በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሁሉም ነገር እንደ ወንድሞቼ ወይም እንደ እህቶቼ እንድሆን የሚጠበቅብኝ ለምንድን ነው?

በሁሉም ነገር እንደ ወንድሞቼ ወይም እንደ እህቶቼ እንድሆን የሚጠበቅብኝ ለምንድን ነው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

በሁሉም ነገር እንደ ወንድሞቼ ወይም እንደ እህቶቼ እንድሆን የሚጠበቅብኝ ለምንድን ነው?

“በራሴ ማንነት መታወቅ እፈልጋለሁ። ሆኖም እንደ እህቶቼ እንድሆን የሚጠበቅብኝ ሆኖ ይሰማኛል። እህቶቼ የደረሱበት ደረጃ ላይ መድረስ ደግሞ ፈጽሞ የምችል አይመስለኝም።”—ክላር

ሁሉን ነገር ያለ ችግር ማከናወን እንደሚችል የሚነገርለት ወንድም ወይም እህት አለህ? ወላጆችህ እንደዚህ ወንድምህ ወይም እህትህ ካልሆንክ እያሉ ነጋ ጠባ ይወተውቱሃል? ከሆነ ጉብዝናህ የሚለካው ወንድምህ ወይም እህትህ የደረሱበት ደረጃ ላይ በመድረስህ ወይም ባለመድረስህ እንደሆነ ሊሰማህ ይችላል።

የባሪ * ወንድሞች ከአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት * የተመረቁና ጥሩ ስም ያተረፉ ምሳሌ የሚሆኑ ክርስቲያኖች ናቸው። ባሪ እንዲህ በማለት ይናገራል:- “የእነርሱን ያህል ጥሩ አድርጌ መስበክ ወይም የእነርሱን ያህል ጥሩ ንግግር ማቅረብ እንደምችል ሆኖ ስለማይሰማኝ በራስ የመተማመን መንፈሴን እያጣሁ መጣሁ። እነርሱ በተጋበዙበት ቦታ ሁሉ አብሬያቸው ስለምሄድ የራሴ የሆኑ ጓደኞች ለማፍራት በጣም ተቸግሬ ነበር። ሰዎች የሚያቀርቡኝ የወንድሞቼን ማንነት አይተው እንጂ ያን ያህል ፈልገውኝ እንዳልሆነ ይሰማኝ ጀመር።”

ሰው ሁሉ የሚያሞጋግሰው ወንድም ወይም እህት ካለህ በቅናት መብከንከንህ የማይቀር ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የኖረው ዮሴፍ ከወንድሞቹ ይልቅ ጎላ ብሎ የሚታይ ልጅ ነበር። ወንድሞቹ በዚህ ምን ተሰማቸው? “ጠሉት፣ በሰላም ይናገሩትም ዘንድ አልቻሉም።” (ዘፍጥረት 37:1-4) እርግጥ ነው ዮሴፍ በማንነቱ የሚኩራራ ልጅ አልነበረም። ሆኖም ወንድምህ ወይም እህትህ ስላገኙት ስኬት ሁልጊዜ የሚናገሩ ከሆነ ቅናት ወይም ቅሬታ እንዲፈጠርብህ ሊያደርግ ይችላል።

አንዳንድ ወጣቶች ዓመፀኛ በመሆን ምናልባትም በትምህርታቸው በመስነፍ፣ በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች የሚያደርጉትን ተሳትፎ በመቀነስ ወይም በአንድ ዓይነት መጥፎ ተግባር በመካፈል ቁጭታቸውን ሊወጡ ይችላሉ። የወንድሞቼን ወይም የእህቶቼን ያህል መሥራት የማልችል ከሆነ ምን አደከመኝ ብለው ሁሉን ነገር እርግፍ አድርገው ሊተዉት ይችላሉ። ሆኖም ማመፅ የኋላ ኋላ የሚጎዳህ ራስህን ነው። ታዲያ ለራስህ ያለህን ጥሩ ግምት ሳታጣ በራስህ ማንነት መታወቅ የምትችለው እንዴት ነው?

