በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አይበገሬዎቹ ጀርሞች ተመልሰው የሚያንሰራሩት እንዴት ነው?

አይበገሬዎቹ ጀርሞች ተመልሰው የሚያንሰራሩት እንዴት ነው?

አይበገሬዎቹ ጀርሞች ተመልሰው የሚያንሰራሩት እንዴት ነው?

ቫይረሶች፣ ባክቴሪያዎች፣ ፕሮቶዞዋዎች፣ ፈንገሶችና ሌሎች ጥቃቅን ሕዋሳት ሕይወት ያለው ፍጡር በምድር ላይ መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ጠፍተው አያውቁም። ከሌሎች ፍጥረታት አንጻር ያልተወሳሰበ ተፈጥሮ ያላቸው እነዚህ ጀርሞች በጣም አስደናቂ የሆነ ከሁኔታዎች ጋር የመላመድ ችሎታ ስላላቸው ምንም ዓይነት ሌላ ሕይወት በማይኖርበት ቦታ ሳይቀር ለመኖር ችለዋል። የሚፋጅ ውሃ በሚተፉ የውቅያኖስ ወለሎችም ሆነ በአርክቲክ በረዷማ ውሃዎች ውስጥ ይገኛሉ። አሁን ደግሞ እነዚህ ጀርሞች ከዚህ ቀደም አጋጥሟቸው የማያውቀውን ከፍተኛ ጥቃት፣ ማለትም በፀረ ተሕዋሳት መድኃኒቶች አማካኝነት የሚደረግባቸውን ዘመቻ በመመከት ላይ ናቸው።

ከአንድ መቶ ዓመት በፊት አንዳንድ ተሕዋሳት ወይም ጀርሞች ለበሽታ ምክንያት እንደሚሆኑ ቢታወቅም ስለ ፀረ ጀርም መድኃኒቶች ግን አንድም የሚያውቅ ሰው አልነበረም። ስለሆነም አንድ ሰው ከባድ የኢንፌክሽን በሽታ ቢይዘው ዶክተሮች አይዞህ ከማለት በስተቀር ምንም ሕክምና ሊሰጡት አይችሉም ነበር። ሰውየው በሽታውን ማሸነፍ ያለበት በሰውነቱ ውስጥ ባለው በሽታ የመከላከል አቅም ብቻ ነበር። በሽታ የመከላከል አቅሙ ደከም ያለ ከሆነ አብዛኛውን ጊዜ ውጤቱ አሳዛኝ ይሆናል። ትንሽ ጭረት እንኳን በጀርሞች ከተበከለ ለሞት ያደርስ ነበር።

በዚህ ምክንያት የመጀመሪያዎቹ ፀረ ጀርም መድኃኒቶች ማለትም አንቲባዮቲኮች ሲገኙ በሕክምና ላይ ከፍተኛ ለውጥ ተከሰተ። * በ1930ዎቹ ዓመታት የሰልፋ መድኃኒቶች፣ በ1940ዎቹ ዓመታት ደግሞ ፔኒሲሊንና ስትሬፕቶማይሲን አገልግሎት ላይ ከዋሉ ጀምሮ በቀጣዮቹ አሥርተ ዓመታት አዳዲስ ግኝቶች ጎረፉ። በ1990ዎቹ ዓመታት አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች ተስፋፍተው በ15 የተለያዩ መደቦች የተከፋፈሉ 150 ውህዶችን በሚያጠቃልሉበት ደረጃ ላይ ደረሱ።

ድል የማግኘቱ ተስፋ ከንቱ ሆነ

በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ ዓመታት አንዳንድ ሰዎች የኢንፌክሽን በሽታዎችን ድል አድርገናል ብለው መፈንጠዝ ጀምረው ነበር። አንዳንድ ማይክሮባዮሎጂስቶች ሳይቀሩ እነዚህ በሽታዎች ከትንሽ ጊዜ በኋላ ያለፈ ታሪክ ብቻ ሆነው ይቀራሉ ብለው ያምኑ ነበር። በ1969 የዩናይትድ ስቴትስ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ለምክር ቤቱ በሰጡት የምሥክርነት ቃል የሰው ልጅ በቅርቡ “የኢንፌክሽን በሽታዎችን መዝገብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይዘጋል” ብለው ነበር። በ1972 የኖቤል ተሸላሚ የነበሩት ማክፋርለን በርነት እና ዴቪድ ኋይት “የኢንፌክሽን በሽታዎች ወደፊት ብዙም አሳሳቢ አይሆኑም” ሲሉ ጽፈዋል። እንዲያውም እነዚህ በሽታዎች ሙሉ በሙሉ ይጠፋሉ ብለው ያሰቡ ብዙዎች ነበሩ።

