በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

የጦጣ ብልጠት

በጣም ብዙ ጦጣዎች በርካታ የታይፕ መጻፊያ መሣሪያዎች ተሰጥተዋቸው እንዲጽፉ ቢደረግ ውለው አድረው የሼክስፒርን የጽሑፍ ሥራዎች በሙሉ ማስገኘት ይችላሉ ብለው የሚያስቡ ሰዎች ነበሩ። በዚህ ምክንያት በእንግሊዝ አገር በፕሊማውዝ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩ ተመራማሪዎች ለስድስት ጦጣዎች አንድ ኮምፒውተር ለአንድ ወር ሰጡ። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ “ጦጣዎቹ አንድ ቃል እንኳን መጻፍ አልቻሉም” ሲል ዘግቧል። በደቡብ ምዕራብ እንግሊዝ በፔይንተን አራዊት መጠበቂያ የሚኖሩት እነዚህ ስድስት ጦጣዎች “አምስት ገጽ ለማውጣት የቻሉ ሲሆን” በገጾቹ ላይ በአብዛኛው የሰፈረው አንድ ፊደል ብቻ ነው። በጽሑፉ መጨረሻ ላይ ሌሎች ጥቂት ፊደላትም ተጽፈው ተገኝተዋል። በተጨማሪም ጦጣዎቹ የኮምፒውተሩን መጻፊያ ለመጸዳጃነት ተጠቅመውበታል።

የዓሣ ዝናብ

ኤለፍተሮቲፒያ የተባለው የግሪክ ጋዜጣ እንደዘገበው በኮሮና መንደር ከዶጅራን ወይም ከኮሮንያ ሐይቅ ከተነሣ ወጨፎ ጋር የመጡ ሳይሆኑ አይቀሩም ተብለው የሚታሰቡ በመቶ የሚቆጠሩ ትናንሽ ዓሣዎች ተገኝተዋል። “የመንደሩ ሰዎች በሄዱበት ሁሉ ከሰማይ የወደቁ ዓሣዎች ያገኙ ነበር።” የተሰሎንቄ ሜትዮሮሎጂ መምሪያ ዳይሬክተር ክርስቶስ ባላፉቲስ እንዳሉት ከሆነ እንዲህ ያለው ክስተት ያልተለመደ አይደለም። አነስተኛ የአየር ግፊት ያለው የአየር ጠባይ የሚፈጥረው አውሎ ነፋስ በሐይቆች ላይ የሚኖሩትን ዓሣዎችና እንቁራሪቶች ከባሕሩ ውኃ ጋር ስቦ ይወስዳል። “በአውሎ ነፋሱ ውስጥ ያለው አየር እስከ ሩቅ ከፍታና ርቀት ሊወስዳቸው እንደሚችል” ሪፖርቱ ይናገራል። የአውሎ ነፋሱ ኃይል በሚዳከምበት ጊዜ ዓሣዎቹ ወደ መሬት ይወድቃሉ።

ጉንዳኖች በጎርፍ ከመወሰድ የሚድኑት እንዴት ነው?

ዝናብ በሚዘንብበት ጊዜ ጉንዳኖች ምን ያደርጋሉ? ሁሉም የጉንዳን ዝርያዎች የሚኖሩት በመሬት ውስጥ ባይሆንም አንዳንዶቹ በጎርፍ ከመወሰድ የሚድኑበት በጣም አስደናቂ የሆነ ዘዴ እንዳላቸው ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ገልጿል። አንዳንድ የምድር ወገብ አካባቢ ጉንዳኖች “በጉድጓዳቸው አፍ ላይ አንድ ጠብታ ውኃ እንኳን ሲያርፍ ከአንደኛው መውጫ በር እስከ ወዲያኛው መውጫ ድረስ ወዲያው የማስጠንቀቂያ መልእክት ይተላለፋል” ይላሉ በጉንዳኖች ላይ በርካታ ምርምር ያደረጉት ዶክተር ኤድዋርድ ዊልሰን እና በርት ሆልዶርበር። “በጉድጓዱ ውስጥ ያሉትን ጉንዳኖች በሙሉ ክፍት ወደሆኑ መተላለፊያዎችና የመውጫ በር የሚመራ ሽታ መንገዳቸው ላይ ይተዋሉ።” ሠላሳ ሴኮንድ በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ መላውን ጉንዳን ማንቀሳቀስ ይችላሉ። ዘ ታይምስ እንደዘገበው ደግሞ በደቡብ ምዕራብ ዩናይትድ ስቴትስና በሰሜናዊው ደቡብ አሜሪካ አንዳንድ የጉንዳን ዝርያዎች “ጉንዳኖቹ ከጉድጓዳቸው ከወጡ በኋላ ንግሥቲቱንና አውራዎቹን ጨምሮ ሁሉም ጉንዳኖች አንድ ላይ ተደራርበው ጎርፉ ላይ ይንሳፈፋሉ። ብዙዎቹ በሕይወት ይተርፋሉ። . . . ተንሳፋፊዎቹ ጉንዳኖች በመጨረሻ ሣር ላይ ወይም ቁጥቋጦ ላይ መልሕቃቸውን ይጥሉና ውኃው ሲደርቅ በሕይወት የተረፉት ወደ ጉድጓዳቸው ይመለሳሉ።”

ሕፃናትን አትወዝውዟቸው!

