በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ግብርና ችግር ላይ የወደቀው በምን ምክንያት ነው?

ግብርና ችግር ላይ የወደቀው በምን ምክንያት ነው?

ግብርና ችግር ላይ የወደቀው በምን ምክንያት ነው?

“ከፍተኛ ውጥረት የገጠማቸውን ገበሬዎች የስልክ ጥሪ የሚቀበሉት ሠራተኞች በግብርና ሥራችሁ ላይ የገጠማችሁን ውጥረት እንዴት እንደምትቋቋሙ ለመርዳት የሚያስችል ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል። እኛም እንደእናንተው ገበሬዎች ስለሆንን ወይም ስለነበርን ገጠር የሚኖሩ ቤተሰቦች የሚያጋጥሟቸው ችግሮች ይገቡናል። ሊረዷችሁ ከሚችሉ ሰዎች ጋር እናገናኛችኋለን። . . . ጥሪዎቻችሁ በሙሉ በምሥጢር ይያዛሉ።”ከአንድ የካናዳ መንግሥታዊ ኢንተርኔት ገጽ የተወሰደ

በአሁኑ ጊዜ ግብርና ከፍተኛ ውጥረት ከሚያስከትሉ ሥራዎች አንዱ መሆኑ በብዙ የጤና ባለሞያዎች ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል። ገበሬዎች የሚያጋጥማቸውን ውጥረት እንዲቋቋሙ ለመርዳት የሥነ አእምሮ ሐኪሞች አንድ ዓይነት ችግር ያለባቸው ገበሬዎች ተሰብስበው ስለችግሮቻቸው የሚወያዩባቸው ማዕከሎችና ለችግሮቻቸው ምክር የሚያገኙባቸው የስልክ መስመሮች አዘጋጅተዋል።

ጄን የተባለች የአንድ ገበሬ ባለቤት በየሳምንቱ ሐሙስ ማታ በሚደረገው የምክር መስጫ ስብሰባ ላይ ትገኛለች። ጄን “እዚህ የመጣሁት ባለቤቴ ራሱን ስለገደለ ነው” በማለት ትገልጻለች። “ሁልጊዜም ሕልሙ ከቤተሰቡ በወረሰው የግብርና ሙያ መሰማራት ነበር። ይህን ማድረግ ካልቻለ ምንም ዓይነት ሌላ ሥራ መሥራት የሚፈልግ አይመስለኝም” ብላለች።

የሚደርስባቸው ውጥረት ጋብ እንዲልላቸው የሚፈልጉ ገበሬዎች ቁጥር ታይቶ በማይታወቅ መጠን ጨምሯል። በብዙ ገበሬዎች ፊት ለተደቀነው ችግር መንስኤው ምንድን ነው?

የተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎችና በሽታ

በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው የመንግሥት የኢንተርኔት ገጽ እንዲህ ብሏል:- “የግብርና ሥራ ከቁጥጥራችን ውጭ ለሆኑ በርካታ ነገሮች የማጋለጥ ባሕርይ አለው። የአየር ጠባይ፣ የገበያ ዋጋ፣ የወለድ መጠንና የመሣሪያ ብልሽት ከገበሬው ቁጥጥር ውጭ የሆኑ ነገሮች ናቸው። ምን ዓይነት እህል ልዝራ፣ መሬቴን ላከራይ ወይስ ልሽጥ እንደሚሉት ያሉ ምርጫዎች እንኳን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ውጤት ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ሊከትቱ ይችላሉ።” በእነዚህ ሁኔታዎች ላይ ደግሞ ድርቅ ወይም በሽታ አሊያም እርሻን በዕዳ ምክንያት የማጣት አደጋ ሲጨመር ውጥረቱን መቋቋም ወደማይቻልበት ደረጃ ላይ ይደረሳል።

