በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መድኃኒትነት ያላቸው እጽዋት ሊረዱህ ይችሉ ይሆን?

መድኃኒትነት ያላቸው እጽዋት ሊረዱህ ይችሉ ይሆን?

መድኃኒትነት ያላቸው እጽዋት ሊረዱህ ይችሉ ይሆን?

መድኃኒትነት ያላቸው እጽዋት ለሕክምና ተግባር ማገልገል ከጀመሩ በጣም ረጅም ዘመን አልፏል። በ16ኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት በግብጽ በተዘጋጀው ኤበርስ ፓፒረስ የተባለ ጽሑፍ ውስጥ ለተለያዩ በሽታዎች የሚያገለግሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ የባሕል መድኃኒቶች ተመዝግበው ተገኝተዋል። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ መድኃኒትነት ያላቸው እጽዋት በጽሑፍ ሰፍረው የሚገኙ ሳይሆን በአፍ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ የቆዩ ናቸው።

በምዕራቡ ዓለም የእጽዋት ሕክምና ደ ማቴርያ ሜዲካ የተባለውን ጽሑፍ ካዘጋጀው ዲየስኮርዲስ የተባለ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ግሪካዊ ሐኪም ሥራ ጀምሮ የዳበረ ይመስላል። ለሚቀጥሉት 1,600 ዓመታት ዋነኛ የመድኃኒት መጽሐፍ ሆኖ የቆየው ይህ መጽሐፍ ነበር። ዛሬም ከእጽዋት የሚዘጋጁ መድኃኒቶች በብዙ የዓለም ክፍሎች የተለመዱ ናቸው። በጀርመን የአገሪቱ ዜጎች ከእጽዋት የተዘጋጁ መድኃኒቶችን ለመግዛት ያወጡትን ወጪ የሚተካ የመንግሥት ጤና ፕሮግራም አለ።

ከእጽዋት የሚዘጋጁ ባሕላዊ መድኃኒቶች ከዘመናዊ መድኃኒቶች ይልቅ ይበልጥ አስተማማኝ ናቸው ቢባልም ምንም ዓይነት ጉዳት አያስከትሉም ማለት ግን አይደለም። ስለዚህ አንድ ሰው ከእጽዋት የሚዘጋጁ መድኃኒቶችን ለመውሰድ በሚያስብበት ጊዜ ምን ዓይነት ጥንቃቄዎች ማድረግ ይኖርበታል? አንድ ዓይነት ሕክምና ይበልጥ ጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል? የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ። *

መድኃኒትነት ያላቸው እጽዋት የሚሰጡት ጥቅም

መድኃኒትነት ያላቸው እጽዋት የተለያየ የመፈወስ ባሕርይ እንዳላቸው ይነገራል። አንዳንዶቹ ሰውነት በሽታዎችን ተዋግቶ እንዲያሸንፍ የመርዳት ችሎታ እንዳላቸው ይገመታል። ሌሎች ደግሞ ምግብ ለመፍጨት፣ ነርቮችን ለማዝናናት፣ ሆድ ለማለስለስ ወይም የእጢዎችን አሠራር ለማስተካከል እንደሚረዱ ይነገራል።

መድኃኒትነት ያላቸው እጽዋት ለምግብነትም ሆነ ለመድኃኒትነት ሊያገለግሉ ይችላሉ። ለምሳሌ እንደ ፐርሰሜሎ (የስጎ ቅጠል) ያሉት ብዙ የማሸናት ባሕርይ ያላቸው እጽዋት ፖታስየም የሚባለው ማዕድን በብዛት ይገኝባቸዋል። በእነዚህ እጽዋት ውስጥ የሚገኘው ፖታስየም ከሽንት ጋር ወጥቶ ለሚባክነው ለዚህ ማዕድን ማካካሻ ይሆናል። ለእንቅልፍ ማጣት የሚወሰደው ቫሌርያን የተባለው እጽ ደግሞ በካልስየም ይዘቱ በጣም የበለጸገ ነው። ይህ እጽ ያለው ነርቮችን የማረጋጋት ኃይል በውስጡ በያዘው ካልስየም ሊጠናከር ይችላል።