ብዙዎች የኢንፌክሽን በሽታዎች ድል ተነስተዋል ብለው በማመናቸው ተዘናግተዋል። አንቲባዮቲኮች ከመገኘታቸው በፊት ጀርሞች ያስከትሉ የነበረውን ሥቃይና መከራ የምታውቅ አንዲት ነርስ አንዳንድ ወጣት ነርሶች ለንጽሕና ግድየለሾች መሆናቸውን አስተውላለች። እጃቸውን እንዲታጠቡ ስታስታውሳቸው “እባክሽ አትጨነቂ፣ አሁን አንቲባዮቲክ አለልን” ብለው ይመልሱላት ነበር።

ይሁን እንጂ በአንቲባዮቲኮች ከመጠን በላይ መታመንና አንቲባዮቲኮችን በብዛት መውሰድ አደገኛ ውጤት አስከትሏል። የኢንፌክሽን በሽታዎች ሊጠፉ አልቻሉም። አለመጥፋት ብቻ ሳይሆን ዳግመኛ አገርሽተው በዓለም ዋነኞቹ የሞት ምክንያቶች ሆነዋል! ለኢንፌክሽን በሽታዎች መስፋፋት አስተዋጽኦ ካደረጉ ሌሎች ምክንያቶች መካከል በጦርነት ሳቢያ የሚፈጠረው ትርምስ፣ በታዳጊ አገሮች ያለው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ ንጹሕ ውኃ አለማግኘት፣ የቆሻሻ በተገቢ ሁኔታ አለመወገድ፣ የዓለም አቀፍ መጓጓዣዎች መቀላጠፍና የምድር የአየር ጠባይ መለዋወጥ ይገኙበታል።

የባክቴሪያዎች መድኃኒት የመቋቋም ችሎታ

በየዕለቱ የሚያጋጥሙ ጀርሞች አደጋ ቻይነት ያልታሰበ ችግር አስከትሏል። መለስ ብለን ስንመለከት ግን ጀርሞች መድኃኒቶችን የመቋቋም አቅም ማዳበር እንደሚችሉ መጠበቅ ይገባ ነበር። ለምን? ለምሳሌ በ1940ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ላይ ዲዲቲ የተባለው ፀረ ተባይ መድኃኒት ከተፈለሰፈ በኋላ የሆነውን ተመሳሳይ ነገር እንመልከት። * በዚያ ጊዜ ዝንቦች ዲዲቲ ሲረጭባቸውና ድምጥማጣቸው ሲጠፋ ከብት አርቢዎች በጣም ተደስተው ነበር። ይሁን እንጂ በሕይወት የተረፉ ጥቂት ዝንቦችና ዝርያዎቻቸው ዲዲቲን የመቋቋም አቅም አዳበሩ። ብዙም ሳይቆይ በዲዲቲ የማይበገሩት እነዚህ ዝንቦች በጣም ተራብተው በዙ።

ዲዲቲ አገልግሎት ላይ ከመዋሉ በፊትም ሆነ ፔኒሲሊን ገበያ ላይ ከመዋሉ በፊት በ1944 ጎጂ ባክቴሪያዎች ምን ዓይነት መከላከያ ማበጀት እንደሚችሉ ታይቷል። ፔኒሲሊንን የፈለሰፈው ዶክተር አሌክሳንደር ፍሌሚንግ ይህን ተገንዝቦ ነበር። አንዳንድ የባክቴሪያ ዓይነቶች እርሱ በፈለሰፈው መድኃኒት ማለትም በፔኒሲሊን የማይደፈር ሽፋን እያበጁ እንደመጡ በቤተ ሙከራው ውስጥ ተመልክቷል።

በዚህ ምክንያት ዶክተር ፍሌሚንግ በበሽተኛ ሰው ውስጥ ያሉ ጎጂ ባክቴሪያዎች ፔኒሲሊንን የመቋቋም ችሎታ ሊያዳብሩ እንደሚችሉ ከ60 ዓመት ገደማ በፊት አስጠንቅቆ ነበር። ስለዚህ የተወሰደው የፔኒሲሊን መጠን ጎጂዎቹን ባክቴሪያዎች በበቂ መጠን ካልገደለ መድኃኒት የመቋቋም ችሎታ ያዳበሩት ዘሮቻቸው መባዛት ይችላሉ። በዚህ የተነሣ ፔኒሲሊን ሊያድነው የማይችለው በሽታ ዳግመኛ ያገረሻል።

