በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጃችሁ ትኩሳት ሲይዘው

ልጃችሁ ትኩሳት ሲይዘው

ልጃችሁ ትኩሳት ሲይዘው

“አሞኛል!” ልጃችሁ እንዲህ ቢላችሁ በአፋጣኝ የምትወስዱት እርምጃ የሰውነቱን ሙቀት መለካት ነው። ትኩሳት ካለው እንደምትደነግጡ የታወቀ ነው።

ዩናይትድ ስቴትስ፣ ባልቲሞር፣ ሜሪላንድ በሚገኘው በጆን ሆፕኪንስ የልጆች ማዕከል በተደረገው ጥናት መሠረት 91 በመቶ የሚሆኑት ወላጆች “መጠነኛ ትኩሳትም እንኳን ራስን አስቶ ሊጥል ወይም እንደ አእምሮ በሽታ ያለ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል” ያምናሉ። ይኸው ጥናት እንዳመለከተው “89 በመቶ የሚሆኑት ወላጆች የልጃቸው ትኩሳት 38.9 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ከመድረሱ በፊት ትኩሳት የሚያበርድ መድኃኒት ሰጥተዋል።”

ልጃችሁ ትኩሳት ሲይዘው መደናገጥ የማይኖርባችሁ ለምንድን ነው? ትኩሳቱን ለማብረድ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

ትኩሳት ያለው ጥቅም

አንድን ሰው ትኩሳት እንዲይዘው የሚያደርገው ምንድን ነው? የአንድ የጤናማ ሰው ሙቀት (ቴርሞሜትሩ አፍ ውስጥ ተደርጎ ሲለካ) 37 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ገደማ ቢሆንም የአንድ ሰው የሰውነት ሙቀት በቀን ውስጥ በአንድ ወይም በሁለት ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሊጨምር ወይም ሊቀንስ ይችላል። * የሰውነትህ ሙቀት ጧት ላይ ዝቅ ሊል ከሰዓት በኋላ ደግሞ ከፍ ሊል ይችላል። ከአንጎል ሥር የሚገኘው ሃይፖታላመስ የሚባለው የአንጎል ክፍል ልክ እንደ ሙቀት መቆጣጠሪያ መሣሪያ የሰውነትን ሙቀት ይቆጣጠራል። ባክቴሪያ ወይም ቫይረስ ወደ ሰውነታችን ሲገባ የሰውነት በሽታ ተከላካይ ሕዋሳት በደም ውስጥ ፓይሮጅንስ የተባሉ ቅመሞችን ያመነጫሉ። ይህም ትኩሳት ያስከትላል። በዚህ ጊዜ ሃይፖታላመስ የተባለው የአንጎል ክፍል የሰውነታችን ሙቀት ከፍ እንዲል ያደርጋል።

ትኩሳት ሕመም ሊያስከትልና የሰውነት ፈሳሽ እንዲቀንስ ሊያደርግ ይችላል። ሆኖም እነዚህ ሁኔታዎች መከሰታቸው ጉዳት አለው ማለት አይደለም። እንዲያውም የማዮ የሕክምና ትምህርትና ምርምር ተቋም ትኩሳት ሰውነት በባክቴሪያ ወይም በቫይረስ የሚከሰቱ ሕመሞችን እንዲያስወግድ በመርዳት ረገድ ቁልፍ ሚና ሳይጫወት እንደማይቀር ገምተዋል። “ጉንፋንንና ሌሎች የመተንፈሻ አካል በሽታዎችን የሚያስከትሉ ቫይረሶች ቀዝቃዛ የአየር ጠባይ ይወዳሉ። ሰውነትህ መጠነኛ ትኩሳት እንዲፈጠር በማድረግ ቫይረሶቹ እንዲወገዱ ያደርጋል።” ይኸው ምንጭ አክሎ እንደገለጸው “መጀመሪያ ላይ የተፈጠረውን አነስተኛ የትኩሳት መጠን መቀነሱ አላስፈላጊ ከመሆኑም በላይ የልጃችሁን የተፈጥሮ የፈውስ ሂደት እንዲቃወስ ሊያደርግ ይችላል።” እንዲያውም በሜክሲኮ የሚገኝ አንድ ሆስፒታል አንዳንድ በሽታዎችን የሚያክመው የሰውነትን ሙቀት ከፍ በማድረግ ሲሆን ይህም ሃይፐርተርሚያ ተብሎ ይጠራል።