ስለ እነርሱ ያለህን የተጋነነ አመለካከት አስተካክል

ለወንድምህ ወይም ለእህትህ የሚዥጎደጎዱትን የአድናቆት ቃላት ስትሰማ ፍጹም እንደሆኑና እንደ እነርሱ መሆን ፈጽሞ የማይታሰብ እንደሆነ ሊሰማህ ይችላል። ሆኖም እንዲህ ያለው አመለካከት ትክክል ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል” በማለት በግልጽ ይናገራል።—ሮሜ 3:23

ወንድምህ ወይም እህትህ ምንም ያህል ድንቅ ችሎታ ወይም ተሰጥኦ ያላቸው ቢሆኑ እንደእኛው ጉድለት ያለባቸው ተራ ሰዎች ናቸው። (የሐዋርያት ሥራ 14:15) ስለዚህ ለእነርሱ የተጋነነ አመለካከት ማዳበርም ሆነ ከልክ በላይ በአድናቆት መመልከት አይገባም። ፍጹም በሆነ መንገድ ምሳሌ የሚሆነን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው።—1 ጴጥሮስ 2:21

ከእነርሱ ትምህርት ለመቅሰም ሞክር!

ያለህበትን ሁኔታ ትምህርት ለመቅሰም የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ አድርገህ ተመልከተው። የኢየሱስ ክርስቶስን ወንድሞችና እህቶች ለዚህ እንደ ምሳሌ አድርገን እንውሰድ። (ማቴዎስ 13:55, 56) አጋጣሚውን ጥሩ አድርገው ተጠቅመውበት ቢሆን ኖሮ ፍጹም ከሆነው ወንድማቸው ምን ዓይነት ትምህርት ሊቀስሙ እንደሚችሉ እስቲ ለአንድ አፍታ አስብ! ሆኖም “ወንድሞቹ ስንኳ አላመኑበትም ነበር።” (ዮሐንስ 7:5) ምናልባት እንዳያምኑበት ያደረጋቸው ኩራት ወይም ቅናት ሊሆን ይችላል። “ከእኔም ተማሩ” ብሎ ላቀረበው ግብዣ አዎንታዊ ምላሽ የሰጡት የኢየሱስ መንፈሳዊ ወንድሞች ማለትም ደቀ መዛሙርቱ ናቸው። (ማቴዎስ 11:29) የሥጋ ወንድሞቹ ከእርሱ መማር እንደሚችሉ የተገነዘቡት ሞቶ ከተነሳ በኋላ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 1:14) በእነዚህ ጊዜያት ከወንድማቸው ሊማሩ የሚችሉባቸው በርካታ ግሩም አጋጣሚዎች አምልጠዋቸዋል።

ቃየንም ተመሳሳይ ስህተት ፈጽሟል። ታናሽ ወንድሙ አቤል ታማኝ የአምላክ አገልጋይ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ “ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ” ተመለከተ በማለት ይናገራል። (ዘፍጥረት 4:4) ይሁን እንጂ በሆነ ምክንያት አምላክ “ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ አልተመለከተም።”ቃየን ኩራቱን ዋጥ አድርጎ ከወንድሙ መማር ይችል ነበር። እንዲህ ከማድረግ ይልቅ ግን “እጅግ ተናደደ፤” ወንድሙን አቤልንም ገደለው።—ዘፍጥረት 4:5-8

አንተ ይህን ያህል በወንድምህ ወይም በእህትህ ላይ እንደማትቆጣ የታወቀ ነው። ሆኖም ኩራትና ቅናት እንቅፋት እንዲሆኑብህ ከፈቀድህ አንተም በዋጋ ሊተመኑ የማይችሉ ትምህርቶችን ለመቅሰም ያለህን አጋጣሚ ልታጣ ትችላለህ። በሒሳብ ወይም በታሪክ ትምህርት ጎበዝ የሆነ ወይም በምትወደው የስፖርት ዓይነት የተካነ፣ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠንቅቆ የሚያውቅ ወይም ጥሩ ንግግር የማቅረብ ችሎታ ያለው ወንድም ወይም እህት ካለህ ቅናት እንዳያድርብህ መጠንቀቅ ይኖርብሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “ቅንዓት ግን አጥንትን ያነቅዛል” ስለሚል የኋላ ኋላ መጎዳትህ አይቀርም። (ምሳሌ 14:30፤ 27:4) በሁኔታው ቅር ከመሰኘት ይልቅ ከእነርሱ ትምህርት ለመቅሰም ጥረት አድርግ። አንተ የሌለህ አንድ ዓይነት ችሎታ ወይም ተሰጥኦ እንዳላቸው አምነህ ተቀበል። ወንድሞችህ ወይም እህቶችህ አንድን ነገር የሚያከናውኑበትን መንገድ በትኩረት ተመልከት፤ እንዲያውም እንዲረዱህ ጠይቃቸው።

