በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሐሳብ ልውውጥ በዙሪያችን ባለው ዓለም

የሐሳብ ልውውጥ በዙሪያችን ባለው ዓለም

የሐሳብ ልውውጥ በዙሪያችን ባለው ዓለም

“የሐሳብ ልውውጥ ባይኖር ኖሮ እያንዳንዱ ሕያው ፍጡር ከሌላው የተነጠለ ደሴት ሆኖ ይኖር ነበር።”—ዘ ላንጉጅ ኦቭ አኒማልስ

በአንድ ደን ወይም በአንድ የግጦሽ ሥፍራ ወይም ግቢህ ውስጥ ባለው የአትክልት ቦታ ቁጥራቸው ይነስም ይብዛ እርስ በርስ “የሚነጋገሩ” ፍጥረታት አይጠፉም። ዘ ላንጉጅ ኦቭ አኒማልስ የተባለው መጽሐፍ “እንስሳት መልእክት ለመለዋወጥ በሁሉም የስሜት ሕዋሳታቸው ይጠቀማሉ። በሰውነታቸው እንቅስቃሴ፣ አንዱን የአካል ክፍላቸውን በማንቀሳቀስ፣ አቋቋማቸውን በመለዋወጥ፣ እንደ ሽኮኮ የሚሰነፍጥ ጠረን በማውጣት፣ እንደ ፉጨት ያለ ድምፅ በማሰማት፣ በማስካካት፣ በመዘመርና በመጮህ፣ የኤሌክትሪክ መልእክቶችን በመላክና በመቀበል፣ መብራት በማብራት፣ የቆዳ ቀለም በመቀየር፣ ‘በመጨፈር’ እንዲሁም የሚሄዱበትን ነገር በማንቀጥቀጥና በመምታት እርስ በርሳቸው መልእክት ይለዋወጣሉ።” ይሁን እንጂ የእነዚህ መልእክት ማስተላለፊያ ምልክቶች ትርጉም ምንድን ነው?

ሳይንቲስቶች ጥንቃቄ የተሞላበት ምርምር በማድረግ እንስሳት መልእክት ለማስተላለፍ የሚጠቀሙባቸውን ምልክቶች ትርጉም ለማወቅ ችለዋል። ለምሳሌ ያህል አንዲት ዶሮ እንደ ሸለምጥማጥ ያለ እንስሳ ብትመለከት ሌሎች ዶሮዎችን ለማስጠንቀቅ በቀጭን ድምፅ ኩክ፣ ኩክ፣ ኩክ የሚል ድምፅ እንደምታሰማ አስተውለዋል። ጭልፊት ብትመለከት ግን ኃይለኛ የሆነ ጆሮ የሚበጥስ ቀጭን ድምፅ ታሰማለች። ሌሎቹ ዶሮዎች የተሰጣቸው የማስጠንቀቂያ ድምፅ ከሚያስተላልፈው መልእክት ጋር የሚስማማ እርምጃ ይወስዳሉ። ይህም አእዋፍ ትርጉም ያለው መልእክት እንደሚለዋወጡ ያሳያል። ሌሎች አእዋፍም ለተለያየ ዓላማ የተለያየ መልእክት እንደሚያስተላልፉ ተስተውሏል።