ዚ አንቲባዮቲክ ፓራዶክስ የተባለው መጽሐፍ “የፍሌሚንግ ትንበያ እርሱ ገምቶት ከነበረውም የበለጠ ጉዳት በማድረስ በትክክል ተፈጽሟል” የሚል አስተያየት ሰጥቷል። እንዴት? አንዳንድ የባክቴሪያ ዓይነቶች በባክቴሪያው ዲ ኤን ኤ ውስጥ የሚገኙት ጂኖች ፔኒሲሊን እንዳይሠራ የሚያደርጉ ኢንዛይሞች እንደሚያመነጩ ታውቋል። በዚህ ምክንያት ፔኒሲሊን ለረዥም ጊዜ ቢወሰድ እንኳ ምንም ጥቅም ሳያስገኝ ይቀራል። ይህ እንዴት አስደንጋጭ ነው!

ከኢንፌክሽን በሽታዎች ጋር የሚደረገውን ግብግብ በአሸናፊነት ለመወጣት ሲባል ከ1940ዎቹ እስከ 1970ዎቹ ዓመታት ብዙ አዳዲስ አንቲባዮቲኮች የተፈለሰፉ ሲሆን በ1980ዎቹና በ1990ዎቹም ቢሆን ጥቂት አንቲባዮቲኮች ተገኝተዋል። ቀደም ያሉትን መድኃኒቶች የሚቋቋሙትን ባክቴሪያዎች በእነዚህ መድኃኒቶች ማከም ተችሏል። ይሁን እንጂ በጥቂት ዓመታት ውስጥ እነዚህንም አዳዲስ መድኃኒቶች የመቋቋም ችሎታ ያላቸው የባክቴሪያ ዝርያዎች ብቅ ማለት ጀምረዋል።

ሰዎች የባክቴሪያዎችን መድኃኒት የመቋቋም ችሎታ በጣም አስገራሚ ሆኖ አግኝተውታል። ባክቴሪያዎች ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች መካከል የሴል ሽፋናቸው አንቲባዮቲኮች የማይዘልቁት እንዲሆን ማድረግ ወይም አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች እንዳይገድሏቸው የራሳቸውን ኬሚካላዊ ባሕርይ መቀየር ይገኝበታል። በሌላ በኩል ደግሞ ባክቴሪያው ወደ ውስጡ የገባውን አንቲባዮቲክ ወዲያው ያስወጣዋል ወይም የአንቲባዮቲኩን ውህድ በመነጣጠል የመግደል ኃይሉን እንዲያጣ ያደርጋል።

የአንቲባዮቲኮች አገልግሎት እየጨመረ በሄደ መጠን መድኃኒት የመቋቋም ችሎታ ያላቸው የባክቴሪያ ዝርያዎችም በዚያው መጠን ተባዝተው ተሰራጭተዋል። ታዲያ ምንም ተስፋ የለም ማለት ነው? ቢያንስ በአብዛኞቹ ሁኔታዎች የተስፋ ጭላንጭል አለ። ለአንድ የተለየ ኢንፌክሽን አንድ ዓይነት አንቲባዮቲክ ውጤት አልባ ከሆነ አብዛኛውን ጊዜ ሌላ ውጤታማ የሆነ አንቲባዮቲክ ይኖራል። የባክቴሪያዎች መድኃኒት የመቋቋም ችሎታ አሳሳቢ ችግር ቢሆንም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከቁጥጥር ውጭ አልሆነም ነበር።

የተለያዩ መድኃኒቶችን መቋቋም

ከዚያም የሕክምና ሳይንቲስቶች አንድ አስደንጋጭ ነገር አወቁ። ባክቴሪያዎች እርስ በርሳቸው ጂኖቻቸውን ይለዋወጣሉ። በመጀመሪያ ላይ የሚታወቀው ጂኖቻቸውን መለዋወጥ የሚችሉት አንድ ዓይነት ባክቴሪያዎች ብቻ እንደሆኑ ነበር። በኋላ ግን መድኃኒት መቋቋም የሚችሉ ተመሳሳይ ጂኖች ፈጽሞ በተለያዩ ባክቴሪያዎች ውስጥ ተገኙ። የተለያዩ ባክቴሪያዎች እንዲህ ባለው ልውውጥ አማካኝነት ተዘውትረው የሚወሰዱ ብዙ ዓይነት መድኃኒቶችን የመቋቋም ችሎታ አዳብረዋል።

