ደኖች የሚሰጡት አገልግሎት—ዋጋው ምን ያህል ነው?
ደኖች የሚሰጡት አገልግሎት—ዋጋው ምን ያህል ነው?
ከምድር የየብስ ክፍል አንድ ሦስተኛው በደን የተሸፈነ ይሁን እንጂ ይህ መጠን በከፍተኛ ፍጥነት እያሽቆለቆለ ነው። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም የሚታተመው ቾይስስ—ዘ ሂውማን ደቨሎፕመንት ማጋዚን በ1998 እንዳለው ገና ባላደገው የዓለም ክፍል ብቻ “በየዓመቱ 4 ሚሊዮን ሄክታር ማለትም ስዊዘርላንድን የሚያክል ስፋት ያለው ደን ይመነጠራል።”
የደን ምንጠራ አጨቃጫቂ የሆነው ለምንድን ነው?
አንዳንድ ሊቃውንት የደን ምንጠራ አጨቃጫቂ ጉዳይ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ የሆነው ደኖች የሚመነጠሩትና የሚቃጠሉት ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማግኘት በመሆኑ ነው። ሆኖም አንድ ባለ ሥልጣን እንዳሉት ዛፎች “በቁማቸው የሚሰጡት ጠቀሜታ ተቆርጠው ወይም ተቃጥለው ከሚሰጡት ይበልጣል።” እንዴት?
በመናኡስ፣ ብራዚል የአማዞን ብሔራዊ ምርምር ተቋም ተመራማሪዎች የሆኑት ዶክተር ፊሊፕ ፈርንሳይድ እና ዶክተር ፍላቪዮ ሉዊዛኦ ደኖች “ለመላው ዓለም የሚጠቅም አገልግሎት” እንደሚሰጡ ለንቁ! ዘጋቢ ተናግረዋል። እነዚህ ደኖች ከሚሰጧቸው አገልግሎቶች መካከል ለምድር ሙቀት መጨመር ምክንያት የሆነውን ካርቦን ዳይኦክሳይድ ከከባቢ አየር ሰብስቦ ማቆየት፣ የአፈር መሸርሸርንና ጎርፍን መከላከል፣ የዝናብ መጠንን ማስተካከልና የመጥፋት አደጋ ለተጋረጠባቸው የእንስሳትና የዱር እጽዋት ዝርያዎች መኖሪያ መሆን ይገኙበታል። በተጨማሪም ደኖች አካባቢ በማስዋብና በመዝናኛነት ያገለግላሉ። እነዚህ ለአካባቢ የሚጠቅሙ አገልግሎቶች በሙሉ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳላቸው ተመራማሪዎቹ ይናገራሉ።
ለምሳሌ ያህል፣ የደኖችን ካርቦንን ሰብስቦ የማቆየት ችሎታ እንመልከት። ዛፎች ተቆርጠው ሲቃጠሉ የሚወጣው ካርቦን በካርቦን ዳይኦክሳይድ መልክ ወደ ከባቢ አየር ይገባና ለምድር ሙቀት መጨመር አስተዋጽኦ ያደርጋል። ስለዚህ ይህን ደን ‘ለመላው ዓለም የሚሰጠውን አገልግሎት’
ማለትም ካርቦንን ሰብስቦ በማቆየት የሚሰጠውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የካርቦንን መጠን በሰው ሠራሽ ዘዴዎች ለመቀነስ በሚጠይቀው ወጪ መተመን ይቻላል።ብራዚል በሚገኘው የኢንተር አሜሪካን ልማት ባንክ ቅርንጫፍ ቢሮ የአካባቢ ጥበቃ አማካሪ የሆኑት ማርክ ዶሮድሺሃኒ እንደሚሉት ከሆነ “ደኖች የካርቦን ማከማቻ በመሆን የሚሰጡት አገልግሎት ዛፎችን መንጥሮ በመሸጥና የእርሻ መሬት በማድረግ ከሚገኘው ገቢ” እንደሚበልጥ ከዚህ ስሌት መረዳት ይቻላል። ያም ሆኖ ግን የደኖች መውደም ሊገታ አልቻለም። ለምን?