“የእንስሳትን የመግባቢያ ዘዴ ለማጥናት ከሚያስችሉት ዋነኛ መንገዶች አንዱ” ይላል ሶንግስ፣ ሮርስ ኤንድ ሪችዋልስ የተባለው መጽሐፍ “ለማጥናት የተፈለገውን ድምፅ ወይም ምልክት ቀድቶ ለእንስሳቱ በማሰማት ወይም በማሳየት የሚሰጡትን ምላሽ መመልከት ነው።” በዶሮዎች ላይ የተደረገው ሙከራ ዱር ባሉት እንስሳት ላይ ከታየው ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ተገኝቷል። ይህ ዘዴ በሸረሪቶች ላይ ሳይቀር ይሠራል። ተመራማሪዎች እንስት ሸረሪቶች ፀጉራማ የፊት እግሮቻቸውን እያርገበገቡ በሚያሽኮረምሟቸው ወንድ ሸረሪቶች እንዲማረኩ የሚያደርጋቸው ምን እንደሆነ ለማወቅ ፈልገው ወንዱን ሸረሪት በቪዲዮ ከቀረጹ በኋላ በኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ ተጠቅመው እግሮቹ ላይ ያለው ፀጉር በሙሉ እንዲወገድ አደረጉ። ቪዲዮውን ከፍተው ለእንስቷ ሸረሪት ሲያሳዩዋት ስሜቷ ፈጽሞ ሳይነሳሳ ቀረ። ይህ ሙከራ ያስገኘው ትምህርት ምንድን ነው? እንስት ሸረሪቶች የሚማረኩት ፀጉራም እግሮቻቸውን ለሚያርገበግቡ ወንድ ሸረሪቶች ብቻ ነው።

በጠረን መልእክት ማስተላለፍ

ብዙ እንስሳት መልእክት የሚለዋወጡት አብዛኛውን ጊዜ ልዩ ከሆኑ እጢዎች በሚያመነጩት ፌረሞንስ በሚባል ኃይለኛ ጠረን ወይም በሽንታቸውና በኩሳቸው ሽታ አማካኝነት ነው። አንድ ሰው ግቢውን በአጥር ከልሎ እንደሚለይ ሁሉ እንደ ውሻና ድመት የመሰሉ አንዳንድ እንስሳትም ክልላቸውን በጠረናቸው አማካኝነት ያጥራሉ። ይህ በጣም ውጤታማ የሆነ ድንበር የመከለል ዘዴ በዓይን የማይታይ ቢሆንም እንኳ አንድ ዓይነት ዝርያ ያላቸው እንስሳት አለአግባብ እንዳይቀራረቡ ያስችላል።

ጠረኑ የሚሰጠው አገልግሎት ግን ድንበር በመከለል ብቻ የተወሰነ አይደለም። ሌሎች እንስሳት በጉጉት “የሚያነቡት” የማስታወቂያ ሰሌዳም ሆኖ ያገለግላል። ሃው አኒማልስ ኮምዩኒኬት የተባለው መጽሐፍ የጠረን ምልክቶች “የነዋሪውን ዕድሜ፣ ፆታ፣ አካላዊ ጥንካሬና ችሎታ እንዲሁም በጊዜው የሚገኝበትን የእርባታ ሂደት የመሰሉትን ተጨማሪ መረጃዎች ሳይዙ አይቀርም ተብሎ ይገመታል . . . የእንስሳው የጠረን ምልክት ማንነቱን እንደሚያሳውቅ መታወቂያ ካርድ ሆኖ ያገለግላል” ይላል። የእንስሳት መጠበቂያ ሠራተኞች አሳምረው እንደሚያውቁት አንዳንድ እንስሳት የጠረን ምልክታቸውን እንደ ቀላል ነገር አድርገው አይመለከቱትም። ብዙ እንስሳት የመኖሪያ አካባቢያቸውና አጥራቸው ከታጠበ በኋላ ወዲያው አካባቢያቸውን በጠረናቸው እንደሚከልሉ ተስተውሏል። በእርግጥም “የራሳቸውን ጠረን ካጡ ውጥረትና ያልተለመደ ባሕርይ እንዲያውም መካንነት ይታይባቸዋል” ይላል ከላይ የተጠቀሰው ማመሳከሪያ ጽሑፍ።