ይህም እንዳይበቃ በ1990ዎቹ ዓመታት የተደረጉ ጥናቶች አንዳንድ ባክቴሪያዎች በራሳቸው መድኃኒት የመቋቋም ችሎታ እንደሚያዳብሩ አመለከቱ። አንድ አንቲባዮቲክ ብቻ በሚኖርበት ጊዜ እንኳን አንዳንድ የባክቴሪያ ዓይነቶች ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ የሆኑ የተለያዩ አንቲባዮቲኮችን የመቋቋም ችሎታ ያዳብራሉ።

የጨለመ ተስፋ

አሁን ብዙዎቹ አንቲባዮቲኮች ለአብዛኞቹ ሰዎች የሚሠሩ ቢሆኑም ወደፊት ምን ያህል ውጤታማ ሆነው ሊቀጥሉ ይችላሉ? በቅርቡ የታተመው ዚ አንቲባዮቲክ ፓራዶክስ የተባለ መጽሐፍ “ከእንግዲህ ማንኛውም ኢንፌክሽን በተመረጠው የመጀመሪያ አንቲባዮቲክ ይድናል ብለን መጠበቅ አንችልም” ብሏል። መጽሐፉ በማከል “በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች እንደልብ የሚገኙ አንቲባዮቲኮች በጣም ጥቂቶች ስለሆኑ ውጤታማ አንቲባዮቲክ ማግኘት የማይቻል ይሆናል። . . . ከ50 ዓመት በፊት ከምድር ገጽ ፈጽመው ይጠፋሉ ተብለው በታሰቡ በሽታዎች ሰዎች ሲሰቃዩና ሲሞቱ ይታያል” ይላል።

ለሕክምና አገልግሎት የዋሉ መድኃኒቶችን የመቋቋም ችሎታ ያዳበሩት ባክቴሪያዎች ብቻ አይደሉም። ቫይረሶችም ሆኑ ፈንገሶች እንዲሁም ሌሎች ጥቃቅን ጥገኛ ተሕዋስያን በጣም አስደናቂ የሆነ መድኃኒት የመላመድ ችሎታ እንዳላቸው በመታየቱ እነዚህን ተውሳኮች የሚዋጉ መድኃኒቶችን ለመፈልሰፍ የተደረገው ጥረት ሁሉ መና ሆኖ ይቀራል ተብሎ ተሰግቷል።

ታዲያ ምን ማድረግ ይቻላል? የጀርሞችን መድኃኒት የመቋቋም ችሎታ ማስወገድ ወይም ቢያንስ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን ማድረግ ይቻላል? በዚህ በኢንፌክሽን በሽታዎች በሚታመስ ዓለም ውስጥ በአንቲባዮቲኮችና በሌሎች ፀረ ተሕዋሳት መድኃኒቶች አማካኝነት የተገኘውን ድል እንዴት ጠብቆ ማቆየት ይቻላል?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 “አንቲባዮቲክ” በቃሉ ተራ አጠቃቀም ባክቴሪያዎችን የሚዋጋ መድኃኒት ማለት ነው። “አንቲማይክሮቢያል” ይበልጥ ሰፋ ያለ ትርጉም ያለው ሲሆን ቫይረሶችም ሆኑ ባክቴሪያዎች አሊያም ፈንገሶች ወይም ጥቃቅን ጥገኛ ነፍሳት፣ ማናቸውንም በሽታ አማጭ ተሕዋሳትን የሚዋጉ መድኃኒቶችን በሙሉ ያመለክታል።

^ አን.10 ፀረ ተባይ መድኃኒቶችም ሆኑ የሚዋጡ መድኃኒቶች መርዝ ናቸው። ሁለቱም ቢሆኑ ጠቃሚም ጎጂም ጎን አላቸው። አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች ጎጂ ጀርሞችን ብቻ ሳይሆን ጠቃሚ ባክቴሪያዎችንም ይገድላሉ።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ፀረ ተሕዋሳት መድኃኒቶች ምንድን ናቸው?