መድኃኒትነት ያላቸው እጽዋት አጠቃቀም

መድኃኒትነት ያላቸው እጽዋት በተለያዩ መንገዶች ሊወሰዱ ይችላሉ። በሻይ መልክ፣ በውኃ ተንተክትከው ወይም በአልኮል ተቀምመው ሊወሰዱ አሊያም በውጭ ሰውነት ላይ በጨርቅ ሊታሰሩ ይችላሉ። በሻይ መልክ የሚዘጋጀው የፈላ ውኃ እጽዋቱ ላይ ጨምሮ ጥቂት በማቆየት ነው። አብዛኛውን ጊዜ እንደ ሻይ የሚጠጡ እጽዋት ውኃ ውስጥ ተጨምረው መፍላት እንደሌለባቸው የመስኩ ጠበብት ይናገራሉ። መድኃኒቶች ከሥራሥርና ከእንጨት ቅርፊቶች በሚዘጋጁበት ጊዜ ፈውስ የሚያስገኙትን ቅመማት ማውጣት እንዲቻል ውኃ ውስጥ ብዙ ማንተክተክ ያስፈልጋል።

በአልኮል የሚቀመሙትስ? አንድ መጽሐፍ እንደሚለው “የእጽዋት መድኃኒቶች በንጹሕ ወይም በተበረዘ አልኮል ወይም በብራንዲ አሊያም በቮድካ ሊቀመሙ ይችላሉ።” በተለያየ መንገድ ተዘጋጅተው ሕመም በሚሰማበት የውጭው የሰውነት ክፍል ላይ የሚታሰሩ ወይም የሚደረጉም አሉ።

ከብዙዎቹ ቫይታሚኖችና መድኃኒቶች በተለየ አብዛኞቹ መድኃኒትነት ያላቸው እጽዋት እንደ ምግብ ስለሚቆጠሩ አብዛኛውን ጊዜ የሚወሰዱት በባዶ ሆድ ነው። ከተፈጩ በኋላ በካፕሱል ውስጥ ተጨምረው የሚወሰዱበት ጊዜም ያለ ሲሆን ይኸኛው ዘዴ ይበልጥ አመቺና ቀላል ነው። ከእጽዋት የተዘጋጀ መድኃኒት ለመውሰድ ከወሰንክ የባለሞያ መመሪያ ብታገኝ ጥሩ ይሆናል።

አብዛኛውን ጊዜ ከእጽዋት የሚዘጋጁ መድኃኒቶች የሚሰጡት እንደ ጉንፋን፣ የምግብ አለመስማማት፣ የሆድ ድርቀት፣ የእንቅልፍ ማጣትና ማቅለሽለሽ ለመሳሰሉት ችግሮች ነው። ይሁን እንጂ ከባድ ለሆኑ በሽታዎች፣ በፈዋሽነት ብቻ ሳይሆን በመከላከያነትም የሚወሰዱበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ ያህል በጀርመንና በኦስትሪያ ሶው ፓልመቶ የተባለው እጽ ወደ ካንሰርነት ደረጃ ላልደረሰ ለፕሮስቴት እጢ እብጠት እንደ መጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ይወሰዳል። በአንዳንድ አገሮች ይህ በሽታ ከ50 እስከ 60 በመቶ የሚሆኑ ወንዶችን ያጠቃል። ይሁን እንጂ በሽታው ወደ ካንሰርነት ተለውጦ ይበልጥ ከበድ ያለ ሕክምና ሊያስፈልግ ስለሚችል የእብጠቱ ምክንያት ምን እንደሆነ በሐኪም መረጋገጥ ይኖርበታል።