ሕፃናትን በኃይል መወዝወዝ ለቅጭት ሊዳርጋቸው ከመቻሉም በላይ “በጭንቅላታቸው ውስጥ ደም እንዲፈስና በአንጎል ውስጥ ከፍተኛ ውጥረት ተፈጥሮ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ” እንደሚችል ቶሮንቶ ስታር የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። የአንድ ሕፃን ጡንቻዎች ገና ያልጠኑ በመሆናቸውና የአንጎል ሕዋሳት ደግሞ በጣም ደካማ በመሆናቸው “ለጥቂት ሴኮንዶች እንኳን ሕፃን ልጅን መወዝወዝ ዕድሜ ልክ የሚቆይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ከሚደርሱት ጉዳቶች መካከል የአንጎል እብጠትና መጎዳት፣ ሰረብራል ፓልሲ፣ የአእምሮ ዝግመት፣ የእድገት መቀጨጭ፣ ዓይነ ስውርነት፣ የመስማት ችሎታን ማጣት፣ ሽባነትና ሞት ይገኙበታል።” በምሥራቃዊ ኦንታርዮ የሕፃናት ሆስፒታል የሕፃናት ሐኪም የሆኑት ዶክተር ጀምስ ኪንግ መወዝወዝ በሕፃናት ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በተመለከተ ጥናት አካሂደዋል። በዚህ ምክንያት የሚደርሰው ጉዳት ወዲያው የሚታወቅ ባለመሆኑና ልጁ ጉንፋን ወይም ሌላ ዓይነት የቫይረስ በሽታ የያዘው ሊመስል ስለሚችል ሕዝቡ በቂ ትምህርት ማግኘት ያስፈልገዋል። “ሕፃን ልጅን ፈጽሞ መወዝወዝ አይገባም የሚለው መልእክት በሠፊው መሰራጨት ይኖርበታል” በማለት ዶክተር ኪንግ ይናገራሉ። “በተለይ አዳዲስ ወላጆች ይህን ማወቅ ይኖርባቸዋል።”

አብያተ ክርስቲያናትን ማመን ቀርቷል

ላይፕሲገር ፎልክሳይቱንግ የተባለው ጋዜጣ “ጀርመኖች ከአብያተ ክርስቲያናት ይልቅ በፖሊሶችና በጦር ሠራዊታቸው ይተማመናሉ” ሲል ዘግቧል። የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ሰዎች ስለሚተማመኑባቸው ድርጅቶች ባደረገው ጥናት 17 ከሚያክሉ ዋና ዋና ሕዝባዊ ተቋሞች መካከል አብያተ ክርስቲያናት የመጨረሻውን ደረጃ ይዘዋል። አርሚን ናሴሂ የተባሉት የማኅበራዊ ጉዳዮች አጥኚ ሥጋት በበዛበት በዚህ ዘመን ጀርመኖች ይበልጥ የሚተማመኑት እንደ ፖሊስና ጦር ሠራዊት ባሉት “ክፉውንና ደጉን በሚለዩ” ድርጅቶች ነው ብለዋል። አብያተ ክርስቲያናት የማይታመኑት ለምንድን ነው? ናሴሂ “ሃይማኖተኝነት እያንሰራራ ያለ ቢሆንም ሰዎች አብያተ ክርስቲያናት መሠረታዊ ችግሮቻቸውን ሊፈቱላቸው እንደሚችሉ አያምኑም” ብለዋል። በጀርመን አገር ያሉት አብያተ ክርስቲያናት “ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን ከማስፈጸም ሌላ አንዳች ፋይዳ የላቸውም” ሲሉ አክለዋል።