በትንንሽ ነፍሳት ዓለምም ጠረን ትልቅ ሚና ይጫወታል። ለምሳሌ ያህል የማስጠንቀቂያ ጠረኖች ነፍሳቱን ለጥቃት ወይም ለሽሽት ያነሳሳሉ። የመጥሪያ ጠረኖች ነፍሳቱ ምግብ ወደሚገኝበት ወይም ጥሩ መስፈሪያ ወደተገኘበት ቦታ እንዲሰባሰቡ ያደርጋሉ። የፆታ ጠረኖችም ከዚህ ክፍል የሚመደቡ ሲሆን አንዳንድ ፍጥረታት ይህን መልእክት የመለየት ችሎታቸው በጣም ከፍተኛ ነው። ወንድ የሐር እሳት እራቶች ሁለት አጫጭር አንቴናዎች አሏቸው። እነዚህ አንቴናዎች መልእክት የመቀበል ኃይላቸው በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ የእንስቷን አንድ ሞለኪውል ጠረን መለየት ይችላሉ! ወንዱ እንስቷን ለመፈለግ እንዲነሳሳ 200 የሚያክሉ ሞለኪውሎች ያስፈልጋሉ። ሆኖም በጠረን አማካኝነት መልእክት የሚለዋወጡት እንስሳት ብቻ አይደሉም።

“ተናጋሪ” እጽዋት

አንዳንድ እጽዋት እርስ በርሳቸው እንዲያውም ከአንዳንድ እንስሳት ጋር ሊነጋገሩ እንደሚችሉ ታውቃለህ? ዲስከቨር መጽሔት ባቄላ የሚመስሉ አንዳንድ ተክሎች እንደ ሸረሪት ባሉ ተባዮች በሚጠቁበት ጊዜ የድረሱልኝ ኬሚካል እንደሚያመነጩና በዚህ መንገድ ተባዮቹን የሚበሉ ሌሎች ተባዮችን እንደሚጠሩ ዘግቧል። በተመሳሳይም የበቆሎ፣ የትንባሆና የጥጥ ተክሎች በአባጨጓሬዎች በሚወረሩበት ጊዜ ኬሚካሎችን ወደ አየር ይረጫሉ። የአባጨጓሬዎች ደመኛ ጠላት የሆኑት ተርቦች በኬሚካሉ ይሳቡና አባጨጓሬዎቹን ለማውደም ይመጣሉ። አንድ ተመራማሪ “እጽዋት የሚናገሩት ጉዳት እየደረሰባቸው እንዳለ ለመግለጽ ብቻ አይደለም። ጉዳቱን እያደረሰባቸው ያለው ማን እንደሆነም ጭምር ለይተው ያሳውቃሉ። የተራቀቀና አስደናቂ ዘዴ ነው” ብለዋል።

እጽዋት ከሌሎች እጽዋት ጋር የሚያደርጉት የሐሳብ ግንኙነትም ቢሆን የዚያኑ ያህል አስደናቂ ነው። ዲስከቨር እንዳለው ተመራማሪዎች የአኻያ፣ የፖፕላር፣ የአልደር እና የበርች ዛፎች እርስ በርሳቸው እንደሚደማመጡ እንዲሁም የገብስ ቡቃያዎችም ከሌሎች የገብስ ቡቃያዎች ጋር እንደሚደማመጡ ደርሰውበታል። በአባጨጓሬዎች፣ በፈንገስ ወይም በዋግ አለበለዚያም በሸረሪቶች ጉዳት ሲደርስባቸው . . . በዙሪያቸው ያሉ እጽዋት ራሳቸውን ለመከላከል እንዲነሳሱ የሚያደርግ ኬሚካል ያመነጫሉ።” ከእነርሱ ጋር የማይዛመዱ ሌሎች እጽዋት እንኳን የኬሚካል ማስጠንቀቂያውን ይሰማሉ።

አንድ ተክል ጥቃት ሲፈጸምበት ወይም ማስጠንቀቂያ ሲደርሰው ራሱን ለመከላከል ይነሳል። ተባዮቹን የሚገድል ወይም ተባዮቹ ተክሉን መብላት እንዳይችሉ ወይም እንዲያቆሙ የሚያደርግ መርዝ ያመነጫል። በዚህ መስክ ወደፊት የሚደረጉ ጥናቶች ይበልጥ አስደናቂ የሆኑ ግኝቶችን ሊያስገኙ ይችላሉ። እንዲያውም አንዳንዶቹ ግኝቶች ለግብርና ሥራ ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ።

በመብራት አማካኝነት የሚተላለፉ ‘የቴሌግራም መልእክቶች’