ሊወሰዱ የሚገባቸው አንዳንድ ጥንቃቄዎች

ለመድኃኒትነት የሚያገለግል አንድ ዓይነት እጽ ምንም ዓይነት ጉዳት አያስከትልም ተብሎ የሚታሰብ ቢሆንም እንኳን ጥንቃቄ ማድረግ ጥሩ ነው። አንድ መድኃኒት “ከተፈጥሮ እጽዋት የተቀመመ” የሚል ጽሑፍ ስለተለጠፈበት ብቻ መዘናጋት አይገባችሁም። መድኃኒትነት ስላላቸው እጽዋት የተዘጋጀ አንድ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል:- “አንዳንድ እጽዋት አደገኛ መሆናቸውን አምነን መቀበል አለብን። . . . አንዳንድ ሰዎች፣ አደገኛም ሆኑ አልሆኑ መድኃኒትነት ባላቸው እጽዋት ረገድ ተገቢውን ጥንቃቄ አለማድረጋቸው ያሳዝናል።” መድኃኒትነት ባላቸው እጽዋት ውስጥ የሚገኙ ኬሚካሎች የልብ ምት ፍጥነትን፣ የደም ግፊትንና የስኳር መጠንን ከፍ ወይም ዝቅ ሊያደርጉ ይችላሉ። ስለዚህ የልብ ሕመም፣ የደም ግፊት ወይም የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች የተለየ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል።

ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ መድኃኒትነት ያላቸው እጽዋት የሚያስከትሉት ችግር ከሰውነት መቆጣት አያልፍም። ራስ ምታት፣ ማዞር፣ ማቅለሽለሽና ሽፍታ ሊያስከትሉ ይችላሉ። በተጨማሪም መድኃኒትነት ያላቸው እጽዋት በሰውነታችን ውስጥ መሥራት ሲጀምሩ እንደ ጉንፋን ያሉ ወይም ሌሎች የሕመም ስሜቶች ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ይነገራል። መድኃኒቶቹን የሚወስደው ሰው ሕመሙ ከመሻሉ በፊት የተባባሰበት ሊመስል ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ይህ ዓይነቱ የሕመም ስሜት የሚፈጠረው ሕክምናው በተጀመረበት ወቅት በሰውነት ውስጥ የተከማቸው መርዛማ ቆሻሻ በመወገዱ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል።

አልፎ አልፎ ከእጽዋት በሚዘጋጁ መድኃኒቶች ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች መኖራቸው ጥንቃቄ ማድረግና መመሪያ መከተል አስፈላጊ መሆኑን ያስገነዝባል። ለምሳሌ፣ አብዛኛውን ጊዜ ክብደት ለመቀነስ የሚወሰደው ኤፌድራ የተባለ እጽ የደም ግፊት እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል። በዩናይትድ ስቴትስ ከ100 የሚበልጡ ሰዎች ከኤፌድራ ውጤቶች ጋር በተያያዘ ሕይወታቸውን እንዳጡ ቢዘገብም በሳን ፍራንሲስኮ ፓቶሎጂስት የሆኑት ስቲቨን ካርች “እኔ እስከማውቀው ድረስ ኤፌድራ በመውሰዳቸው ምክንያት የሞቱት ከባድ የልብ ሕመም ያለባቸው ወይም መድኃኒቱን ከመጠን በላይ የወሰዱ ሰዎች ብቻ ናቸው” ብለዋል።

መድኃኒትነት ካላቸው እጽዋት ስለሚዘጋጁ መድኃኒቶች መጽሐፍ የጻፉት ዶክተር ሎገን ቻምበርለን “በቅርብ ዓመታት እጽዋት ስላስከተሉት ጉዳት የተነገረው ሁሉ ሰዎች የተሰጣቸውን መመሪያ ባለመከተላቸው የደረሰ ነው። . . . አስተማማኝ በሆኑ የእጽዋት ውጤቶች ረገድ የሚሰጡ የአወሳሰድ መጠን መመሪያዎች ምንም ችግር የማያስከትሉና እንዲያውም አደጋ ሊያደርስ ከሚችለው መጠን በጣም ያነሱ ናቸው። የሠለጠነ ባለሞያ ምክር ካላገኛችሁ በስተቀር እነዚህን መመሪያዎች ለመለወጥ መሞከር የለባችሁም” ብለዋል።

መድኃኒትነት ያላቸው እጽዋት ባለሞያ የሆኑት ሊንዳ ፔጅ የሚከተለውን የማስጠንቀቂያ ምክር ሰጥተዋል:- “ሕመሙ ከባድ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ የሚወሰደው መድኃኒት ከአነስተኛ መጠን መብለጥ አይኖርበትም። ቀለል ያለና ረዥም ጊዜ የሚፈጅ ሕክምና የተሻለ ውጤት ያስገኛል። ከበሽታ ለመዳን ረዘም ያለ ጊዜ ያስፈልጋል።”