አሜሪካ የሚገኙት ዶክተር አል ሳክሼቲ እንዲህ በማለት ተናግረዋል:- “አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ትኩሳት በራሱ ችግር አያስከትልም። ሆኖም በሰውነታችን ውስጥ በሽታ ሊኖር እንደሚችል የሚጠቁም ምልክት ይሰጣል። ስለዚህ አንድ ሕፃን ትኩሳት ሲይዘው ትኩረት ልናደርግ የሚገባን በልጁና ባጋጠመው ሕመም ላይ እንጂ ሙቀት መለካቱ ላይ መሆን የለበትም።” አሜሪካ የሚገኝ አንድ የልጆች አካዳሚ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል:- “ልጃችሁ አመመኝ እያለ ካላስቸገራችሁ ወይም ከዚህ በፊት በትኩሳት የተነሳ የሰውነት መንቀጥቀጥ አጋጥሞት ካልነበረ በስተቀር ከ38.3 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በታች ለሆነ ትኩሳት ሕክምና አያስፈልግም። ልጃችሁ ከዚህ በፊት በትኩሳት የተነሳ የሰውነት መንቀጥቀጥ ወይም ሥር የሰደደ በሽታ አጋጥሞት የሚያውቅ ካልሆነ በስተቀር ከ38.3 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ የሆነ የሰውነት ሙቀትም እንኳን ቢሆን በራሱ አደገኛ ወይም አሳሳቢ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የልጃችሁን ሁኔታ መከታተሉ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል። በጥሩ ሁኔታ የሚበላና የሚተኛ እንዲሁም የሚጫወት ከሆነ ሕክምና ላያስፈልገው ይችላል።”

መጠነኛ ትኩሳትን ማከም የሚቻለው እንዴት ነው?

ይህ ማለት ግን ልጃችሁን ለመርዳት ልታደርጉ የምትችሉት ምንም ነገር የለም ማለት አይደለም። አንዳንድ የሕክምና ባለሞያዎች መጠነኛ ትኩሳትን ለማከም የሚረዳ የሚከተለውን ምክር ይሰጣሉ:- ልጃችሁን ቀዝቀዝ ባለ ክፍል ውስጥ አስተኙት። ቀለል ያለ ልብስ አልብሱት። (ከልክ በላይ እንዲሞቀው ማድረግ ትኩሳቱን ሊያባብስበት ይችላል።) ትኩሳት የሰውነትን ፈሳሽ ሊያሟጥጥ ስለሚችል እንደ ውኃ፣ ውኃ የተደባለቀበት የፍራፍሬ ጭማቂና ሾርባ የመሳሰሉ ፈሳሾችን አጠጡት። * (እንደ ለስላሳ መጠጥ ወይም ሻይ ያሉ ካፌይን ያለባቸው መጠጦች ብዙ የማሸናት ባሕርይ ስላላቸው ከሰውነት ውስጥ ብዙ ፈሳሽ እንዲወጣ ሊያደርጉ ይችላሉ።) ሕፃናት ከጡት እንዳይነጠሉ ማድረግ ያስፈልጋል። ትኩሳት ጨጓራ ሥራውን በቅልጥፍና እንዳያከናውን ስለሚያደርግ ልጃችሁን በቀላሉ የማይፈጩ ምግቦችን አትመግቡት።

የልጁ ትኩሳት ከ38.9 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሲያልፍ እንደ ፓራሴታሞል ወይም አይቢዩፕሮፈን ያሉ ትኩሳት የሚቀንሱ መድኃኒቶችን መስጠት ይቻላል። ይሁንና በመድኃኒቶቹ ላይ የሚገኘውን መመሪያ መከተል አስፈላጊ ነው። (ከሁለት ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት ሐኪም ሳያማክሩ ምንም ዓይነት መድኃኒት መስጠት አይገባም።) ትኩሳት የሚያበርዱ መድኃኒቶች ቫይረሶችን አይገድሉም። ስለዚህ መድኃኒቶቹ ሥቃይ ለማስታገስ ካልሆነ በስተቀር ልጁ ከያዘው ጉንፋን ወይም ጉንፋን መሰል ሕመም ቶሎ እንዲድን አይረዱም። አስፕሪን ሬየስ ሲንድሮም የተባለ ለሕይወት አስጊ የሆነ የነርቭ በሽታ ሊያስከትል ስለሚችል ትኩሳት ለማብረድ ብሎ ከ16 ዓመት በታች ለሆኑ ልጆች መስጠት ተገቢ እንዳልሆነ አንዳንድ ባለሞያዎች ይመክራሉ። *

እስከ ቁርጭምጭሚት የሚደርስ ለብ ያለ ውኃ ሳፋ ውስጥ ጨምሮ ልጁን እዚያ ውስጥ ካስቀመጡ በኋላ ስፖንጅ ወይም ጨርቅ በውኃ እያራሱ ሰውነቱ ላይ በማፍሰስ ትኩሳቱ እንዲቀንስ ማድረግ ይቻላል። (መርዝነት ሊኖረው ስለሚችል ገላውን ለማሸት አልኮል አትጠቀሙ።)