ቀደም ሲል የተጠቀሰው ባሪ ከወንድሞቹ አርዓያ ትምህርት መቅሰም ጀመረ። እንዲህ ይላል:- “ወንድሞቼ በጉባኤ ውስጥም ሆነ በስብከቱ ሥራ ሰዎችን መርዳታቸው ምን ያህል ደስታ እንዳስገኘላቸው ተመለከትኩ። ስለዚህ እኔም እንደ ወንድሞቼ ለማድረግ ወሰንኩና በመንግሥት አዳራሽና በቤቴል የግንባታ ሥራ መካፈል ጀመርኩ። በዚህም ያገኘሁት የሥራ ልምድ በራሴ እንድተማመንና ከይሖዋ ጋር ያለኝን ዝምድና ይበልጥ እንዳሳድግ ረድቶኛል።”

የራስህን ጠንካራ ጎኖች ፈልግ

የወንድሜን ወይም የእህቴን ምሳሌ ለመኮረጅ የማደርገው ጥረት የራሴን ማንነት ቢያሳጣኝስ ብለህ ትፈራ ይሆናል። ሆኖም ፍርሃት አይግባህ። ሐዋርያው ጳውሎስ የመጀመሪያውን መቶ ዘመን ክርስቲያኖች “እኔን የምትመስሉ ሁኑ” ብሎ መክሯቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 4:16) ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ሲናገር የራሳቸውን ማንነት እርግፍ አድርገው ትተው እርሱን እንዲሆኑ መምከሩ ነበር? በፍጹም። አንድ ሰው ማንነቱን ሙሉ በሙሉ መቀየር ሳያስፈልገው ሌሎች ግሩም ባሕርያትን መቅሰም ይችላል። እንደ ወንድምህ ወይም እህትህ በሒሳብ ትምህርት ጎበዝ አይደለህም ማለት አንድ ዓይነት ጉድለት አለብህ ማለት አይደለም። ይህ ከእነርሱ የተለየህ መሆንህን የሚያሳይ ብቻ ነው።

ጳውሎስ “እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፣ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ የሚመካበትን ያገኛል” በማለት ጠቃሚ ምክር ሰጥቷል። (ገላትያ 6:4) የራስህ የሆኑ ችሎታዎችን ወይም ሙያዎችን ለምን አታዳብርም? የውጭ አገር ቋንቋ መናገር፣ የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት ወይም ኮምፒውተር መጠቀም ብትማር ስለ ራስህ ጥሩ ግምት እንዲኖርህ ከማስቻሉም በላይ ጥሩ ሙያ እንድታዳብርም ይረዳሃል። ለምን ተሳሳትኩ ብለህ አትጨነቅ። ጠንቃቃ፣ ትጉህና ቀልጣፋ ለመሆን ጥረት አድርግ። (ምሳሌ 22:29) አንድን ነገር ለማከናወን ያን ያህል ተፈጥሯዊ ተሰጥኦ ላይኖርህ ይችላል። ሆኖም “የትጉ እጅ ትገዛለች” የሚለው የምሳሌ 12:24 ጥቅስ በዋነኝነት የሚያስፈልገው ትጋት እንደሆነ ያሳያል።