የሥነ ምህዳር ሊቅ የሆኑት ሱዛን ትዌት ፋየር ፍላይስ ስለሚባሉት ብርሃን አብሪ በራሪ ነፍሳት በጻፉት ጽሑፍ ላይ “በአየር ላይ ሆኖ ከከዋክብት በታች ብልጭ ድርግም የሚለው መብራታቸው ተራ የሆነ የገጠር መንደሬን ያስውበው ነበር” ብለዋል። እነዚህ የጥንዚዛ ቤተሰብ የሆኑ አነስተኛ ነፍሳት “ከቀላል የማስጠንቀቂያ መብራት አንስቶ ወንዱና እንስቷ እስከሚለዋወጡት የተወሳሰበ ጥሪ የሚደርሱ መልእክቶችን ይለዋወጣሉ” ይላሉ ቱዌት። የሚፈነጥቁት የብርሃን ቀለም የሚለያይ ሲሆን አረንጓዴ፣ ቢጫ አሊያም ብርቱካንማ ሊሆን ይችላል። እንስቶቹ ብዙ ጊዜ ስለማይበሩ አብዛኛውን ጊዜ የምንመለከተው የወንዱን መብራት ነው።—“ሙቀት አልባው የፋየር ፍላይ መብራት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

እነዚህ አብሪ ነፍሳት 1,900 የሚያክል ዝርያ ያላቸው ሲሆን የሚፈነጥቁት ብርሃንም የአንዱ ከሌላው ይለያል። ለምሳሌ ያህል በእያንዳንዱ ሴኮንድ ልዩነት ውስጥ ሦስት ጊዜ ብልጭ ድርግም የሚል ወይም የተለያየ ቆይታ ያላቸው ብልጭታዎች ያሉት መልእክት ሊሆን ይችላል። ወንዱ አብሪ ነፍሳት ተጓዳኝ በሚፈልግበት ጊዜ ተጓዳኝ መፈለጉን የሚያሳየውን ኮድ ብልጭ ድርግም እያደረገ ዙሪያውን ይበራል። “እንስቷ የብልጭታውን መልእክት ትረዳና” ይላል ኦዶቦን መጽሔት “‘እዚህ ነኝ’ የሚል መልእክት የሚያስተላልፍ ብርሃን ትፈነጥቃለች።” ወንድየው ግብዣዋን ይቀበልና ወደ እርሷ ይበራል።

በዝማሬ የተካኑ ፍጥረታት

ዴቪድ አተንበሮ ዘ ላይፍ ኦቭ በርድስ በተባለው መጽሐፋቸው “በርዝመቱ፣ በውስብስብነቱና በዓይነቱ ብዛት ከአእዋፍ ዝማሬ ጋር የሚተካከል ድምፅ የሚያወጣ አንድም እንስሳ የለም” ይላሉ። የወፎች ዝማሬ የሚወጣው ከጉሮሯቸው ሳይሆን ደረታቸው ላይ ከሚገኘውና የመተንፈሻ ቧንቧቸው ወደ ሳንባ ከመድረሱ በፊት ለሁለት በሚከፈልበት አካባቢ ከሚገኘው የአካላቸው ክፍል ነው።

