ዘመዶችህ እምነትህን የማይጋሩ ቢሆኑስ?
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
ዘመዶችህ እምነትህን የማይጋሩ ቢሆኑስ?
በአንድ ግምት መሠረት በዓለም ላይ ከ10,000 የሚበልጡ ሃይማኖቶችና ኑፋቄዎች አሉ። በአንድ አገር ካሉት ትልልቅ ሰዎች መካከል 16 በመቶ የሚሆኑት በአንድ ወቅት ሃይማኖታቸውን ቀይረዋል። ስለዚህ በሥጋ ዘመዳሞችና በጓደኛሞች መካከል በሃይማኖት የተነሳ አለመግባባት ቢፈጠር ምንም አያስደንቅም። አንዳንድ ጊዜ ይህ አለመግባባት ሊባባስና ዝምድናቸውን እስኪነካባቸው ድረስ ሊያጋጫቸው ይችላል። ይህም ክርስቲያኖች እምነታቸውን የማይጋሯቸውን ዘመዶቻቸውን እንዴት ሊይዟቸው ይገባል? የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል።
የተለየ ዝምድና
ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ በወላጆችና በልጆቻቸው መካከል ስላለው የተለየ ዝምድና ምን እንደሚል እንመልከት። ዘጸአት 20:12 ላይ ያለው “አባትህንና እናትህን አክብር” የሚለው ትእዛዝ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ሠርቶ እንዲያቆም ተብሎ እንደተሰጠ የሚያመለክት ምንም ፍንጭ የለም። እንዲያውም ኢየሱስ በማቴዎስ 15:4-6 ላይ ይህን ትእዛዝ ጠቅሶ ሲያብራራ የተናገረው ትልልቅ ልጆች ለወላጆቻቸው ሊሰጡ ስለሚገባቸው ክብር መሆኑ ግልጽ ነው።
የምሳሌ መጽሐፍም ለወላጆች ንቀት ስለማሳየት ጠንከር ምሳሌ 23:22 “እናትህም ባረጀች ጊዜ አትናቃት” በማለት ይመክራል። ምሳሌ 19:26 “አባቱን የሚያስከፋ እናቱንም የሚያሳድድ የሚያሳፍርና ጎስቋላ ልጅ ነው” በማለት በግልጽ ያስጠነቅቃል።
ያለ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል።ወላጆቻችንን ችላ ማለት እንደሌለብን ቅዱሳን ጽሑፎች በግልጽ ያስረዳሉ። ወላጆቻችን የእኛን ሃይማኖት የማይቀበሉ መሆናቸው ከእነሱ ጋር ያለንን ዝምድና አያፈርሰውም። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለሌሎቹ የሥጋ ዝምድናዎችና ለትዳር ጓደኛም ይሠራሉ። በግልጽ ማየት እንደምንችለው ክርስቲያኖች ዘመዶቻቸውን የመውደድ ሥነ ምግባራዊና ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታ አለባቸው።
ምክንያታዊ መሆን አስፈላጊ ነው
እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ መጥፎ ባልንጀርነትን የሚያወግዝ ሲሆን ይህ ተጽዕኖም ከቅርብ ዘመዶች ሊመጣ ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) በጥንት ጊዜ የነበሩ ብዙ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ወላጆቻቸው ከእነርሱ የተለየ አቋም ቢይዙም እንኳን ትክክል የሆነውን ነገር ደግፈው ቆመዋል። ይህ ሁኔታ በቆሬ ልጆች ላይ በግልጽ ታይቷል። (ዘኍልቁ 16:32, 33፤ 26:10, 11) እውነተኛ ክርስቲያኖች ዘመዶቻቸውን ጨምሮ ሌሎችን ለማስደሰት ብለው አቋማቸውን አያላሉም።—ሥራ 5:29
