ፋሽን ተከታይ መሆን ያለው ጎጂ ገጽታ
ፋሽን ተከታይ መሆን ያለው ጎጂ ገጽታ
ፋሽን መከተል ቁመና እንደሚያሳምርና በራስ የመተማመን ስሜት እንደሚያዳብር ምንም ጥርጥር የለውም። የሚያምርብንን ልብስ መልበሳችን አንዳንድ ጉድለታችንን የሚሸፍን ከመሆኑም በላይ በውበት ላይ ውበት ሊጨምርልን ይችላል። በተጨማሪም ሌሎች ለእኛ ጥሩ አመለካከት እንዲኖራቸው ሊያደርግ ይችላል።
ይሁን እንጂ የፋሽኑ ዓለም ችላ ሊባል የማይገባው ጎጂ ገጽታም አለው። ሸማቾች አዳዲስ ልብስ በመግዛት ማለቂያ የሌለው ሽክርክሪት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። የፋሽኑ ኢንዱስትሪ አዳዲስ ስታይሎችን ማውጣት እንደማያቆም የታወቀ ነው። ምክንያቱም ፋሽኖች ጊዜያቸው ቶሎ ባለፈ መጠን ፋሽን አውጪዎችና ልብስ ነጋዴዎች የሚያጋብሱት ትርፍ የዚያኑ ያህል ይበልጥ ይጨምራል። ፋሽን አውጪ የሆኑት ጋብርኤሌ ቻነል “ፋሽን የሚወጣው እንዴት እንደሚያልፍበትም ታስቦበት ነው” በማለት በትክክል ተናግረዋል። ስለዚህ ጥንቁቅ ያልሆነ ሸማች ከጊዜው ጋር እኩል ለመራመድ ሲል ብቻ አዳዲስ ልብሶችን መግዛት እንደሚኖርበት ይሰማዋል።
በተጨማሪም ማስታወቂያዎች ለሚያሳድሩት ጫና የመሸነፍ አደጋም አለ። የፋሽን ኩባንያዎች ብዙውን ጊዜ ልብሶቻቸውን በመልበስ ደስታ እንዳገኙ ለሚያሳዩ ማስታወቂያዎች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያጠፋሉ። እነዚህ መልእክቶች ጠንካራ ጫና ሊያሳድሩ ይችላሉ። በስፔይን የሚኖር አንድ መምህር “ለወጣቶች በወቅቱ ተወዳጅ የሆነውን ጫማ ለማድረግ አለመቻልን ያህል ቅስማቸውን የሚሰብር ነገር የለም” ብለዋል።
በፋሽን መማረክ
አንዳንድ ቡድኖች አንድን ዓይነት አለባበስ የሚመርጡት ማንነታቸውን ለማሳየት ነው። የሚለብሱት ልብስ የማኅበረሰቡ ተቃዋሚዎች፣ ልቅ የሆነ አኗኗር የሚከተሉ፣ ሌላው ቀርቶ ዓመፀኞች ወይም ዘረኞች መሆናቸውን ሊያመለክት ይችላል። ከእነዚህ አለባበሶች አንዳንዶቹ በጣም ቅጥ ያጡ ወይም የሚያስጠሉ ቢሆኑም እርስ በርስ ለመመሳሰል ሲሉ የቡድኑ አባሎች በሙሉ ይለብሱታል። የቡድኑን አስተሳሰብ የማይከተሉ እንኳን በአለባበሳቸው ሊማረኩ ይችላሉ። እነዚህ በቡድኑ አለባበስ የተማረኩ ሰዎች የቡድኑ አባል ባይሆኑም እንኳን መሠረታዊ እምነቶቻቸውን እንደሚከተሉ ተደርገው ሊታዩ ይችላሉ።
ፋሽኖች ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ። እንዲያውም አንዳንዶቹ ከጥቂት ወራት ያለፈ ዕድሜ አይኖራቸውም። ጀማሪው አንድ የታወቀ ሙዚቀኛ ወይም ሌላ ታዋቂ ሰው ሊሆን ይችላል። ጥቂት ፋሽኖች ግን ዘላቂ ሆነው ይቀራሉ። ለምሳሌ ያህል ሰማያዊ ጂንስ በ1950ዎቹና 60ዎቹ ዓመታት ማኅበረሰቡን የሚቃወሙ ወጣቶች የሚያዘወትሩት ልብስ ነበር። አሁን ግን በተለያየ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች በተለያየ ወቅት የሚለብሱት ልብስ ሆኗል።
በጣም አምሮ የመታየት ፍላጎት
