ሕፃናት የሚያስፈልጋቸውና የሚፈልጉት
ሕፃናት የሚያስፈልጋቸውና የሚፈልጉት
ሕፃኑ ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ አቅፎ በፍቅር እየደባበሰ የሚንከባከበው ሰው ያስፈልገዋል። ከተወለደ ጀምሮ ያሉት 12 ሰዓታት እጅግ ወሳኝ እንደሆኑ አንዳንድ ሐኪሞች ያምናሉ። ሕፃኑ እንደተወለደ እናቱና ልጁ ወዲያው የሚያስፈልጋቸውም ሆነ የሚፈልጉት ነገር “እንቅልፍ ወይም ምግብ ሳይሆን ሕፃኑን መደባበስና ማቀፍ፣ እንዲሁም እርስ በርስ መተያየትና መደማመጥ እንደሆነ” ይናገራሉ። *
ወላጆች በደመ ነፍስ ሕፃን ልጃቸውን አንስተው ደረታቸው ላይ ያቅፉታል፣ ይደባብሱታል እንዲሁም ያሻሹታል። ሕፃኑም ያለ ምንም ስጋት ወላጆቹ ላይ ልጥፍ በማለት ለፍቅራቸው ምላሽ ይሰጣል። በመካከላቸው ያለው ትስስር በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ ወላጆቹ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሕፃኑን ለመንከባከብ ማንኛውንም መሥዋዕትነት ይከፍላሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ ሕፃኑ የወላጆቹን ፍቅር ካላገኘ ቃል በቃል እየደከመ ሊሄድና ሊሞት ይችላል። ስለዚህ አንዳንድ ሐኪሞች ሕፃኑ እንደተወለደ ወዲያውኑ ለእናቱ መሰጠቱ አስፈላጊ እንደሆነ ያምናሉ። ሕፃኑ እንደተወለደ ቢያንስ ቢያንስ የመጀመሪያዎቹን ከ30 እስከ 60 ደቂቃ ድረስ ከእናቱ ጋር እንዲሆን ሐሳብ ያቀርባሉ።
አንዳንድ ባለሞያዎች እንዲህ ላለው የመጀመሪያ ትስስር ከፍተኛ ቦታ ቢሰጡም በአንዳንድ ሆስፒታሎች ይህን ማድረግ አይቻልም ባይባልም እንኳን አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ብዙውን ጊዜ አራስ ልጆች ተላላፊ በሽታ እንዳይዛቸው ለመከላከል ሲባል ከእናቶቻቸው ነጥለው ይወስዷቸዋል። ይሁን እንጂ አራስ ልጆች ከእናቶቻቸው ጋር ሲሆኑ ለሞት በሚዳርጉ በሽታዎች የመያዝ አጋጣሚያቸው እንደሚቀንስ አንዳንድ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ። ስለዚህ አንድ ሕፃን እንደተወለደ ረዘም ላለ ጊዜ ከእናቱ ጋር እንዲቆይ የሚፈቅዱ ሆስፒታሎች ቁጥር እየተበራከተ መጥቷል።
አንዳንዶች ከልጃቸው ጋር የሚኖራቸው ትስስር ያሳስባቸዋል
አንዳንድ እናቶች ልጃቸው እንደተወለደ ሲያዩት ስሜታዊ ትስስር አይሰማቸውም። በመሆኑም ‘ልጄን አልወደው ይሆን?’ ብለው ያስባሉ። በእርግጥ ልጃቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያዩ ፍቅር የሚይዛቸው ሁሉም እናቶች አይደሉም። ሆኖም ስለዚህ ጉዳይ መጨነቅ አያስፈልግም።
መጀመሪያ ላይ እናት ለልጅዋ ወዲያውኑ የፍቅር ስሜት ባይኖራትም እንኳ በጊዜ ሂደት እየወደደችው ትመጣለች። አንዲት ተሞክሮ ያላት እናት “በምትወልጅበት ጊዜ ከልጅሽ ጋር የሚኖርሽን ዝምድና የሚያጠናክርም ሆነ የሚያበላሽ አንድ ዓይነት ክስተት ይፈጠራል ብለሽ ማሰብ የለብሽም” ብላለች። ያም ሆነ ይህ ነፍሰ ጡር ከሆንሽና የሚያሳስብሽ ጉዳይ ካለ ከአዋላጅሽ ጋር በቅድሚያ ብትወያዪ ጥሩ ሊሆን ይችላል። ከወለድሽ በኋላ ልጅሽ መቼና ለምን ያህል ጊዜ ከአንቺ ጋር እንዲሆን እንደምትፈልጊ በግልጽ ተናገሪ።
“አነጋግሩኝ!”