ለምሳሌ ያህል ድርቅ በሁለት በኩል እንደተሳለ ሠይፍ ሊሆን ይችላል። ሃዋርድ ፖልሰን የተባለ አንድ ገበሬ በካናዳ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቀው በ2001 የደረሰው ድርቅ በእህል ምርቱ እና በከብቶቹ ላይ ጉዳት እንዳደረሰ ይናገራል። የግጦሽ ሣርም ሆነ የእህል ምርት ስላልነበረው የከብቶች መኖ መግዛት ነበረበት። “ከብቶቼን ለመመገብ እስካሁን ድረስ 10,000 ዶላር [50,000 ብር] ያህል አውጥቼያለሁ። አሁን የማበላቸው ለክረምቱ ወራት ይሆናቸዋል ብዬ ያስቀመጥኩትን ነው” ይላል። “ይህን ማድረግ ከጀመርክ ከከብቶቹ እንኳን ምንም ትርፍ ማግኘት አትችልም።” በሌሎች አካባቢዎች የደረሰው የጎርፍ መጥለቅለቅ ደግሞ በርካታ ማሣዎችን አውድሟል።

በብሪታንያ በ2001 በቤት እንስሳት ላይ የደረሰው የእግርና የአፍ በሽታ ገበሬዎች ከዓመታት ጀምሮ ከተፈራረቁባቸው በርካታ ችግሮች አንዱ ብቻ ነበር። የእብድ ላም በሽታና የአሣማ ትኩሳት ከእነዚህ ችግሮች የሚቆጠሩ ናቸው። እነዚህ በሽታዎችም ሆኑ በሽታዎቹ በሕዝብ ላይ የሚጥሉት ፍርሃት የኢኮኖሚ ውድመት በማስከተል ብቻ አያቆሙም። አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንዲህ ሲል ዘግቧል:- “ችግር የማይበግራቸውና መንፈሰ ጠንካራ የሆኑ ገበሬዎች ዕድሜያቸውን ሙሉ የደከሙባቸውን ከብቶች የመንግሥት የእንስሳት ሐኪሞች ከምረው ሲያቃጥሉባቸው ሲመለከቱ ስቅስቅ ብለው አልቅሰዋል።” የእግርና የአፍ በሽታ ወረርሽኝ ከፈነዳ በኋላ ፖሊሶች ራሳቸውን ከመግደል ወደኋላ አይሉም ተብለው ከታሰቡ ገበሬዎች ቤት ጠመንጃና ሽጉጥ አስሰው እስከመውሰድ ደርሰዋል። የምክር መስጫ አገልግሎቶች በፍርሃት በተዋጡ ገበሬዎች የድረሱልኝ ጥሪ ተጥለቅልቀዋል።

የኢኮኖሚ አለመረጋጋት

በተጨማሪም አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች በጣም ተለዋውጠዋል። ብሮክን ሃርትላንድ የተባለው መጽሐፍ በጀርባ ሽፋኑ ላይ እንዲህ የሚል አስተያየት አስፍሯል:- “ከ1940 እስከ 1980 ባለው ጊዜ ውስጥ በመካከለኛው የአሜሪካ ክፍል የማምረቻ ወጪ በሦስት እጥፍ፣ የመሣሪያዎች ዋጋ በአራት እጥፍ፣ የወለድ መጠን በአሥር እጥፍ ሲያድግ ትርፍ በ10 በመቶ እንዲሁም የገበሬዎች ቁጥር በሁለት ሦስተኛ ቀንሷል። የግብርና ተዳዳሪ ማኅበረሰቦች ቁጥር፣ የገቢ መጠንና የኢኮኖሚ መረጋጋት ቅናሽ አሳይቷል ማለት ይቻላል።”