ከሁሉም ይበልጥ ትኩረት ልትሰጠው የሚገባህ ነገር መንፈሳዊ እድገትህ እንደሆነ አትዘንጋ። የሌሎችን ትኩረት ሊስብ ከሚችል ከየትኛውም ተሰጥኦ ይልቅ ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኘው መንፈሳዊ እድገትህ ነው። ዔሳውና ያዕቆብ የተባሉትን መንትያ ወንድማማቾች እንደ ምሳሌ አድርገን እንውሰድ። ዔሳው “አደን የሚያውቅ የበረሃ ሰው” ስለነበር አባቱ በጣም ያደንቀው ነበር። ወንድሙ ያዕቆብ ግን መጀመሪያ ላይ ‘ጭምትና በድንኳን የሚቀመጥ ስለነበር’ ያን ያህል ዞር ብሎ የሚመለከተው ሰው አልነበረም። (ዘፍጥረት 25:27) ሆኖም ዔሳው መንፈሳዊ እድገት ማድረግ እንዳለበት ዘነጋና በረከት ሳያገኝ ቀረ። ያዕቆብ ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍቅር በማዳበሩ የይሖዋን በረከት አግኝቷል። (ዘፍጥረት 27:28, 29፤ ዕብራውያን 12:16, 17) ከዚህ ታሪክ ምን ትማራለህ? መንፈሳዊነትህን ካዳበርክና ‘ብርሃንህ እንዲበራ ካደረግክ’ ‘ማደግህ በነገር ሁሉ ግልጥ ሆኖ ይታያል።’—ማቴዎስ 5:16፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:15

በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችው ክላር እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “እንደ ታላላቅ እህቶቼ መሆን የማልችል ከሆነ መጀመሪያውኑ ለምን ጥረት አደርጋለሁ የሚል አመለካከት ነበረኝ። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ለሌሎች የምናሳየውን ፍቅር በተመለከተ ‘ልባችሁን አስፉ’ በማለት የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ወሰንኩ። በጉባኤ ውስጥ ካሉት የተለያዩ ወንድሞችና እህቶች ጋር አብሬ ማገልገል ጀመርኩ፤ እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ችግር ያለባቸውን መርዳት የምችልባቸውን መንገዶች አሰብኩ። የተለያየ ዕድሜ ያላቸውን ወንድሞችና እህቶችን ምግብ አዘጋጅቼ ወደ ቤታችን ጋበዝኳቸው። አሁን ብዙ ወዳጆች ያፈራሁ ሲሆን በራስ የመተማመን መንፈስም አዳብሬያለሁ።”—2 ቆሮንቶስ 6:13

ወላጆችህ ወንድምህን ወይም እህትህን በመጥቀስ ለምን እንደ እነርሱ አትሆንም እያሉ አልፎ አልፎ ይናገሩህ ይሆናል። ሆኖም ወላጆችህ እንዲህ የሚሉህ ለአንተ ካላቸው አሳቢነት የተነሳ እንደሆነ ማወቅህ የሚሰማህን የብስጭት ስሜት በተወሰነ መጠን ሊቀንስልህ ይችላል። (ምሳሌ 19:11) ሆኖም አንድን ልጅ ከሌላው ጋር እያወዳደሩ መናገር ምን ያህል ስሜት እንደሚጎዳ ለወላጆችህ በአክብሮት ልታስረዳቸው ትችላለህ። እንዲህ ማድረግህ ምናልባት ለአንተ ያላቸውን አሳቢነት በሌላ መንገድ እንዲገልጹ ሊያነሳሳቸው ይችላል።

ይሖዋ አምላክ እርሱን የምታገለግል ከሆነ በቁም ነገር እንደሚመለከትህ ፈጽሞ አትርሳ። (1 ቆሮንቶስ 8:3) ባሪ ሁኔታውን እንዲህ በማለት ያጠቃልላል:- “ይሖዋን ማገልገሌን በቀጠልኩ መጠን ደስታዬም የዚያኑ ያህል እያደገ እንደሚሄድ ተገንዝቤያለሁ። አሁን ሰዎች በራሴ ማንነት የሚያውቁኝ ሲሆን ከወንድሞቼ እኩል ያዩኛል።”

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 አንዳንዶቹ ስሞች ተለውጠዋል።

^ አን.5 የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጁት ትምህርት ቤት ነው።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰዎች ለወንድሞችህና ለእህቶችህ የበለጠ ትኩረት እንደሚሰጡ ሆኖ ይሰማሃል?

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የራስህን ተሰጥኦና ፍላጎት ለማሳደግ ጥረት አድርግ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መንፈሳዊነትህን በማሻሻል ‘ብርሃንህ እንዲበራ አድርግ’