የአእዋፍ ዝማሬ በከፊል በውርሻ በከፊል ደግሞ ከወላጆች በመማር የሚገኝ ነው። በዚህም የተነሳ የወፎች ዝማሬ እንደየሚኖሩበት አካባቢ ለየት ያለ ቅላጼ ሊኖረው ይችላል። ዘ ላይፍ ኦቭ በርድስ እንዲህ ይላል:- “ብላክበርድ የሚባሉ የአእዋፍ ዝርያዎች በአሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመን አውሮፓውያን ሠፋሪዎች አገራቸው ሳሉ የለመዱትን ድምፅ ሰምተው እንዲደሰቱ ለማድረግ ሲባል ወደ አውስትራሊያ የተወሰዱ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የሚያሰሙት ድምፅ ከአውሮፓዎቹ የተለየ ነው።” ከአእዋፍ ዝማሬዎች ሁሉ ይበልጥ የተወሳሰበና ውብ ቃና አለው የሚባለው ላየርበርድ የሚባለው የወፍ ዝርያ ዝማሬ ሲሆን ይህም ሙሉ በሙሉ ከሌሎች አእዋፍ የተኮረጀ ዝማሬ ነው። እንዲያውም እነዚህ የወፍ ዝርያዎች ሌሎችን የመቅዳት ከፍተኛ ችሎታ ስላላቸው የሙዚቃ መሣሪያዎችን፣ የውሾችን ጩኸት፣ የማንቂያ ድምፆችን፣ የመጥረቢያ ምቶችንና የካሜራ ፊልም ማጠንጠኛ ድምፆችን ጨምረው ማንኛውንም ድምፅ መቅዳት ይችላሉ! ይህን ሁሉ አስመስሎ የመጮህ ጥረት የሚያደርጉት በዋነኝነት ተጓዳኛቸውን ለመማረክ ሲሉ ነው።

አብዛኛውን ጊዜ አፋቸውን ምግብ ቆፍሮ ለማውጣት የሚጠቀሙበት ግንደ ቆርቁሮች የአእዋፍ ዓለም ታምቡር መቺዎች ሲሆኑ ውስጡ ባዶ የሆነ ግንድ ወይም ቅርንጫፍ በአፋቸው እየደበደቡ ለሌሎች ወፎች መልእክት ያስተላልፋሉ። አንዳንዶች እንዲያውም “እንደ ቤት ክዳን ቆርቆሮ ባሉ አዳዲስ መሣሪያዎች ሊጠቀሙ ይችላሉ” ይላሉ ዴቪድ አተንበሮ። በተጨማሪም አእዋፍ በሙዚቃ እየታጀቡም ሆነ ሳይታጀቡ የሚታይ መልእክት ያስተላልፋሉ። ለምሳሌ ያህል የሚያምረውን ላባቸውን ዘርግተው በማሳየት እርስ በርሳቸው መልእክት ይለዋወጣሉ።

አውስትራሊያን ፓልም ኮካቱ የተባለው ወፍ የመኖሪያ ድንበሩን በሚያስታውቅበት ጊዜ በሁሉም ዓይነት መልእክት የማስተላለፊያ ዘዴዎች የሚጠቀም ሲሆን ይኸውም ከበሮ ይመታል፣ ያስካካል፣ ይጨፍራል እንዲሁም ክንፎቹን ያራግባል። የዛፍ ቅርንጫፍ ከቆረጠ በኋላ ቅርንጫፉን በእግሩ ይዞ የደረቀ ግንድ ይደበድብበታል። ይህንኑ እያደረገም ክንፎቹን በሠፊው ይዘረጋል፣ ጉትያውን ያወዛውዛል፣ ጭንቅላቱን ወደፊትና ወደኋላ እያደረገ ያንቀሳቅሳል፣ ከፍተኛ ድምፅ ያሰማል። በእርግጥም በጣም የሚያስደንቅ ትርዒት ነው!

አንዳንድ አእዋፍ የሚያሰሙትን የጥሪ ድምፅ ሌሎች እንስሳትም ያውቁታል። በአብዛኛው አፍሪካ ውስጥ የምትገኘውን ማር ጠቋሚ ድንቢጥ መሳይ ወፍ እንውሰድ። ይህች ወፍ ራተል ለሚባለው ፍልፈል መሳይ እንስሳ ንቦች የሠፈሩበትን ዛፍ በድምፅዋ ትጠቁማለች። ወፏ ዛፉ ላይ ወይም በዛፉ አቅራቢያ በምታርፍበት ጊዜ “ማሩ የሚገኘው እዚህ ነው!” የሚል መልእክት የሚያስተላልፍ ለየት ያለ ጥሪ ታሰማለች። እንስሳውም ዛፉ የትኛው እንደሆነ ካወቀ በኋላ ግንዱን ሰንጥቆ ማሩን መብላት ይጀምራል።