ሐኪም የሚያዝልህ አንቲባዮቲክ መድኃኒት አንቲማይክሮብያልስ (ፀረ ተሕዋሳት) በሚባል የመድኃኒቶች ክፍል ይመደባል። በዚህ ክፍል የሚመደቡት መድኃኒቶች “ኬሞቴራፒ” ተብሎ በሚጠራው የሕክምና ዓይነት የሚጠቃለሉ ሲሆን ቃሉ በሽታዎችን በኬሚካሎች የማከምን ዘዴ ያመለክታል። “ኬሞቴራፒ” የሚለው ቃል አብዛኛውን ጊዜ የሚጠቀሰው ለካንሰር በሽታ የሚሰጥን ሕክምና ለማመልከት ቢሆንም መጀመሪያ ያገለግል የነበረው ለኢንፌክሽን በሽታዎች የሚሰጠውን ሕክምና ለማመልከት ነበር። ዛሬም ቢሆን ለኢንፌክሽን በሽታዎች የሚሰጠው ሕክምና አንቲማይክሮብያል ኬሞቴራፒ በመባል ይታወቃል።

ማይክሮቦች (ተሕዋሳት) በአጉሊ መነጽር እርዳታ ብቻ ሊታዩ የሚችሉ ረቂቅ ነፍሳት ናቸው። ፀረ ተሕዋሳት መድኃኒቶች በሽታ አምጪ የሆኑ ተሕዋሳትን የሚያጠቁ ኬሚካሎች ናቸው። ክፋቱ ግን እነዚህ መድኃኒቶች ጠቃሚ የሆኑ ተሕዋሳትን ጭምር ሊያጠቁ መቻላቸው ነው።

ስትሬፕቶማይሲን የተባለውን መድኃኒት ከፈለሰፉት ሰዎች አንዱ የሆነው ሰልማን ዋክስማን በ1941 ረቂቅ ከሆኑ ነፍሳት ለሚቀመሙት ፀረ ባክቴሪያ መድኃኒቶች “አንቲባዮቲክ” የሚል አጠቃላይ ስያሜ ሰጠ። አንቲባዮቲኮችም ሆኑ ፀረ ተሕዋሳት መድኃኒቶች ባንተ ላይ ከባድ ጉዳት ሳያደርሱ ጀርሞቹን ብቻ መርዘው ስለሚገድሉ በጣም ጠቃሚ ናቸው።

ይሁን እንጂ ሁሉም አንቲባዮቲኮች በመጠኑም ቢሆን መርዛማነት አላቸው። በበሽታው ላይ ጉዳት በሚያደርሰው የመድኃኒት መጠንና በእኛ በወሳጆቹ ላይ ጉዳት በሚያደርሰው የመድኃኒት መጠን መካከል ያለው ልዩነት ቴረፕዩቲክ ኢንዴክስ ይባላል። ልዩነቱ ከፍተኛ ሲሆን የመድኃኒቱ ጎጂነት ይቀንሳል፣ ሲያንስ ደግሞ የመድኃኒቱ አደገኛነት ይጨምራል። እንዲያውም በሺህ የሚቆጠሩ የአንቲባዮቲክ ንጥረ ነገሮች ቢገኙም አብዛኞቹ ለሰውም ሆነ ለእንስሳት አደገኛ በመሆናቸው ምክንያት ለሕክምና አገልግሎት መጠቀም አልተቻለም።

የመጀመሪያው ጥቅም ላይ የዋለ ከተፈጥሮ የተገኘ አንቲባዮቲክ ፔኒሲሊን ሲሆን የተገኘውም ፔኒሲሊየም ኖታተም ከተባለ ሻጋታ ነው። ፔኒሲሊን ለመጀመሪያ ጊዜ በመርፌ የተሰጠው በ1941 ነበር። ከዚያም ብዙ ሳይቆይ በ1943 ስትሬፕቶማይሲን የተባለ መድኃኒት ስትሬፕቶማይሲስ ግሪስየስ ከተባለ በአፈር ውስጥ ከሚገኝ ባክቴሪያ ተቀመመ። ከዚያ በኋላ በርካታ ተጨማሪ አንቲባዮቲኮች ከሕያዋን ፍጥረታት የተቀመሙ ሲሆን ሰው ሠራሽ በሆኑ ዘዴዎች የተመረቱም አሉ። ቢሆንም ባክቴሪያዎች ከእነዚህ መድኃኒቶች አብዛኞቹን የመቋቋም ችሎታ አዳብረዋል። ይህም በመላው ዓለም ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል።

[ሥዕል]