ለፋሽን ትልቅ ቦታ የሚሰጡ ሰዎች ስለ መልካቸውና ስለ ቁመናቸው ከሚገባው በላይ መጨነቅ ሊጀምሩ ይችላሉ። የፋሽን አስተዋዋቂዎች አብዛኛውን ጊዜ ለግላጎችና ቀጭኖች ሲሆኑ ቁመናቸውንና መልካቸውን በያለንበት እንድናይ እንደረጋለን። * “ትክክለኛ” እንደሆነ ተደርጎ የሚታየው ቁመና ከመኪና እስከ ከረሜላ የሚደርሱ የተለያዩ ሸቀጦችን ለማሻሻጥ ይውላል። የብሪታንያ የማኅበራዊ ጉዳዮች ምርምር ማዕከል “በአሁኑ ጊዜ ወጣት ሴቶች በአንድ ቀን ውስጥ የሚያዩአቸው ቆነጃጅት ቁጥር እናቶቻችን በወጣትነት ዕድሜያቸው በሙሉ ካዩአቸው ይበልጣል” ብሏል።
ይህ ዓይነቱ የማስታወቂያ ውርጅብኝ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ለምሳሌ ያህል በዩናይትድ ስቴትስ በኒውስዊክ * የአመጋገብ ሥርዓት መቃወስ የገጠማት ኒአቨዝ አልቫረዝ የተባለች አንዲት ስፔይናዊት የፋሽን አስተዋዋቂ “መወፈር ከሞት ይልቅ ያስፈራኛል” ብላለች።
መጽሔት ላይ የሠፈረ አንድ ጥናት ከነጭ ወጣቶች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት በመልካቸውና በቁመናቸው እንደማይደሰቱ አመልክቷል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ መልካቸውንና ቁመናቸውን ለማስተካከል የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። ሆኖም የማኅበራዊ ጉዳዮች ምርምር ማዕከሉ እንደገለጸው ከጠቅላላዎቹ ሴቶች መካከል በመገናኛ ብዙኃን የሚወደሰው የክብደትና የቁመት መጠን ላይ የሚደርሱት 5 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። ይሁን እንጂ ለቀጫጭን ሴቶች ከፍተኛ አድናቆት መሰጠቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶችን ለባርነት ዳርጓቸዋል። አንዳንዶቹ ለመክሳት በሚያደርጉት ጥረት አኖሬክሲያ የተባለ የአመጋገብ ሥርዓት ቀውስ ገጥሟቸዋል።እርግጥ እንደ አኖሬክሲያ እና ቡሊሚያ የመሰሉት የአመጋገብ ሥርዓት መቃወስ በሌሎች በርካታ ምክንያቶችም ሊመጡ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ዶክተር አን ጌይሞ እና ሚሸል ላክዞነር “በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ለዚህ ምክንያቱ ቅጥነትን ማምለክ ነው” ብለዋል።
ፋሽን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ገጽታ እንዳለው ግልጽ ነው። መሠረታዊ የሆነውን አምሮ የመታየትንና አዲስ ልብስ የመልበስን ሰብዓዊ ፍላጎት ያሟላል። ይሁን እንጂ ቅጥ ያጡ ፋሽኖችን መከተል መጥፎ ስም ሊያሰጠን ይችላል። ለመልካችንና ለቁመናችን ከመጠን በላይ የምንጨነቅ ከሆነ ማንነታችን በውስጣዊ ባሕርያችን ሳይሆን በውጪያዊ ገጽታችን ላይ የተመካ ነው ብለን እንደምናምን ሊያስመስልብን ይችላል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው አልቫረዝ “ለአንድ ሰው ውጪያዊ መልክና ቁመና ሳይሆን ለችሎታውና ለውስጣዊ ማንነቱ የበለጠ ዋጋ መስጠት ይኖርብናል” ብላለች። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው የአመለካከት ለውጥ በቅርብ ጊዜ ይመጣል ተብሎ አይታሰብም። ታዲያ ለፋሽን ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖረን የሚችለው እንዴት ነው?