መድኃኒትነት ስላላቸው እጽዋት የተዘጋጀ አንድ መጽሐፍ እንደገለጸው አንዳንድ እጽዋት ከመጠን በላይ ከተወሰዱ ጉዳት እንዳያስከትሉ የሚያደርግ የራሳቸው መከላከያ አላቸው። ለምሳሌ ሰውነትን ለማዝናናት የሚወሰድ ከእጽ የተዘጋጀ አንድ መድኃኒት ከመጠን በላይ ከተወሰደ ያስመልሳል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ባሕርይ በሁሉም እጽዋት ላይ የማይገኝ በመሆኑ የአወሳሰድ መጠን መመሪያዎችን ችላ ለማለት ምክንያት አይሆንም።

ሆኖም አንድ ፈዋሽ እጽ ተፈላጊውን ውጤት እንዲያስገኝ በበቂ መጠንና በትክክለኛው መንገድ መወሰድ እንዳለበት ብዙዎች ያምናሉ። አንዳንድ ጊዜ ይህን ማድረግ የሚቻለው በውኃ ብዙ ተንተክትኮ የተዘጋጀ መድኃኒት በመውሰድ ነው። የማስታወስ ችሎታና የደም ዝውውር ለማሻሻል ለብዙ ዘመናት ሲወሰድ የቆየው ጊንኮ ቢሎባ እንደዚህ ካሉት እጽዋት አንዱ ነው። ለአንድ ጊዜ የሚወሰድ መድኃኒት ለማዘጋጀት ብዙ ኪሎ ቅጠል ያስፈልጋል።

አደገኛ ሊሆን የሚችል ውህደት

መድኃኒትነት ያላቸው እጽዋት ከዘመናዊ መድኃኒቶች ጋር አብረው ሲወሰዱ ያልተጠበቀ ውጤት ሊያስከትሉ ይችላሉ። ለምሳሌ የአንዳንድ መድኃኒቶችን ኃይል ሊያጠናክሩ ወይም ሊያዳክሙ፣ ከወትሮው በበለጠ ፍጥነት ከሰውነት እንዲወገዱ ሊያደርጉ ወይም የሚያስከትሉትን ጉዳት ሊያባብሱ ይችላሉ። በጀርመን አገር ቀለል ላለ የአእምሮ ጭንቀት የሚታዘዘው ሴይንት ጆንስ ወርት የተባለ እጽ አንዳንድ መድኃኒቶች ከሰውነት የሚወገዱበት ፍጥነት በእጥፍ እንዲጨምር ስለሚያደርግ የመድኃኒቶቹ ኃይል በእጅጉ ይዳከማል። ስለዚህ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብልን ጨምሮ፣ ማንኛውንም በሐኪም የታዘዘ መድኃኒት የሚወስድ ሰው መድኃኒትነት ያለው እጽ ከመውሰዱ በፊት ሐኪሙን ማማከር ይኖርበታል።

ስለ እጽዋት የመፈወስ ባሕርይ የተዘጋጀ አንድ መጽሐፍ “አልኮል፣ ማሪዋና፣ ኮኬይን፣ ሌሎች የባሕርይ ለውጥ የሚያስከትሉ እጾችና ትንባሆ ከአንዳንድ መድኃኒትነት ያላቸው እጽዋት ጋር ከተወሰዱ ሕይወት ሊያሳጣ የሚችል ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ። . . . በተለይ በምትታመምበት ጊዜ [ከእነዚህ እጾች] መራቅ ጥበብ ይሆናል” ይላል። በተጨማሪም ነፍሰ ጡር የሆኑና የሚያጠቡ እናቶች ይህን ምክር ልብ ማለት ያስፈልጋቸዋል። እርግጥ ክርስቲያኖች “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ” የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክር ስለሚከተሉ ትንባሆና ሱስ የሚያስይዙ እጾች የሚያስከትሉት ጉዳት አይደርስባቸውም።—2 ቆሮንቶስ 7:1

