በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የግብርናው መስክ የገጠመው ቀውስ መፍትሔ ያገኛል

የግብርናው መስክ የገጠመው ቀውስ መፍትሔ ያገኛል

የግብርናው መስክ የገጠመው ቀውስ መፍትሔ ያገኛል

ከአያቱ አንስቶ በግብርና በሚተዳደር ቤተሰብ ውስጥ ያደገውና እርሱም ገበሬ የሆነው ሮድኒ “በግብርና ላይ የተጋረጠውን ከባድ ችግር ከዳር ቆሞ የሚመለከት ሰው ይህ ሁሉ ችግር እያለ ግብርናን ሥራዬ ብሎ መያዝ ለምን አስፈለገ ብሎ ሳይገርመው አይቀርም” ብሏል። ቢሆንም በመላው ዓለም ከግብርና መላቀቅ የማይፈልጉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። በአንዳንድ ታዳጊ አገሮች የሚኖሩ ገበሬዎች ሌላ አማራጭ ሥራ ማግኘት አይችሉም። ግብርና ቢያንስ ቤተሰቡ የዕለት ጉርሱን እንዲያገኝ ያስችላል።

ከዚህም በላይ ግብርና እንደ መተዳደሪያ እንጂ እንደ ተራ ሥራ መታየት እንደሌለበት የሚሰማቸው ቤተሰቦች በርካታ ናቸው። ድርቅ፣ በሽታ፣ ከባድ የኢኮኖሚ መዋዠቅና ሌሎች ችግሮች እየተፈራረቁባቸው ከግብርና ሥራ ጋር የሙጥኝ ብለው የሚኖሩ ብዙ ሰዎች መኖራቸው ለግብርና ሥራ ምን ያህል ጥልቅ ፍቅር እንዳላቸውና ችግር የማይበግራቸው ብርቱ ሰዎች መሆናቸውን ይመሰክራል። በግብርናው መስክ ላይ ለተደቀኑት ችግሮች መፍትሔው ምን እንደሆነ ከመመርመራችን በፊት አንዳንድ ገበሬዎች ያጋጠሟቸውን ችግሮች እንዴት መቋቋም እንደቻሉ እንመልከት።

አንዳንዶች የተቋቋሙት እንዴት ነው?

ግብርና ሊቀሩ የማይችሉ በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎችን ያስከትላል። የአየር ጠባይን፣ የኢኮኖሚ ውጣ ውረዶችንና ሌሎች በርካታ ሁኔታዎችን መቆጣጠር እንደማይቻል አምኖ መቀበል የግድ ነው። የሰሜን ካሮላይና የኅብረት ሥራ ማስፋፊያ አገልግሎት “በርካታ ገበሬዎች መልፋትና ጠንክሮ መሥራት ሁልጊዜ የተሳካ ውጤት እንደማያስገኝ ለመማር ተገድደዋል” ይላል። “የእያንዳንዱ ገበሬ የሕይወት ክፍል የሆነው የሥራ ሥነ ምግባር የታሰበውን ዋጋ ላያስገኝ ይችላል። እያንዳንዱ ገበሬ ከቁጥጥሩ ውጭ የሆኑ ሁኔታዎች ያጋጥሙታል።” አንድ አረጋዊ ገበሬ ደስተኛ ሆኖ ሊኖር የቻለው እንዴት እንደሆነ ሲናገር “ከቁጥጥሬ ውጭ ከሆኑ ሁኔታዎች ጋር ተስማምቼ መኖር ተምሬያለሁ” ብሏል።

አንድ የጥንት ምሳሌ “ነፋስን የሚጠባበቅ አይዘራም፣ ደመናትንም የሚመለከት አያጭድም” ይላል። (መክብብ 11:4) ወደፊት ምን እንደሚመጣ አለማወቅና ውሳኔ ማድረግ አለመቻል አንድን ሰው አንድ እርምጃ እንኳ እንዳይራመድ ሊያስሩት ይችላሉ። አፍራሽና አሉታዊ አስተሳሰቦችን አስወግዶ አዎንታዊ በሆኑ ድርጊቶች መተካት አላስፈላጊ ውጥረቶችን ይቀንሳል።