ሣጥኑ አንድ ሰው ልጁን ወደ ሐኪም ቤት መቼ መውሰድ እንዳለበት አንዳንድ ጠቃሚ መረጃዎችን ይዟል። እንደ ጉድፍ፣ ኢቦላ፣ ታይፎይድ ወይም ቢጫ ወባ ያሉ በቫይረስ የሚመጡ ተዛማች በሽታዎች ባሉበት አካባቢ የሚኖር ሰው ትኩሳት ሲይዘው ቶሎ ብሎ ወደ ሐኪም ቤት መሄድ ይኖርበታል።

በአጠቃላይ ሲታይ በቅድሚያ ማድረግ ያለብህ ልጅህን ማረጋጋት ነው። በትኩሳት ምክንያት የነርቭ ችግር ወይም ሞት ሊያጋጥም የሚችለው አልፎ አልፎ እንደሆነ መዘንጋት የለብህም። በትኩሳት ምክንያት ራስን ስቶ መውደቅ ሊያጋጥም ቢችልም ይህ ሁኔታ ከማስደንገጡ በቀር የሚያስከትለው ዘላቂ መዘዝ አይኖርም።

እርግጥ ነው፣ ከሁሉ የተሻለው ልጃችሁ እንዳይታመም ጥንቃቄ ማድረግ ነው። እንዲህ ማድረግ የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለው ውጤታማ መንገድ ንጽሕናን እንዴት መጠበቅ እንደሚቻል ልጃችሁን ማስተማር ነው። ልጆች በተለይ ምግብ ከመብላታቸው በፊት፣ ከተጸዳዱ በኋላ፣ ሕዝብ በበዛበት አካባቢ ከቆዩ ወይም ለማዳ እንስሳትን ካሻሹ እጃቸውን እንዲታጠቡ አስተምሯቸው። የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርገህ ልጅህ መጠነኛ ትኩሳት ቢይዘው መደናገጥ አይኖርብህም። እስካሁን እንዳየነው ልጅህ እንዲያገግም ለመርዳት ልታደርገው የምትችለው ብዙ ነገር አለ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.6 የሰውነት ሙቀት በሚለካበት ቦታና በመለኪያው መሣሪያ ዓይነት ሊለያይ ይችላል።

^ አን.10 ተቅማጥና ማስመለስ የታከለበት ትኩሳት ሲያጋጥም የሰውነትን ፈሳሽ ለመጠበቅ የሚያገለግል መመሪያ በሚያዝያ 8, 1995 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 11 ላይ ወጥቷል።

^ አን.11 ሬየስ ሲንድሮም በቫይረስ የሚመጣ ሕመምን ተከትሎ የሚከሰት ከባድ የልጆች የነርቭ በሽታ ነው።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ትኩሳት የያዘው ልጅ ሐኪም ቤት መወሰድ የሚኖርበት. . .

▪ ዕድሜው ገና ሦስት ወር ወይም ከዚያ በታች ከሆነና ትኩሳቱ 38 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ወይም ከዚያ በላይ ከሆነ

▪ ዕድሜው ከሦስት እስከ ስድስት ወር ሆኖ የሰውነት ሙቀቱ 38.3 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ወይም ከዚያ በላይ ከሆነ

▪ ዕድሜው ከስድስት ወር በላይ ሆኖ የሰውነት ሙቀቱ 40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ወይም ከዚያ በላይ ከሆነ

▪ ፈሳሽ መውሰድ እምቢ ካለና የሰውነቱ ፈሳሽ እንደተሟጠጠ የሚያሳይ ምልክት ሲኖር

▪ ራሱን ስቶ ከወደቀ ወይም ከልክ ያለፈ መዝለፍለፍ ከታየበት

▪ ሰባ ሁለት ሰዓት ካለፈ በኋላም ትኩሳቱ ካልበረደለት

▪ ያለማቋረጥ ካለቀሰ፣ እንደ ቅዠትና የአእምሮ መታወክ ከገጠመው

▪ ገላው ላይ ሽፍታ ከወጣበትና የመተንፈስ ችግር ካጋጠመው፣ የሚያስቀምጠው ወይም በተደጋጋሚ የሚያስመልሰው ከሆነ

▪ አንገቱን ማዞር ካቃተው ወይም ከባድ ራስ ምታት ከገጠመው

[ምንጭ]

ምንጭ:- የአሜሪካ የሕፃናት ሕክምና አካዳሚ