆች ጤንነት ላይ ምን ያህል ጉዳት እንደሚያስከትሉ ወላጆች ላያውቁ እንደሚችሉ የሜክሲኮ ሲቲ ጋዜጣ የሆነው ኤል ዩኒቨርሳል ዘግቧል። የሜክሲኮ የልብ ሕክምና ማኅበር ፕሬዚዳንት የሆኑት አንቶንዮ ጎንዣለዥ ሄርሞሲሎ እንደሚሉት ከሆነ የቪዲዮ ጨዋታዎችን አዘውትረው ከሚጫወቱ ልጆች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት የደም ብዛት በሽታ ይይዛቸዋል። ለምን? ልጆቹ በቂ አካላዊ እንቅስቃሴ ካለማድረጋቸው በተጨማሪ በጨዋታው ላይ የሚሰነዘሩት ጥቃቶች፣ አምባጓሮዎችና ሌሎች ግጭቶች ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንዲገቡ ስለሚያደርጓቸው ነው። “ስፔሽያሊስቱ በዚህ ምክንያት በሜክሲኮ ዋነኛ የሞት ምክንያት የሆነው የልብና የደም ዝውውር በሽታ በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል ሲሉ አስጠንቅቀዋል” ይላል ጋዜጣው።
ከጋብቻ ውጭ የሚወለዱ ሕፃናት
በአውሮፓ ኅብረተሰብ ውስጥ “ከሚወለዱት ሕፃናት መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት የሚወለዱት ከጋብቻ ውጭ” እንደሆነ ላ ባንጋርድያ የተባለው የስፓንኛ ጋዜጣ ዘግቧል። ነባሮቹ የማኅበረሰብ እሴቶች እየተለወጡ በሄዱ መጠን “ከጋብቻ ውጭ የሚወለዱት ልጆች ቁጥር በመላው አውሮፓ እየበዛ መጥቷል።” የአውሮፓ ማኅበረሰብ የስታትስቲክስ መሥሪያ ቤት እንደሚለው ስዊድን፣ ዴንማርክና ፈረንሣይ ተቀዳሚውን ደረጃ ሲይዙ ብዛታቸውም በቅደም ተከተል 54 በመቶ፣ 46 በመቶና 39 በመቶ ሆኗል። ከዚያ የሚቀጥሉት ፊንላንድ እና ብሪታንያ ሲሆኑ በሁለቱም አገሮች ከጋብቻ ውጭ የሚወለዱ ሕፃናት ብዛት 37 በመቶ ነው። የቤተሰብ ትስስር ጠንካራ ሆኖ በኖረባቸው የሜድትራንያን አገሮች ተመሳሳይ አዝማሚያ ተስተውሏል። ለምሳሌ ያህል በቅርቡ የተጠናቀረ አኃዛዊ መረጃ በስፔይን ትዳር ከሌላቸው እናቶች የሚወለዱ ሕፃናት 19 በመቶ እንደሆነ ሲያመለክት እንደ ካታሎንያ ባሉ አንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ 22 በመቶ ደርሷል። ከአሥር ዓመት በፊት ከነበረው አኃዝ መቶ በመቶ ጨምሯል።
ከመጠን በላይ መወፈር የሚያስከትለው አደጋ
ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ “በአርባ ዓመት ዕድሜያቸው ከፍተኛ ውፍረት የሚኖራቸው ሰዎች ከቀጫጭኖቹ ቢያንስ ሦስት ዓመት ቀድሞ የመሞት አጋጣሚ ይኖራቸዋል። ይህም በመካከለኛ ዕድሜ ላይ አለመጠን መወፈር በዕድሜ ርዝመት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከማጨስ ያልተናነሰ ነው” ሲል ዘግቧል። “ይህ ጥናት እንደሚያመለክተው ከ30ዎቹ አጋማሽ እስከ 40ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ባለው ዕድሜ ከመጠን በላይ የወፈረ ሰው ከጊዜ በኋላ ቢከሳም የመሞት አጋጣሚው ከፍተኛ እንደሚሆን” ክብደት ለመቀነስ የሚረዳ የአንድ ክሊኒክ ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ሰርዠ ዣቡር ተናግረዋል። “ውፍረትህን ለመቀነስ መታገል ያለብህ ገና ወጣት ሳለህ ነው። ብዙ ከቆየህ ሊጠገን የማይችል ጉዳት ይደርስብሃል።” በተጨማሪም ክብደት መቀነስ በካንሰር የመሞት አደጋን ሊቀንስ ይችላል። የአሜሪካ ካንሰር ማኅበር በ900,000 ሰዎች ላይ ያደረገውን 16 ዓመት የፈጀ ጥናት በተመለከተ “ከወንዶች መካከል 14 በመቶ የሚሆኑት፣ ከሴቶቹ ደግሞ 20 በመቶ የሚሆኑት በካንሰር የሞቱት በውፍረታቸው ምክንያት ሳይሆን አይቀርም” ብሏል ታይምስ። ውፍረትና ካንሰር ዝምድና እንዳላቸው በርካታ ጥናቶች አረጋግጠዋል።