በስተርጅና መፋታት

በርሊነር ሞርገንፖስት የተባለው ጋዜጣ በጀርመን አገር “ከብዙ ዓመት የጋብቻ ኑሮ በኋላ የሚፋቱ ሰዎች ቁጥር ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እንደጨመረ” ዘግቧል። በሚዩኒክ፣ ጀርመን የጋብቻ አማካሪ የሆኑት ጂና ካስቴሌ ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ሴቶች በተለይ በገንዘብ ረገድ ራሳቸውን መቻላቸው ነው ይላሉ። “ወንዱ የነበረውን የቤተሰብ አስተዳዳሪነት ድርሻ አጥቷል” ይላሉ ካስቴሌ። በስተርጅና የሚፋቱ ሰዎች ቁጥር የበዛው ባልና ሚስቶች ልጆቻቸው ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ የፍቺውን ሐሳብ ስለሚያዘገዩት ነው የሚል አመለካከት አለ። ይሁን እንጂ ካስቴሌ እንደሚሉት አብዛኛውን ጊዜ ለፍቺ ምክንያት የሚሆነው ባሎች ከሚስታቸው ሌላ ወዳጅ መያዛቸው ነው።

ጡት የጠቡ ሕፃናት ይበልጥ ብልህና ጤናማ ናቸው

“በብሪስበን በ4,000 ሕፃናት ላይ ጥናት ያካሄዱ የኩዊንስላንድ ተመራማሪዎች ጡት የጠቡ ሕፃናት በብልህነት መመዘኛ የበለጠ ነጥብ አግኝተዋል” ይላል የሲድኒ፣ አውስትራሊያ ዘ ዴይሊ ቴሌግራፍ። የኩዊንስላንድ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ጃክ ናጅማን “አንዲት እናት ልጅዋን ያጠባችበት ጊዜ በረዘመ መጠን ብልህነቱ ይጨምራል። ጡት የጠባ ሕፃን የሚኖረው ብልጫ አነስተኛ አይደለም። በብልህነት መለኪያ ላይ እስከ ስምንት ነጥብ የሚደርስ ብልጫ ይኖራቸዋል። ይህም ማለት ጡት የጠባው ልጅ ካልጠባው ልጅ ይልቅ እጅግ ብልህ ይሆናል” ብለዋል። ጡት ማጥባት የሚያስገኘው ሌላ ጥቅም የአንድን ሕፃን በጣም የመወፈር አጋጣሚ በ30 በመቶ መቀነሱ ነው ይላል የሲድኒው ሳንዴይ ቴሌግራፍ። ጡት የሚያጠቡ እናቶች አማካሪ የሆኑት ጆይ ሄድስ እንዳሉት “በእናት ጡት ወተት ውስጥ ትርፍ ሆኖ በቆሻሻነት የሚወገድ ብዙ ነገር ስለማይኖር ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ ይውላል። ጡት የጠባ ልጅ በጣም የፋፋ ቢሆን እንኳ ምንም ችግር አያስከትልበትም። ጡጦ የጠባ ወፍራም ልጅ ግን የኋላ ኋላ በጣም የመወፈር አጋጣሚው ከፍተኛ ይሆናል።”

ትምህርት በዕድሜ አይወሰንም

መሃይምነት እጅግ በተስፋፋበት በኔፓል 12 የልጅ ልጆች ያሏቸው አንድ አረጋዊ ለመማር ባደረጉት ጥረት ምክንያት ትልቅ ዝና አትርፈዋል። ደራሲው ባዣ በሚል ስም የሚታወቁት ባል ባሃዱር ካርኪ የተወለዱት በ1917 ሲሆን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተዋግተዋል። በ84 ዓመት ዕድሜያቸው ከአራት ጊዜ ሙከራ በኋላ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና አልፈዋል። አሁን በ86 ዓመት ዕድሜያቸው የኮሌጅ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ናቸው። የመረጡት የትምህርት መስክ እንግሊዝኛ ሲሆን ይህንኑ ቋንቋ ለሌሎች እስከ ማስተማር ደርሰዋል። በወጣት ተማሪዎች ተከብበው በትምህርት ዴስካቸው ላይ ሲቀመጡ ዕድሜያቸውን ረስተው ወጣት እንደሆኑ እንደሚሰማቸው ተናግረዋል። ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ዋና ከተማዋ ወደ ካትማንዱ በሄዱ ጊዜ ላገኙት ውጤት ከፍተኛ አድናቆትና ሽልማት አግኝተዋል። ሌሎችም አርጅቻለሁ ብለው ተስፋ እንዳይቆርጡ አበረታተዋል። ይሁን እንጂ ደራሲ ባዣ አንድ ስሞታ እንዳላቸው ተናግረዋል። ወደ ዋና ከተማዋ ሲሄዱ ቅናሽ ስላላገኙና መደበኛውን የአውሮፕላን ዋጋ መክፈል ስላልቻሉ አውቶቡስ ለመሳፈር ሦስት ቀን ያህል በእግር ለመጓዝ ተገድደዋል። ዘ ካትማንዱ ፖስት ለተባለው ጋዜጣ “እኔም ተማሪ ስለሆንኩ አየር መንገዱ የተማሪ ቅናሽ ሊሰጠኝ ይገባ ነበር” ሲሉ ገልጸዋል።