በባሕር ውስጥ የሚደረግ የመልእክት ልውውጥ

ሃይድሮፎን የተባለው የባሕር ውስጥ ማዳመጫ መሣሪያ ከተፈለሰፈ ወዲህ ተመራማሪዎች ከጥልቁ ባሕር በሚወጡት በርካታ ድምፆች በጣም ተደንቀዋል። ጎርነን ካለ ማስገምገም እስከ ቀጭን ፉጨት የሚለያዩት እነዚህ ድምፆች በጣም በርካታ በመሆናቸው ባሕር ሰርጓጅ መርከቦች እንቅስቃሴያቸውን ለማሳሳት ተጠቅመውባቸዋል። ይሁን እንጂ የዓሦቹ ድምፆች ሥርዓት የሌላቸው አይደሉም። የባሕር ሥነ ፍጥረት ተመራማሪ የሆኑት ሮበርት በርገስ ሲክሬት ላንጉጅስ ኦቭ ዘ ሲ በተባለው መጽሐፋቸው እንዲህ ብለዋል:- “አንደኛው ዓሣ ‘ካጉረመረመ፣ ካስካካና ከጮኸ’ በኋላ ያንኑ ያሰማውን ድምፅ በትክክል ሲደግም ሌላው ደግሞ ‘ካቃጨለና የተንጣጣ ድምፅ ካሰማ’ በኋላ ‘አንድ ነገር እንደሚፍቅ ወይም እንደሚሞርድ’ ባለ ድምፅ ያጅበዋል።”

ዓሦች የድምፅ አውታር ሳይኖራቸው ድምፅ ማሰማት የሚችሉት እንዴት ነው? በርገስ እንደሚሉት “አንዳንዶቹ በአየር ከሚሞላው የመዋኛ ፊኛቸው ጋር የሚያያዘውን ጡንቻ በመጠቀም የፊኛቸው ግድግዳ እንዲርገበገብ በማድረግ እንደ ከበሮ ያለ ድምፅ እንዲሰማ ያደርጋሉ።” ሌሎቹ ዓሦች ደግሞ ጥርሳቸውን እያፋጩ ወይም ስንጥባቸውን እየከፈቱና እየዘጉ ልዩ የሆነ እንደማጨብጨብ ያለ ድምፅ ያሰማሉ። ታዲያ ይህ ሁሉ ምንም ትርጉም የሌለው ባዶ “ጫጫታ” ነውን? እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ዓሦችም በየብስ እንደሚኖሩ እንስሳት ድምፅ የሚያሰሙት “ተቃራኒ ፆታን ለመሳብ፣ የጉዞ አቅጣጫቸውን ለማስተካከል፣ ጠላትን ለመከላከል፣ መልእክት ለመለዋወጥና ለማስፈራራት ነው” ይላሉ በርገስ።

በተጨማሪም ዓሦች ጥሩ የማዳመጥ ችሎታ አላቸው። እንዲያውም ብዙዎቹ የዓሣ ዝርያዎች ውስጣዊ ጆሮ ያላቸው ከመሆኑም በላይ በሽንጣቸው ላይ ከላይ እስከታች የተደረደሩ ግፊት ለመለየት የሚያስችሉ ሕዋሳት አሏቸው። እነዚህ ሕዋሳት በውኃው ውስጥ የሚጓዙትን የድምፅ ሞገዶች ንዝረት ለመለየት ያስችሏቸዋል።

ሐሳብ ለሐሳብ በመለዋወጥ ረገድ ቁንጮ የሆነው የምድር ፍጡር

የቋንቋዎች ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ኖአም ቾምስኪ “የሰው ልጆችን ቋንቋ በምናጠናበት ጊዜ የሰው ልጅ አእምሮ ልዩ ባሕርይ ወደሆነውና ወደማንነቱ መገለጫ መቅረባችን ነው” ብለዋል። የቋንቋዎች ጥናትና የሰብዓዊ እድገት ፕሮፌሰር የሆኑት ባርባራ ለስት ደግሞ “ገና ሦስት ዓመት ያልሞላቸው ጨቅላ ሕፃናት እንኳን እስካሁን በሚታወቀው የመማር ማስተማር ንድፈ ሐሳብ መሠረት ለማስረዳት የሚከብድ ቋንቋን የማቀነባበርና የማሰካካት ችሎታ አላቸው” ብለዋል።