ሕፃናት ለአንዳንድ ሁኔታዎች ምላሽ የሚሰጡበት የተወሰነ ወቅት ያለ ይመስላል። ይህ ወቅት ለተወሰነ ጊዜ ቆይቶ ያልፋል። ለምሳሌ ያህል የሕፃኑ አንጎል አንድና ከዚያም በላይ የሆኑ ቋንቋዎችን በደንብ ለመልመድ ብዙ ጥረት አይጠይቅበትም። ይሁን እንጂ አንጎል ቋንቋን በቀላሉ ለመማር ያለው አቅም ከአምስት ዓመት ገደማ በኋላ መቀነስ ይጀምራል።
አንድ ልጅ ከ12 እስከ 14 ዓመት ሲደርስ ቋንቋ መማር በጣም አዳጋች ሊሆንበት ይችላል። ፒተር ሁተንሎኸር የተባሉ የሕፃናት የነርቭ ሥርዓት ሐኪም እንደሚሉት ከሆነ ይህ የዕድሜ ክልል “ቋንቋ መማርን በሚመለከተው የአንጎል ክፍል ውስጥ ያሉት የነርቭ አውታር መገጣጠሚያዎች የሚሳሱበትና ቁጥራቸው የሚቀንስበት” ጊዜ ነው። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት ቋንቋ መማር የሚቻልባቸው ወሳኝ ጊዜያት ናቸው!
ታዲያ ሕፃናት ለተቀረው የአእምሮ እድገታቸው አስፈላጊ የሆነውን የመናገር ችሎታ የሚያዳብሩት እንዴት ነው? በአመዛኙ ከወላጆቻቸው ጋር በሚያደርጉት የቃላት ልውውጥ አማካኝነት ነው። ሕፃናት በተለይ ከሰው አንደበት ለሚወጣ ድምፅ ምላሽ ይሰጣሉ። በማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ተቋም ባልደረባ የሆኑት ባሪ አሮንስ “አንድ ሕፃን . . . የእናቱን ድምፅ ይኮርጃል” ብለዋል። ይሁን እንጂ ሕፃናት የሰሙትን ድምፅ ሁሉ የሚኮርጁ አለመሆናቸው የሚያስገርም ነው። አሮንስ እንደተናገሩት ሕፃኑ “የሚተኛበት አልጋ ሲወዛወዝ የሚያሰማውን ሲጥጥ የሚል ድምፅ ከእናቱ ድምፅ ጋር አንድ ላይ ቢሰማውም የአልጋውን ድምፅ አይዘውም።”
የተለያየ ባሕል ያላቸው ወላጆች ለሕፃናት ልጆቻቸው ሲያወሩ የሚያሰሙት ድምፅ ተመሳሳይ የሆነ ቅላጼ አለው። ወላጅ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ሲናገር የሕፃኑ የልብ ምት ፍጥነት ይጨምራል። ይህም ሕፃናቱ በቃላትና ቃላቱ በሚያመለክቱት ነገር መካከል ያለውን ዝምድና ቶሎ እንዲለዩ ያስችላል ተብሎ ይታመናል። ሕፃኑ አንድም ቃል ባይናገርም እንኳን “አነጋግሩኝ!” የሚል ጥሪ ያሰማል።
“ተመልከቱኝ!”