በአንዳንድ ሁኔታዎች ወላጆች ወይም የቅርብ ዘመዶች የአንድን ክርስቲያን እምነት አጥብቀው ሊቃወሙ ይችላሉ። እንዲያውም አንዳንዶቹ የእውነተኛ ክርስትና ጠላቶች ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲህ ያለ ሁኔታ በሚከሰትበት ጊዜ ክርስቲያኖች መንፈሳዊነታቸውን ለመጠበቅ ምክንያታዊ እርምጃዎችን ይወስዳሉ። ኢየሱስ “ለሰውም ቤተ ሰዎቹ ጠላቶች ይሆኑበታል። ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም” በማለት በግልጽ ተናግሯል።—ማቴዎስ 10:36, 37
እርግጥ ነው፣ ብዙዎቹ ክርስቲያኖች ከዘመዶቻቸው ከባድ ተቃውሞ አይደርስባቸውም። እነርሱ የሚያምኑባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቶች ካለመቀበል ያለፈ ነገር አያደርጉም። ቅዱሳን ጽሑፎች የክርስቶስ ተከታዮች የማያምኑ ዘመዶቻቸውን “በየዋህነት” እና “በፍርሃት” ወይም በአክብሮት እንዲይዟቸው ያበረታቷቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 2:25፤ 1 ጴጥሮስ 3:15) መጽሐፍ ቅዱስ “የጌታም ባሪያ ለሰው ሁሉ ገር ለማስተማርም የሚበቃ ለትዕግሥትም የሚጸና ሊሆን እንጂ ሊጣላ አይገባውም” በማለት በግልጽ ይመክራል። (2 ጢሞቴዎስ 2:24) ሐዋርያው ጳውሎስም ክርስቲያኖች “ማንንም የማይሰድቡ፣ የማይከራከሩ፣ ገሮች፣ ለሰው ሁሉ የዋህነትን ሁሉ የሚያሳዩ እንዲሆኑ” መክሯል።—ቲቶ 3:2
ጠይቋቸው፣ ፍቅርም አሳዩዋቸው
በ1 ጴጥሮስ 2:12 ላይ ክርስቲያኖች “ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ . . . እግዚአብሔርን ያከብሩት ዘንድ በአሕዛብ [በማያምኑት] መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን” የሚል ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። ብዙውን ጊዜ እምነታችንን የማይጋሩ ዘመዶቻችን መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወታችን ላይ ያመጣውን ለውጥ ያያሉ። ግዴለሾች ወይም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ይቃወሙ የነበሩ ብዙ ሰዎች እንደተለወጡ አስታውሱ። አንዳንድ ግለሰቦች አንድ ክርስቲያን ጥሩ ጠባይ የሚያሳየው ለምን እንደሆነ ለማወቅ የትዳር ጓደኛቸውን ወይም የልጃቸውን ጥሩ ጠባይ ለብዙ ዓመታት በቅርብ ማስተዋል ጠይቆባቸው ሊሆን ይችላል። ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሳይቀበሉ የቀሩት ክርስቲያን በሆነው ዘመዳቸው ችላ በመባላቸው ምክንያት መሆን የለበትም።
ሁኔታዎች እንደሚለያዩና አንዳንድ ክርስቲያኖች ከወላጆቻቸው ርቀው እንደሚኖሩ መገንዘብ ያስፈልጋል። ሁኔታው እንዲህ ከሆነ የተፈለገውን ያህል አዘውትሮ መጠየቅ አይቻል ይሆናል። ቢሆንም ደብዳቤ በመጻፍ፣ ስልክ በመደወል ወይም በሌላ መንገድ አዘውትሮ በመገናኘት ዘመዶቻችንን እንደምንወዳቸው ማሳየት እንችላለን። እውነተኛ ክርስቲያን ያልሆኑ ብዙ ሰዎች ሃይማኖታቸው ምንም ይሁን ምን ወላጆቻቸውንና ሌሎች ዘመዶቻቸውን ይወዳሉ አዘውትረውም ይጠይቃሉ። ታዲያ ክርስቲያን ምሥክሮች ከዚህ ያነሰ ማድረግ ይኖርባቸዋል?
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዘመዶችህን መጠየቅህ እንደምትወዳቸው እንዲሰማቸው ያደርጋል