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጅ የቋንቋን ተአምራዊ ስጦታ ከየት እንዳገኘ ምክንያታዊ ማብራሪያ ይሰጣል። ይህን ስጦታ ያገኘው የሰው ልጆችን ‘በአምሳሉ’ ከፈጠረው ከይሖዋ አምላክ እንደሆነ ይገልጻል። (ዘፍጥረት 1:27) ይሁን እንጂ በቋንቋ ክህሎታችን መለኮታዊ ኃይል የሚንጸባረቀው እንዴት ነው?

ለምሳሌ ያህል ስለ ስም አወጣጥ እንመልከት። የንግግር ጥበብ ፕሮፌሰር የሆኑት ፍራንክ ዳንስ “ስም የማውጣት ችሎታ ያለው ፍጡር የሰው ልጅ ብቻ” እንደሆነ ጽፈዋል። ይህ ችሎታ ከመለኮታዊ ምንጭ የተገኘ ተሰጥኦ እንደሆነ ቅዱሳን ጽሑፎች በግልጽ ያመለክታሉ። መጽሐፍ ቅዱስ የፍጥረት ትረካውን ገና ሲጀምር “እግዚአብሔርም ብርሃኑን ቀን ብሎ ጠራው፣ ጨለማውንም ሌሊት አለው” ይላል። (ዘፍጥረት 1:5) ኢሳይያስ 40:26 እንደሚለው አምላክ ለእያንዳንዱ ኮከብ ስም እንደሰጠ ግልጽ ነው። ይህ ደግሞ በጣም የሚያስደንቅ ችሎታ ነው!

አዳም ከተፈጠረ በኋላ ፈጣሪ ከሰጠው የመጀመሪያ ሥራዎች አንዱ ለእንስሳት ስም ማውጣት ነበር። ይህ ሥራ የአዳምን የማስተዋልና የፈጠራ ችሎታ ሳይፈታተን አልቀረም! በኋላም አዳም ለሚስቱ ሔዋን የሚል ስም አወጣላት። እርሷ ደግሞ በተራዋ የመጀመሪያ ልጃቸውን ቃየን ብላ ሰየመችው። (ዘፍጥረት 2:19, 20፤ 3:20፤ 4:1) ከዚያ ጊዜ ወዲህ የሰው ልጆች አእምሯቸው ሊያስብ ለቻለው ነገር ሁሉ ስም ከማውጣት ወደኋላ ያሉበት ጊዜ የለም። ይህን ሁሉ ያደረጉት ደግሞ ሐሳብ ለሐሳብ መግባባት እንዲችሉ ነው። አዎን ስሞች ባይኖሩ ኖሮ ሐሳብ ለሐሳብ መግባባት ምን ያህል አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል አስብ።

የሰው ልጆች ስም የማውጣት ችሎታና ፍላጎት ያላቸው ከመሆኑም በላይ ሐሳባቸውን የሚገልጹባቸው በርካታ ችሎታዎች አሏቸው። እነዚህ ሁሉ ችሎታዎች በአንደበት ላይ ብቻ የተመኩ አይደሉም። በእርግጥም ውስብስብ የሆኑ ጽንሰ ሐሳቦችን ብቻ ሳይሆን ጥልቅ የሆኑ ውስጣዊ ስሜቶችንም የምንገልጽባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። ይሁን እንጂ ቀጥለን እንደምንመለከተው የሰው ልጆች የሐሳብ ልውውጥ የሚያደርጉት እርስ በርሳቸው ብቻ አይደለም። ይህ ደግሞ ትኩረት ሰጥተን ልንመረምረው የሚገባ ጉዳይ ነው።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ሙቀት አልባው የፋየር ፍላይ መብራት