ሕፃኑ በተወለደ በመጀመሪያው ዓመት ላይ ከሚንከባከበው ሰው ጋር (አብዛኛውን ጊዜ እናቱ ነች) ስሜታዊ ትስስር እንደሚመሠርት ታውቋል። አስተማማኝ በሆነ መንገድ ከእናቱ ጋር ትስስር መፍጠር የቻለ ሕፃን የወላጅ ፍቅር ካላገኙት ሕፃናት ይልቅ ከሌሎች ጋር ወዳጅነት የመመሥረት ችሎታው ከፍተኛ ነው። ሕፃኑ ከእናቱ ጋር የሚኖረው እንዲህ ያለው ትስስር እስከ ሦስት ዓመት ዕድሜው ባለው ጊዜ ውስጥ መመሥረት እንዳለበት ይታመናል።
የአንድ ሕፃን አእምሮ በውጫዊ ተጽዕኖ በቀላሉ ሊነካ በሚችልበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ችላ ቢባል ምን ሊያጋጥም ይችላል? በ267 እናቶችና በልጆቻቸው ላይ ከ20 ዓመት በላይ ጥናት ያካሄዱ ማርታ ፋሬል ኤሪክሰን የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል:- “አንድ ሕፃን ችላ መባሉ ከሌሎች ጋር ለመግባባት ወይም በዙሪያው ያለውን ዓለም ለማወቅ ያለው ፍላጎት እስኪጠፋ ድረስ የሕፃኑን መንፈስ ቀስ በቀስ ይሸረሽረዋል።”
በቴክሳስ የልጆች ሆስፒታል ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ብሩስ ፔሪ ልጆች ችላ መባላቸው በስሜታቸው ላይ ስለሚያስከትለው አስከፊ መዘዝ በምሳሌ ሲያስረዱ እንዲህ
ብለዋል:- “የ6 ወር ሕፃን ሰጥታችሁኝ በሰውነቱ ላይ ያለውን አጥንት አንድ በአንድ ከመስበርና ለሁለት ወር ችላ ከማለት ለዘለቄታው የሚጎዳው የትኛው ነው ብላችሁ ብትጠይቁኝ የሰውነቱ አጥንት አንድ በአንድ ቢሰባበር ይሻለዋል እላለሁ።” ለምን? በዶክተር ፔሪ አስተያየት መሠረት “አጥንት ይጠገናል፣ አንድ ሕፃን ለሁለት ወራት አእምሮውን እንዲያሠራ የሚያደርገው ነገር ካጣ ግን ለዘለቄታው አጥርቶ ማሰብ የማይችል አንጎል ይዞ ይቀራል።” እንዲህ ያለው ጉዳት ሊጠገን አይችልም በሚለው ሐሳብ የሚስማሙት ሁሉም አይደሉም። ይሁን እንጂ በስሜት እንዲጎለብት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ለሕፃኑ አእምሮ አስፈላጊ መሆኑን የተደረጉት ሳይንሳዊ ጥናቶች ይጠቁማሉ።ኢንፋንትስ የተሰኘው መጽሐፍ “በአጭሩ፣ ሕፃናት ለማፍቀርም ሆነ ለመፈቀር ፍላጎቱም ሆነ ችሎታው አላቸው” ብሏል። አብዛኛውን ጊዜ አንድ ሕፃን ሲያለቅስ “ተመልከቱኝ!” እያለ ወላጆቹን መለመኑ ነው። ወላጆቹም ለዚህ ልመና ርህራሄ በተሞላበት መንገድ ምላሽ መስጠታቸው አስፈላጊ ነው። እንደዚህ ባለው የሐሳብ ልውውጥ አማካኝነት ሕፃኑ የሚፈልገውን ነገር ለሌሎች ለማሳወቅ እንደሚችል ይገነዘባል። ከሌሎች ጋር ማኅበራዊ ግንኙነት መመሥረትን እየተማረ ነው።
‘ልጁ አይሞላቀቅብኝም?’
‘ሕፃኑ ባለቀሰ ቁጥር የሚፈልገውን ነገር የማደርግለት ከሆነ አይሞላቀቅብኝም?’ ብለሽ ትጠይቂ ይሆናል። ምናልባት ይሞላቀቅ ይሆናል። ለዚህ ጥያቄ የሚሰጡት መልሶች በእጅጉ ይለያያሉ። እያንዳንዱ ልጅ የተለየ በመሆኑ ወላጆች ምን ቢያደርጉ የተሻለ እንደሚሆን መወሰን አለባቸው። ይሁን እንጂ በቅርብ ጊዜ የተደረገ ጥናት እንደሚጠቁመው አራስ ልጅ ሲርበው፣ ሳይመቸው ሲቀር ወይም ሲበሳጭ ሰውነቱ ለሁኔታው ምላሽ በመስጠት ሲጨነቅ የሚረጨውን ሆርሞን ያመነጫል። ስሜቱን በማልቀስ ይገልጻል። እናቱ ለልጁ ልቅሶ ምላሽ በመስጠት ፍላጎቱን ስታሟላለት በሕፃኑ አንጎል ውስጥ ራሱን ለማረጋጋት የሚረዱት የሴል አውታሮች እንዲፈጠሩ እንደምታስችለው ይነገራል። በተጨማሪም ዶክተር ሚገን ጉናር እንዳሉት ሕፃኑ እንክብካቤ ሲያገኝ ኮርቲሶል የተባለውን የጭንቀት ሆርሞን የሚያመነጨው በጥቂቱ ይሆናል። ሕፃኑ ቢበሳጭም እንኳን የጭንቀት ሆርሞን ማመንጨቱን ቶሎ ያቆማል።