ወጪዎች እያሻቀቡ ሲሄዱ በዚያው መጠን ትርፉ ያልጨመረው ለምንድን ነው? ዓለም እንደ ትንሽ መንደር በሆነችበት በዛሬው ጊዜ ገበሬዎች በገበያ ውጣ ውረድ ይነካሉ። በዚህም ምክንያት ገበሬዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቀው ከሚኖሩ አምራቾች ጋር ለመወዳደር ይገደዳሉ። ዓለም አቀፉ ንግድ ለግብርና ምርቶች አዳዲስ ገበያዎችን መፍጠሩ የማይካድ ቢሆንም ይኸው ዓለም አቀፍ ገበያ በአደገኛ ሁኔታ ሊዋዥቅ ይችላል። ለምሳሌ ያህል በ1998 በእስያ የሚኖሩ ደንበኞቻቸው በደረሰባቸው የኢኮኖሚ ውድቀት ምክንያት በካናዳ የሚኖሩ በርካታ የእህልና የአሣማ ሥጋ አምራቾች ለከፍተኛ ኪሣራ ተዳርገዋል።

በማኅበረሰቦች ላይ የሚደርስ ጉዳት

የአይዋ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑትና በገጠር አኗኗር ላይ በርካታ ጥናት ያደረጉት ማይክ ጃኮብሰን በግብርና ላይ የደረሰው ቀውስ በገጠሩ ኅብረተሰብ ላይ ችግር እንደሚፈጥር አስተውለዋል። እንዲህ ብለዋል:- “እነዚህ ቦታዎች ለሕፃናት በቂ እንክብካቤ የሚደረግባቸው፣ ንጹሕና ትዳር ይዛችሁ ልጆቻችሁን ለማሳደግ የምትመኙባቸው አካባቢዎች ነበሩ። ትምህርት ቤቶቹ በጣም ጥሩዎችና ምቹ እንዲሁም ሰላማውያን ነበሩ። ስለ ገጠር ሲነሣ ወደ አእምሯችን የሚመጣው ሥዕል እንዲህ ያለ ነበር። ይሁን እንጂ የእነዚህ ትንንሽ ከተሞች የኢኮኖሚ ሁኔታ በአካባቢው በሚገኙ ትናንሽ እርሻዎች ገቢ ላይ በእጅጉ የተመካ ነው።” በዚህ የተነሣ በግብርናው መስክ ላይ የደረሰው ችግር በገጠራማ መንደሮች የሚገኙ ሐኪም ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ምግብ ቤቶች፣ ሱቆችና አብያተ ክርስቲያናት እንዲዘጉ ምክንያት ሆኗል። የግብርና ኑሮ ከሚወደድባቸው ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ የሆነው መቀራረብና ጥሩ ጉርብትና እየጠፋ መጥቷል።

ኒውስዊክ መጽሔት እንዳለው በገጠር ከሚኖሩ አሜሪካውያን 16 በመቶ የሚሆኑት ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ መሆናቸው አያስደንቅም። ሎረንስ ጀፍሪ “የአውስትራሊያ ገጠሮች የደረሰባቸው ከባድ ችግር” በሚል ርዕስ ባዘጋጁት ሪፖርት ‘ሥራ አጥነትና ድህነት ከከተሞች ይልቅ በገጠሮች በጣም ከፍተኛ ነው’ ብለዋል። በርካታ ቤተሰቦች በተለይም ወጣቶች ባጋጠማቸው የኢኮኖሚ ውጣ ውረድ ምክንያት ወደ ከተሞች ለመሰደድ ተገድደዋል። ከቤተሰቧ ጋር በግብርና ሥራ የምትተዳደረው ሺላ “ይህ ሁኔታ ዝም ተብሎ የሚታየው አርሶ የሚኖር ፈቃደኛ ሰው እስኪታጣ ድረስ ነው?” በማለት ጠይቃለች።

ወጣቱ ትውልድ ወደ ከተሞች በብዛት በመፍለሱ ምክንያት ብዙ የገጠር ከተሞች በአብዛኛው አረጋውያን ብቻ የሚኖሩባቸው መንደሮች ሆነዋል። እንዲህ ያለው ፍልሰት የልጆቻቸውን ጉልበት ብቻ ሳይሆን አቅማቸው በደከመበት ወቅት ጧሪ ቀባሪ አሳጥቷቸዋል። ብዙ አረጋውያን በእነዚህ ፈጣን ለውጦች ምክንያት ሥጋት ላይ መውደቃቸውና ግራ መጋባታቸው የሚያስደንቅ አይደለም።