በተጨማሪም ጥሩ የአመጋገብ ሥርዓት መከተል፣ በቂ እረፍት ማግኘትና ተስማሚ የሆነ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ውጤት ማስገኘቱ አይቀርም። ዘ ዌስተርን ፕሮድዩሰር የተባለው መጽሔት “ጤንነታቸውን የሚንከባከቡ ገበሬዎች የተሻሉ ውሳኔዎች ያደርጋሉ” ሲል ዘግቧል። ዩጂን የተባለ ገበሬና ባለቤቱ ካንዳስ “በቂ እረፍት ማግኘት የሚያጋጥሙንን ውጥረቶች እንድንቋቋም ይረዳናል። እረፍት ካደረግን በኋላ ችግሮቻችን ቀለል ያሉና ለመፍታትም የማይከብዱ ሆነው እናገኛቸዋለን። በተጨማሪም ጥሩ ምግብ በተለይ ከቤተሰብ ጋር አንድ ላይ ሆኖ መመገብ በጣም ይረዳል” በማለት ለንቁ! ዘጋቢ ተናግረዋል። ይህ አባባል “ደግሞም ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ጋር ይስማማል።—መክብብ 3:13

የቤተሰብ መተዳደሪያ ማቅረብ

አንድ ገበሬ ለንቁ! ዘጋቢ ሲናገር “በግብርና የሚተዳደሩ ብዙ ቤተሰቦች ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር ከግብርና በተጨማሪ ሌሎች ሥራዎችን ለመሥራት ተገድደዋል። ይህን የሚያደርጉት የቤተሰባቸውን ወጪ ለመሸፈን ሲሉ ቢሆንም በዚህ ምክንያት በቤተሰባቸው ውስጥ ሌሎች ጫናዎች መጥተውባቸዋል። በአንድ ወቅት በጣም ይቀራረቡ የነበሩ የገበሬ ቤተሰቦች ዛሬ ሆድና ጀርባ ሆነዋል” ብሏል። ታዲያ ቤተሰቦች እንዲህ ያለውን ችግር ሊወጡ የሚችሉት እንዴት ነው?

ከዛሬ 2,700 ዓመታት በፊት አባወራዎች “በስተ ሜዳ ሥራህን አሰናዳ፣ ስለ አንተ በእርሻ አዘጋጃት፤ ከዚያም በኋላ ቤትህን ሥራ” የሚል ምክር ተሰጥቷቸው ነበር። (ምሳሌ 24:27) ከቅድመ አያቱ ጀምሮ በግብርና በሚተዳደር ቤተሰብ ውስጥ ያደገውና እርሱ ራሱ የልጆች አባት የሆነው ራንዲ “ጊዜ ወስዶ ለቀሩት የቤተሰብ አባላት አድናቆትና ፍቅር መግለጽ ያስፈልጋል። ሁሉም የቤተሰብ አባል ድጋፍና ፍቅር ማግኘት ያስፈልገዋል። የደግነት ቃላትና ድርጊቶች ሁሉም የቤተሰብ አባላት ተፈላጊዎች እንደሆኑና እንደሚወደዱ እንዲሰማቸው ያደርጋል” ብሏል።

በተለይ ልጆች በኑሯቸው ላይ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ ሲከሰት ማበረታቻና ማጽናኛ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። ልጆች በዕዳ ምክንያት የቤተሰባቸው እርሻ ከተሸጠ በኋላ የሚሰማቸው ስሜት ወላጆቻቸው የተፋቱባቸው ወይም በሞት ምክንያት የተለዩዋቸው ልጆች ከሚሰማቸው ስሜት ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ተገልጿል። ለደረሰው ችግር ምክንያቶቹ እነርሱ እንዳልሆኑና የመጣው ቢመጣ ቤተሰቡ እንደማይነጣጠል ማወቅ ያስፈልጋቸዋል።

ሌሎችስ እንዴት ሊረዱ ይችላሉ?

ችግር ያጋጠማቸው ገበሬዎች ከወዳጆቻቸው ሊርቁና ራሳቸውን ሊያገልሉ ይችላሉ። (ምሳሌ 18:1) ይሁን እንጂ አንድ ሰው ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የሌሎች ድጋፍ የሚያስፈልገው አስጨናቂ የሆኑ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት ነው።

በግብርና ላይ በሚደርሱ ችግሮች ምክንያት ችግር ላይ የወደቀ ወዳጅ ወይም ጎረቤት አለህ? በደረሰባቸው ሁኔታ ያዘንክ መሆንህን መግለጽህ ብቻ በጣም ሊረዳቸው ይችላል። ሮን የተባለ አንድ ገበሬ “ወዳጆቻችን እያጋጠመን ያለው ችግር ምን ዓይነት እንደሆነ እንደሚገነዘቡ ማወቃችን ብቻውን ያጽናናናል” ብሏል። አዎን፣ በራስህ ተነሳስተህ ወዳጆችህን በመጠየቅ ስሜታቸውን ሲገልጹልህ አዳምጣቸው።

