ሳሙና—“ራስህ የምትወስደው ክትባት”
ሳሙና—“ራስህ የምትወስደው ክትባት”
“በዓለማችን ላይ የሕፃናትን ሕይወት በመቅጠፍ ሁለተኛውን ደረጃ የያዘው ትልቁ ገዳይ የወባ በሽታ፣ ሳምባ ነቀርሳ ወይም ኤድስ አይደለም። ይህ ቀሳፊ በሽታ . . . ተቅማጥ ነው” ሲል ዚ ኢኮኖሚስት መጽሔት ዘግቧል። ሆኖም ለሞት የተዳረጉት እነዚህ ሕፃናት እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው አዘውትረው እጃቸውን በሳሙና የሚታጠቡ ቢሆኑ ኖሮ በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ልጆች በሕይወት በተገኙ ነበር።
በለንደን ስኩል ኦቭ ሃይጂን ኤንድ ትሮፒካል ሜዲሲን (የለንደን የንጽሕና አጠባበቅና የቆላማ አካባቢዎች ሕክምና ትምህርት ቤት) ባልደረባ የሆኑ ተመራማሪዎች “እጅን በተገቢው መንገድ መታጠብ የተቅማጥ በሽታን 43 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል” በጥናት እንዳረጋገጡ ዚ ኢኮኖሚስት ተናግሯል። “ይኸው ዘዴ ዋነኛው የሕፃናት ገዳይ በሆነው የመተንፈሻ አካላት በሽታ ረገድም የዚያኑ ያህል ውጤታማ ሊሆን ይችላል። በአሜሪካ ጦር ሠራዊት ላይ የተካሄደ አንድ ሰፊ ጥናት ወታደሮቹ በቀን አምስት ጊዜ እጃቸውን መታጠብ በመጀመራቸው የነበረባቸው ከአፍንጫ ጋር የተያያዘ ችግርና ሳል 45 በመቶ መቀነሱ ተረጋግጧል።” በታዳጊ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ቤተሰቦች ሳሙና መግዛት ከአቅማቸው በላይ አይደለም። በመሆኑም እጅን በሳሙና መታጠብ “ራስህ የምትወስደው ክትባት” እንደሆነ መገለጹ ትክክል ነው። ያውም አንዳች ሥቃይ የማያስከትል ክትባት!
መጽሐፍ ቅዱስም ንጽሕናችንን እንድንጠብቅ ያበረታታናል። ሁለተኛ ቆሮንቶስ 7:1 “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ” ይላል። አምላክ በዋነኝነት ትኩረት የሚሰጠው ለመንፈሳዊ ንጽሕናችን ቢሆንም አካላዊ ንጽሕናም አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል። (ዘሌዋውያን ምዕራፍ 12-15) እርግጥ፣ በዚህ ረገድ አክራሪ እንድንሆን አይጠብቅብንም። ይሁንና ከተጸዳዳን በኋላ፣ የሕፃን ልጅ የሽንት ጨርቅ ካጠብን ወይም ከቀየርን በኋላ፣ ምግብ መሥራት ከመጀመራችን ወይም ለመመገብ ከመቅረባችን በፊት እንዲሁም ለጤና ጠንቅ የሆኑ ጀርሞች ወይም ቫይረሶች ወደ ሌሎች ልናስተላልፍ እንደምንችል በሚሰማን በማንኛውም ጊዜ እጃችንን የመታጠብ ልማድ ሊኖረን ይገባል። አዘውትረን እጃችንን በመታጠብ ለቤተሰባችንም ሆነ ለምናገኛቸው ሰዎች በሙሉ ክርስቲያናዊ ፍቅር እንዳለን ማሳየት እንችላለን።—ማርቆስ 12:31