ስለዚህ በግብርናው መስክ ላይ የደረሰው ቀውስ ያስከተለው መዘዝ በጣም ሠፊና በቀላሉ የማይታይ ነው። ሁላችንንም ይነካል። ይሁን እንጂ የሚቀጥለው ርዕስ እንደሚያሳየው ይህ በግብርናው መስክ ላይ የደረሰው ችግር የሚያበቃበት ጊዜ ይመጣል ብለን እንድናምን የሚያደርግ በቂ ምክንያት አለ።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ዓለም እንደ ትንሽ መንደር በሆነችበት በዛሬው ጊዜ ገበሬዎች በገበያ ውጣ ውረድ ይነካሉ

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ይህ ሁኔታ ዝም ተብሎ የሚታየው አርሶ የሚኖር ፈቃደኛ ሰው እስኪታጣ ድረስ ነው?”

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

በተፈጥሯዊ ዘዴ ማልማት

በተፈጥሮ የተመረቱ ምግቦች ያላቸው ተፈላጊነት በጣም እየጨመረ መጥቷል። በካናዳ በተፈጥሯዊ ዘዴ የሚለሙ ምግቦች ገበያ በየዓመቱ 15 በመቶ ያድጋል።

በተፈጥሯዊ ዘዴ ማልማት ሲባል ምን ማለት ነው? የአልበርታ የእርሻ፣ የምግብና የገጠር ልማት መሥሪያ ቤት እንዲህ በማለት ይገልጸዋል:- “ሰው ሠራሽ ኬሚካሎች ጥቅም ላይ የማይውሉበት ከመሆኑም በላይ የአፈር ጤንነት፣ ብዝሀ ሕይወት፣ የአካባቢ ደህንነት እንዲጠበቅ የሚያደርግና በእንስሳት ላይ ጭካኔ በማያደርስ መንገድ የሚደረግ የግብርና ሥርዓት ነው።”

ይህ ደግሞ በዚህ የግብርና መስክ የተሰማሩ ገበሬዎች እንደሚሉት ከሠፋፊ እርሻዎች በአመራረቱ በእጅጉ ይለያል። ካተሪን ቫንሲታርት በካናዲያን ጂኦግራፊክ ላይ “ማሽኖችን እንዲሁም በርካታ ሰው ሠራሽ ፀረ ተባዮችንና ማዳበሪያዎችን በመጠቀም በሰፋፊ እርሻዎች ላይ አንድ ዓይነት ምርት በብዛት ይመረታሉ” ሲሉ ጽፈዋል። “በዚህ መንገድ በተመረቱ የምግብ ውጤቶች ውስጥ በርካታ የኬሚካል ቅሪቶች ከመኖራቸውም በላይ ምርቱ በርካታ ርቀት ተጉዞ ለገበያ ስለሚቀርብ በደንብ ከመብሰሉ በፊት መሰብሰብ ግድ ስለሚሆን በምግቡ ውስጥ ያለው ንጥረ ነገር ይዘቱ በእጅጉ ይቀንሳል። ሳይበላሹ ለገበያ እንዲደርሱ ለማድረግ ሲባል ደግሞ ጋዝና የኑክሊየር ጨረር ሊረጭባቸው እንዲሁም እንደ ሰም ያለ ቅባት ሊቀቡ ይችላሉ።”

በተፈጥሯዊ ዘዴ የሚለሙ ምግቦችን የሚሸምቱት ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው? የአልበርታው ሪፖርት “ስለጤንነታቸው የሚያስቡ ወጣቶች፣ የልጆቻቸው ጤንነት የሚያሳስባቸው እናቶችና ጠና ያሉ ሰዎችን ጨምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይሸምቷቸዋል።”