አንድ ተራ አምፑል ከሚፈጀው የኤሌክትሪክ ኃይል 90 በመቶ የሚሆነውን የሚያጠፋው በሙቀት መልክ ነው። ውስብስብ ከሆኑ ኬሚካላዊ ለውጦች የሚመነጨው የፋየር ፍላይ መብራት ግን ከ90 እስከ 98 በመቶ የሚሆነው ኃይል ወደ ብርሃን ስለሚለወጥ በሙቀት መልክ የሚባክን ምንም ኃይል የለም ሊባል ይችላል። ስለሆነም ሙቀት አልባ መብራት ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው። ብርሃን ፈጣሪዎቹ ኬሚካላዊ ለውጦች የሚካሄዱት ፎቶሳይትስ በሚባሉ ልዩ ሴሎች ውስጥ ነው። ፎቶሳይቶቹን እንዲበሩና እንዲጠፉ የሚያደርጉት ነርቮች ናቸው።

[ምንጭ]

John M. Burnley/Bruce Coleman Inc.

[በገጽ 26, 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ሐሳብ የመለዋወጥ ችሎታህን ለማሻሻል የሚረዱ ጠቃሚ ነጥቦች

1. ሌሎች የሚናገሩትን በትኩረት አዳምጥ። እኔ ብቻ ካልተናገርኩ አትበል። ሰዎች የቃላት ወይም የሰዋስው ግድፈቶችን ችላ ብለው ያልፋሉ፣ እኔ ብቻ ካልተናገርኩ በሚልና ለመስማት በማይፈልግ ሰው ግን ቅር መሰኘታቸው አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስም “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ” ይሁን ይላል።—ያዕቆብ 1:19

2. በሕይወት ስለሚያጋጥሙና በዙሪያህ ስላሉ ነገሮች የማወቅ ፍላጎት ይኑርህ። ጥሩ መራጭ በመሆን የተለያዩ ዓይነት ጽሑፎችን አንብብ። ስላወቅኸው ነገር ከሰዎች ጋር በምትወያይበት ጊዜ ትሑትና ራስህን ዝቅ የምታደርግ ሁን።—መዝሙር 5:5፤ ምሳሌ 11:2

3. የቃላት እውቀትህን አስፋ። የምትጠቀምባቸው ቃላት ግን በሌሎች ዘንድ የሚታወቁ መሆን አለባቸው እንጂ ማንነትህን ለማሳየት የሚነገሩ መሆን የለባቸውም። ሰዎች ስለ ኢየሱስ ሲናገሩ “እንደዚህ ሰው ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም” ብለው ነበር። (ዮሐንስ 7:46) አዎን “መጽሐፍን የማያውቁና ያልተማሩ” ሰዎች እንኳን የኢየሱስን ቃላት መረዳት አላዳገታቸውም።—ሥራ 4:13

4. ንግግርህ ግልጽ ይሁን። ቃላትንም አጥርተህ ጥራ። ይሁን እንጂ ቃላትን በተራቀቀ መንገድ በመጥራት በሌሎች ዘንድ ለመታየት አትሞክር። አንዳንድ ፊደሎችን ሳንውጥ ቃላትን አጥርተን ስንጠራ ንግግራችን ግርማ ሞገስ ያለው እንዲሆን ከማድረጋችንም በላይ አድማጮቻችንን እንጠቅማለን።—1 ቆሮንቶስ 14:7-9

5. የመነጋገር ችሎታህ ከፈጣሪ ያገኘኸው ውድ ስጦታ መሆኑን አትዘንጋ። ይህን ማስታወስህ ለዚህ ለተሰጠህ ችሎታ ተገቢ አክብሮት እንዲኖርህ ያነሳሳሃል።—ያዕቆብ 1:17

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሐር የእሳት እራት መልእክት የመቀበል ኃይላቸው ከፍተኛ የሆነ አንቴናዎች አሉት

[ምንጭ]

Courtesy Phil Pellitteri

[በገጽ 24 እና 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ግንደ ቆርቁር

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የገነት ወፍ

[ምንጭ]

© Michael S. Yamashita/CORBIS

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፓልም ኮካቱ

[ምንጭ]

Roland Seitre