ጃክ እንዲህ ያለው ጥየቃ ጥቅም እንዳለው ተመልክቷል። “ወዳጆቼ ያለሁበትን ችግር ተረድተው ሊጠይቁኝና ሊያበረታቱኝ የመጡበትን ጊዜ ፈጽሞ አልረሳውም” በማለት ታሪኩን ይናገራል። እንዲህ ዓይነቱን ድጋፍ ለመስጠት ስለ ግብርና ሥራ የጠለቀ እውቀት ማካበት አያስፈልግም። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ሮድኒ “ወዳጆቼ በጣም ከባድ የሆነ የሥራ ጫና እንዳለብኝ እንደሚገነዘቡልኝ ማወቄ ብቻውን ብርታትና የቻልኩትን ሁሉ የማድረግ ፍላጎት ያሳድርብኛል” ብሏል። እዚህ ላይ “ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል፤ ወንድምም ለመከራ ይወለዳል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ለማስታወስ እንገደዳለን።—ምሳሌ 17:17

ዘላቂ መፍትሔ

በግብርናው መስክ ላይ የተጋረጠው ችግር የሰው ልጅ ምድርንና ሀብቷን ለማስተዳደር አቅምና ችሎታ እንደሌለው ከሚያሳዩት በርካታ ማስረጃዎች አንዱ ብቻ ነው። ነቢዩ ኤርምያስ “አቤቱ፣ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም” ብሏል። (ኤርምያስ 10:23) የሰው ልጅ መለኮታዊ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ግልጽ ነው። ይህ ዓይነቱ እርዳታ ደግሞ ሩቅ እንዳልሆነ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ።

መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በዔድን ገነት አኖረው” ይላል። (ዘፍጥረት 2:15) አዎን፣ ግብርናን ያስጀመረው ፈጣሪያችን ነው። ከበርካታ ዓመታት በኋላ ደግሞ አምላክ ሕዝቡን እስራኤላውያንን በከነዓን ምድር እንዲኖሩ አደረገ። በመንፈስ የተጻፈው ታሪክ ስለዚህች ምድር ሲናገር “በሰማይ ዝናብ ውኃ ትረካለች። አምላክህ እግዚአብሔር የሚጐበኛት አገር ናት፤ ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ የአምላክህ የእግዚአብሔር ዓይን ሁልጊዜ በእርስዋ ላይ ነው” ይላል። (ዘዳግም 11:11, 12) በተጨማሪም ይሖዋ ተስፋይቱ ምድር ጉስቁልና እንዳይደርስባት የሚከላከሉ ሕጎች ሰጥቶ ነበር። ለምሳሌ ያህል እስራኤላውያን በየሰባት ዓመቱ ማሳዎቻቸውን፣ የወይንና የወይራ እርሻቸውን እንዲያሳርፉ ታዝዘው ነበር። (ዘጸአት 23:10, 11) በዚህ መንገድ የመሬቱ ለምነት ይጠበቅ ነበር።

ወደፊትም ቢሆን በኢየሱስ ክርስቶስ በሚተዳደረው የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ሥር ምድር በታሪኳ ታይቶ የማያውቅ ምርት ትሰጣለች። (ኢሳይያስ 35:1-7) የዚህ መንግሥት አስተዳዳሪ እንዲሆን የተሾመው ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ ሳለ በግብርና ላይ ከባድ ተጽዕኖ የሚያሳድሩትን የተፈጥሮ ኃይሎች የመቆጣጠር ችሎታ እንዳለው በተግባር አሳይቷል። (ማርቆስ 4:37-41) ይህን ችሎታውን ተጠቅሞ ምድርንና የምድርን ነዋሪዎች በሚፈውስበት ጊዜ የሚኖረው ሁኔታ በመዝሙር 65 ላይ ተገልጿል። “ምድርን ጐበኘሃት አጠጣሃትም፣ ብልጥግናዋንም እጅግ አበዛህ፤ የእግዚአብሔር ወንዝ ውኃን የተመላ ነው፤ ምግባቸውን አዘጋጀህ፣ እንዲሁ ታሰናዳለህና” የሚል ዋስትና ይሰጠናል። (መዝሙር 65:9) በዚህ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ የአምላክ ሕዝቦች የተትረፈረፈ ምርት በታላቅ ሐሴት ይሰበስባሉ።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በርካታ ገበሬዎች መልፋትና ጠንክሮ መሥራት ሁልጊዜ የተሳካ ውጤት እንደማያስገኝ ለመማር ተገድደዋል”

[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የቤተሰብ አባሎችን ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎት ማሟላት ችግሮቻቸውን እንዲቋቋሙ ሊረዳቸው ይችላል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ምድር በአምላክ አገዛዝ ሥር ስትሆን የተትረፈረፈ ምርት ትሰጣለች

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Garo Nalbandian