ይሁን እንጂ በተፈጥሯዊ ዘዴ የሚለሙ ምግቦች የተሻሉ ስለመሆናቸው የሚጠራጠሩ ክፍሎችም አሉ። ካናዲያን ጂኦግራፊክ “በተፈጥሯዊ ዘዴ የሚለሙ ምግቦች በአብዛኛው ውድ ዋጋ የሚያስከፍሉ ሲሆን ጠቃሚ ስለመሆናቸው ተጨባጭ ሳይንሳዊ ማረጋገጫ ሳይኖር ይህን ያህል ዋጋ መክፈል አስፈላጊ ስለመሆኑ የሚጠራጠሩ ብዙ ሰዎች አሉ። ሌሎች ደግሞ ድሆችን የሚያገልል ሁለት ዓይነት የምግብ ስርጭት ሥርዓት እየተፈጠረ መሆኑ በእጅጉ ያሳስባቸዋል” ብሏል። በተፈጥሯዊ ዘዴ የሚለሙ ምግቦችን የሚደግፉ ሰዎች የአመጋገብ ለውጥ፣ የአቅርቦትና የግብይት ሥርዓት መሻሻል ሲደረግ በተፈጥሯዊ ዘዴ የሚለሙ ምግቦች በሁሉም የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ሰዎች ሊዳረሱ ይችላሉ በማለት መልስ ይሰጣሉ። ሳይንሳዊ መረጃዎችና አስተያየቶች በጣም የተለያዩ መሆናቸውን ስንመለከት በተፈጥሯዊ ዘዴ በሚለሙ ምግቦች ላይ የሚደረገው የጦፈ ክርክር ቶሎ የሚቋጭ አይመስልም።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ፀረ ተባይ መድኃኒት ገበሬዎችን ግራ ያጋባ ችግር

በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ተባዮችና የተክል በሽታዎች ሊገኝ ከታሰበው ምርት ውስጥ እስከ 75 በመቶ የሚሆነውን አውድመዋል። ይህን ችግር ለመቋቋም የሚቻልበት አንደኛው መፍትሔ ምርቱ የሚበዛበትን መንገድ መፈለግ ነው። ግሎብ ኤንድ ሜይል የተባለው ጋዜጣ “የካናዳ ገበሬዎች ብዙ ለመሸጥ የሚያስችላቸውን ምርት የመጨመር ዘዴ በመፈለግ ውድድሩን በአሸናፊነት ለመወጣት ጥረት አድርገዋል” በማለት ተናግሯል። ሆኖም የካናዳ የአካባቢ ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ተረንስ ማክሬ “ከእነዚህ ለውጦች መካከል ብዙዎቹ በእርሻ ምክንያት የሚደርሰውን የአካባቢ መጎዳት የሚያባብሱ ናቸው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ፀረ ተባይ መድኃኒቶችን መጠቀምስ? ፀረ ተባይ መድኃኒቶች ውጤታማ ስለመሆናቸውም ሆነ በጤና ላይ ስለሚያስከትሉት ጉዳት ገና እልባት ያላገኙ ብዙ ክርክሮች በመካሄድ ላይ በመሆናቸው ገበሬዎች ምን እንደሚያደርጉ መወሰን ቸግሯቸዋል። አንድ የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት የአብዛኞቹ ፀረ ተባይ መድኃኒቶች መርዛማነትና አደገኛነት ገና ሙሉ በሙሉ ያልታወቀ መሆኑን አምኗል። እንስሳት ፀረ ተባይ መድኃኒት የተረጨባቸውን እጽዋት ይመገባሉ። ሰዎች ደግሞ እንስሳቱን ሲመገቡ መድኃኒቶቹ የሚያስከትሉት ችግር የዚያኑ ያህል የሰፋ ይሆናል።

[ምንጭ]

USDA Photo by Doug Wilson