ሳህኑ ውስጥ የሚታየው የፔኒሲሊን ሻጋታ የባክቴሪያውን እድገት ገትቶታል

[ምንጭ]

Christine L. Case/Skyline College

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

የጀርም ዓይነቶች

ቫይረሶች ከሁሉም የሚያንሱ በጣም ረቂቅ የሆኑ ጀርሞች ናቸው። እንደ ጉንፋን፣ ፍሉና የጉሮሮ መቁሰል የመሰሉትን ሕመሞች የሚያስከትሉት ቫይረሶች ናቸው። በተጨማሪም እንደ ፖሊዮ፣ ኢቦላና ኤድስ ያሉትን አደገኛ በሽታዎች ያመጣሉ።

ባክቴሪያዎች ባለ አንድ ሕዋስ ፍጥረታት ሲሆኑ የራሳቸው ኑክሊየስ የላቸውም። አንድ ክሮሞዞም ብቻ አላቸው። በሰውነታችን ውስጥ በትሪሊዮን የሚቆጠሩ ባክቴሪያዎች ያሉ ሲሆን አብዛኞቹ የሚገኙት ምግብ በሚፈጭባቸው የሰውነታችን ክፍሎች ውስጥ ነው። ባክቴሪያዎች የበላነው ምግብ ከሰውነታችን ጋር እንዲዋሃድ የሚረዱ ሲሆን ለደም መርጋት አስፈላጊ የሆነው የቪታሚን ኬ ዋነኛ ምንጮች ናቸው።

እስካሁን ከታወቁት 4,600 የሚያክሉ የባክቴሪያ ዓይነቶች መካከል በሽታ አምጪ የሆኑት 300ዎቹ ብቻ ናቸው። ቢሆንም ባክቴሪያዎች በእጽዋት፣ በእንስሳትና በሰዎች ላይ በርካታ በሽታዎች ማምጣታቸው አልቀረም። በሰዎች ላይ ከሚያመጧቸው በሽታዎች መካከል ሳንባ ነቀርሳ፣ ኮሌራ፣ ዲፍተሪያ (ተላላፊ የጉሮሮ በሽታ)፣ አንትራክስ፣ የጥርስ መበስበስ፣ የተወሰኑ ዓይነት የኒሞኒያ በሽታዎችና በርካታ የአባለዘር በሽታዎች ይገኛሉ።

ፕሮቶዞዋዎች እንደ ባክቴሪያዎች ባለ አንድ ሕዋስ ፍጥረታት ሲሆኑ ቢያንስ አንድ ኑክሊየስ አላቸው። አሜባ፣ ትሪፓኖሶምና ወባ አምጪው ጥገኛ ተውሳክ ከእነዚህ ይመደባሉ። ከፕሮቶዞዋዎች መካከል አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት ጥገኛ ተውሳኮች ሲሆኑ ወደ 10,000 የሚጠጉ ዝርያዎች አሏቸው። ይሁንና ከእነዚህ ጥገኛ ተውሳኮች መካከል ሰዎችን የሚያሳምሙት ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው።

ፈንገሶችም በሽታ ሊያስከትሉ ይችላሉ። እነዚህ ነፍሳት ኑክሊየስ ያላቸው ከመሆኑም በላይ እንደ መረብ ያለ ውጭያዊ አካል ይሰራሉ። ከእነዚህ መካከል በጣም የታወቀው በሽታ አምጪ ሪንግወርም የተባለው ፈንገስ ሲሆን ጮቅና ካንዲድያሲስ የተባለውን በሽታ ያመጣል። ከበድ ያለ የፈንገስ ኢንፌክሽን የሚፈጠረው በቂ ምግብ ባለማግኘት፣ በካንሰር፣ በአደንዛዥ ዕፅ ወይም በሽታ የመከላከል አቅም በሚያሳጣ ቫይረስ የተነሳ አቅማቸው በተዳከመ ሰዎች ላይ ነው።

[ሥዕሎች]

የኢቦላ ቫይረስ

“ስታፊሎኮከስ ኦውሪየስ” ባክቴሪያ

“ጂያርዲያ ላምብሊያ” ፕሮቶዞዋ

ሪንግወርም ፈንገስ

[ምንጮች]

CDC/C. Goldsmith

CDC/Janice Carr

Courtesy Dr. Arturo Gonzáles Robles, CINVESTAV, I.P.N. México

© Bristol Biomedical Image Archive, University of Bristol

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፔኒሲሊንን የፈለሰፈው አሌክሳንደር ፍሌሚንግ