ማርታ ፋረል ኤሪክሰን እንዲህ ብለዋል:- “እንዲያውም ባለቀሱ ቁጥር በፍጥነትና ያለማቋረጥ ምላሽ የሚሰጣቸው ከ6 እስከ 8 ወር ዕድሜ ያላቸው ሕፃናት፣ ሲያለቅሱ ዝም ከተባሉት ሕፃናት ጋር ሲወዳደሩ ብዙ አያለቅሱም።” ምላሽ የምትሰጡበትን መንገድ መለዋወጥም አስፈላጊ ነው። ሕፃኑ ባለቀሰ ቁጥር በመመገብ ወይም በማቀፍ ሁልጊዜ በአንድ ዓይነት መንገድ ምላሽ የምትሰጡ ከሆነ በእርግጥም ሊሞላቀቅ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ማልቀሱን እንዳወቃችሁለት በድምፃችሁ መግለጽ ብቻ ይበቃ ይሆናል። ወይም ደግሞ ወደ አልጋው ቀረብ ብላችሁ ቀስ ብላችሁ መናገር ውጤታማ ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ጀርባውን ወይም ሆዱን በእጃችሁ ነካ ነካ ማድረግ በቂ ይሆናል።
“የሕፃን ሥራ ማልቀስ ነው” የሚል አንድ የሩቅ ምሥራቃውያን አባባል አለ። ማልቀስ አንድ ሕፃን የሚፈልገውን ነገር የሚገልጽበት ዋነኛ መንገድ ነው። አንድ ነገር እንዲደረግላችሁ በጠየቃችሁ ቁጥር ችላ ብትባሉ ምን ይሰማችሁ ነበር? ታዲያ ያለ ተንከባካቢ ራሱን መርዳት የማይችለው ሕፃን ልጃችሁ ትኩረት እንድትሰጡት በፈለገ ቁጥር ችላ ቢባል ምን ይሰማዋል? ይሁንና ለልቅሶው ምላሽ መስጠት ያለበት ማን ነው?
ሕፃኑን ማን ይንከባከበው?
በቅርብ ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ የተደረገ የሕዝብ ቆጠራ እንዳሳየው 54 በመቶ የሚሆኑት ልጆች ከተወለዱበት ጊዜ አንስቶ ሦስተኛ ክፍል እስከሚደርሱበት ጊዜ ድረስ በተወሰነ መጠን እንክብካቤ የሚያገኙት ከወላጆቻቸው ሳይሆን ከሌላ ሰው ነው። በብዙ ቤተሰቦች ውስጥ በቂ ገቢ ለማግኘት ሁለቱም ወላጆች መሥራት ያስፈልጋቸው ይሆናል። ብዙ እናቶች አራስ ልጃቸውን ለመንከባከብ ሲሉ የሚቻል ሲሆን ለጥቂት ሳምንታት ወይም ወራት የወሊድ ፈቃድ ይወስዳሉ። ሆኖም ከዚያ በኋላ ሕፃኑን መንከባከብ ያለበት ማን ነው?
እርግጥ ነው፣ እንደዚህ ያለው ውሳኔ የሚደረግበት ድርቅ ያለ ደንብ የለም። ይሁን እንጂ ልጁ በዚህ ወሳኝ ዕድሜው ላይ በቀላሉ ለአደጋ የተጋለጠ እንደሆነ ማስታወሱ ጠቃሚ ነው። ሁለቱም ወላጆች ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል። ምን ማድረግ እንዳለባቸው በሚወስኑበት ጊዜ ያሉትን አማራጮች በጥንቃቄ ማመዛዘን አለባቸው።
“በጣም ጥሩ ናቸው የሚባሉት የልጆች መንከባከቢያ ተቋማትም እንኳን ልጆቻችንን እንዲያሳድጉልን ማድረግ ልጆች ከእናትና ከአባታቸው ማግኘት የሚገባቸውን ጊዜ እንደማይተካ እያደር ግልጽ እየሆነ መጥቷል” በማለት የአሜሪካ የሕፃናት ሕክምና ተቋም ዶክተር የሆኑት ጆሰፍ ዛንጋ ይናገራሉ። በልጆች የቀን እንክብካቤ መስጫ ተቋማት የሚውሉ ሕፃናት ከሞግዚቶቹ ጋር የሚያስፈልገውን ያህል ጊዜ ማሳለፍ እንደማይችሉ በመስኩ የተሠማሩ አንዳንድ ባለሞያዎች ይሰማቸዋል።
