በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በገበሬዎች ላይ የተደቀኑ ችግሮች

በገበሬዎች ላይ የተደቀኑ ችግሮች

በገበሬዎች ላይ የተደቀኑ ችግሮች

ሪቻርድ ዛሬም የሚያርሰው ቅድመ አያቱ ከ100 ዓመት በፊት ያርሱ የነበረውን መሬት ነው። ይሁን እንጂ ይህ ካናዳዊ ገበሬ በ2001 ለመጀመሪያ ጊዜ አራት ትውልዶችን ከመገበው ከዚህ እርሻ ምንም ምርት ሳያገኝ ቀረ። ሰብሉን ድርቅ አወደመበት። ባለፉት ዓመታት የነበረው የእህል ዋጋ መርከስና የግብርና መሣሪያዎች ወጪ መጨመር የደረሰበትን ችግር አባብሶበታል። ሪቻርድ “የችግሩ ማጥ ከቀን ወደ ቀን ይበልጥ እየባሰ ቢሄድም ምንም ዓይነት መፍትሔ ማግኘት አልተቻለም” በማለት ያማርራል።

በበቆሎ ምርቷ በምትታወቀው በዩናይትድ ስቴትስ መካከለኛ ምዕራብ ክፍል የሚኖረው ላሪ ለ115 ዓመታት የቤተሰቦቹ ንብረት ሆኖ የቆየ እርሻ ነበረው። “እርሻውን የማቆየትና ትርፋማ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለብኝ ይሰማኝ ነበር። . . . ግን አልቻልኩም” ይላል። ላሪ እና ባለቤቱ እርሻቸውን አጡ።

የችግሩ ሰለባ የሆኑት ገበሬዎች ላሪና ሪቻርድ ብቻ አይደሉም። በብሪታንያ በቤት እንስሳት ላይ የደረሰው የእግርና የአፍ በሽታ በገበሬዎች ላይ ከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራና የስሜት ጉዳት አስከትሏል። አንድ የዜና ዘገባ “የብሪታንያ ገበሬዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ በሽታው ባልደረሰባቸው አካባቢዎች ጭምር በስጋት፣ በመገለልና ከአበዳሪዎች ጋር በሚደረግ ትንቅንቅ የተዋጠ ሆኗል” ብሏል። በታዳጊ አገሮችም ጦርነት፣ ድርቅ፣ የሕዝብ ብዛት መጨመርና ሌሎች በርካታ ችግሮች የገበሬዎችን ልፋት መና አስቀርተዋል። መንግሥታት ከሌሎች አገሮች ለመሸመት ቢገደዱም ሸማቹ ሕዝብ ገዝቶ ለመብላት የሚያስችል አቅም የለውም።

በገበሬዎች ላይ የደረሰው ችግር የሚያስከትለው መዘዝ በጣም ሠፊ ነው። እንዲያም ሆኖ በግብርናው መስክ የተከሰቱት ችግሮች የሚያሳስቧቸው የከተማ ነዋሪዎች በጣም ጥቂት ናቸው። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት የነበሩት ድዋይት አይዘንሐወር ከ50 ዓመታት በፊት “ግብርና ማረሻው ብዕር ለሆነና ከበቆሎው ማሳ ርቆ ለሚኖር ሰው በጣም ቀላል ይመስላል” በማለት ሁኔታውን ጥሩ አድርገው ገልጸውታል። ዛሬም ቢሆን አብዛኛው የዓለም ክፍል ስለ ግብርናና ገበሬዎች ስለሚያበረክቱት ድርሻ ብዙም ደንታ እንደሌለው ገበሬዎች ይሰማቸዋል። አንድ ካናዳዊ ገበሬ “ምግባችን ከየት እንደሚመጣ ብዙም የሚያሳስበን አይመስልም” ብሏል። “ምግቡ በፕላስቲክ ከመታሸጉና ሱቆች መደርደሪያ ላይ ከመቀመጡ በፊት የብዙ ሰዎችን ልፋት ጠይቋል።”

የሁላችንም ሕልውና በግብርናው ኢንዱስትሪ ላይ የተመካ በመሆኑ የገበሬዎችን ችግር አይተን እንዳለየ ማለፍ አንችልም። ዶን ዲልማን እና ዳርል ሆብስ የተባሉት ሶስዮሎጂስቶች “አንዱ በሌላው ላይ ጥገኛ በሆነበት በዚህ ኅብረተሰብ ውስጥ የገጠሩ ችግር ወዲያው የከተማ፣ የከተማው ደግሞ ውሎ ሳያድር የገጠር ችግር ይሆናል። አንደኛው በችግር ሲማቅቅ ሌላኛው ደልቶት ሊኖር አይችልም” በማለት አስጠንቅቀዋል። ከዚህም በላይ ዓለማችን እንደ ትንሽ መንደር በሆነችበት በዚህ ዘመን በአንድ አገር የተከሰተ የኢኮኖሚ ውድቀት በሌላው አገር ያለውን የእህል ዋጋ ይነካል እንዲሁም የማምረቻ ወጪ ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል።

የኒው ዮርክ የእርሻ ሕክምናና ጤና ማዕከል “በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ለከፍተኛ ውጥረት ከሚዳርጉ 10 የሥራ ዓይነቶች መካከል አንዱ ግብርና ነው” ሲል መዘገቡ አያስደንቅም። ለግብርና ችግሮች መንስኤ ከሆኑት ምክንያቶች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? ገበሬዎች ችግሮቻቸውን መቋቋም የሚችሉትስ እንዴት ነው? ችግሮቹ መፍትሔ ያገኛሉ ብለን እንድናምን የሚያደርገን ምክንያት ይኖራል?

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ግብርና ማረሻው ብዕር ለሆነና ከበቆሎው ማሳ ርቆ ለሚኖር ሰው በጣም ቀላል ይመስላል”