የደን ጭፍጨፋን ለመግታት የቀረበ የመፍትሔ ሐሳብ
እስቲ የሚከተለውን ማነጻጸሪያ ተመልከት። በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች አንድ የኤሌክትሪክ ማመንጫ አላቸው። ይህ የኃይል ማመንጫ በአካባቢው ለሚገኙ ከተሞች አገልግሎት ይሰጣል። ተጠቃሚዎቹ ግን ለሚያገኙት አገልግሎት አምስት ሳንቲም አይከፍሉም። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የኤሌክትሪክ ማመንጫው ባለቤቶች ‘ምንም ዓይነት የገንዘብ ትርፍ የማያስገኝ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ይዘን ቁጭ ከምንል መሣሪያውን አወላልቀን ብንሸጥ ይሻላል’ ብለው አሰቡ። በደን በበለጸጉ አገሮች የሚኖሩ አንዳንድ ባለ ሥልጣናት ይህን የመሰለ አስተሳሰብ ያላቸው ይመስላል። በዓለም ውስጥ ያሉ ተጠቃሚዎች ከደኖች ለሚያገኙት አገልግሎት ምንም ዓይነት ዋጋ ስለማይከፍሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዳጎስ ያለ ትርፍ ለማግኘት ደኖቹን መንጥሮ ዛፎቹን መሸጥ ያዋጣል ብለው ያስባሉ።
ዶሮድሺሃኒ እንዲህ ያለውን አመለካከት ማስለወጥ የሚቻለው ደኖችን ጠብቆ ማቆየት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲኖረው በማድረግ ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ። በብራዚል የኑክሊየር ፊዚክስ ሊቅና የሳኦ ፓውሎ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ቻንስለር የሆኑት ዶክተር ዦሴ ጎልደንበርግ ከከርሰ ምድር በሚወጣ ነዳጅ ተጠቃሚዎች ላይ “ዓለም አቀፍ የካርቦን ታክስ” መጫን አንዱ አማራጭ እንደሚሆን ሐሳብ ሰጥተዋል።
የዚህ ሐሳብ ደጋፊዎች እንደሚያስቡት የሚጫነው ታክስ መጠን አንድ አገር በሚያቃጥለው ነዳጅና በሚያወጣው ካርቦን መጠን ላይ የተመካ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ ከዓለም ሕዝቦች 5 በመቶ ለሚሆኑት መኖሪያ የሆነችው ዩናይትድ ስቴትስ ከመላው ዓለም 24 በመቶ የሚሆነውን የካርቦን መጠን ታወጣለች። አንዳንድ ፖሊሲ አውጪዎች እንዲህ ያለው አገር የሚከፍለው ታክስ የደኖችን ሕልውና ለመጠበቅ ሲሉ ከዛፍ ሽያጭ የሚያገኙትን ጊዜያዊ ትርፍ መሥዋዕት ለሚያደርጉ አገሮች እንደማካካሻ ሊከፈል ይችላል ብለው ያስባሉ። እንዲህ ከተደረገ ተጠቃሚዎቹ ለሚያገኙት ‘የኤሌክትሪክ አገልግሎት’ ተመጣጣኝ ዋጋ ይከፍላሉ፣ ‘የማመንጫውም ባለቤቶች’ ማመንጫቸውን እንዳይሸጡ የሚያደርግ የገንዘብ ጥቅም ያገኛሉ።
ይሁን እንጂ ደኖች ለሚሰጡት አገልግሎት ተጠቃሚዎች የሚከፍሉትን ዋጋ ማን ይወስናል? ማንስ ሰብስቦ ያከፋፍላል?
የባሕርይ ለውጥ አስፈላጊነት
ዶሮድሺሃኒ “እንደነዚህ ያሉት ጥያቄዎች ደንን በሚመለከት በሚደረግ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ቢነሱ መልካም ይሆናል” ይላሉ። ይህን የመሰለው ጉባኤ ደኖች ለሚሰጡት አገልግሎት መከፈል የሚገባውን የዋጋ መጠን ሊወስን ይችላል። ከዚያም “ይህን ዓለም አቀፍ ሥርዓት የሚያስተዳድርና የሚያቀናጅ የዓለም ደኖች ድርጅት ይቋቋማል።”
አንድን ዓለም አቀፍ ችግር ለመፍታት ዓለም አቀፋዊ ተቋም ማቋቋም ተገቢ መሆኑ የማያጠያይቅ ቢሆንም ዶሮድሺሃኒ እንዳሉት “ከደን ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎችን እንዲፈቱ እስከአሁን የተቋቋሙት በርካታ ተቋሞችና ኮሚሽኖች ያስገኙት አንዳች ፋይዳ የለም።” አክለው እንደተናገሩት አሁን የሚያስፈልገው “ሥር ነቀል የሆነ የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ ባሕርይ ለውጥ ነው።” በእርግጥም የደኖች ጭፍጨፋ ሕግ በማውጣት ብቻ የሚገታ አይደለም። የአስተሳሰብ ወይም የአመለካከት ለውጥም ያስፈልጋል።
ታዲያ ይህ ችግር መፍትሔ የሚያገኝበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? የምድር ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ አዎ፣ ይመጣል በማለት ቃል ይገባል። በቅርቡ መላውን ምድር የሚገዛና የምድርን ችግሮች የሚያስወግድ መንግሥት እንዳቋቋመ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ይህ መንግሥት ፈጽሞ ‘አይፈርስም።’ (ዳንኤል 2:44) ከዚህም በላይ የምድር ነዋሪዎች በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ስሙ ይሖዋ እንደሆነ ስለሚናገርለት ስለ ፈጣሪያቸው ተከታታይ ትምህርት ስለሚያገኙ የምድር ሥነ ምህዳር በአግባቡ እንዲጠበቅ ያደርጋል። (ኢሳይያስ 54:13) በዚያ ዘመን የሚኖሩ ሰዎች በሙሉ ለደኖችና ለመላው ምድር አድናቆትና አክብሮት ያላቸው ይሆናሉ።
[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]
Ricardo Beliel/SocialPhotos
© Michael Harvey/Panos Pictures