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.9 ፋሽን አስተዋዋቂዎች “ቢያንስ 1.74 ሜትር ቁመት ያላቸው፣ በጣም ቀጫጭኖች፣ ከጉንጫቸው በላይ ያለው አጥንታቸው ወጣ ያለ፣ ወፈር ያለ ከንፈር፣ ትላልቅ ዓይኖች፣ ረዣዥም ቅልጥሞች፣ በጣም ትልቅ ሳይሆን ቀጥ ያለ አፍንጫ ያላቸው” እንዲሆኑ እንደሚፈለግ ታይም መጽሔት ዘግቧል።
^ አን.10 የዩናይትድ ስቴትስ የአኖሬክሲያ ነርቮሳና የተዛማጅ በሽታዎች ብሔራዊ ማኅበር በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ስምንት ሚሊዮን አመጋገባቸው የተቃወሰባቸው ሕሙማን ሲኖሩ ጥቂት የማይባሉ ደግሞ በሕመሙ ምክንያት ይሞታሉ። ከእነዚህ መካከል 86 በመቶ የሚሆኑት የአመጋገብ ሥርዓት ቀውስ የሚገጥማቸው ከ21 ዓመት ዕድሜያቸው በፊት ነው።
[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
አሁን ይኼን የሚለብስ ሰው አለ?
የኒው ዮርክ፣ የፓሪስና የሚላን ፋሽን ቤቶች በጸደይና በበልግ ወራት ታዋቂ ፋሽን አውጪዎች ያዘጋጅዋቸውን ልብሶች ለሕዝብ ያሳያሉ። ከእነዚህ ልብሶች ብዙዎቹ በጣም ውድ ከመሆናቸውም በላይ ፈጽሞ ሊለበሱ የማይችሉ ናቸው ባይባሉም ለመልበስ የሚመቹ ግን አይደሉም። ስፔይናዊው ፋሽን አውጪ ሑዋን ዱዮስ “የምትመለከቷቸው ቅጥ የለሽና ውድ ፋሽኖች ሕዝቡ እንዲለብሳቸው ተብለው የሚዘጋጁ አይደሉም” ብለዋል። “የፋሽን ትርዒቱ ዋነኛ ዓላማ ለእይታ የቀረቡትን ልብሶች ከማሻሻጥ ይልቅ ንድፍ አውጪውን ወይም የልብሶቹን የንግድ ምልክት ማስተዋወቅ ነው። ለምሳሌ ያህል አንድ ፋሽን አውጪ ልዩ ልብስ በማዘጋጀቱ ምክንያት በመገናኛ ብዙኃን የሚያተርፈው አድናቆት ስሙ የተለጠፈበትን ሽቶ ለማሻሻጥ ሊረዳው ይችላል።”
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፋሽን ተከታይ መሆን ብዙ ኪሣራ ሊያስከትል ይችላል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዳንዶች ለመክሳት በሚያደርጉት ጥረት ለከባድ ህመም ይዳረጋሉ
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዳንድ የአለባበስ ፋሽኖችን መከተል ከአንድ ዓይነት ቡድን ጋር ሊያስመድበን ይችላል