መድኃኒትነት ባላቸው እጽዋት ረገድም ቢሆን አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ይሰጣል:- “መድኃኒትነት ያለው እጽ እየወሰደች እያለ ያረገዘች ሴት ለሐኪሟ መናገርና ከሐኪሟ ጋር እስከምትመካከር ድረስ መድኃኒቱን ማቋረጥ ይኖርባታል። መድኃኒቱን በምን ያህል መጠንና ለምን ያህል ጊዜ ስትወስድ እንደቆየች ለማስታወስ ብትሞክር ጥሩ ይሆናል።”

መድኃኒትነት ስላላቸው እጽዋት የተዘጋጀ አንድ ኢንሳይክሎፒዲያ “ባለሞያ ሳያማክሩ ከፈዋሽ እጽዋት የተዘጋጁ መድኃኒቶችን መውሰድ ብዙ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል” ይላል። ከዚህ ጽሑፍ ጋር አባሪ በሆነው “ባለሞያ ሳያማክሩ መድኃኒት መውሰድ የሚያስከትላቸው ችግሮች” በሚለው ሣጥን ውስጥ በዚህ ኢንሳይክሎፒዲያ ላይ የተገለጹ ከእጽዋት የተዘጋጁ መድኃኒቶች ሊያስከትሉ የሚችሏቸው አደጋዎች ተዘርዝረዋል።

መድኃኒትነት ያላቸውን እጽዋትም ቢሆን እንደማንኛውም የሕክምና ውጤት በጥንቃቄና በእውቀት እንዲሁም በመመሪያው መሠረት መጠቀም አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም ለአንዳንድ በሽታዎች በአሁኑ ጊዜ ፈውስ ማግኘት እንደማይቻል አትርሳ። እውነተኛ ክርስቲያኖች የበሽታና የሞት ምክንያት የሆነው ከመጀመሪያ ወላጆቻችን የወረስነው አለፍጽምና በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የሚወገድበትን ጊዜ በናፍቆት ይጠብቃሉ።—ሮሜ 5:12፤ ራእይ 21:3, 4

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 ንቁ! የሕክምና መጽሔት አይደለም። ስለሆነም ማንኛውም ዓይነት የእጽዋትም ሆነ ሌላ ዓይነት ሕክምና ወይም የአመጋገብ ሥርዓት ከሌላው ይሻላል ብሎ ምክር አይሰጥም። በዚህ ጽሑፍ ላይ የቀረበው መረጃ ለጠቅላላ እውቀት እንዲሆን ታስቦ የቀረበ ነው። በጤናና በሕክምና ጉዳዮች ረገድ አንባቢያን የራሳቸውን ውሳኔ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ባለሞያ ሳያማክሩ መድኃኒት መውሰድ የሚያስከትላቸው ችግሮች

ብቃት ያለው ባለሞያ ሳያማክሩ ከእጽዋት የተዘጋጁ መድኃኒቶችን መውሰድ የሚከተሉትን ችግሮች ሊያስከትል ይችላል።

የችግሩ መንስኤ ምን እንደሆነ በትክክል ላታውቅ ትችላለህ።

በሽታህ ምን እንደሆነ በትክክል ብታውቅ እንኳን በራስህ ትእዛዝ የምትወስደው መድኃኒት ለበሽታህ ትክክለኛው መድኃኒት ላይሆን ይችላል።

ባለሞያ ሳታማክር የምትወስደው መድኃኒት በሽታህን ከሥሩ ሊነቅል የሚችልና የግዴታ አስፈላጊ የሆነ ሕክምና የምትወስድበትን ጊዜ ሊያዘገይብህ ይችላል።

ባለሞያ ሳታማክር የምትወስደው መድኃኒት ለምሳሌ ለአለርጂና ለደም ግፊት በሐኪም ትእዛዝ ከምትወስደው መድኃኒት ጋር ሊጋጭ ይችላል።

ባለሞያ ሳታማክር የምትወስደው መድኃኒት ቀለል ያለ ሕመምህን ሊያድንልህ ቢችልም እንኳን እንደ ደም ብዛት የመሰለውን የጤና ችግር ሊያባብስብህ ይችላል።

[ምንጭ]

ምንጭ:- ሮደልስ ኢለስትሬትድ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ኧርብስ