ሥራ የሚውሉ አንዳንድ እናቶች ለልጆቻቸው ስሜታዊ እድገት ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው በመገንዘብ ይህን ኃላፊነት ለሌሎች ከመስጠት ይልቅ ቤት ውለው ልጆቻቸውን ራሳቸው ለማሳደግ ወስነዋል። አንዲት ሴት “ማንኛውም ሌላ ሥራ ከሚሰጠኝ የበለጠ እርካታ በማግኘት እንደተባረክሁ ከልብ አምናለሁ” ብላለች። እርግጥ ነው፣ ሁሉም እናቶች እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ለማድረግ የገንዘብ አቅማቸው አይፈቅድላቸውም። ብዙ ወላጆች ሌላ አማራጭ ስለሌላቸው ልጆቻቸው በእንክብካቤ መስጫ ተቋም እንዲውሉ በማድረግ ከሥራ በሚመለሱበት ጊዜ ለልጃቸው ትኩረትና ፍቅር ለመስጠት ተጨማሪ ጥረት ያደርጋሉ። ሥራ የሚውሉ ብዙ ነጠላ ወላጆች በዚህ ረገድ ያላቸው ምርጫ በጣም አናሳ በመሆኑ ተመሳሳይ ነገር የሚያደርጉ ቢሆኑም ልጆቻቸውን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ፤ ጥሩ ውጤትም አግኝተዋል።
ወላጅነት ብዙ ደስታ የሚያስገኝ አርኪ ሥራ ነው። ሆኖም ተፈታታኝና አድካሚም ነው። ታዲያ ሊሳካላችሁ የሚችለው እንዴት ነው?
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.2 በዚህ ጉዳይ ላይ የተገኙ የጥናት ውጤቶች ለወላጆች ጠቃሚና ትምህርት ሰጪ ሊሆኑ ስለሚችሉ ንቁ! በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ላይ በርካታ የሕፃናት እንክብካቤ ባለሞያዎች የሰጡትን ሐሳብ ያቀርባል። የሆነ ሆኖ የባለሞያዎቹ አመለካከት በአብዛኛው ከጊዜ በኋላ የሚለወጡና ማሻሻያ የሚደረግባቸው መሆኑ መታወቅ አለበት። በአንጻሩ ግን፣ ንቁ! የሚያቀርባቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሥፈርቶች ፈጽሞ አይለወጡም።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ዝምተኛ ሕፃናት
የማያለቅሱና የማይስቁ ሕፃናት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አንዳንድ የጃፓን ሐኪሞች ይናገራሉ። የሕፃናት ሐኪም የሆኑት ሳቶሺ ያናጊሳዋ እንደዚህ ያሉትን ልጆች ዝምተኛ ሕፃናት ብለዋቸዋል። ሕፃናቱ ስሜታቸውን መግለጽ የሚያቆሙት ለምንድን ነው? አንዳንድ ዶክተሮች ይህ ሁኔታ የሚከሰተው ከወላጅ ጋር የመገናኘት አጋጣሚ በማጣታቸው እንደሆነ ያምናሉ። ይህ ሁኔታ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ችግር ተብሎ ይጠራል። አንድ አስተያየት እንደሚገልጸው ሕፃናቱ የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ ያላቸው ፍላጎት ሁልጊዜ ችላ ሲባል ወይም የተሳሳተ ትርጉም ሲሰጠው ተስፋ ይቆርጡና የኋላ ኋላ የሐሳብ ግንኙነት ማድረጉን ጨርሶ ይተዉታል።
አንድ ሕፃን በተገቢው ጊዜ የማያጫውቱትና የማያነጋግሩት ከሆነ የሌሎችን ስሜት ወይም ችግር እንዲረዳ የሚያደርገው የአንጎሉ ክፍል ላይዳብር እንደሚችል በቴክሳስ የሕፃናት ሆስፒታል የአእምሮ ሕክምና ዶክተር የሆኑት ብሩስ ፔሪ ተናግረዋል። ሕፃናት ከመጠን በላይ ችላ ከተባሉ የሌላውን ችግር እንደራስ የመመልከት ስሜታቸው ሊያንሰራራ በማይችል መልኩ ሊጠፋ ይችላል። በአንዳንድ ሁኔታዎች አደንዛዥ ዕፆችን መውሰድና የወጣቶች ዓመፀኝነት፣ በልጅነታቸው ካጋጠማቸው እንደዚህ ካለው ሁኔታ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ዶክተር ፔሪ ያምናሉ።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወላጅና ልጅ እርስ በርስ የሐሳብ ልውውጥ ባደረጉ መጠን በመካከላቸው ያለው ትስስር እየጠነከረ ይሄዳል